Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:53

ኢዜማ የፖሊሲ ጥናቶችን እየተወያየ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የራሱን የመሬት፣ የትምህርት፣ የኢኮኖሚ--ፖሊሲዎች አዘጋጅቷል

               ከተመሰረተ ጥቂት ወራትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ ባለፉት ወራት በተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች፣
አባላት የመመልመልና የማደራጀት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የገለጸ ሲሆን ለምርጫ የሚወዳደርባቸውንና መንግስት ሆኖ ሲመረጥ
የሚተገብራቸውን የፖሊሲ ጥናቶች በምሁራን አስጠንቶ በማዘጋጀት ከሰሞኑ ለውይይት ማቅረቡ ታውቋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ
አንበሴ፣ በፓርቲው አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ በተለይም በፖሊሲ ጥናቶቹ ዙሪያ ከኢዜማ ም/ ሊቀመንበር፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

          ከሰሞኑ አዲስ የተቀረጹ የፖሊሲ ጥናቶችን አስተዋውቃችኋል፡፡ እስቲ ስለ ፖሊሲዎቹ ይንገሩን---
ያዘጋጀነው ነገ በምርጫ አሸንፈን የመንግስት መዋቅር ስንቆጣጠር፣ የምንተገብራቸውን ግልጽ ፖሊሲዎች ነው፡፡ መቼም የፖሊሲ ትንተና የሌለው ፓርቲ፤ በምርጫ ባይወዳደር ነው የሚሻለው:: ከዚህ ቀደም ግልጽ የፖሊሲ ትንተና የነበረው ፓርቲ፣ ኢዴፓ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢዴፓ ሰፊ የፖሊሲ ትንተና አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግልጽ የፖሊሲ ትንተና ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም፡፡ እኛ ኢዜማን ከመመስረታችንም በፊት፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማድረግ የሚችሉ ምሁራንን ስናነጋግር ቆይተናል፡፡ በመጨረሻም መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ፣ ፕ/ር በፍቃዱ ደግፌ (የኢዜማ አባል አይደሉም)፣ የታሰበውን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ቡድን እንዲመሩ በማድረግ፣ በእሣቸው ሰብሳቢነት፣ በርካታ ምሁራን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተውጣጥተው፣ ላለፉት 7 ወራት ጥናትና ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከሰሞኑም የተወሰኑት ጥናቶች ለውይይት  ቀርበዋል፡፡ ሐምሌ 27 እና 28 ቀን 2011 ዓ.ም እጅግ የሚያረካ ውይይት አድርገንባቸዋል:: የፖሊሲ ትንተናዎቹ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ላይ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በቀጣይ ደግሞ በፖለቲካ ዘርፍ ያለው ለውይይት ይቀርባል፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች ብሔራዊ ጉባኤያችን ላይ ቀርበው ከፀደቁ በኋላ አባሎቻችን ሰልጥነውባቸው ለምርጫ ይዘጋጁባቸዋል፡፡ እኛ ከወዲሁ ለምርጫ በሙሉ አቅማችን እየተዘጋጀን ነው፡፡ ይህ የፖሊሲ ጥናትም የዝግጅታችን አካል ነው፡፡  
የኢኮኖሚ ፖሊሲያችሁን በተመለከተ ማብራሪያ ሊሰጡን  ይችላሉ?
ለምሣሌ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ፣ አሁን ኢህአዴግ ያለውን ፖሊሲ ገምግመን፣ አዲስ አዘጋጅተናል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲያችን፣ የባንክ ስርአታችን፣ የፊሲካል ፖሊሲ፣ የኢንሹራንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት በጀት አስተዳደር እንዲሁም የገጠር ልማትንና እርሻን በተመለከተ የራሣችንን አዲስ ፖሊሲ ነው ያዘጋጀነው፡፡ ገበሬው በእውቀት ላይ ተመስርቶ እንዴት ማምረት ይችላል የሚለውም ዋነኛ የፖሊሲ ትኩረታችን ነው፡፡ የገጠር አሠፋፈርን በተመለከተም አዲስ ፖሊሲ ቀርጸናል፡፡   
የገጠር ልማት ፖሊሲያችሁን ይንገሩኝ?
