Print this page
Saturday, 09 June 2012 11:16

አርቲስቶቻችን እና የመለያየት አባዜያቸው!

Written by  ዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(0 votes)

በገበና የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ሲሳተፉ ከነበሩት ተዋናዮች የተወሰኑት ለቀቁ

የሰው ለሰው ተከታታይ ድራማ ወሳኝ ሰው አጣ

ቴዲ አፍሮ ከአዲካ ጋር ተጋጨ፤ ከማናጀሩም ጋር ተለያየ

መቲ (መታሰቢያ) ከሰይፉ ጋር ተለያየች…

ጭልም ካለው ነገር ላለመጀመር አሰብኩና ወደ ኋላ መለስ ብዬ በኪነ ጥበባችን ዙርያ የነበሩትን አብሮነት ለመዳሰስ ወደድኩ፡፡ ዳሰሳዬ እውነትም ዛሬ ዛሬ እየጨለመብን የመጣውን የኪነ ጥበብ ሰዎች አብሮነት ጥያቄ ውስጥ አልከተተብኝም፡፡ በርግጥም ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ዘርፎች የኪነ ጥበብ ሰዎች ለረጅም ዓመታት በአብሮነታቸው ዘልቀዋል፡፡ የጋራ ስምና ዝናም ሸምተዋል፡፡

በኮሜዲው ዘርፍ - አለባቸውና ልመንህ ዓመታት ባስቆጠረው አጋርነታቸው የአንድ ወቅት የአገራችን የኮሜዲ ንጉሶች ሆነው በውጤታማነት ለረጅም ዓመታት እንደዘለቁ እናስታውሳለን፡፡ የእነርሱን አርአያነት በመከተል እንግዳዘር ነጋና አበበ በለው ቡድኑን ተቀላቅለው አቅሙን አጠናክረውለታል፡፡ የእነርሱን አርአያነት ተከተለው ደግሞ ደረጀና ሀብቴ የተባሉ እጅግ አዝናኝ የነበሩ ኮሜዲያኖች በአጋርነት ተፈጥረዋል፡፡ ይህ ቅብብል እስከ ቅርብ ጊዜዎቹ ዋኖሶችም ድረስ ዘልቆ ጥንድ እየሆኑ የሚሰሩ ኮሜዲያን ጠንካራ አብሮነት ለታሪክ በቅቶአል፡

በሙዚቃው ረገድ - በዚህ ዘርፍ ደግሞ እጅግ አስደናቂ ተመክሮ እናገኛለን፡፡ ታዋቂዎቹ የግጥምና የዜማ ደራሲዎች ይልማ ገ/አብና አበበ መለሰ በአንድ ክፍል ውስጥ እየኖሩ ለረጅም ዓመታት እነዚያን ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አስኮምኩመውናል፡፡ እነዚህ ጥንዶች እስከ  ስድስት ወር ድረስ ከቤት ሳይወጡ፣ በእነርሱ አገላለፅ የፀሃይ ብርሃንን ሳያዩ ለጥበቡ በአጋርነት የከፈሉት መስዋእትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከድምፃውያን ላፎንቴኖች፤ አሌክስና ጐሳዬ እና ሌሎች አመታትን በስኬት መንገድ ጋልበዋል፡፡

በቴሌቭዥን ተከታታይ ጭውውቶች - በዚህ ዘርፍ ደግሞ አለልኝና ጥላሁን የተባሉት ሁለት የጥበብ ልጆችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ ጥንዶች ለበርካታ አመታት እንደ አንድ በመጠንከርና በመተባበር ልዩ ልዩ የጥበብ አበርክቶት ለረጅም አመታት በወቅቱ የመቶ ሃያ የቲቪ ፕሮግራም ጀባ ሲሉን ቆይተዋል፡፡

እንዲህ እንዲህ ብለን እናንሳ ካልን በርግጥም በአጋርነት ሥራ የአገራችን ኪነ ጥበብ ጭልም ያለ የኋላ ታሪክ እንደሌለው ልንገነዘብ እንችላለን፡፡

አብሮነት ዛሬስ? - ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ፤ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፤ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ወዘተ እያለ አማርኛችን አባባሎችን እያስቀመጠ አጋርነት ታላቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡

