Saturday, 27 July 2019 13:58

አድማስ ዩኒቨርሲቲ፣ ቅድስተ ማሪያምና ጌጅ ኮሌጅ ተማሪዎቻቸውን አስመረቁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    ኪዊንስ ኮሌጅ ማክሰኞ ያስመርቃል
                                                   

                 ባለፉት 20 ዓመታት የተማረ የሰው ሀይልን በማፍራት አስተዋፅኦ ሲያበረክት የቆየው አድማስ ዩኒቨርሲቲ፤ ባለፈው እሁድ ሀምሌ 14 በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በሚሊኒየም አዳራሽ አስመረቀ፡፡ ዩኒቨርስቲው 3121 በዲግሪ፣ 1668 በደረጃ 3 እንዲሁም 2059 በደረጃ 4 ቴክኒክና ሙያ ተማሪዎቹን አስመርቋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወ/ሃና በክብር እንግድነት ተገኝተው ተማሪዎቹን ከመረቁ በኋላ ለተመራቂ ተማሪዎች ምክርና የሥራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 1ሺህ 300 ያህል ተማሪዎቹን በመቀሌ ካምፓሱ ያስመረቀ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ 141 በዲግሪ እና 302 በደረጃ 4 በቴክኒክና ሙያ የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን የቢሾፍቱ ካምፓስ ተማሪዎቹን እንደሚያስመርቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሞላ ፀጋዬ አስታውቀዋል፡፡ አድማስ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት 20 ዓመታት ከ70 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
በተያያዘ ዜና ቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲም ባለፈው ቅዳሜ ሀምሌ 13 በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አስመርቋል፡፡ ቅድስት ማሪያም በመጀመሪያ ዲግሪ 382 ወንዶችና 749 ሴቶችን በድምሩ 1131፣ በሁለተኛ ዲግሪ 639 ወንድና ሴት ተማሪዎችን በድምሩ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ዲግሪ 1770 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ዲያስፖራትረስት ፈንድ የቦርድ ሰብሳቢና የህብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዛፉ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፤ ለተመራቂ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በትምህርታቸው ብልጫ ላሳዩ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀውን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፉት 16 ዓመታት የተማረ የሰው ሃይል በማብቃት አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየውና የካምፓሶቹን ቁጥር በማብዛት አገልግሎቱን እያሰፋ የሚገኘው ጌጅ ኮሌጅ፤ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ፤ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ደረጃዎች ያሰለጠናቸውን 6 ሺ 300 ተማሪዎች ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቋል፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክብር እንግዶች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ከ21 ዓመታት በላይ በመማር ማስተማር ዘርፍ በጽናት የዘለቀው ኩዊንስ ኮሌጅ፤ በቴክኒክና ሙያ፣ በአጫጭር ኮርሶች እንዲሁም በዲግሪና በድህረ ምረቃ ፕሮግራም እንዲሁም በርቀት የትምህርት መርሃ ግብሮች፣ የትምህርት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ሀምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በዲግሪ ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን 5007 ተማሪዎች ከ3፡00 ጀምሮ እንደሚያስመርቅ ኮሌጁ በላከው መግለጫ አስታወቋል፡፡

Read 3135 times