Saturday, 27 July 2019 13:53

የአባጅፋር አገር - ጂማ!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

 እዚህ አንድ ሰው ብሔሩን ቢጠየቅ “ጅማ ነኝ” ነው የሚለው
- አባጅፋር ከ150 ዓመት በፊት በሳኡዲ ቤት ሰርተዋል
- ሥራ ለመፍጠር ወይም ለመስጠት ቋንቋ አንጠይቅም
- ከተማዋን የማዘመን ሥራ ትልቁ የቤት ሥራችን ነው

             ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ የሆነችው ጂማ ከተቆረቆረች ወደ 200 ዓመት ገደማ  እንደሚጠጋት ይነገራል፡፡ የእድሜዋን ያህል አድጋና ተመንድጋ ባትታይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ መሻሻሎች እያሳየች መምጣቷን መመስከር ይቻላል” በታላቁ ንጉሷ አባጅፋር፣ በፍቅር ከተማነቷ እንዲሁም በቡና ምርቷ የምትታወቀው ጂማ፤ በቅርቡ ደግሞ   ሌላ አራተኛ ኩራት ጨምራልናለች ይላሉ - የከተማዋ ነዋሪዎች፡፡ ለመሆኑ የጅማ አራተኛ ኩራት ምን ይሆን? የኢንዱስትሪ ፓርክ ከተገነባባቸው ከተሞች አንዷ ብትሆንም፣ ፓርኩ እስከ ዛሬ ስራ አልጀመረም” ምን ገጠመው? የቱሪስት መዳረሻ የሆነው የአባ ጅፋር ቤተመንግስት የዛሬ አመት በበጀትና በባለሙያ ችግር ሳይታደስ ለአደጋ መጋለጡን ተመልክተን ነበር፡፡   የከተማዋ አስተዳደር ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ምን አቅዷል?  በሚሉትና በአጠቃላይ በከተማው እንቅስቃሴ ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መክዩ መሐመድ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡


            የጅማ ከንቲባ ከመሆንዎ በፊት የነበርዎትን ኀላፊነቶች ቢገልፁልኝ…
ትውልድና እድገቴ በዚሁ በጅማ አካባቢ ማና ወረዳ፣ የቡ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከጅማ ዩኒቨርስቲ በማህበረሰብ ጤና (ፐብሊክ ኸልዝ) ተቀብያለሁ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን፤ ከእንግሊዝ ክራምፕፊልድ ዩኒቨርስቲ በሴኩሪቴ ሴክተር ማኔጅመንት አግኝቻለሁ:: በሥራ ዓለም፤ የጅማ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ነበርኩ:: በፌደራል ደረጃም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ስሰራ ቆይቼ ነው በከንቲባነት ማገልገል የጀመርኩት::
እስቲ የጅማ  ከተማን የተለዩ “ኩራቶች” ይንገሩኝ…?