ግና ዛሬ በየዕለቱ በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች የምናደምጣቸውና የምንመለከታቸው ክስተቶች የኪነ ጥበብ ልጆችን መፃኢ አብሮነት አደብዝዞ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ “ገበና” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን እጅግ በርካታ ተመልካች ከልቡ ለዓመት ያህል ሲከታተለው ቆይቷል፡፡ እንዲያውም ባንድ ወቅት ድራማው በሚተላለፍበት ሰዓት ከተማዋ ጭር እስከማለት የተደረሰበት ጊዜ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ እስከ ሽልማቱ ቀን ድረስ አድናቆት የተቸረው የ”ገበና” ቡድን በአብሮነት ከህዝብ የተሰጠውን ክብር ይዞ ወደ ሁለተኛው ዙር መሻገር ግን አልተቻለውም፡፡

የመጀመሪያው ግጭት በገበና ቁ.1 ፀሃፊ  አዶኒስና በድራማው ፕሮዱዩሰሮች መካከል ተፈጠረና አዶኒስ ሁለተኛውን ዙር ከመፃፍ ራሱን አገለለ፡፡ ነገሩም ወደ ፍርደ ቤት አመራ፡፡ በመቀጠል አንጋፋውና ተወዳጁ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ምክንያቱን በውል ሳይገልፅ ቅሬታ እንዳለበት በማያሳብቅ ሁናቴ፣ በሁለተኛው ዙር ገበና ድራማ ሳይሳተፍ ቀረ፡፡ ተወዳጅና የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት ተዋናይት ጀማነሽ ሰለሞንም እንደዚሁ ባጋጠማት አለመግባባት ከቡድኑ ራሷን ማግለሏን ሰማን፡፡ ይሄንኑ ተከትሎ አዘጋጆቹ የፊልሙን አቅጣጫ ለማስቀየር ይታትሩ ገቡ፡፡

የገበና ቁ.1 ኮከብ ብለን የሰየምናትና የተሸለመችው ተወዳጅ ወጣት አርቲስት መሰረት መብራቴም አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ሙላቱ አስታጥቄ በአሜሪካ በርክሌይ ዩኒቨርስቲ ሽልማት ሊቀበል ሲሄድ በሙላቱ አማካኝነት ተጋብዛ፣ ወደ አሜሪካ ከተጓዘች በኋላ እስካሁን ድረስ ወደ አገሯ አልተመለሰችም፡፡ ይህም ተቀርፆ ባልተጠናቀቀው “ገበና” ቴሌቪዥን ድራማ ላይ ምን አይነት ጥላ እንደሚያጠላ አንባቢ ልብ ይሏል፡፡

ወደ “ሰው ለሰው” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ስመጣ፣ ከዛሬ አመት በፊት ይሄ ድራማ መጀመሩን ለማብሰር በቴሌቪዥን የተለቀቀውን ማስታወቂያ የተመለከትኩኝ ጊዜ “ዋው ምን አይነት ምርጥ ቡድን ተወቀረ” ብዬ እጅግ ተደንቄ ነበረ፡፡ የደራሲዎቹ ልምድና ብቃት አስተማምኖኛል፡፡ እጅግ የምናከብራቸው ተዋንያን አበበ ባልቻና ሙሉአለም ታደሰ ከአንጋፋዎቹ፣ ከወጣቶቹ ደግሞ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢና) ሌሎችም አርቲስቶች ተካትተውበታል፡፡ ነብዩ ባዩን የመሰለ ምርጥ ኤክስክዩቲቭ ፕሮዲውሰር የቡድኑ ቁንጮ ሆኗል፡ ታዲያ ይሄ ጥምረት ካልተደነቀ የቱ ይሆን የሚደነቀው?

ድራማው ቀስ በቀስ ወደ ሰው ልቦና ገብቶ ቀልብ መግዛት ሲጀምር፣ ከየት መጣ ያልተባለ ነፋስ ወደ ውስጡ ይነፍስ ገባ፡፡ የአስናቀ የቅርብ አገልጋይ ሆኖ ይተውን የነበረው ተዋናይ (መርሻ ጌታሁን) ከደራሲያኖቹ ጋር አልተስማማሁም፤ አስተካክሉ ያልኳቸውንም አያስተካክሉም በማለት ከቡድኑ ራሱን አገለለ፡ ቀጠል አድርጐ ተዋናይ ፍቃዱ ከበደ ደራሲዎቹ ራስ ወዳድ ናቸው ብሎ በመፅሄት እንደገለፀልን፤ የተሰጠኝ ገፀ-ባህሪ ለእኔም አልገባኝም የሚል አይነት ቅሬታ ይዞ ሹልክ አለ - ከድራማው፡ ጥቂት ቆየና ደግሞ ሶስቱ ደራሲዎቹ “እኔ ነኝ ዋነኛ እገሌ፣ በድርሰቱ ላይ ያለው ድርሻ አናሳ ነው” የሚል ክርክር አስነሱና በየመፅሄቱ በፈጠሩት አተካራ የቡድኑን መርከብ ማዕበል ሆነው አናወጡት፡፡

