Sunday, 18 August 2019 00:00

ሙጋቤ በብሔራዊ ጀግና ክብር እንዳትቀብሩኝ አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣የአገሪቱ ጀግኖች አስከሬን በክብር በሚያርፍበት የብሔራዊ ጀግኖችና ሰማዕታት የመቃብር ስፍራ እንዳትቀብሩኝ ሲሉ መናዘዛቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በሲንጋፖር በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት የ95 አመቱ ሮበርት ሙጋቤ፤ሰሞኑን ለቤተሰቦቻቸው ባስተላለፉት የኑዛዜ ቃል፣ ፓርቲያቸው ዛኑ ፒኤፍ፣ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ፣ እሳቸው ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ፣ የክብር የቀብር ስነስርዓት እንዳያደርግላቸውና በጀግኖች የመቃብር ስፍራ እንዳይቀበሩ መናዘዛቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ሙጋቤ የወቅቱን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋን ስም በመጥቀስ፣”ከአስከሬኔ ፊት ቆሞ የይምሰል ክብር በመስጠት፣ የግል ዝናውን እንዲያጎለብትብኝ አልፈልግም” ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ቤተሰቦቻቸውን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ሙጋቤ አስከሬናቸው ሞሾናላንድ ዌስት ዲስትሪክት በተባለው የአገሪቱ አውራጃ ውስጥ  በሚገኘው የእናታቸው የመቃብር ስፍራ እንዲያርፍ ኑዛዜ ፈጽመዋል፡፡
ሙጋቤን ላለማስቀየምና በኤመርሰን ምናንግዋ መንግስት ላይ ያላቸውን ኩርፊያ ለማረሳሳት በሚል ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ሙጋቤን  በማሳከም ላይ የሚገኙት የመንግስት ባለስልጣናት፤ ሙጋቤ በብሔራዊ ጀግና ክብር አልቀበርም ብለው መናዘዛቸውን ከሰሙ በኋላ  ክፉኛ መደናገጣቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 2396 times