Saturday, 24 August 2019 13:45

በነጠላ ጫማ ባንቺ አረማመድ እንዴት ያልቅልሻል ያ ሁሉ መንገድ

Written by 
Rate this item
(9 votes)


          ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊቶች ሁሉ ተሰባስበው፤
 “እንዴት ነው ነገሩ? የምንበላው ጠፋ፡፡ ሁሉም የሚታደን እንስሳ እየሸሸ ጐረቤት አገር ገባ፡፡ ተጨማሪ እንዳንፈልግ ጫካውም ሥራ ፈትቶ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ጥረን ተጣጥረን ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለንን ምግብ ገዝተን ማከማቸት አለብን፡፡ ለዚህ ገበያ ስምሪት የሚላክ ተወካይ ያስፈልገናል፡፡ ማን ቢሆን ይሻላል?”
“ነብር ይሁን!” አለ አንዱ እጁን አውጥቶ፡፡
 ብዙዎቹ ተቃወሙ፤ በተለይ ጦጢት፡፡
“አያ ነብሮ፣ ምግባችንን ቧጦ ቧጦ ከጨረሰብን፣ ሙልጫችንን መቅረታችን ነው፡፡ አለቀልን ማለት ነው፡፡”
“እሺ ሌላ የዱር አራዊት ጠቁሙ?”
“አያ አንበሳ ቢሆንስ?” አለ ዝንጀሮ፡፡
“አያ አንበሳ አይሆንም፤ እሱ ጉልበተኛ ስለሆነ ሁሉንም ጠቅልሎ ይበላብናል፡፡”
“እሺ ሌላስ?”
“ግስላ ቢሆን?”
“ግስላማ በፍፁም አይሆንም”
“እሺ ሌላ እጩ አምጡዋ?”
“ቀበሮስ ብትሆን?”
“ቀበሮም አትሆንም፡፡ ሰውን ማመን ከንቱ ነው እያለች ምኗ ይታመናል!”
“ታዲያ ማንን እናድርግ?”
“ኤሊ ትሁን” አለ ዝሆን
ሁሉም፤
“ኤሊ ጥሩ ናት፤ ኤሊ ታማኝ ናት…እሷ ትሁንልን” አሉ፡፡
ኤሊ ተመረጠችና፤
 “በይ ቶሎ ሸማምተሽ ነይ” ተባለች፡፡
ኤሊ ወጣች፡፡ ግን በጣም ቆየች፡፡ ሀሜት ተጀመረ፡፡
“ዱሮውኑስ ኤሊን መላክ ለምን አስፈለገ”
‹‹ዕውነት ነው፡፡ ቀርፋፋ መሆኗን እያወቅን፣ ምን አቅብጦን ነው እሷን የመረጥነው?››
“ሁለተኛ እሷን አንልክም!”
አጥብቀው ተቃወሙ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሩ ተከፈተና ኤሊ አንገቷን ብቅ አደረገች፡፡
“እኔ እንደዚህ የምታሙኝ ከሆነ አልሄድም” አለች፡፡
***
በማናቸውም ሰዓት መንቀርፈፍ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ወይ መጀመሪያውኑ ሲመረጡ፣ “ፈቃደኛ አይደለሁም” ማለት ነው፡፡ ከፈቀዱ መከራውን መቻል እንጂ ማማረር አይገባም::  ዕድል ከጊዜ ጋር ቁርኝት አላት፡፡ ዕድል ከጊዜ ጋር ስትቀናጅ ተራማጅ እግር አላት፡፡ ስለዚህ እግር እንስጣት፡፡ በእኛ እግር ትራመድና ቀጥላ እርሷኑ ታራምድ፡፡
ግባችን ሩቅ ነው፡፡ መንገዱ መራራ ነው፤ ስንቁም ብርቱ ትጥቅ ይጠይቃል፡፡ ጉዞው ከባድ የመሆኑን ያህል፣ ከባድ መስዋዕትነትን ይሻል፡፡ ያለዚህ መስዋዕትነት አጭር ነው ያልነው መርዘሙ፣ አቃለልነው ያልነው መክበዱ አይቀሬ ነው፡፡
ከቶም የተስፋችን አበባው ሳይረግፍ
ዕምቡጥ ሳይፈነዳ ህይወት ሳይታቀፍ
የዕውነት ዜማ ሳይታቀፍ
የዕውነት ዜማ ሳይጠፍ
የዓለም ሃይሏ ሳይሰንፍ
ልብ፣ ቧንቧ ሳይዘጋ
እስትንፋስ ሳይቆልፍ
መንፈሳችን ሳያድፍ
ማነው መላ መቺ
ህዝቡን የሚታደግ
መፍትሔ የሚያፋልግ     
መንገዱን የሚጠርግ
በነጠላ ጫማ በአንቺ አረማመድ
እንዴት ያልቅልሻል ይህ ሁሉ መንገድ
የሚባለው ለዚሁ ነው!  

Read 9288 times