Saturday, 17 August 2019 14:15

ፈጣሪ እንደፃፈው

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(2 votes)

(የአጭር አጭር ልቦለድ)
                   
           በዚች ጠባብ ክፍል ውስጥ የተሸነቆረች አልጋዬ፣ በናፍቆት የምትጠብቀው እኔን ብቻ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እሷ ላይ ጋደም እንዳልኩ ጀምሮ፣ በቅጡ ያልተረዳኋቸው ስሜቶችና ሀሳቦች ይመላለሱብኛል፡፡ የትዝታዬ ባህር ናት፡፡
ግን ግን…ቁዘማ አብዝቻለሁ፡፡ የሚሰማኝም ይኸው ነው፡፡ ብቻ በዝምታ ውስጥ ህይወት አለ፡፡ በህይወት ውስጥ ደግሞ ተፈጥሮ ይገማሸራል፡፡ የትዝታ መረቡ ዝምታ ነው፤ ስንቱን ሰብስቦ ልብ ያቆማል፡፡ ደግሞኮ ስሜቱ…እንደ ህፃን እያንቧቸረ፣ ገስግሶ፣ በመረጥኩት ሳይሆን በራሱ አቅጣጫ፣ የፈለገው ስፍራ ይወሽቀኛል፡፡
አያቴ፣ “ትዝታዬ አንቀልባ ነው፡፡ የመሸከም ፍላጐትህን አነሳስቶ፣ እላይህ ላይ ይጨፍራል” ትለኝ ነበር፡፡
ምን ማለቷ እንደነበር የገባኝ አሁን ነው፡፡
አሁን…! አሁን…! የአንቀልባውን የዛጎል ድምፅ፣ የህይወት ሙዚቃ ሳይሆን የትዝታ ጩኸት፤ ስፋቱ ደግሞ የህልም ዓለሜ የሆነ ያህል ይሰማኛል፡፡
ህልም ልጅ ነውና እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡ በርግጥ የህሊናዬ ትኩረት ሊያቀጭጨውም ሆነ ሊያለመልመው ይችላል፡፡ ለዚህ መሰለኝ የውስጤ ፍላጐት እየተብሰከሰከ የሚያሰቃየኝ፡፡
ስለሆነም ቅጽበት እንጂ ዘላለም በውስጤ የለም፡፡ እንደ ቁልቋል ወተት አልተፋ፡፡ እንባ እንጂ፡፡ ግን የእኔ ትዝታ የሚለየው፤ ስትሄድ ስትመጣ ጥላ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ብርታቱ ይሰብረኛል፡፡ አሁን በቀደም ለት …ጠፍታ ኑራ፣ መልዕክቷ ሲደርሰኝ፣ በቅጽበት፣ “አንቀልባ ትዝታዬን” አዘልኩት፡፡ ይሄው!! በርትቶብኛል፡፡ ይዠው እዞራለሁ፡፡
ተፈጥሮዬ ይሆን እያልኩ እብሰለሰላለሁ፡፡ ግን ደግሞ የቸገረኝ፤ የእሷ ዥዋዥዌ ቅጥ ማጣት ነው፡፡ በርግጥ አንድ የገባኝ ነገር፣ በዝምታ ውስጥ የተፈጥሮ ህልውና መጠበቁ ነው፡፡ ዝም ያለ ቢመስልም ይለወጣል፡፡ ልክ እራስ ሲመለጥ አይነት፡፡ የእሷ ፍቅርም በፀጥታ ውስጥ ህይወት ዘርቶ፣ አድጐ አሳስቶኛል፡፡ እገነፍላለሁ፡፡ እንተከተካለሁ፡፡ አንዳንዴ ሁሉን እጥላለሁ፡፡ ሁሉን አነሳለሁ፡፡ ዥዋዥዌ፡፡
ህይወት ዋጋ ታስከፍላለች ወይስ ትከፍላለች? የዘወትር ጥያቄዬ ነው፡፡ አማካሪ ጋር ብሄድ መልሱ እንደ መደብ ይዥጎረጎርብኛል በሚል ፍርሃት ተተብትቤ አቀረቅራለሁ፡፡ እውነት ግን ህይወት ብርሃን ናት ወይስ ጨለማ? ህግ አላት? መኖርን ትሻለች? ህይወት፣ እውነትና ህግ፤ የተፈጥሮ ዛላ፣ ዘለላ ይሆኑ? ወይስ ህልም ይሆኑ?
እኒህንና መሰል ጥያቄዎች፣ በቅጽበት የምታዥጎደጉድብኝ፣ ህይወት ማናት? እላለሁ፡፡ እጠይቃለሁ፡፡ እመላለሳለሁ፡፡ ስሄድ እቀርባለሁ፡፡ ስመለስ እሸሻለሁ፡፡ ቅጽበት ዘላለሜ፤ ዘላለሜ ህልሜ ናቸውና አሳድዳቸዋለሁ፡፡ ያሳድዱኛል፡፡
(ማስታወሻነቱ፡- ለውስብስቧ ህይወት ይሁንልኝ)
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1085 times