የአረንጓዴ መንደር (Green Village) የሚል አስተሳሰብን ነው የምንከተለው፡፡ የገጠር ከተማ መንደር ምስረታ መኖር አለበት ብለን ነው ያስቀመጥነው፡፡ ይሄ ደግሞ በዋናነት በየአካባቢው የተማረው ወጣት እዚያው አካባቢው ላይ ሆኖ፣ ዘመናዊ ኑሮ እየመራ፣ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእርሻ ልማት እያካሄደ፣ የእርሻ ልማት ውጤቶችን እንዲያመርት፣ በዚያውም  በአረንጓዴ መንደርነት የተመሰረተው ከተማ እየሰፋ ትልልቅ ከተማ የሚመሰረትበትን መንገድ የሚቀይስ ነው፤ ፖሊሲያችን፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮዎች ተፈትሸዋል፡፡ የሲንጋፖር፣ ብራዚልና ኮሪያ ተሞክሮዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመላ ሃገሪቱ እንዲህ ያለውን ስትራቴጂ መጠቀም አለብን ብለን እናምናለን፡፡ ፖሊሲያችን፤የእርሻ ምርት በሚመረቱባቸው አካባቢዎች፣ የእርሻ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች እስከ ማቋቋም ይደርሳል፡፡ ይህም አርሶ አደሮች የእርሻ ምርቶችን በየአካባቢያቸው አሳድገውና አበልፅገው፣ ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ እርሻን በተመለከተ የመስኖ ልማትን ማዕከል ያደረገ የእርሻ ፖሊሲ ነው ያለን፡፡ የመስኖ ልማት በተመረጡ አካባቢዎች በማስፋፋት፣ ከመስኖ ልማቱ ጋር አብሮ እዚያው አካባቢ የአረንጓዴ መንደር ምስረታ ያስፈልጋል የሚል አስቀምጠናል፡፡ አርሶ አደሩ፤ እዚያው አካባቢ በመስኖ እያለማ፣ ከተማ እየመሰረተ የሚሄድበትን መንገድ ነው የምከተለው፡፡ ይህ ሲሆን አሁን ያለው የስራ አጥነት ይቀረፋል፡፡ በዚህ የእርሻ ልማትና የሰፈራ ፕሮግራም ውስጥ የተማረው ወጣት የሚሳተፍበት የፖሊሲ አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡
ኢህአዴግ ግብርና መር ኢንዱስትሪ የሚል ስትራቴጂ ነበረው፡፡ የእናንተስ ምንድነው ስትራቴጂያችሁ?
የኢትዮጵያ ግብርና መር ፖሊሲ ተሞክሮ ታይቷል፡፡ ምን ውጤት አመጣ የሚለውን ለማወቅ ባለፉት 27 ዓመታት የተገኘውን ትርፍና ኪሳራ ማስላት ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ፖሊሲ ብዙ አማራጮችን ሞክሯል፡፡ አሁን የደረሰበት ደግሞ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ነው፡፡ የዚህን ሶስተኛ እቅድ እያዘጋጀ እንደሆነም  መረጃ አለን፡፡ ይሄን ስንመለከት፣ እርሻ መር ኢንዱስትሪያላዜሽን የሚባለው በረጅም ርቀት የሚመጣ ውጤት ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መጀመሪያ የሚያስፈልገው፣ የእለት ጉርሳችንን መሙላት የሚያስችለንን ምርት በበቂ ሁኔታ ማምረት  ነው:: በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ረሀብ የምንፈታበት ስትራቴጂ ነው መነደፍ ያለበት፡፡ ያለንን መሬት በአግባቡ ተጠቅመን ምርታማ ማድረግ አልቻልንም:: አሁንም በበሬ፣ በፈረስና በአህያ ነው የምናርሰው:: ስለዚህ የአስተራረስ መንገድን አዘምኖ፣ የምርት አቅምን በመጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እኛም ቅድሚያ የምንሰጠው ለዚህ ስትራቴጂ ነው፡፡
የግብርና ምርትን አትረፍርፎ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን አቅርቦትን መፍጠር የሚያስችል ስትራቴጂ ነው የምንከተለው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እርሻ፣ ለኢንዱስትሪ ቦታውን የሚለቀው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ መሬትና ተስማሚ አየር ቢኖርም፣ አሁንም ከረሀብ አልወጣንም፡፡ ባሌ፣ አሩሲና ጎጃም በሰፊው ስንዴ ማምረት የሚችል ከፍተኛ አቅም አላቸው፡፡ እነዚህን አካባቢዎች በሚገባ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ ምርታማ ማድረግ ይቻላል፡፡  በሌላ በኩል፣ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ፣ የምግብ እህል ማምረት እየተወ፣ ወደ ገበያ ምርቶች ማለትም፣ ጫት የመሳሰሉት ላይ እያተኮረ ነው፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ ለዚህ ነው የዋጋ ግሽበት በጊዜው እየጨመረ የሚገኘው፡፡ ይሄን የሚያስተካክል ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፈናል፡፡ ዜጎች የሚበሉትን ሲያጡ ነው ለስደት የሚዳረጉት:: በዋናነት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘመናዊ ግብርናን የማስፋፋት ስትራቴጂ ነው የምንከተለው፡፡ ግብርና ላይ በትኩረት ሰርተን፣ መጀመሪያ ረሃብን ማጥፋት አለብን የሚል እምነት አለን፡፡  
የመሬት ፖሊሲያችሁስ ምን ይመስላል?