ጅማ እንግዲህ የጥንት ከተማ ናት፡፡ የጥንት ብቻ ሳትሆን ታሪካዊ ከተማም ጭምር ናት፡፡ በኢትዮጵያ 3ኛዋ ከተማም ናት፡፡ ከተቆረቆረች ወደ 200 ዓመት እየተጠጋት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጣሊያንም መሰረት ያደረጋት ከተማ ናት፡፡ የመጀመሪያውን በጣሊያን የተሰራውን ማስተር ፕላን እንኳን ያገኘችው በ1935 ዓ.ም ነው:: በአጠቃላይ ጅማ ብዙ ሊነገርላት የሚችሉ ታሪኮች አሏት፡፡ ግን በዋናነት ግን ሶስት ነገሮች ጅማ ሲነሳ አብረው ይነሳሉ፡፡ አንደኛው ጅማ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ቡና ነው፡፡ ጅማ የቡና መገኛ ብቻ ሳይሆን ቡና በስፋት የሚመረትበት አካባቢ ነው፡፡ አብዛኛው ወረዳ ቡና በብዛት ያመርታል፡፡ የህዝቡም ህይወት ቡና ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሁለተኛው ጅማ ሲነሳ የሚነሳው ፍቅር ነው፡፡ ጅማ የፍቅር አገር ነው:: የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ከተማ ብትኖር ጅማ ናት፡፡
ጅማ ስትመጪ በቃ ጅማነት ይጐላል፡፡ በኪነ-ጥበቡም ብዙ የተሰራበት ከተማ ነው፡፡ “የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና” የተሰኘው ቡናን ከፍ አድርጐ ያስተዋወቀው መዝሙር፣ እዚሁ ጅማ ነው የተሰራው፡፡ ሌሎች በርካታ የኪነ-ጥበብ ስራዎችም ተሰርተውባታል፡፡ ኪነ-ጥበብ ባለበት ደግሞ ፍቅር - መተሳሰብ አለ፡፡ እዚህ ከተማ አንድን ሰው ብሔሩን ብትጠይቂው፤ “ጅማ ነኝ” ነው የሚልሽ፡፡ አባ ጅፋር ከሌላው የኢትዮጵያ ንጉሶች የሚለዩበት ብዙ ነገር እያላቸው ብዙ ያልተፃፈላቸውና ያልተነገረላቸው ንጉስ ናቸው፡፡ ስድስት ሚስቶችን ከተለያየ ብሔር አግብተዋል፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የሚታወቁ ሲሆኑ በንግስና ዘመናቸው አንድም ጊዜ ለጦርነት ያልተጋበዙ ንጉስ ናቸው፡፡
አባጅፋር ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ታገኛለሽ፤ አባጅፋር ውስጥ ዲፕሎማሲንም ታገኛለሽ፡፡ እንግዲህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ የሀገሬ ሰው ሳዑዲ ሲሄድ የሚያርፍበት ቤት ልስራ ብለው ከዛሬ 152 ዓመት በፊት ቤት የሰሩ የሚገርሙ ንጉስ ናቸወ፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ መካ መዲና የሄደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ እሳቸው በሰሩት በዚያ ቤት ውስጥ ያርፋል፡፡ ከዚህም አልፎ ከተለያዩ የሩቅ ምስራቅ አገራት ጋር ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነበራቸው:: አባጅፋር በአጠቃላይ ለጅማና ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕሴት ጥለው ያለፉት ንጉስ ናቸው፡፡ ይሄ የመልካም ግንኙነትና አስተዳደር እሴታቸው ደግሞ በጅማ ህዝብ ላይ ይንፀባረቃል:: በጅማ ህዝብ መሃል ረብሻና ግጭት አይስተዋልም:: ሁሌም ፍቅርና ሰላም ነው፡፡ አገሪቱ በአስቸጋሪ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ሆና ጅማ ሁሌም የተረጋጋች ነበረች:: ይሄ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን አባጅፋር ጥለውት ካለፉት መልካም አሻራ የተወረሰ ነው፡፡
ጅማ አራተኛ ኩራት ጨምራለች ብለውኛል - ነዋሪዎች፡፡ አራተኛው የጅማ “ኩራት” ምንድነው?
አራተኛው የጅማ ኩራት፤ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከጅማ ማህፀን የወጣ ነው፡፡ ቀደም ሲል የጅማ አንዱ ኩራት ስለሆነው ስለ ፍቅርና መተሳሰብ ነግሬሽ ነበር፡፡ የጅማ ህዝብ አንድም ፍቅርን የተማረው በቡናው ነው፡፡ ጠዋት ቡና ይጠራራል፤ ይወያያል፤ ማን ተጣልቷል? ማን ተኳርፏል? ይባላል፡፡ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ በጋራ ይፈልጋል፡፡ እርግጥ ይሄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባህልና ተግባር ቢሆንም፣ እዚህ ጅማ ላይ ግን ይጐላል፡፡ ከዚህ የፍቅር ከተማ የወጣው ዶ/ር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያን በፍቅርና በአንድነት ለማስተሳሰርና ለመምራት ብዙ እየለፋ ነው፡፡ ህዝቡ ከመጠላላትና ከመጠላለፍ ወጥቶ ለአንዲት አገሩ ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት እንዲሰራ እየጣረና እየተሳካለት ነው:: ወደፊት አምስተኛ… ስድስተኛ እያልን… ኩራቶችን እየጨመርን እንሄዳለን፡፡
በለውጡ ጊዜ ከተማዋን በከንቲባነት መምራት ብዙ ተግባዳሮቶች እንደሚኖሩት ይታወቃል፡፡ የእርስዎን ተሞክሮ ይንገሩኝ?
