Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:09

ቃለ ምልልስ “ስቶክ ማርኬት” - ያልተጠቀምንበት የገንዘብ ገበያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • በዓለም 80 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ሀብት በስቶክ ማርኬት ውስጥ ይንቀሳቀሳል
      • በየዓመቱ 19 ትሪሊዮን ዶላር የአክስዮን ድርሻ - ሽያጭና ግዥ ይፈጸማል

               “-- ድርጅቶች የዚህ ዓይነት ዕድል ባገኙ ቁጥር ብዙ የሰው ኃይል ይቀጥራሉ፡፡ በአነስተኛ ዋጋ ብዙ የማምረት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ በአገር ደረጃ የሚኖረውን የሸቀጥ ዋጋ ይቀንሳል፣ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን ያስችላቸዋል፡፡ የውጭ ምርቶችን የመተካት ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ድርጅቶች ደግሞ በውጭ አገር ገበያ በዋጋ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል፡፡--

              የተመረቁት በሕክምና ቢሆንም በሙያቸው የሰሩት ለጥቂት ወራት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በሌላ ሙያ ላይ ነው የተሰማሩት፡፡ የተለያዩ የቢዝነስና
የሥነ-ልቦና መጻሕፍት በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ የመንግሥትና የግል ተቋማትንም በቢዝነስ ሙያ ያማክራሉ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ
አድሚኒስትሬሽን ከአሜሪካው ሊንከን ዩኒቨርሲቲአግኝተዋል - ዶ/ር አቡሽ አያሌው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በኔክሰስ ሆቴል፣ ለንግዱ ማኅበረሰብ ስለ”ስቶክ ማርኬት” ዕውቀትና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የፓናል ውይይት አዘጋጅተው ነበር፡፡ በተመሳሳይ ቀንም “ኢንቨስትመንትና ስቶክ ማርኬት” በሚል ርዕስ በስቶክ ማርኬት ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ አስመርቀዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ፤ዶ/ር አቡሽ አያሌውን፣ ለአገራችን እንግዳ በሆነው በስቶክ ማርኬት ዙሪያ በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-



             ስቶክ ማለት ምንድነው?
ስቶክ ማለት የአንድ ድርጅት የሀብት መጠን ድርሻ ማለት ነው፡፡ ሕጋዊ ስቶክ ማርኬት ደግሞ የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አካል የሆነ፣ ሕጋዊ የገንዘብ ሰነድ መገበያያ ቦታ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ድርጅት መቶ ሚሊዮን ብር ካፒታል ቢኖረውና ከዚህ ሀብት ውስጥ 10 ሚሊዮኑን ለሌላ ሰው ቢያስተላልፍ የ10 ፐርሰንት ስቶክ አስተላለፈ ማለት ነው፡፡ ስቶኮች፤ ሼሮችም ይባላሉ፡፡ በእኛ አገር እነዚህ ሼሮች አክሲዮን እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ስለዚህ ስቶክ ማርኬት፤ እነዚህ ሼሮች ወይም አክሲዮኖች፣ ሕጋዊነትን በጠበቀና ግልጽነትን ባዳበረ መንገድ፣ የሼሮች ሰርተፊኬቶችን ኅብረተሰቡና ነጋዴው የሚገበያዩበት ስፍራ ማለት ነው፡፡ ከእዚህም ሌላ ቦንድ በመባል የሚጠሩ የዕዳ ሰነዶችንም ይጨምራል፡፡
ስንት አይነት ስቶኮች አሉ?
እንደየ ድርጅቱ የተለያዩ ዓይነት ስቶኮች አሉ፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች አዳጊ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ግዙፍ ይሆናሉ፡፡ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ስቶኮችም አሉ:: ስለዚህ ስቶኮች እንደ ድርጅቱ ዓይነት ይለያያሉ፡፡ የቴክኖሎጂ ስቶክስ፣ ሳይክሊካል ስቶክስ ይባላሉ፡፡ አዳጊ ድርጅት ከሆኑ ግሮውዝ ስቶክስ፣ ትልልቅ ድርጅቶች ከሆኑ ደግሞ ብሉቺፕስ ስቶክስ እንላቸዋለን፡፡ የሚዋዥቅ (ተቀያያሪ) ዋጋ ያላቸው ሲሆኑ ደግሞ ሳይክሊካል ስቶክስ ይባላሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ኮመን ስቶክና ፕሪፈርድ ስቶክ ይባላሉ፡፡ አንድ ድርጅት ሆኖ ፕሪፈርድና ኮመን ስቶክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ፕሪፈርድ ስቶክ የምንለው፣ የተለየ ጥቅም የሚያስገኝ የሀብት ድርሻ ዓይነት ነው፡፡ ኮመን ስቶክ ደግሞ የተለየ ጥቅም የሚያስገኝ ሳይሆን በስቶክ ማርኬት ደረጃ የሚሸጥና የሚገዛ የስቶክ ዓይነት ነው፡፡ በድርጅቶች ውሳኔ ላይም ድምጽ የመስጠት ዕድልን ለባለቤቶቹ ይሰጣል፡፡  
ስቶኮች የሚገዙትና የሚሸጡት የት ነው?
