Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 10:57

የሐሳብ ታቦታት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መጋረጃው ሲገለጥ የንጉሡ ዙፋን አለ፡፡ መንጠላቴቱ ሲከፈት መንበሩን እናያለን፡፡ በመንበሩ ላይ ታቦቱን …በታቦቱ ውስጥም …ፅላቱን…በፅላቱ ላይ ቃላቱ፡፡ የትዕዛዝ ቃላቶች፡፡ ቃላት የሐሳብ መሠወርያ ታቦታት ናቸው፡፡ ሐሳቡ በራሱ ደግሞ ሊል የሚፈልገው ነገር ጽላት ነው፡፡ የምንደርስበት ነገር ደግሞ ነገሩ በቁሙ ካለው ማንነት ውጪ መንፈስ የሚመገበው መስዋዕት ነው፡፡

ምሳሌ አንድ…

ሊነገረን የተፈለገው ነገር በውስጡ አለ እንጂ ነገሩ (ሃሳቡ) ራሱ በራሱ ፍፁም መልዕክት ሊሆን አይችልም…(የጠይም ሕዝብ ማንነት ነውና)…

ይህ ከላይ የተፃፈው ሐሳብ ለመፃፍ የምሻው ነገረ - ሐሳብ ተምሣሌቱ ነው፡፡ በየሠከንዱ በተናገረንና በፃፍን ቁጥር “ለምሣሌ” ማለታችን ነው…

ዘወትር “ለምሳሌ” እንዳልን ነው፡፡ ለምሣሌ ብለን ስንናገር…ስንጽፍ …ስናወራ እራሱ ምሳሌን ለማስረዳት ነው (ምን ዐይነት መደናቆር ነው…ባካችሁ…ግራ የገባ ነገር)ምሣሌ አንድ ብዬ ምሣሌዬን የቀጠልኩት “እንዴት” ሊል የሚችል ሰው ይኖራል በሚል ግምት እንጂ…ሐሳቤን ጠቅልዬ ነበር (ነበር ለምን አልኩ?...)“እንዴት?” የሚለው ሐሳብ ለወለደው ጥያቄ ማናቸውም ማብራሪያ…በውስጡ ለምሣሌ የሚል የገለፃን መንደርደሪያ ያዘለ ነው (ይኸው ለኛ ሐገር ሥላልገባንና ሥላልተግባባን እስከመጨረሻይቱ ሕቅታ ድረስ ለምሣሌ እንደተባልንና እንዳልን …ከእንቅልፋችን ሳንነቃ…ወደ ዘለዓለሙ እናሸልባለን) ጥቂቶች “መንግሥተ ሰማያትን የማወቅ ምስጢር ስለተገለጠላቸው” ከምሣሌው ተነጥለዋል…

በተፃፈው ነገር ውስጥ ሌላ የሚነገረን አለ፡፡ የተፃፈው ልብስ ነው፡፡ ሐሳብ የምትባል ውብ ሴት ጡቶቿንና ሐፍረቷን…በሥሥ…የቃላት ሐር… የተሸፈነችበት ልብስ፡፡ ያውም የሌሊት ልብስ፡፡ ሐሳብ የለበሰችውን የቃላት ሐር ከገላዋ ….ስንገፈው…ሐፍረቷንና…ጡቶቿን…ማንነቷንና ውበቷን ብንመለከትስ…የመጨረሻው ነው ወይ?

ለምሣሌ ሁለት…

አሁን እየፃፍኩት ባለው ነገር ውስጥም የሚፈለገውን ሐሳብ…. ቃላቱን ለመዳሰስ መሞከር ከንቱ ልፋት ነው…ቃላቶቹ ልብሶች ናቸው፡፡ ግልጽ የመሰሉን ቃላት እንኳ ስውር ናቸው፡፡ (የሴቲቱን ሴትነት መመልከት ሴቲቱን ማወቅ ላይሆን ይችላል)…

ለምሣሌ ሦስት…

ከላይ በሕቡዕ የተናገረውን ደገመው ለሚል አስተዋይ

የኔ ፍላጐት የአንተ መረዳት ብቻ አይደለም፡፡ የአምላክ ፍላጐት የሰው መፈጠር እንዳልሆነ… ሁሉ ከመሆን (ከመፈጠር) ኋላ…ብዙ መገለጦች ስለሚያስፈልጉ… በተፃፈው መሃል ሊባል የተፈለገው…ሴቲቱ የራት ልብሷን ለብሳ በጐዳና ብናገኛት…የሚመስለን እና የምትመስለው…አንዳች የራት ግብዣ ላይ ለመገኘት ሊሆን ይችላል…ግን ባይሆንስ…የሚመስለን …ለምን የሚሆነው ይመስለናል…

…ጽሑፍ ወይም ድርሰት …መቸም መች ራቁታቸውን አናገኛቸውም፡፡ የተፃፈውን ሐሳብ መዘን ስንተነትን እንኳ እሱ (የሚተነተነው ነገረ ሐሳብ) የምናብራራለት ሃሳብ አልባስ እንጂ…ራሱ ሁኔታውን አይደለም…ሁኔታ አካላዊ እንጂ ፊደላዊ ሃሳብ አይደለምና፡፡ ፊደላዊ ሐሳብ ግን የአካላዊ ሁኔታ ተምሣሌት ነው፡፡

አዝማች …

ቃላት…የሐሳብ መሰወርያ ታቦታት ናቸው፡፡…ሐሳቡ በራሱ ደግሞ ሊነግረን የሚፈልገው ጉዳይ… ፅላት ነው፡፡ … በቃላት ድንጋይ…በሐሳብ ሸለቆ- የተሠወረው ደግሞ …ልንደርስበት የምንጉዋዝበት ጎዳና ነው፡፡ ለጥቅሉ ሐሳብ… መንፈስ የሚመገበው መስዋዕት ነው…

ለምሣሌ አራት…

የዚህ ጽሑፍ ሐሳብ ክቡርነት ቢኖረውም፤ ተምሣሌትነቱ ግን…በሚስማሙበት ነገር ላይ የሚነታረኩ…የሚጨቀጭቁ …የሚጨቃጨቁ…የከንቱ ሃበሾችን…የሙሉ ጊዜ ዲስኩር ሊወክል ይችላል….

እንደ ምሁር ሠምተው እንደደብ የሚናገሩ…ሰዎች…ተምሣሌት፡፡

ለምሣሌ አምስት…

እዚህ ጽሑፍ ላይ…ጥያቄ … ቢኖርህ …ነቀፌታ … ቢኖርህ …ምሥጋና…ቢኖርህ…ማንኛውም ዓይነት ሐሣብ…ቢኖርህ ለምሳሌ እያልከኝ ነው ማለት ነው፡፡

ምክንያቱም …

ሊነገረን የተፈለገው ነገር በውስጡ አለ እንጂ ራሱ የተገለፀው ሃሳብ ግን ፍፁም መልዕክቱን (ነገሩን) አይደለምና…

ይሄ ከላይ ያለው…መዝጊያ…የሚመስለው ሃሳብ…በራሱ ዕንኳ…ለምሣሌ …አይበለን…እንጂ…ለምሣሌ …እያለን…ነው…

ለምሣሌ ስድስት…

ስለ መዝጊያ የተፃፈው …ሐሳብ…ስለመዝጊያው ሊነግረን…ነው…ወይስ …በራሱ…የራሱ ትርጉም አዝሏል፡፡

ለምሣሌ ሰባት…

አሁን የምጽፈው …ያልፃፍኩት… ስለዓለመፃፌ….የፃፍኩት…ይኼስ?

 

 

 

Read 1685 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 11:09