በከንቲባነት ማገልገል ከጀመርኩ አንድ አመት ከስምንት ወር ገደማ ሆኖኛል፡፡ የመጣሁት በለውጡ ወቅት ስለነበር በጣም በአስቸጋሪ ጊዜ ነው ከተማዋን ማስተዳደር የጀመርኩት:: እኔ ወደ ኃላፊነት ስመጣ፣ በርካታ የህዝብ ጥያቄ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በጅማ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ለለውጥ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ የፈተና ወቅት ነው ምንም ግጭት ሳይነሳ፣ የሰው ህይወት ሳያልፍ ለውጡን ለመምራት ስንጥር የቆየነው፡፡
የጅማ ከንቲባ ስሆን በሁለት ምክንያት ደስ ብሎኛል፡፡ አንደኛው፤ ጅማ ላይ ሁለት አይነት አመለካከቶች አሉ፡፡ የጅማን ታሪክ የሚያነሱ አሉ:: ጅማ ከኢትዮጵያ ሶስተኛ ከተማ ሆኖ ሳለ ምንም አለመለወጧን እያነሱ ያልረኩ ሰዎች አመለካከት የጐላበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን እውነታው፤ እኛ ስንመጣ፣ ወደ ጥሩ አቅጣጫ እየሄደች የነበረችበት ወቅት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ታሪክ የሚያነሱ ነበሩ፡፡ “ነበረች… ነበረች” ማለት የሚያዘወትሩት ስለሚጐሉ፣ ከተማዋን ለመለወጥና ለማልማት ተነሳሽነት ያለው ወጣት ላይ ጫና ይፈጥራሉ፡፡ ወጣቱ ታሪክ ተናጋሪ የሆነበት አዝማሚያ ነበር፡፡ ይህን የመቀየር ሥራ ላይ ነው የገባነው፡፡ እውነት ጅማ እንደ ትላንቱ ናት? አልተቀየረችም? ትላንት ትንሽ ኤርፖርት ነበራት፣ አሁን ትልቅ ኤርፖርት ነው ያላት፡፡ ጅማ ትላንት አንድ የግብርና ምርምርና አንድ የመምህራን ኮሌጅ ነበር ያላት፤ አሁን 40ሺህ ተማሪ የመቀበል አቅም ያለው ትልቅ ዩኒቨርስቲ ነው ያላት፡፡ ጅማ ትላንት አንድ ሁለት ፋብሪካ ነበራት፤ ዛሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነባበት ከተማ ሆናለች… ይህንን ለማህበረሰቡ እያሳወቅን፣ ህዝቡ ተነሳሽነት እንዲኖረው፣ ወጣቱ ራሱ ታሪክ ሰሪ እንዲሆን አጥብቀን እየሰራን ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ተጠናቆ ቢመረቅም እስካሁን ሥራ  ያልጀመረው ለምንድድን ነው?