ይኸንን ጥያቄ በምሳሌ እንይ፡፡ ሰዎች ዕቃ መግዛት በሚፈልጉበት ጊዜ የሚሄዱት ወደ ሱፐር ማርኬት ነው እንበል፡፡ ሱፐር ማርኬት ማለት በሕግ ደረጃ፣ ፈቃድ የተሰጠው፣ በሼር ካምፓኒ ወይም በፒኤልሲ የተቋቋመ ሆኖ፣ ዋና ስራው ከሻጮች የተለያዩ ሸቀጦችን በመሰብሰብ ገዢዎች ሲመጡ፣ ሻጮች በሚተምኑት ዋጋ ልክ፣ ለገዥዎች መሸጥ ነው፡፡ ዕቃው ሳሙና፣ ምግብ፣ የባልትና ውጤት… ሊሆን ይችላል፡፡ ገዥዎች የዕቃውን ዋጋ ለገንዘብ ተቀባይዋ ይሰጡና እሷም ደረሰኝ ሰጥታቸው፣ የገዙትን ዕቃ ይዘው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ሱፐር ማርኬት የተለያዩ ሸቀጦች የሚሸጡበት፣ ሻጮችና ገዥዎች የሚገናኙበት ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ሸቀጥ ማገበያያ ቦታ ማለት ነው፡፡
ስቶክ ማርኬት ስንልም፤ ራሱን የቻለ በሼር ኩባንያ የተቋቋመ፣ ባለቤቶች ያሉት ሕጋዊ ተቋም ነው፡፡  የዚህ ኩባንያ ዋና ዓላማ፤ የተለያዩ ድርጅቶችን የአክሲዮን ሰርተፊኬት ወይም የቦንድ ሰርተፊኬት በሚተመንላቸው የዋጋ መጠን፣ ለገዥዎች የሚሸጥበት የገንዘብ ሰነዶች ማገበያያ ተቋም ነው፡፡ በሱፐር ማርኬት ምሳሌ ብናየው፣ በሱፐር ማርኬት የሚኖሩት ሸቀጦች ሲሆኑ ስቶክ ማርኬት ስንመጣ፣ የአክሲዮን ሰርተፊኬቶችና የቦንድ ሰርተፊኬቶች ይሆናሉ፡፡ የአክሲዮን ሰርተፊኬቶች፣ የሀብት ድርሻ ሰነዶች ማለት ናቸው፡፡ የቦንድ ሰርተፊኬቶች የሚባሉት ደግሞ የዕዳ ሰነዶች ማለት ናቸው፡፡ ስለዚህ ስቶክ ማርኬት ማለት እነዚህን ሰነዶች በሕጋዊ ማዕቀፍ በግልጽ መንገድ፣ በሻጮችና በገዥዎች መካከል የሚያገበያይ፣ በመንግስት ደረጃ ቁጥጥር የሚደረግበት ተቋም ማለት ነው፡፡
ስቶክ ማርኬትን በአገራችን ከምናውቀው የአክሲዮን ገበያ ለየት የሚያደርገው የሕግ ማዕቀፉ ነው፡፡ በስቶክ ማርኬት ተቋም ሼሩን ከአንድ ድርጅት የገዛ ሰው፣ ለሌላ ሰው መሸጥ ይችላል፡፡ ከአሁን በፊት በነበረው አሰራር፣ ብዙ ግለሰቦች ከድርጅቶች ብዙ አክሲዮኖችን ገዝተዋል፡፡ ነገር ግን ለሌላ ሰው አትርፈው የሚሸጡበት መንገድ አልነበረም፡፡ ስቶክ ማርኬት ግን አትርፈው መሸጥ ያስችላቸዋል፡፡ ሌላ ደግሞ ግልጽነት ባለው መንገድ ሼራቸውን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ ግልጽነት ባለው መንገድ ማጭበርበር ሳይኖርበት፣ ትክክለኛና ወቅታዊ የስቶክ ዋጋውን በጠበቀ መልኩ፣ ለሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ የሚችልበት ሕጋዊ ማዕቀፍ ይኖረዋል፡፡