ልክ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ምሽት ላይ ኢትዮፒካል ሊንክ በተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ እንደሰማነው ከሆነ ደግሞ፤ የ”ሰው ለሰው” ድራማን በብዛት በመፃፍና እንደዚሁም በትወናም ላይ በመሳተፍ ሲያገለግል የነበረው ደራሲ መስፍን ጌታቸው ራሱን ከድራማው ፀሃፊነትም ሆነ ተዋናይነት ማግለሉን አሳወቀን፡፡ ይደንቃል እኮ ባካችሁ!

ከዚህ ወጣ ብለን ደግሞ እንመልከት፡፡ የቴዲ አፍሮ አልበም እንዲወደድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደረገው አዲካ፤ ያን ሁሉ ፖስተርና ቢል ቦርድ አሳትሞ አዲስ አበባንና ሌሎች ከተሞችን ካደመቀልን፣ የስልክ መጥሪያ ይሆነን ዘንድ የቴዲን ዘፈን ወደ ሞባይላችን ከለቀቀልን፤ ለቴዲ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከፍሎ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን ካነቃቃልን፤ ቴዲንም በመድረክ ላይ ከአድናቂዎቹ ጋር አገናኘዋለሁ ብሎ ቃል ከገባልን በኋላ ከድምፃዊው ጋር ተፈጠረ በተባለው አለመግባባት ይህ ሁሉ ደማቅ ታሪክ ጥላሸት ሊቀባ ትንሽ ሲቀረው ፈጣሪ አተረፈን፡፡ ከዚህኛው ብንተርፍም ቴዎድሮስ ካሳሁንና የረጅም ጊዜ ማናጀሩ አዲስ ገሠሠ መለያየታቸውን ሰማን፡፡

በሬዲዮ መዝናኛ ዘርፉ ደግሞ ያደመጥነው ሌላ ዜና በልዩ ውህደታቸው ስናደንቃቸው የነበሩ ሰይፉ ፋንታሁን፣ መታሰቢያ (መቲ) እና ተቦርነ ከሸገር የሬዲዮ ጣቢያ ኃላፊዎች ጋር በሳያት ደምሴ ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት ቡድናቸው እንደተሸረሸረ የሚያረዳን ነበር፡፡ ሌላም ሌላም…

ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? በእቁብ በእድር በቅርጫና በመሳሰሉት የለመድነው አብሮነት … በአገር ጉዳይ የምናሳየውስ አንድነት ኧረ ወዴት ገባ? “ኢትዮጵያኖች አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መስራት አይሆንላቸውም” የሚባለው ተረት እውነት ይሆን እንዴ?

በዚህ ከቀጠለ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በቀጣይ የመመልከት ዕጣ ፈንታችን ምን ላይ ይወድቅ ይሆን? …አንዱ አንዱን እየተጠራጠረ፣ አንዱ ሌላውን አሳንሶ እየተመለከተ፣ አንዱ በሌላኛው ትከሻ ሰማይ ካልነካሁ ካለ፤ አንዱ ላንዱ የማይተኛ ከሆነ፣ መናናቅ፣ መኮነን፣ መፈረጅ፣ መሳደብ፣ ማግለል በአብሮነታችን ውስጥ ሰፊውን ቦታ እየያዘ ከመጣ መጪው ጊዜ አያስፈራም ትላላችሁ?

ወዳጄ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደን ስለዚሁ ጉዳይ ሳጫውተው “እውነትህን እኮ ነው፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር በጥበቡ ውስጥ እየጠፋ መምጣቱ ነው” ብሎ ፈገግ አስባለኝ፡፡ ቀጠለና ደግሞ “ድሮ በሰንበት ት/ቤት በሰላም ያስጀመርከን በሰላም አስጨርሰን ተብሎ ይነገር የነበረው ትልቅ ምኞት ነው” ብሎ ልፅፈው ያሰብኩትን ሃሳብ አጠናከረልኝ፡፡

