Saturday, 17 August 2019 13:16

ሙጋቤ በሲንጋፖር ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለቤታቸውና የወቅቱ ፕሬዚዳንት ልጅ በሚሊዮኖች ዶላር ሙስና ተከስሰዋል


              የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከአራት ወራት በፊት በጸና ታምመው ሲንጋፖር ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል መግባታቸውንና አሁንም ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ኦልአፍሪካን ኒስው ዘግቧል፡፡
የ95 አመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ ወደ ሆስፒታሉ ከገቡ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በተደረገላቸው የህክምና እርዳታ ጤናቸው እየተሻሻለ መምጣቱንና በቅርቡ ከሆስፒታል ይወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋ ማስታወቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ምናምግዋ ከወራት በፊትም ሙጋቤ በህመምና በእርጅና ሳቢያ ራሳቸውን ችለው መቆምም ሆነ መራመድ እንደማይችሉ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ አሁንም የሙጋቤ ጤንነት መሻሻሉን እንጂ ያጋጠማቸውን የህመም አይነት በተመለከተ ምንም አይነት መረጃ እንዳልሰጡ ገልጧል፡፡ ዚምባቡዌን ለ38 አመታት ያህል ያስተዳደሩትና በ2017 በተደረገባቸው ጫና ያለ ፍላጎታቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ የጤናቸው ሁኔታ እየተስተጓጎለ በመምጣቱ  በየወሩ በሚባል ደረጃ ወደ ሲንጋፖር እየተመላለሱ የህክምና ክትልል ሲያደርጉ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋ ልጅና የቀድሞዋ የአገሪቱ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያለአግባብ ተበድረው ሳይከፍሉ ቀርተዋል በሚል የሙስና ክስ እንደተመሰረተባቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሁለቱን ግለሰቦች ጨምሮ 26 ያህል የአገሪቱ የቀድሞ ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2014 በነበሩት አመታት የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ህግና አሰራር ከሚፈቅደው ውጭ በድምሩ 15 ሚሊዮን ዶላር በመበደር ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውንና ዕዳቸውን አለመክፈላቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከግለሰቦቹ መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተበድረው አስቀርተዋል የተባሉት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ሲሆኑ የባለቤታቸውን ስልጣን መከታ በማድረግ፣ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ያህል ከባንኩ ወስደው አለመመለሳቸውንና የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋ ልጅ ኤመርሰን ጁኒየር በበኩሉ፤ 400 ሺህ ዶላር ወስዷል መባሉንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 1172 times