ሕጋዊነቱን የሚቆጣጠር ኮሚሽንም ይቋቋማል:: የአሜሪካንን የስቶክ ማርኬት  ልምድ ብንወስድ፣ የሴኩሪቲ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን የሚባል ተቋም አላቸው፡፡ የዚህ ተቋም ዋና ዓላማ፤ የሰነዶችን ትክክለኝነት ለገዢዎችም ለሻጮችም ዋጋ ባለው መንገድ ሳይጭበረበሩ፣ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍበትን መንገድ የሚቆጣጠር፣ በመንግሥት የሚቋቋም ተቋም ነው፡፡ በውስጡ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎች አሉት፡፡  ሌላው ደግሞ ስቶክ ማርኬት ውስጥ የተለያዩ ፕሮፌሽናል ሰራተኞች ይሳተፋሉ:: ለምሳሌ የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ የድርጅቶችን የሀብት መጠን ይተምናሉ፤ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሪፖርቶች በትክክለኛው ባለሙያና ተዓማኒ በሆነ መንገድ መሠራታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ስቶክ ብሮከርስ (የስቶክ ደላሎች) የሚባሉም አሉ፡፡ ስቶክ የሚሸጠውም ሆነ የሚገዛው በስቶክ ብሮከሮች (ወኪሎች) በኩል ነው፡፡ እነዚህ ወኪሎች ትክክለኛ ሙያው፣ እውቀቱና ባህሪው ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ፕሮፌሽናሎች ሊቆጣጠር የሚችል ሌላ ተቋም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ ፋይናንሻል ኢንዱስትሪ ሬጉላቶሪ ኦውቶሪቲ ይባላል:: በእኛ አገር ስቶክ ማርኬት ሲቋቋም፣ ያንኑ ስያሜ ልንወስድ እንችላለን፡፡ ወይም ደግሞ አገርኛ ስያሜ ልናወጣለት እንችላለን፡፡ ይህም ተቋም ከልዩ ልዩ ሙያ ነክ አስገዳጅ ህጐቹ ጋር ያስፈልገናል፡፡  
የስቶክ ኤክስቼንጅ መቋቋም ምን ጥቅም አለው?
ግለሰቦች ባላቸው ትንሽ ገንዘብ የድርጅቶችን የሀብት ድርሻ በአክሲዮን መልክ (በስቶክ) ወይም በቦንድ መልክ በመግዛት፣ አቆይተው፣ ለሌሎች ሰዎች በመሸጥ የሚያተርፉበትን መንገድ ይፈጥራል:: ለምሳሌ አንድ ሰው ቤት ቢገዛ፣ ያንን ቤት አንድ ወይም ሁለት ዓመት አቆይቶ ቢሸጠው የሚያገኘው የቤት ዋጋ ከፍታ አለ፡፡ በየዓመቱ የቤት ዋጋ ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ ቤቱን አንድ ሚሊዮን ብር ቢገዛው፣ ከሦስት ዓመት በኋላ 1.5 ሚሊዮን ብር ሊሸጠው ይችላል፡፡ በዚህ መካከል 500 ሺህ ብር አተረፈ ማለት ነው፡፡
ስቶክም ላይ አንድ ሰው በ10 ሺሕ ብር የገዛውን ስቶክ፣ 6 ወር አቆይቶ በ15 ሺሕ ወይም በ20 ሺህ ብር ሊሸጠው ይችላል፡፡ ስለዚህ አንድ የስቶክ ማርኬት ጥቅም ባለን ገንዘብ መጠን ልክ፣ የድርጅቶችን የሀብት ድርሻ ከገዛን በኋላ ለሌላ ፈላጊ የምንሸጥበትን መድረክ ስለሚያመቻች፣ ሰዎች ያላቸውን ገንዘብ ኢንቨስት አድርገው ትርፍ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ በዋናነት ደግሞ ግለሰቦች ከድርጅቶች የሀብት ድርሻ በሚገዙበት ጊዜ ድርጅቶች ለሚያስፈልጋቸው የሥራ ማካሄጃና ማስፋፊያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ዕድል ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ አንድ የሳሙና ፋብሪካ ብንወስድ፣ ይህ ፋብሪካ ጥሩ እየሰራ ነው ብለን