Print this page
Monday, 29 July 2019 00:00

የአድማስ ትውስታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከአዘጋጁ፡-

        ጋዜጣችን አዲስ አድማስ የተመሰረተችበትን 20ኛ ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ታከብራለች:: የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ ቅዳሜ
ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር ለአንባብያን የደረሰው፡፡ ወደ 20ኛው ዓመት በዓላችን በሚያዳርሱን ጥቂት ወራት “የአድማስ ትውስታ” በሚል በሰየምነው በዚህ አዲስ ዓምድ፤ ከቀድሞ ዕትሞች እየመረጥን ጊዜውንና ጋዜጣችንን እናስታውሳችኋለን፡፡

                    የዲሞክራሲ እጥረት ወይስ ጥሰት? (ለዜጐቻችን ህይወት ቅድምያ እንስጥ!)
                            አልአዛር ኬ

          በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳዮች የተነሳ ብጥብጥ ተከስቶ የሰዎች ህይወት ሊጠፋ ስለብጥብጡ መንስኤና ስለ ሰዎቹ ህይወት መጥፋት ሳይሆን ህይወታቸው ስለጠፋው ሰዎች ቁጥር በፓርላማዋ ክርክር የምትገጥም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር በአለም ለመኖርዋ እጠራጠራለሁ፡፡ ይህ አባዜአችን መቼ እንደሚለቀን አይታወቅም፡፡
ያለፈውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ በገጠመን የፖለቲካ ቀውስ በርካታ ዜጐች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ መንግስት የሞቱት ዜጐች ቁጥር በአስሮች የሚቆጠር ነው ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ የለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው በሚል በፓርላማ ክርክር ተደርጐበት ነበር፡፡ በኋላ ላይ አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ የራሱን ማጣራት አድርጐ ሟቾቹ 193 ሲቪሎችና 6 ፖሊሶች ናቸው ብሎ ሪፖርቱን ሲያቀርብ መንግስት በፊት የገለፀው ቁጥር በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ባለመደገሙ ቅር ሲለው ተቃዋሚዎች ደግሞ እኛ ያልነው ቁጥር ልክ ቢሆንም ባይሆንም መንግስት የጠቀሰው ቁጥር ብቻ እንኳን ልክ አልሆነም በሚል የትክክለኝነት ስሜት ተሞልተው አይተናቸዋል፡፡ የሰው ህይወት ክብር በሌለበት፣ የዜጐች ደህንነት ሁለተኛ አጀንዳቸው በሆነበት ሀገር እንዲህ አይነቱ ክርክር በፓርላማ መካሄዱ ብዙም አያስገርምም፡፡
ነገር ግን በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት በፖለቲካ ጉዳይ የተነሳ ዜጐች የማይሞቱበትና አካላቸውን የማያጐድሉበት ስርአት እንዴት አድርገን እንገንባ በሚል አንድም አይነት ውይይት ለማድረግ አለመፈለግ ግን የሀገራችን ትልቁ እርግማን ነው፡፡
የሞቱብንን የቀብርን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሞቱብንም የምናውቅ እኛ፤ የቆሰሉብንን ያስታመምንና በምንና እንዴት ሆነው እንደቆሰሉብንም የምናውቀው እኛ፤ የቆሰሉብንን ያስታመምንና በምንና እንዴት ሆነው እንደቆሰሉብንም የምናውቀው እኛው ሆነን፤ አንድ ኮሚቴ አጣራሁ ብሎ ብሎ ቢነግረን የምንመዝነው እቤታችን ጓዳ ካለው እውነተኛ የራሳችን ሪፖርት ጋር ነው፡፡
