Print this page
Saturday, 09 June 2012 10:58

የፈረንሳውያንን ውለታ የሚዘክረው መፅሃፍ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

በ1891 ዓ.ም ከጅቡቲ አዲስ አበባ ለመምጣት በእግር የሚጓዙ ሰዎች አንድ ወር ይወስድባቸው ነበር፡፡ በ1900 ዓ.ም ይህንኑ ርቀት በባቡር ለማቋረጥ ሁለት ቀን ብቻ እንደሚያስፈልገው ታየ፡፡ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ከጅቡቲ የተነሳው አውሮፕላን አዲስ አበባ ስጋ ሜዳና (ታጠቅ) ደርሶ ለማረፍ ጥቂት ሰዓታት ነበር የፈጀበት፡፡ በዕለቱ በተከሰተው ኃይለኛ ዝናብና ንፋስ ምክንያት አውሮፕላኑ ሞጆ ባያርፍ ኖሮ የጉዞ ሰዓቱን በደቂቃዎችም ቢሆን ማሻሻል በቻለ ነበር፡ ሰዓቱ እንዳያጥር ምክንያት የሆኑ ሌሎች ነገሮችም ነበሩ፡፡

“ካርታ በሌለበትና አውሮፕላን ማረፊያ ባልተጠረገበት ሁኔታ፣ ፓይለቱ በአፋር በኩል የሚወስደውን ቀጥተኛ መስመር ተወና፣ የባቡር ሐዲዱን መስመር ከሥር ከሥሩ እያየ መብረርን መረጠ፡፡ ይህ አማራጭ የተሻለ ነበር፡፡ ምክንያቱም የበረራውን ጉዞና ሂደት በየባቡር ጣቢያው ያሉ ቴሌግራፎች አዲስ አበባ ድንኳን ውስጥ ሆነው ለሚከታተሉት ለራስ ተፈሪ በየጊዜው እንዲያስተላልፉላቸው አመቺ ሆነ…

“ባሁኑ ጊዜ እንደ እብድ ሊቆጠር የሚችለው ይህ ፓይለት አዲስ አበባ ሲደርስ ከተማዋን አስፈነደቃት፡፡ የፈረንሳዩን አምባሳደር ትንሽ አሽኮረመመው፡፡ የሌሎች አገሮች ዲፕሎማቶችን ግን አበሳጨ፡፡ አውሮፕላንን ያህል አዲስ ፈሊጥ ፈረንሳይ ለኢትዮጽያ ማስተዋወቋን ኢጣሊያንና ጀርመን በክፉ ዓይን ተመለከቱት፡፡ እውነታው ፊታቸው አፍጥጦ ሲደቀን ግን፣ እነሱም አውሮፕላን ለመስጠት ወዲያውኑ እሽቅድምድም ውስጥ ገቡ፡፡ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ዩኒከርስ የሚባል የጀርመን አውሮፕላን አዲስ አበባ ሲገባ፣ ኢጣሊያን ደግሞ ለአፄ ኃይለሥላሴ ንግስ በዓል ብሬዳ የሚባል አውሮፕላን አበረከተች፡፡”

የሸዋው ንጉሥ ሳህለሥላሴና የፈረንሳይ ንጉስ ሊዊ ፊሊፕ፤ በ1836 ዓ.ም የተዋዋሉት ውል የግንኙነት መጀመሪያ ተደርጐ ቢወሰድም “ሀብትና አዱኛ ፍለጋ” ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፈረንሳዊው ባለቅኔ አርትዩር ሪንቦ፤ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል፡ አያታቸው ከፈረንሳይ ጋር የተዋዋሉትን ውል በ1889 ዓ.ም እንዲታደስ ያደረጉት አፄ ምኒልክ፤ የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው መሠረት የጣለ ሆኗል፡፡

ፈረንሳይና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 100ኛ ዓመት በግንቦት ወር 1989 ዓ.ም መከበሩን ምክንያት በማድረግ “የመቶ ዓመት ወዳጅነት አጭር የታሪክ ማስታወሻ” በሚል ርዕስ በበኃይሉ ሃብቱ ተተርጉሞ የቀረበው መጽሐፍ 66 ገፆች ያሉት አነስተኛ ጥራዝ ነው፡፡ ስለ ሁለቱ አገራት ግንኙነት ግን በቂ መረጃ ይሰጣል፡፡