እናስብ:: ከተቋቋመ ከሦስት ዓመት በኋላ ድርጅቱን ለማሳደግ ተጨማሪ ፋብሪካ መሥራት የሚያስችል 30 ሚሊዮን ብር አስፈለገው እንበል፡፡ የድርጅቱ ካፒታል 100 ሚሊዮን ብር ቢሆን፣ ባለንብረቱ 30 ሚሊዮን ብር ካገኘ ተጨማሪ ፋብሪካ በማቋቋምና ከፍተኛ ምርት በማምረት፣ ብዙ ብር ማፍራት ይችላል፡፡ ድርጅቱን በዚህ መልክ ለማስፋፋት የሚያስፈልገውን 30 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ያለው አማራጭ 1ኛ፤ ካለው ከራሱ አውጥቶ፣ ማለትም፣ የድርጅቱን ትርፍ በመጠቀም ማስፋፋት ነው፡፡ 2ኛ፤ ከባንኮች ብድር በመውሰድ ነው፡፡ ከባንኮች ከሆነ የማበደሪያ መስፈርት አለ፡፡ ወለድ አለው፣ መያዣ ይፈልጋሉ:: የድርጅቱን ወቅታዊ የፋይናንስ አቋም ያያሉ፡። ስቶክ ማርኬትን ያየን እንደሆነ፣ 30 ሚሊዮኑን ብር ለማግኘት፣ ከ100 ሚሊዮኑ ካፒታል ውስጥ 30 ሚሊዮኑን የድርጅቱን የሀብት ድርሻ በወቅቱ በሚኖራቸው የድርጅቱ የሃብት ተመን ላይ በመንተራስ፣ በአክሲዮን መልክ ይሸጣል፡፡ 30 ሚሊዮን ሲሸጥ፣ የ30 ፐርሰንቱን ሀብት ሸጠ ማለት ነው፡፡ ሰውዬው 30 ሚሊዮን ብር ካገኘ፣ ፋብሪካውን በማስፋፋት ብዙ ያመርታል ማለት ነው፡፡ ብዙ ሣሙና ባመረተ ቁጥር ወጪው ይቀንሳል፡፡ ይህንን በጋዜጣ ሕትመት ብናይ፣ ብዙ በታተመ ቁጥር የአንድ ነጠላ ጋዜጣ ዋጋው ይቀንሳል። ትንሽ ብዛት ያለው ሲታተም ዋጋው ይጨምራል፡፡
የድርጅቶች የካፒታል አቅም ባደገ ቁጥር ብዙ ማምራት ስለሚችሉ የማምረቻ  ዋጋ ይቀንሳል:: ለኅብረተሰቡ በጥሩ ዋጋ ይሸጣሉ፡፡ አቅማቸውን ስላሳደጉ ቀደም ሲል ከሚያተርፉበት በላይ ያተርፋሉ ማለት ነው፡፡ ድርጅቶች ይህንን ገንዘብ አግኝተው ሲስፋፉ፣ ተጨማሪ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልገው፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ማለት ነው። ይህን ጉዳይ በአገር ደረጃ ብናይ፣ ድርጅቶች የዚህ ዓይነት ዕድል ባገኙ ቁጥር ብዙ የሰው ኃይል ይቀጥራሉ፡፡ በአነስተኛ ዋጋ ብዙ የማምረት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ በአገር ደረጃ የሚኖረውን የሸቀጥ ዋጋ ይቀንሳል፣ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን ያስችላቸዋል፡፡ የውጭ ምርቶችን የመተካት ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ድርጅቶች ደግሞ በውጭ አገር ገበያ በዋጋ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቶችን ያሳድጋል፣ ምርታማነታቸውን ይጨምራል፣ በዋጋ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል። በአገር ደረጃ የዋጋ ንረቱን (ኢንፍሌሽን) ይቀንሳል:: የአገርን ኢኮኖሚ ያሳድጋል፡፡ በኤክሰፖርት ደረጃ ተወዳዳሪነትን በማሻሻል የውጭ ምንዛሬ ምጣኔን ያሳድጋል፡፡
ስቶክ ማርኬት ከታክስ አኳያ ያለው ጥቅም ምንድነው?