ባለፈው በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው የፓርላማ ውይይት ግርምቱ ሳይጠፋብን አሁን በቅርቡ በዚሁ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በፓርላማ የተካሄደው ውይይት ሌላ አስገራሚ ነገሮች ነበሩት፡፡
በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ የፓርላማው የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፣ በሁከቱ ወቅት የተከሰተው የሰብአዊ መብት አያያዝ እጥረት ላይ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፣ በቀጣይም ትምህርት ተወስዶበት ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው:: የደረገው ውይይት ግን ከላይ የተጠቀሰው ሃሳብ በተግባር እንደማይውል ያረጋገጠ፤ በፖለቲካ አያያዛችን ወደፊት በተአምርም ቢሆን መራመድ እንደማንችል ያሳየ ነበር፡፡
በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የተደነገገው የዲሞክራሲ እጥረት፣ የዲሞክራሲ ጥሰት በሚለው ቃል ይተካልን በሚል በተቃዋሚዎች የቀረበው ሃሳብ ውሳኔው መንግስትን አጥፊ ነው ብሎ ስላልጠቀሰ የዲሞክራሲ ጥሰት ተፈጽሟል ቢባል በዘወርዋሬ መንግስትን ያመለክታል ከሚል ሃሳብ የመነጨ ይመስለኛል:: የዲሞክራሲ ጥሰት ሆነ እጥረት ተከስቷል ተብሎ በፈለገው አይነት አገላለጽ ቢፃፍ የሞቱትና የቆሰሉት ወገኖቻችን በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደሞቱና እንደቆሰሉ እኛው ዋነኛ ባለቤቶቹ ጠንቅቀን ስለምናውቅ የቃላት አተካራው ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡
ነገር ግን ከኢህአዴግ ወገን የቀረበው ሙግት ከምንሠራው ስህተት መቸም ቢሆን ትምህርት ለመቅሰም ዝግጁነት እንደሌለን የሚያሳይ ነው:: አንድ የኢህአዴግ ተወካይ የተከበሩ የፓርላማ አባል፤ ነገሩን ያስረዱት፡፡ “እጥረት በባህሪው ጉድለት እንዳለ ያሳያል፤ የተሟላ ነገር የለም የሚል ነው፡፡ ጥሰት የሚለው ቃል ተመጣጣኝ አይደለም፤ ገደብ አልፏል በሚል ይቀመጥልኝ ተብሎ በሌላ መልኩ የቀረበ ስለሆነ እጥረት በሚለው ይቀመጥ እንላለን” በሚል ነው፡፡ እኒህ ተወካይ ያው የድርጅታቸው ነገር ሆኖባቸው የተናገሩት እንጂ የህዝቡን ስሜት ለመረዳት ሞክረው አሊያም በቀናነት ገምተውት ቢሆን ኖሮ ከዚህ የተሻለ ነገር ሊያቀርቡ ወይም ያቀረቡትን ከማቅረብ ይቆጠቡ ነበር ብዬ አስባለሁ:: መንግስት የዲሞክራሲ እጥረት አለብኝ ማለቱ እኔ የምፈልገውን ያህል ዲሞክራሲን አላሰፈንኩም እንጂ የቻልኩትን እየሰራሁ ነው፤ ለማለት እንደሆነ ይሁንለት እንበል፡፡ ነገር ግን 193 ዜጐች ህይወታቸውን ያጡት በምን ዓይነት ችግር እንደሆነ እኛ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ዲሞክራሲ ያጥራቸዋል ሳይሆን በግልጽ ይጥሳሉ እየተባሉ በየጊዜው የሚወገዙት ሀገሮች በፖለቲካዊ ብጥብጥ 193 ዜጐቻቸው የማይሞቱባቸው እነሱ ከመላእክት ጋር እየሰሩ ይሆን?
በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት አያያዛቸው ለዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ደፍሮ የሚከራከርላቸው ሰው መቼም ብዙ እንደማይገኝ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ በመቶ የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎቻቸውን የማይገድሉት ስለ ሰማይ ቤቱ ህይወታቸው ስለሚያስቡ ይሆን? ግብፅ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኡጋንዳ ወዘተ…መሪዎቻቸው በስልጣናቸውን በተቃውሞ ቀልድ አያውቁም፡፡ ግን በመቶ የሚቆጠሩ ዜጐቻቸውን ሲፈጁ አይታዩም፡፡ ሞትና ፍጅት እኛ ሀገር ቀልድ የሆነበት ምክንያት ግን በእጅጉ ያስገርማል፡፡
መንግስት በጊዜው የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በወሰደው እርምጀ የ193 ዜጐች እልቂት ተከስቷል፡፡ ይህ እርምጃ ገደብ ያለፈ እርምጃ ነው:: ተብሎ በመንግስት በኩል እንዲታመን መሞትና መቁሰል የነበረባቸው ዜጐች ስንት ሺ መሙላት ነበረበት፡፡ ነገሩ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ያ ሁኔታ መንግስት እንደተመኘውና እንዳደረገው ተመጣጣኝ ነው ተብሎ መወሰኑ ለኢህአዴግ የልቡን አድርሶለት ይሆናል፡፡ የህዝቡን ስሜትና ልብ ግን ከቶም አያሽርለትም፡፡
የእውነተኛው ሪፖርት ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለቀባሪው አረዱት እንደተባለው ተመጣጣኝ ነው አይደለም፤ አጥሯል የለም ተጥሷል በሚል ለማሳመን እንዲያው ደከመ እንጂ ዋነኛው ትኩረቱ ሊሆን የሚገባው ከዚህ ስህተት ምን ተምሬአለሁ፤ ወደ ፊትስ እንዴት መራመድ አለብኝ የሚሉትን ጉዳዮች ነበር፡፡
ኢህአዴግ የዲሞክራሲ ጥሰት አልፈፀምኩም፤ የዲሞክራሲ እጥረት እንጂ በማለት በተወካዮቹ አማካሯነት መከራከሩ “ሞኝ በሞኝነት ሃሳቡ ለራሱ ይራቀቃል” የሚለውን የአይሁዶች አባባል ያስታውሳል፡፡
ጥሰት ፈጽመሀል አለመባል ከተጠያቂነት ነፃ ያደርገው ከመሰለው ላመነበት የዲሞክራሲ እጥረትና ዲሞክራሲ ላጠረበት ህዝብ የሚከሰው በምንድን ነው? ለዚህስ አልጠየቅም ሊል ይሆን? ለበርካታ አመታት ዲሞክራሲን ካላሰፈንን ወይም የዲሞክራሲ ግንባታችንን ካላሟላን እንደሀገር የመቀጠላችን ጉዳይ አጠያያቂ ነው፤ ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳያችን ነው ብሎ ኢህአዴግ አስረግጦ ሲያስረዳን ኖሮአል፡፡ ታዲያ አሁን የዲሞክራሲ እጥረት ተከስቶብኛል ማለቱ በራሱ ማስጠንቀቂያ መሠረት የሀገሪቱን ህልውና ወደየት እየወሰደ ነው?
የኢህአዴግ አጋር ድርጅት አባል የሆኑ አንድ የተከበሩ የፓርላማ አባል፤ “መቻቻል፣ ዲሞክራሲን ማስፋትና ካለፈው ስህተት መማር ይጠቅማል”  ብለዋል፡፡
እኒህ የተከበሩ ሰው ስለ ኢህአዴግና ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን ግልጽ አቋም በደንብ ስለምናውቅ እንዲህ ያለ ሃሳብ መሰንዘራቸው አሪፍ ነገር ነው፡፡
በእርግጥም መቻቻልና ዲሞክራሲን ማስፋት፣ ካለፈ ስህተትም መማር ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ነገር ነው፡፡
እነዚህን ቅዱስ ሀሳቦች በተግባር ለመተርጐም ደግሞ አጥፊ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ቢጠይቅ፣ የበደለውን ቢክስ ከባላንጣው ጋር እርቅ ቢያደርግ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ቢያደርግ በእነዚህ አይነት አሰራሮች ዘመን ባጠገበችው ሀገራችን ይበልጥ ያተርፋል፡፡
ይህን ሃሳብ ኢህአዴግ በአባሉና በተወካዩ የተከበሩ የፓርላማ አባል በኩል የመለሰው “አገርን ከባለ ብጥብጥና አደጋ ለመታደግ ስለሆነ የተወሰነው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ብሎ ባስቀመጠበት ሁኔታ፤ አጥፍታችኋልና ይቅርታ ጠይቁ፤ ጐድታችሁአልና ካሳ ክፈሉ የሚል ነገር ማስቀመጥ ተገቢነት ያለው አይመስለኝም” በሚል ነው፡፡ እኒህ ሰው እንደ ኢህአዴግ አባልነታቸው ሳይሆን እንዲያው በሰውነታቸው ብቻ አስበው መልስ የሚሰጡ ቢሆን የ193 ሲቪል ዜጐችን መገደል ምን ይሉት ይሆን?
