Saturday, 17 August 2019 12:55

“ኢዮሃ እንቁጣጣሽ ኤክስፖ” ዛሬ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትና ኡቨንት ያዘጋጀው “ኢዮሃ እንቁጣጣሽ ኤክስፖ 2012” ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ትልልቅ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ አርቲስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች በሚገኙበት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይከፈታል፡፡
በዘንድሮው ኢዮሃ እንቁጣጣሽ ኤክስፖ “የኢዮሃ ስጦታ” በሚል መርህ ሥር በአገራችን የመጀመሪያውና ትልቁ አገልግል ባማረና በደመቀ መልክ ተሰርቶ ለእይታ እንደሚቀርብ ኢዮሃ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኤግዚቢሽን ማዕከልን ዲዛይን በመቀየርና ባለአንድ ፎቅ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የፌስቲቫል ይዘት ያለው ኤክስፖ እንዲሆን ጥረት መደረጉም ታውቋል፡፡
በ4 ባንዶች የሚታጀቡ ከ40 በላይ እውቅ ድምፃዊያን ለ26 ቀናት ኮንሰርት ማቅረባቸው፣ ከ50 በላይ በሆኑ የከተማችን ወጣቶች የሚቀርብ ዘመናዊና ባህላዊ ዳንስ፣ የታዋቂው ሰርከስ ደብረብርሃን አስደናቂ ትዕይንቶችና ሌሎችም ዝግጅቶች ኤክስፖውን የተለየና ከግብይት የበለጠ የፌስቲቫል ጣዕም እንደሚሰጡት የኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትና ኢቨንት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አዩ አለሙ ገልፀዋል፡፡
ከአንድ አመት ህፃን ጀምሮ ለልጆች ማቆያና መዝናኛ ቦታ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመዝናኛ ፓኬጁ የተዘጋጀው ህብረተሰቡን የሚያሳትፍና የሚያሸልፍ ዝግጅት እንደተጠበቀ ሲሆን፤ ዘንድሮ በኤክስፖው የሚሳተፉት አብዛኞቹ አምራቾች በመሆናቸው ህብረተሰቡ በፋብሪካ ዋጋ እቃዎችን በመግዛት ካላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ይድናልም ተብሏል፡፡
ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ቦታ የተዘጎጀ ሲሆን፤ መጥተው ገብይተውና ተዝናንተው እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረበው ኢዮሃ በዘንድሮው ኤክስፖ ከ400 በላይ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል፤ ኤክስፖውን በየቀኑ 9ሺህ ያህል ሰዎች ለ26 ቀናት እንደሚጐበኙትም ታውቋል፡፡  

Read 1006 times