አሁን ባለው ፖሊሲ፣ በገጠር፣ ገበሬው፣ መሬት በባለቤትነት እንዲይዝ አይፈቀድም፡፡ ለአርሶ አደሩ፣ የመጠቀምያ ደብተር እንጂ የባለቤትነት ካርታ አይሰጠውም፡፡ በዚያ ላይ ያለው የእርሻ መሬት የተበጣጠሰ ነው፡፡ ስለዚህ ለተተኪው ትውልድ የሚከፋፈል የእርሻ መሬት የለም፡፡ መሬት ያጣ የገጠር ወጣት፣ ወደ ከተማ ይፈልሳል፡፡ አሁንም እየፈለሰ ነው፡፡ በከተማ ያለው የመሬት አጠቃቀም ደግሞ ለሙስናና ለዘረፋ የተመቻቸ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የሚያስፈልገው የመሬት መጠቀምያ ደብተር ሳይሆን የመሬት ባለቤትነት ካርታ ነው፡፡ የከተማ መሬትም በተመሳሳይ ቤት ትሰራለህ እንጂ ያንተ አይደለም፡፡ በእኛ ፖሊሲ መሰረት፤ መሬቱ የግለሰብ መሆን አለበት፡፡ ያ ግለሰብ ለልጅ ልጆቹ የሚያወርሰው፣ ካሻው የሚሸጠው የሚለውጠው ርስቱ መሆን አለበት፡፡ የጋራ መሬት የሚሆኑ ብለን የያዝናቸውም አሉ፡፡ ከከተማ ውስጥ ለምሳሌ አደባባዮች፣ መንገዶች የመሳሰሉት --- በመንግስት ስር ሆነው፣ የጋራ መጠቀሚያ ይሆናሉ፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ማንም ያልነካቸው፤ ያልሰፈረባቸው መሬቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ አፋር ወዘተ--የሚገኙ  መሰል መሬቶች፤ በአረንጓዴ መንደር ልማት መልማት አለባቸው፡፡ እነዚህ መሬቶች በመንግስት ስር ይሆኑና፣ ሰፋፊ ሰፈራዎች እየተሰሩ፣ የእነዚያ ሰፈራዎች ባለቤት፣ ግለሰቦች እየሆኑ የሚመራበትን አማራጭ ቀርጸናል፡፡
የትምህርት ፖሊሲያችሁስ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
አሁን ያለው የትምህርት ፖሊሲ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ እድገትም ሆነ እውቀት አስተዋፅኦ አለማድረጉን ገምግመናል፡፡ እንደውም በዚህ ስርዓተ ትምህርት ተገንብተው የወጡ ወጣቶች፣ ያን ያህል እውቀትና አቅም የሌላቸው መሆናቸውን ነው የገመገምነው፡፡ እነዚህን ወጣቶች “ያን ያህል እውቀት የሌለው ግን ዩኒቨርሲቲ የጨረሰ” በሚል ትውልድ ውስጥ ነው ያካተትናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት የትምህርት ሂደት ረጅም እንዲሆን ነው የታቀደው፡፡ እያንዳንዱም ሂደት ከመሰረቱ ተስተካክሎ እንዲሄድ የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጅቷል፡፡ አንዳንድ ጥናቶችን ስንመለከት፣ IMF ያጠናው ለምሳሌ፣ 3ኛ ክፍል የደረሰ የኢትዮጵያ ተማሪ ማንበብ አይችልም፤7ኛ ክፍል የደረሰ ተማሪ፣ አራቱን የሂሳብ መደቦች በሚገባ አያውቃቸውም የሚል ነው፡፡ ይሄ አሳፋሪ ነው፡፡ ይሄን ያመጣው ደግሞ የትምህርት ስርአቱ ነው፡፡ እኛ ባዘጋጀነው ፖሊሲ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሰጥ ሲሆን፤ ይሄ እስከ ስንተኛ ክፍል መቀጠል እንዳለበት