እንደ ኢህአዴግ የእርቅ፤ የይቅርታና የካሳን ጉዳይ ፈጽሞ ሊቀበል የማይችልባቸው ሁለት መሠረታዊ ባህሪዎች እንዳሉት ይሰማኛል፡፡ አንደኛው፡- እንዲህ ማድረግ ለጠላቶች መንበርከክና መሸነፍ ነው ብሎ ከህዝብ አንፃር ሳይሆን ከፓርቲ አንፃር ብቻ ከማየት ባህሪው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ጠላቶች ብቻ እንጂ እኔ ስህተት ፈፃሚና አጥፊ አይደለሁም፤ ከሚለው አስተሳሰቡ ነው፡፡ ድሮ ንጉሱ እኔ ከዙፋኔ ከወረድኩ ኢትዮጵያ ያልቅላታል ይሉ ነበር እንደሚባለው፤ እኔ ካልመራሁዋት ይህቺ አገር የምጽአት ቀኗ ነገ ይሆናል ብሎ ከሚያስብ ድርጅት፤ እንዲህ ያለ አቋም መንፀባረቁ ብዙም አስገራሚ ነገር አይደም፡1 እንደ ሀገር መሪ ድርጅት ኢህአዴግ፤ ለኛም ለራሱም ሲል ከስህተት መማሩን ሊያሳየንና ከህዝብ ጋር እልህ መጋባቱን ማቆም ይገባዋል፡፡ አስራሁለተኛው ሰአት ሲመጣና ጊዜ ሲመሽ የሁሉም ማረፊያ ያው ህዝቡ ነው፡፡ ያኔ እንዲህ ያልኩት እንዲህ ያደረኩት ተገድጄ ነው፤ ተሳስቼ ነው ብዙም አያዋጣም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የኢህአዴግ ስህተትና የኢህአዴግ ድክመት በምንም ነገር ቢሆን እነሱን የተሻሉና እንከን አልባ እንደማያደርጋቸው ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡ ለሁሉም ችግሮች ኢህአዴግን ብቻ መርገም ኢህአዴግን ብቻ ማውገዝ ለህዝብ ጥቅም አያመጣም፡፡
ህዝብና ታሪክ ሁሉን እንደ የእጅ ስራው ብቻ ነው የሚመዝነው፡፡ የመንግስት ስልጣን አለመጨበጥ ከጥፋት ነፃ አያደርግም፡፡ በድጋፍ አብሮ ተሰልፎ ህይወቱን ለሰጠ ህዝብ፤ ካሳው ህብረት፣ አንድነትና የተሻለ ስራን እንጂ ለግል ስልጣን ያለ እረፍትና እፍረት መሿኮት ከቶም መሆን የለበትም፡፡
ለማጠቃለል በሀገራችን ፓርላማ፣ ዜጐች በፖለቲካ የተነሳ የማይሞቱበትና የማይቆስሉበት ስርአት እንዴት በህብረት እንገንባ በሚል ጉዳይ ላይ ውይይት ሲደረግ ማየት እናፍቃለሁ፡፡ ለትንሽ ለትልቁ ጉዳይ ይዋጣልን እያልን ጦርና ዘገር ሰባቂ ጀግኖች ሆነን ያተረፍነው ነገር ቢኖር የዜጐች ህልፈትን ብቻ ነው፡፡ አምላክ ይርዳን!!   

Read 6222 times
Administrator

Latest from Administrator