እርግጥ ከተመረቀ ገና 6 ወሩ ነው፡፡ ግን ይህንንም ያህል ለመዘግየቱ ጅማ ከአዲስ አበባ ያላት ርቀት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ባለሀብት ደግሞ ውጤታማ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ለውጤቱ ትንሽ ርቀቱ የተወሰነ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም::  የአዳማንና የጅማን ማወዳደር አይቻልም፡፡  ሆኖም አሁን ባለሀብቶች እየመጡ ነው፡፡ ጅማ ላይ አስተማማኝ ሰላም አለ:: እዚህ መጥቶ፣ ሰርቶ ሀብት ያላፈራ የለም፡፡ አሁን አዲስ አበባ ከሚገኙ ባለሀብቶች መካከል ብዙዎቹ ጅማ  ላይ የሰሩ ናቸው፡፡ ተመልሰው እዚሁ ጅማ ኢንቨስት የማድረግ ሃሳብ ያላቸውም አሉ፡፡ ይህንን ደግሞ እናበረታታለን፡፡
በጅማ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ላልሆኑ የሌላ ክልል ተወላጆች በተለይም ለወጣቱ የስራ እድልን በተመለከተ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
የሚገርምሽ ነገር ከስራ እድል ጋር በተያያዘ ሁለት አይነት አመለካከቶች አሉ:: እኛ ሥራ ለመስጠት ወይም ስራ ለመፍጠር ቋንቋ አንጠይቅም፡፡ እንደውም አልፎ አልፎ የምንወቀስበት ጉዳይ “ለተወላጆቹ ሥራ ለመስጠት ችግሮች አሉ” እየተባልን ነው፡፡ እኛ እንግዲህ ለቢዝነስ ንቃተ ህሊና እንጂ የቋንቋ ልዩነት ያስፈልጋል ብለን አናምንም፡፡ ሁለተኛ ልምድም ይጠይቃል፡፡ ተፎካካሪ መሆን ያስፈልጋል እንጂ ቋንቋ እኛ ጋ አናምንበትም:: እንዳልኩሽ፤ በአዲሱ አመት ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ስራ ሲጀምሩ 13ሺህ ወጣቶች ሥራ ለማስያዝ እቅድ ተይዟል፡፡ አሁን እየተነጋገርን ባለንበት እንኳን ከ12ሺህ 600 በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ አግኝተዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ከእቅዳችን 96 ከመቶ በላይ አሳክተናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጅማ በብሔር አጥር የምትታወቅ ከተማ አይደለችምና… ከተማዬ ቤቴ ብሎ ለሚኖርባትና ለሚሰራባት እድሉ ሲገኝ ስራ እንሰጣለን እንጂ ቋንቋን አንጠይቅም፡፡
አልፎ አልፎ ሃሜቶች ሊመጡ ይችላሉ:: ሀሜቱ ከባለሀብቶችም ይመጣል፡፡ ቅጥ ያጣ ህገ ወጥነት ውስጥ ሲገቡና ተከታትለን እርምጃ ስንወስድ፣ “እኔ እንዲህ ስለሆንኩ ነው፤ ከዚህ አካባቢ ስለመጣሁ ነው ምናምን..” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ህገ ወጥነትን ማንም ይስራው ማን… አንታገስም፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ሰው ጅማ ላይ ሰርቶ ጥሪት ያፈራው ወይም ባለሆቴል የሆነው በብሔር አይደለም፡፡ ይሄ ይሄ እሴት ስላለን እኮ ነው ጅማ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት ከተማ ናት የምንለው፡፡ በብሔር ሥራ ከሰጠንማ፣ ለምን የፍቅር ከተማ የአብሮነት እሴት መገለጫ እያልን ለመናገር እንደፍራለን፡፡
ትልቁ የቱሪስት መዳረሻ አባጅፋር ቤተ-መንግሥት የዛሬ አመት ጅማ ስመጣ አደጋ ተጋርጦበት ከጉብኝት ተከልክሎ ነበር፡፡ በወቅቱ የበጀትና ታሪኩን ጠብቆ የሚያድስ የባለሙያ እጥረት አጋጥሞት እንደነበር ሰምቻለሁ:: አሁንም እድሳቱ አልተጀመረም፡፡ ችግሩ አልተፈታም ማለት ነው?