በግልፅ ይቀመጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የሚሰጠው፡፡ 9ኛ ክፍል የደረሰ ተማሪ፣ ሙሉ ለሙሉ እንግሊዝኛ መናገርና መፃፍ የሚያስችለው የትምህርት ፖሊሲ ነው የቀረጽነው:: ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ያሉ የሳይንስና ምርምር ስራዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚጠኑ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል፤የመምህራኑም የብቃት ጉዳይም አለ፡፡ መምህራን እንደገና የሚሰለጥኑበትና ብቃታቸውን የሚያሳድጉበት ሁኔታ እንዲኖር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ አሁን ባለው ፖሊሲ 10ኛ ክፍል ላይ ጨርሰው የሚቀመጡ ወጣቶች፣ የሃገሪቱ ትልቅ ችግር መሆናቸው  ተመልክቷል፡፡ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአገሪቱ በተከሰተው አመጽና ተቃውሞም፣ በዋነኛነት የተሳተፉት እነዚህ ታዳጊ ወጣቶች ናቸው፡፡ ተምረው መቀመጣቸው አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማጠቃለያ ፈተና 12ኛ ክፍል ላይ ተሰጥቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ያለው እንዲገባ፣ ሌላው ደግሞ ወደ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንዲገባ የሚያስችል አቅጣጫ ነድፈናል:: የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ዝቅተኛው 4 ዓመት መሆን አለበት ይላል-ፖሊሲያችን፡፡ የትምህርት ስርዓቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ማህበራዊ ሚዲያዎች ለትምህርት አገልግሎት የተመቻቹ እንዲሆኑ  የሚያደርግ ፖሊሲ ነው የቀረጽነው፡፡
የኢዜማ ብቻ ነው የምትሉት የተለየ ፖሊሲ ይኖራችሁ ይሆን?
የቴክሎጂ ፖሊሲያችን፤ ከሁሉም የተለየ ያደርገናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምርትን ለማሳደግና ምርታማ ለመሆን ቴክኖሎጂን አሟጠን መጠቀም አለብን ከሚል መነሻ የተዘጋጀ ፖሊሲ ነው፡፡ ኋላ ቀር የሆነውን ቴክኖሎጂ በሙሉ የማዘመንና አዲስ ጠቃሚ ቴክኖሎጂን ያለ ገደብ የመጠቀም ፖሊሲ አዘጋጅተናል፡፡ ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለባንክና ለሌሎችም የአገልግሎት ዘርፎች የሚውል ቴክኖሎጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተተገበረም፡፡ ፖሊሲው ዋነኛ ትኩረቱ እዚህ ላይ ነው፡፡
ከፖሊሲ ወደ ህገ መንግስት እንሂድ፡፡ ህገ መንግስቱ ሳይሻሻል ምርጫ መታሰብ የለበትም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእናንተ አቋም ምንድን ነው?