ከታክስ አኳያ ካየነው፤ ድርጅቶች ባደጉ ቁጥር ሽያጫቸውና ትርፋማነታቸው አብሮ ስለሚያድግ ለመንግስት የሚከፍሉት የታክስ መጠን ወይም የንግድ ስራ ገቢ ይጨምራል፡፡ ድርጅቶች ብዙ የሰው ኃይል በቀጠሩ ቁጥር መንግስት ከደሞዝ ታክስ የሚያገኘው ገቢ በዚያው መጠን ያድጋል:: ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ ስቶክ ማርኬት ለህብረተሰቡ ሁለት ዓይነት ጥቅሞች ይሰጣል፡፡ የአክሲዮኑ እንዲሁም የቦንዱ የዋጋ መጠን ያድጋል፤ ይኼ ካፒታል ጌይን የሚባለው ነው፡፡ መንግሥት ከካፒታል ጌይን ታክስ ይወስዳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቶች አክሲዮን ለገዛቸው ሰዎች ሲያተርፉ፣ የትርፍ ክፍያ (ዲቪደንድ) ይከፍላሉ፤ ሼር የገዙ ሰዎች በዓመቱ መጨረሻ ድርጅቱ ዲቪደንድ ሲከፍላቸው፣ የዲቪደንድ ታክስ ይከፍላሉ፡፡ መንግስት ከዲቪደንድ የሚያገኘው ታክስ ይጨምራል፡፡ እንዲሁም ቦንድ የገዙ ሰዎች ደግሞ ወለድ ሲያገኙ የወለድ ታክስ ይከፍላሉ፡፡ በአጠቃላይ ከካፒታል ጌይን የሚያገኘው ታክስ ይጨምራል፤ ኢኮኖሚው  ባደገና ድርጅቶች ብዙ በሸጡና ባተረፉ ቁጥር መንግሥት የገቢ ታክስ ያገኛል፡፡ ድርጅቶች ባደጉ ቁጥር ብዙ ሰዎችን ስለሚቀጥሩ የደሞዝ ታክስ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ መንግስት የታክስ መሰረቱን (ቤዙን) ከማስፋት አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ በጀቱንም ከውጭ እርዳታ ለመደጎምና ብድር ለመሸፈን የሚያደርገውን ድካምም ይቀንስለታል፡፡  
 ከአሁን ቀደም የዚህ አይነት ማርኬት ባለመኖሩ ብዙ ግለሰቦች ከተለያዩ ድርጅቶች አክሲዮን የገዙ አሉ፡፡ ለምሳ ከኢንሹራንሶች፣ ከሪል ስቴቶች፣ ከባንኮች፣ ከቢራ ፋብሪካዎች -- አክሲዮኖችን የገዙ ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በድርጅቶች ውስጥ ያላቸውን ሼር መሸጥ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም በግልጽነት የካፒታል ጌይን አግኝተው ወይም አትርፈው ያላቸውን ሼር ማሻሻጥ የሚችል ሕጋዊ ማዕቀፍ ያለው አሰራር አልነበረም፡፡ ይኼ የስቶክ ማርኬት ያለመኖር ያመጣባቸው፣ ሀብት የማፍራት ነፃነታቸውን የነፈገ አሠራር ነው፡፡
ማንኛውም ሰው ሃብት የማፍራት ነፃነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ብዙ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ያየን እንደሆነ፣ ወደ አገሪቱ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ኢንቨስት አድርገው ተመልሰው መውጣት ሲፈልጉ ድርሻቸውን ወይም አክሲዮኖቻቸውን ሸጠው መሄድ ይፈልጋሉ። ነገር ግን አክሲዮኖቻቸውን መሸጥ የሚያስችል የገበያ ማዕቀፍ የለም፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ነገር የለም፡፡ ስቶክ ማርኬት ቢኖር ኖሮ ግን፣ ስቶክ ማርኬት ላይ ወይም የንግድ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች፤ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክቱ ነበር፡፡
በዓለም  ደረጃ በተደረገ ጥናት በዓመት ወደ 80 ትሪሊዮን ዶላር የሚተመን ሀብት በስቶክ ማርኬት ውስጥ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ ወደ 19 ትሪሊዮን ዶላር የሚሆን የሼር ድርሻ ግዢና ሽያጭ ይከናወናል፡፡ ይህ ማለት በቅንነትና በብልሀት ልንጠቀምበት ከፈለግን በስቶክ ማርኬት ውስጥ በጣም ብዙ ሀብት አለ ማለት ነው፡፡
በስቶክ ማርኬት ዙሪያ የሚያጠነጥነውና በቅርቡ የተመረቀው መጽሐፍህ፣ ከስቶክ ማርኬት ንግድ አንፃር ምን ያግዛል?
መጽሐፉ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን በስቶክ ማርኬት ሳይንስና ግብይት ዙሪያ እንዲሁም በኢንቨስትመንት አወሳሰን ሥልቶች ሰፊ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያግዛል፤ ህብረተሰቡም ከወዲሁ እራሱን አዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡    

Read 3169 times
Administrator

Latest from Administrator