ትክክል ነሽ! ጅማ አባጅፋር የዛሬ አመት ችግር ላይ ነበር፡፡ አሁንም ችግሩ ተቀርፎ አላለቀም:: ከአሜሪካ ኤምባሲ “ኢንተርናሽናል ሞኑመንት ፈንድ” የሚባል ድርጅት፣ ከፌደራልና ከክልል ባህልና ቱሪዝም ጋር በመሆን ቤተ-መንግስቱ እንዲታደስ ስምምነት አድርገን፤ ባለሙያዎቹም መጥተው የዲዛይንና መሰል ስራዎች አልቀዋል፡፡ ነገር ግን በመሃል ከአሜሪካ የሚለቀቁ የገንዘብ ድጋፎች ዘግይተውብን ነበር፤ አሁን ተለቋል:: በቅርብ ጊዜ ወደ ስራ ይገባል ማለት ነው፡፡ እስካሁን የዲዛይን ስራ የእንጨት መለየት መሰል ስራዎች ተጠናቀዋል:: በነገራችን ላይ ባለሙያዎቹ የማማከር ሥራ እንጂ ቀሪው ስራ በአገራችን ባለሙያዎች ነው የሚሰራው:: ምክንያቱም አባጅፋር ቤተ - መንግስትን የዛሬ 152 ዓመት የሰሩት ከአሜሪካ መጥተው አይደለም:: የዚሁ አካባቢ ህዝብ ነው የሰራው:: የውጭዎቹ የቀድሞው እንጨት ምን አይነት ነው? ከየት ነው የመጣው? አካባቢውን ይለያሉ፤ ናሙና ወስደው ይሰራሉ፤ በዚህ መልኩ ነው ድጋፍ የሚያደርጉት ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው እድሳቱ ዘግይቷል፤ እኛም ከፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ጋር በጥልቀት የተነጋገርነው ፈጥኖ እድሳቱ ካልተጀመረ ሌላ ችግር ያጋጥመዋል በሚለው ላይ ስለሆነ፣ አሁን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ከአሜሪካ ኤምባሲም ባለሙያዎች መጥተው በፍጥነት ዕድሳቱ ሊጀመር ነው፡፡
ለዕድሳቱ ምን ያህል በጀት ነው የተመደበው?
የበጀቱ ጉዳይ ገና በሂደት ላይ ነው፡፡ አሜሪካ ኤምባሲ የሚያግዘን ግን 12 ሚ. ብር አካባቢ ነው:: ዋናው የምንፈልገው የሙያ ድጋፉን ነው እንጂ ቀሪው በጀት በፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሚሸፈን ይሆናል፡፡
አሁን ላይ የጅማ ከተማ ዋነኛ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
በከተማ ደረጃ ያለን ፈተና አንደኛው ስትራክቸራል (መዋቅራዊ) ፈተና ነው፡፡ ለምሳሌ የመዋቅራዊ ችግር ስንል ከተማዋ በስሌት ከ252 ሺህ በላይ ህዝብ እንዳላት ነው የሚታወቀው:: እውነታው ግን በከተማዋ ከ362ሺህ በላይ ህዝብ አለ፡፡ ይሄ ማለት ወደ ከተማ የሚገባውና የሚወለደው ሰው ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ የሚተዳደረው በ17 ቀበሌ ተከፍሎ ነው፡፡ ይሄ ማለት በአንድ ቀበሌ በርካታ ህዝብ አለ ማለት ነው፡፡
በአንዱ ቀበሌ ምን ያህል ሰው ይኖራል?
