Saturday, 27 July 2019 14:05

አዋሽ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ 10 ሺህ ችግኞች ተከሉ
                                 
              የአዋሽ ባንክና የአዋሽ ኢንሹራንስ ሠራተኞች፤ በመጪው ህዳር ወር የሚያከብሩትን 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ በእንጦጦ 41 እየሱስ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ 10 ሺህ የዛፍ ችግኞች ተክለዋል፡፡
የችግኝ ተከላው የተካሄደበት ቦታ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለ አደራ ማኅበር ሲሆን ለችግኝ መትከያ ጉድጓድና ለችግኞቹ ዝግጅት የሚያስፈልጉ ወጪዎች በሙሉ የተሸፈኑት እንዲሁም ለተተከሉት ችግኞች የወደፊት እንክብካቤ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ባንኩና ኢንሹራንስ ኩባንያው ለመሸፈን ቃል ገብተው፣ ችግኞቹ የራሳቸው መሆናቸውን ለመግለጽ በስማቸው ቦርድ አቋቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር፣ በእንጦጦ ኮረብታማ ስፍራ 1,300 ሄክታር መሬት ከመንግስት ተረክቦ፣ 500 ሄክታር በደን ማልበሱን ተከትሎ፣ አካባቢው ለዱር እንስሳትና ለአዕዋፋት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ እንደ አነር፣ ሚዳቋ፣ የምንሊክ ድኩላ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ የተለያዩ ወፎችና ሌሎች የዱር እንስሳት ከተሰደዱበት ወደ ፓርኩ መመለሳቸውን የማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሶበወርቅ ቅጣው ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ከአገሪቱ ቆዳ ስፋት 40 በመቶ ይሸፍን እንደነበር የሚነገርለት የአገራችን የደን ሀብት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሌሎች ክፍለ ኢኮኖሚዎች ሚና እየተመናመነ ወደ 3 በመቶ ደርሶ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ ያሉት የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው፤ የከፍተኛ ተራራዎችና አካባቢዎች መራቆት፣ በተወሰኑ ዓመታት ልዩነት ድርቅ በአገራችን መከሰት የዚሁ ወሳኝ የደን ሀብት መመናመን ውጤት መሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡
በ14.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በ486 ባለ አክሲዮኖች የተመሰረተው አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 4.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ፣ ከ400 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉትና በ2011 የበጀት ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡ ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በ10 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በ456 ባለ አክሲዮኖች የተመሰረተው አዋሽ ኢንሹራንስ፤ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ ከ425 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን ባለአክሲዮኖች ደግሞ 1,300 መድረሱ ታውቋል::  



Read 1963 times