ስለ ምድር ባቡር ታሪክ በኢትዮጵያ ሲነገር፣ የፈረንሳዊያን ሥምና ተግባር አብሮ እንደሚነሳው ሁሉ በጽሑፌ መጀመሪያ ያቀረብኩት የአውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ጨምሮ አዳዲስ ነገሮችን ለኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ፤ ለነፃነት፣ ለለውጥና ዕድገት አብረው በመስራት ፈረንሳዊያን ብዙ ተሳትፎ እንደነበራቸው መጽሐፉ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም ከተቀረው የዓለም ሕዝቦች ጋር ለመገናኘት አፄ ምኒልክ ፍላጐት አሳይተው መንቀሳቀስ በጀመሩበት ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛትን ማእከል በማድረግ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ እያንዳንዳቸው በአካባቢው የበላይነት ለማግኘት በጥረት ላይ ነበሩ፡፡ በ1888 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ በማቅረብ የተባበረችው፣ ከኀይል ሚዛኑ ውድድር ጋር በተያያዘ ሲሆን አፄ ምኒልክም ብልህነታቸውን በተግባር አሳዩ - በ1890 ዓ.ም የባቡር መስመሩን በማስጀመር የአገራቸው ነፃነት እንዲታወቅላቸው በማድረግ፡፡

ሁለቱ አገራት በመንግሥታትና በሕዝቦች ደረጃ የነበራቸው መቀራረብ እያደገ ከመምጣቱ የተነሳ ከ1928 ዓ.ምቱ የጣሊያን ወረራ በፊት ፈረንሳይኛ ቋንቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለትምህርት ቤቶችና ለዘመናዊ የአስተዳደር ሥራ ያገለግል እንደነበር የሚያብራራው “የመቶ ዓመት ወዳጅነት” መጽሐፍ፤ ቅኝ ግዛትን በጦር ሜዳ ያሸነፈችው አገር፤ የኃይል ሚዛን መቆጣጠር ፈላጊዎቹ ቋንቋቸው በኢትዮጵያዊያን ተፈላጊ እንዲሆን ያደረጉትን ትግል ሲያመለክት፤

“ፈረንሳይኛ ቋንቋ ከጦርነቱ በኋላ በእንግሊዝኛ ተተካ፡ አፄ ኃይለሥላሴና ዙሪያቸው የነበሩ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ባለሟሎቻቸው ይህንን የእንግሊዝኛ ተጽእኖ ለመገደብና፣ ፈረንሳይኛን ለመጠበቅ ፈለጉ፡፡ ልክ ከጦርነቱ በኋላ በኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ የተከሰተው ይህን የእንግሊዝኛና የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች መፋጠጥ ለመግታት፣ የሊሴ ገብረማርያም የፈረንሳይ ትምህርት ቤት ተከፈተ፡፡ በተጨማሪም አሊያንስ ፍራንኮ ኢትዮፕየንም እንደገና በአዲስ መልክ እንዲዋቀር ተደረገ፡፡

አልፎ አልፎ ቃልን መጠበቅ ያለመቻል ነገር ቢታይም ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ነፃ አገርነት በ1889 ዓ..ም በተዋዋለችው ስምምነት ጭምር ግልጽ አድርጋ ነበር፡፡ በዚያ ስምምነት ፈረንሳይ ጅቡቲን በቅኝ ገዢነት ስትለቅ ለኢትዮጽያ ልትሰጥ ተስማምታ እንደነበርና ንጉሥ ኃይለሥላሴም ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ለፈረንሳይ ያነሱ እንደነበር መጽሐፉ ያብራራል፡፡

አፄ ኃይለሥላሴ ከሌሎች ቋንቋዎች ይልቅ ፈረንሳይኛ በአገራቸው እንዲስፋፋ የፈለጉት በዚህ ምክንያት እንደሆነ መገመት ቢቻልም ሌላም ሰበብ ነበራቸው ይላል መጽሐፉ፡ እንግሊዝና አሜሪካን የጫኑባቸውን የሞግዚትነት ቀንበር አሽቀንጥሮ ለመጣል ይፈልጉ ስለነበር ከሩሲያ፣ ከዩጐዝላቪያ፣ ከቻይና፣ ከግብጽ …መንግሥታትና ሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠንከር ይተጉ የነበረው በዚህ ዓላማ ነው፡፡ ንጉሥ ኀይለሥላሴ ለፈረንሳዊያንና ለቋንቋቸው የተለየ አክብሮት እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው ሌሎች ታሪካዊ ምክንያቶችም ነበሩ፡፡ በ1893 ዓ.ም በሐረር የሥጋ ደዌ ሆስፒታል የሚሰሩ የፈረንሳይ ቄሶች እያሳተሙት እስከ አዲስ አበባ ድረስ የሚያሰራጩት ጋዜጣ ነበር፡፡ ከ1905 -1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሚኖሩ ፈረንሳዊያን የሚዘጋጅ ጋዜጣ ነበር - ለ፡ኩርየር የሚባል፡፡

