Saturday, 17 August 2019 14:31

ዴይላይት አፕላይድ ቴክኖሎጂስ የቆርኪና የምግብ ማሸጊያ ጣሳ ፋብሪካ አስመረቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆነው የዴይላይት አፕላይድ ቴክኖሎዲስ በማስፋፊያ ፕሮግራሙ የቆርኪና የምግብ ማሸጊያ ጣሳ ፋብሪካዎች ግንባታ ጨርሶ ከትናንት በስቲያ አስመረቀ፡፡
ፋብሪካውን በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አቶ ተካ ገብረየሱስና የሚድሮክ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ናቸው፡፡
ፋብሪካው ቀድሞ ለአምፑል የተዋቀረበትን የምርት ዓይነት በመቀየር፣ የመጠጥ ጠርሙሶች፣ የጠርሙስ መክደኛዎችና (ኮርኪዎች Crownkorks) የምግብ ማሸጊያ ጣሳዎች ማምረት መጀመሩን ዶ/ር አረጋ ገልፀዋል፡፡
የጠርሙስ ማምረቻ ፋብሪካው በዓመት 12 ሚሊዮን ጠርሙስ የማምረት አቅም ሲኖረው የቆርኪ ማምረቻ መሳሪያው በሁሉም የምርት ሂደቱ ማለትም የህትመት የላከር ቅብና ቆርኪውን ቆርጦ በውስጡ ፕላስቲክ የመለጠፍ ሥራ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ በአንድ ፈረቃ (8 ሰዓት) 700ሺህ ቆርኪዎች ማምረት አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የቆርኪ ማምረቻ ፋብሪካው 72 ብር ሚሊዮን ፈጅቷል ያሉት ዶ/ር አረጋ ለ35 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ የደንበኞችን ፍላጐት የበለጠ ለማርካት ሌላ የቆርኪ ማምረቻ በመትከል የምርት አቅሙን በእጥፍ በማሳደግ (1.4 ሚሊዮን ቆርኪ በአንድ ፈረቃ) ማምረት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በሀገራችን ለምግብ ማሸጊያነት የሚውሉ የቆርቆሮ ጣሳዎች በሙሉ ከውጭ አገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስመጣት ለመከላከያ፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለክልል ፖሊሶችና ለሌሎችም ምግብ ለማሸግ ይውል ነበር ያወሱት ዶ/ር አረጋ፣ ሦስት መጠን ያላቸው ጣሳዎች የማምረት አቅም ያለው መሳሪያ 57 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ ሥራ ማስጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
የዴይላይት የምግብ ነክ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የማምረቻ ግቢ ከምግብና መጠጥ ጋር የተያያዙ ሌሎች የምርት ግብአቶች እንዲያቀርብ አስፈላጊውን ማስፋፋት በማድረግ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ሥራዎችን ለመፈጸም የሚያስችል ቀጣይ ጥናት በማካሄድ ላይ ነው ብለዋል - ዶ/ር አረጋ ይርዳው፡፡   

Read 2542 times