እውነቱን ነው እንዳለጌታ፡፡ በሰላም አስጀምሮ በሰላም ካላስጨረሰን ቀጣዮቹ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ከጨዋታ ውጪ መሆናቸው ነው፡፡ እያቆጠቆጠ የሚታየው የፊልም ኢንዱስትሪያችንም ገደል መግባቱ ነው፡፡ በቡድን ሆኖ ቴአትር ማቅረብ ሊናፍቀን ነው፡፡ ይህንኑ መካካድ በመፍራት በአንድ ፊልም ላይ ራሳቸው ደራሲያን፣ ራሳቸው ዳይሬክተር፣ እንደዚሁም ተዋናይና ፕሮዲውሰር የሚሆኑ ግለሰቦች እንደ አሸን ሊፈሉብን ነው፡፡ በጥበብ ልጆች መካካድና አተካሮ ልባችን ስብር ሊል ነው፡፡

የዚህ ጊዜ ነው “ጥበብ ትጣራለች” ብሎ ዳኛ ሊሆን የተዘጋጀ አንዳች ሃይል ጣልቃ ሊገባ የሚገባው፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ ጥልቅ ጥናት አድርጐ የሚያወያይ፤ የሚያከራክር፣ የሚያማምርና የሚያስታርቅ አንዳች ሃይል!

ያን ጊዜ ታሪክ ይለወጣል፡፡ “በእውቀቱ ስዩም በለንደን ኦሎምፒክ በክብር እንግድነት ተጋብዞ ይሄዳል፡፡ ግጥሞቹም ከሄሊኮፕተር ላይ ተለቅቀው ለህዝብ ይበተናሉ” የሚል ዜና ስንሰማ የጥበብ ጓደኞቹ ባንድነት ከዚሁ ከአገሩ አንግሰነው አብረነው ቺርስ ማለት እንጀምራለን፡፡ ከልብ በመነጨ ሁኔታም የደስታው ተካፋይ እንሆናለን፡፡ ድሉ የበእውቀቱ ብቻ ሳይሆን የአገር ድል ነውም እንላለን፡፡

በቺጌ ኮንሰርትና በአለማየሁ ታደሰ “የብዕር ስም” ቴአትር ምርቃት ላይ ቴዲ አፍሮ ድንገት ተገኝቶ ለመድረኩ ተጨማሪ ድምቀት እንደሆነው ሁሉ አንደኛው የጥበብ ሰው ለሌላኛው ድምቀት መሆኑን ይቀጥላል፡፡

በእነ ሠራዊት ፍቅሬና ሰለሞን ዓለሙ ይመራ የነበረው አፍለኛው የቴአትር ግሩፕ ጥቂት ግለሰቦችን ጫፍ አስረግጦ የመበታተን ታሪክ እንዳስመዘገበው አይነት ሳይሆን የቄራ ልጆች የእነ ቢኒያም ወርቁ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) አጋርነትና የእርስ በርስ መደጋገፍ ታሪክ ግንባር ቀደም ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

ያኔ በየወሩ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል መድረክ ላይ የምናየው የወጣቶቹ የፖይቲክ ጃዝ አቅራቢዎች ሕብረት አሸበርቆ ይታያል፡፡ያን ጊዜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ጥበበኞች ችግር ለመናገር በአንድነት መግባባት ላይ ይደረሳል፡፡ እሳቸውም ለጥበበኞቹ ጥያቄዎች ተገቢውን ትኩረት ይሰጣሉ፡፡

ያኔ የጥበበኞቹ መሰባሰቢያ የሆኑት የሞያ ማህበራት ከስም በዘለለ በልምድ፣ በቴክኒክ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ተጠናክረው ጥበቡን አንድ እርምጃ ወደፊት ይገፉታል፡፡ የጥበቡ ከያኒ ሲታመምና ሲሞት ሁልጊዜ ለልመና አቤቱታ ከመቅረቡ በፊት፣ በአጋርነት ውስጥ ሆኖ በቁም ላለ ከያኒ መፍትሄ ይፈለጋል፡፡

አብረን ከሆንን ብዙ እጅግ ብዙ ነገሮች ይከናወናሉ፡፡ የዚህን ጊዜ ነው ተተኪዎች ከቀደምት ሊማሩበት የሚችሉትን ተመክሮ ትተን ለማለፍ የምንችለው፡፡ ካልሆነ ግን በመጪዎቹም (በተተኪዎቹም) ላይ መጨከናችን ነው፡፡ አስጀምሮ ላስጨረሰን አምላክ ምስጋና ይግባው! አሜን፡፡

 

 

 

Read 3444 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 11:24