“ኢትዮጵያ የሊግ ማሕበር አባል እንድትሆን፣ አባል ከሆነች በኋላና እንዲሁም የፋሽስት ወረራ ጥላ ያንዣብብ በነበሩበት ከባድ የፈተና ዓመታት ሁሉ የኢትዮጵያ ጥቅም ዋና ደጋፊ ከነበሩት ጋዜጦች መካከል አንዱ ይሄው ለ ኩርየር ጋዜጣ ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ጣሊያኖች ኢትዮጵያ እንደገቡ ከተባረሩት የመጀመሪያዎቹ ፈረንሳዮች አንዱ ሮቢያር የተባለው የዚህ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው፡፡”

ፈረንሳዊያን ለኢትዮጵያ በባሕል፣ በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በሳይንስ፣ በቴክኒክ…ብዙ ተግባራትን ማከናወናቸውን የሚያበራራው “የመቶ ዓመት ወዳጅነት“ የተሰኘው መጽሐፍ፤ በአገሪቱ መዲናና ከአዲስ አበባም ውጭ ፈረንሳዊያን ማተሚያ ቤት በመክፈት፣ ትላልቅ የንግድ ኩባንያዎችን በማቋቋም፣ አሊያንስ ፍራንሲስን ጨምሮ ወደ 30 የሚደርሱ የባህል ማዕከላትና ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት ዕውቀትና እድገት እንዲስፋፋ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ይጠቅሳል፡፡ በሕትመት ዘርፍ ያደረጉትን ጥረት መጽሐፉ ሲያትት፡-

“በአንቷን ዳባዲ መሪነት በ1843 ዓ.ም ፓሪስ በሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መፃሕፍት ውስጥ የተቀረፀውን የግዕዝ ፊደል ሕትመት ሞንዶን ቪዲዬ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ አለማመደው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ የሕትመት ፊደል ለኢትዮጵያ ጽሕፈት አጣጣል ሥርዓት ዋነኛ መለኪያና ማነፃፀሪያ ሊሆን ችሏል፡፡ የማተሚያ ቤት ሥራ መጀመር ለኢትዮጵያ የአብዮት ያህል የሚቆጠር ነበር፡፡ ምክንያቱም የጽሕፈት ጥበብ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንኳን ጥንታዊነት ቢኖረውም፤ የጥበቡን መስፋፋት የሚቃወሙ የጥቂትና የውስን ሰዎች ብቸኛ ይዞታና ሞያ (ወይም ሞኖፖል) ነበርና፡፡ እነዚህም ፀሐፍት በእጅ የሚጽፏቸውን የብራና መሕፍት ሌሎች ሰዎች እንዳያዩዋቸው ጥብቅ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፡፡”

ፈረንሳዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ የፍትሐ ብሔር ሕግ ሲረቀቅ፤ የእንስሳት ሕክምናን በተመለከተ የፖስተር ኢንስቲትዩት ሲመሠረት፤ በማዘጋጀ ቤት የሚተዳደር የምሕንድስና ትምህርት ቤት በመክፈቱ ሂደት…ሰፊ አስተዋጽኦ ነበራቸው የሚለው መፅሃፉ፤ የብሔራዊ ባንክ ሕንፃን የሠራው አርክቴክትና ብሔራዊ ቴአትር አጠገብ የሚገኘውን የአንበሳ ሐውልት የቀረፁ ፈረንሳዊያን ማንነትን ይገልፃል፡፡

“የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ጥናት” በሚል ርዕስ በቀረበው ምዕራፍ ደግሞ ፈረንሳዊያን በዘርፉ ያደረጉትና ያስመዘገቡት ውጤት በስፋት ቀርቦበታል፡፡ ከቋንቋ እስከ አርኪኦሎጂ ጥናት፤ ከቤተመንግሥት እስከ ተራው ሕዝብ ኑሮ መፈተሻቸው ይታያል፡፡ በዛርና በርኩስ መናፍስት አሰራር ዙሪያ ሳይቀር ለጥናት የማሰኑ ፈረንሳዊያን ነበሩ - ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡

የፈረንሳዊያኑ ተግባርና በአገራችን ያቋቋማቸው ማዕከላትን ለኢትዮጵያውያን እንዳበረከቱት አስተዋጽኦ ተቆጥሮ በኪነጥበብ ባለሙያዎች የምስጋና ፕሮግራም ሊዘጋጅላቸው እንደሆነ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ “ኪነጥበባዊ ዜና” ላይ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 115ኛ ዓመት ላይ የፈረንሳይ ባህል ማዕከል የተቋቋመበትን 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የምስጋና መድረክ ማሰናዳታቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡

 

 

Read 1298 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 11:07