እኛም ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት ነው የምንለው፡፡ ነገር ግን ሊያሻሽለው የሚችለው አካል የቱ ነው? የሚለው ላይ ነው ትልቁ ልዩነታችን፡፡ መሻሻል ካለበት አሁን ባለው የኢህአዴግ ፓርላማ አይደለም፡፡ በዚህ ፓርላማ ማሻሻል አይቻልም የሚል አቋም አለን፡፡ ስለዚህ የግድ ምርጫ ተደርጎ ሌላ ፓርላማ ተመርጦ ነው መሻሻል ያለበት ማለት ነው፡፡
አዲሱ የፓርቲዎችና የምርጫ ህጉ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ እናንተ ደግሞ “እንከን የለሽ ነው” ብላችኋል--
እኔ ነባሩ የምርጫ ህግና የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሻሻል እንዳለበት ስሞግት ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን የሚፈሉበት የምዝገባ አዋጅ ነው የነበረው፡፡ በአንድ ፓርቲ ውስጥ አንጃ የፈጠረ፣ የፖለቲካ ድርጅት የሚያቋቁምበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይሄን እኔም ሆንኩ ኢዜማ አንደግፈውም፡፡ በተለይ አገር አቀፍ ፓርቲ ሲመሰረት፣ 10ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ የሚለው፣ ከዚህም መጨመር አለበት ነው የምለው፡፡ ብሔር ተኮር ለሆኑ ፓርቲዎች፣ 4ሺህ ፊርማ የሚለውም ትንሽ ነው ባይ ነኝ፡፡ ላለፉት 27 አመታት የተጓዝንበትን የፖለቲካ አቅጣጫ፣ አሁንም መከተል ያለብን አይመስለኝም፡፡  አሁን ጠንካራና  ሞጋች ሃሳብ ያላቸው ፓርቲዎች መፈጠር አለባቸው::
በርግጥ ይሄ መስፈርት አንዳንዶቹን ፓርቲዎች ከጨዋታው ሊያስወጣቸው ይችላል፡፡ እነዚህ ሃይሎች፣ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ፣ 10ሺህ ድምፅ ማግኘት ካልቻሉ፣ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ምን ያደርጋሉ? በኛ በኩል፣ የተዘጋጀው ህግ ሊያሰራ የሚችልና ፓርቲዎችን የሚያጠናክር ነው ብለን እናምናለን፡፡ በህጉ ላይ ምንም ቅር ያለን ነገር የለም፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድ፣ ነባሮቹንም ፓርቲዎች፣ 10ሺህ ድምፅ እንዲያመጡ ይጠይቃል መባሉ የሚደገፍ ነው፡፡ እኔ ሙሉውን አንብቤዋለሁ፤ ህጉ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን መንግስት ለ140 ፓርቲዎች እንዴት ነው የገንዘብ ድጋፍ አድርግ የሚባለው? ውጤት ለማያመጣ ፓርቲ፤ የገንዘብ ድጋፍ አድርግ ማለት ምንድነው ትርጉሙ? ትርፉ ቀለብ መስፈር ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ኢዜማ መንግስት ቢሆን ኖሮ፣ ሁለንተናዊ ችግሮችንና የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን የሚፈታው እንዴት ነበር?
እኛ ስልጣን ላይ ብንሆን ኖሮ የምናስቀድመው ነገር አለ፡፡ አንደኛ ከየአቅጣጫው የተነሱ ግጭቶች መንስኤያቸው ምንድን ነው? እውነት ፖለቲካ ነው? የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው? የስልጣን ጥያቄ ነው? ወይስ የኑሮ ጉስቁልና ነው? የቱ ላይ ነው ክፍተቱ? ከበስተጀርባ ሃይሎች አሉ? እነማን ናቸው? ፍላጎታቸው ምንድን ነው? ይሄን የማተራመስ ስራ የሚሰሩ ሃይሎች፣ የገንዘብ ምንጫቸው ከየት ነው?--- የሚሉትን ነገር እንፈትሻለን፡፡ በተለይ የብሄራዊ ደህንነት መስሪያ ቤቱ ቅድሚያ ሰጥቶ፣ ይሄን ጉዳይ እንዲያጠና እናደርጋለን፡፡ ከዚያ በኋላ ለችግሮቹ መፍትሄ ማመንጨት ነው፡፡ የግጭት መንስኤና መፍትሄው ከቀረበ በኋላ ችግሩን ለመፍታት ወደ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ነው የምናመራው፡፡ ይህቺ ሃገር ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ያስፈልጋታል፡፡ ብሄራዊ እርቅ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ከዚህ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡

Read 2936 times