ለምሳሌ በቾ ቦሬ ቀበሌን ልንገርሽ፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ 70ሺህ ሰው አለ፡፡ ስለዚህ ጅማ በክፍለ ከተማ ደረጃ መዋቅር ተሰርቶ ካልመራናት፣ አሁን ባለው መዋቅር የህዝብን እርካታ ማሟላት አንችልም:: በአንድ ማዘጋጃ አገልግሎት ይህንን ሁሉ ህዝብ በብቃትና በጥራት ማገልገል አይቻልም፤ ስለዚህ ጥናት አድርገን፣ በአራት ክ/ከተማ ለመክፈልና እነዚህ 70ሺህ የያዙ ቀበሌዎችን ወደ ሶስት ከፍለን ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት አቅደናል:: ከ30ሺህ በታች ህዝብ ያለው ቀበሌ የለም፡፡ ስለዚህ የህዝብን የአገልግሎት እርካታ ለማሟላት የመዋቅር ችግር ዋነኛው ነው:: ሁለተኛው ፈተና የስራ አጥነትና የስራ ባህል አለመዳበር ነው፡፡ ወጣቱ በተለይ ከሱስ ተላቆ፣ ሰርቼ አድጋለሁ የሚለውን አስተሳሰብ በውስጡ እንዲያሰርጽ ሰፊ ስራ ይፈልጋል፡፡
እስካሁን ባለን ጥናት፤ በከተማችን ከ30 ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣት አለን፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘንድሮ ስራ ለመስጠት በዕቅድ የያዝነው 13ሺህ ያህሉን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ወጣት ሥራ ያጣው ስራ ጠፍቶ አይደለም:: የስራ ባህሉ ደካማ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ እኛ እንደ መንግስት፣ የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም፣ ወጣቱ የስራ ባህሉን እንዲያጠናክር፣ ከሊስትሮነት ጀምሮ ያሉ ሥራዎችን ሳይንቅ እንዲሰራና እንዲለወጥ ማንቃት ይኖርብናል፡፡ አካባቢው የገበያ እህል የሚመረትበት ነው፡፡ ከተማው ብዙ ሰው ገብቶ የሚወጣበት ነው፡፡ በፓርኪንግ ስራ እንኳን ከ3ሺህ በላይ ወጣት ማሰማራት እንደሚቻል በጥናታችን ለይተናል፡፡  ችግሮችን ለይተን ሁኔታዎችን በጥሩ መልኩ ለመቀየር በስራ ላይ ነን፡፡
ለአንድ ከተማ ልማት ሁለት አይነት እንቅፋቶች እንዳሉ በስፋት ይጠቀሳል፡፡ አንዱ የመሬት አቅርቦት ነው፡፡ ሁለተኛው የቢሮክራሲ ችግር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እናንተ እንዴት ናችሁ?
ኢንቨስትመንት በአጠቃላይ ጅማ ላይ እየጨመረ ነው፡፡ ነገር ግን በዘርፉ ሁለት አይነት ችግር ነው ያለው፡፡ አንደኛው፤ ባለሀብቱ እሰራለሁ ብሎ መሬት ይወስድና ወደ ስራ ሳይገባ መሬቱን ለ10 እና 15 ዓመታት አጥሮ ይዞ ይቀመጣል፡፡ እስካሁን እንዲህ ካደረጉ ባለሀብቶች ላይ 337 ሺህ ካሬ ሜትር ነጥቀን ወደ መሬት ባንክ አስገብተናል - በዚህ አመት ብቻ ማለት ነው፡፡
በእኛ በኩል ደግሞ መሰረተ ልማት አሟልተን፣ መሬት አዘጋጅተን፣ ባለሀብቶች የሚፈልጉትን ሁሉ አደራጅተን በማቅረቡ ላይ ችግሮች ነበሩብን፡፡ በሱም ላይ እየተሰራ ነው፡፡ ጅማ የጥንት ከተማ እንደመሆኗ እያረጀች ነው፡፡ ስለዚህ የመልሶ ማልማት ሥራ ይጠብቀናል ማለት ነው፡፡ አሁን  ብዙ ህንፃዎችና ሆቴሎች እየተሰሩ ቢሆንም፣ ፍጥነቱ ደካማ በመሆኑ ይህን የማቀላጠፍና ከተማዋን የማዘመን ሥራም ትልቁ የቤት ሥራችን ነው:: በአሁኑ አመት ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ:: መልሶ የማልማቱ ሥራ ግን ትልቅ የቤት ሥራችን ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ ያለ ኢንቨስትመንት ከተማ አይለማም፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ኢንቨስትመንቱ እየተስፋፋ ነው፡፡ ጅማ በአጠቃላይ አሁን ካሉት ከተሞች ትልቅ እድል ያላት ናት፡፡
ብዙ እንቅስቃሴ እየተደረገባት ነው:: በአጠቃላይ እኔ በኃላፊነት እያለሁ መቶ በመቶ ዳር ለማድረስ ባልችል እንኳን ብዙ ልማቶችን መስመር አስይዤ መውረድ እፈልጋለሁ፡፡

Read 8349 times