Saturday, 27 July 2019 13:47

የኢሕአዴግ ሕመም ወዴት ያደርሰን ይሆን?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

መሪር እውነታ
ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ሞቷል፤ የሚሉ ልሂቃን ቁጥራቸው ዕለት ተዕለት እያሻቀበ ነው፡፡ በርግጥም ፓርቲው እየተፍረከረከ ለመሄዱ ዋቢ የሚሆኑን እውነታዎችን መታዘብ  ከጀመርን ሰንበተናል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ተቃናቃኞቹን ከፖለቲካው ምህዳር የሚጠራርግበት ድርጅታዊ ባህሉ ዳዋ በልቶታል፡፡ በተለይ በዴሞክራሲ ማእከልነት ስም የሚዘወረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ፤ አዲሱ የለውጥ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የውሃ ሽታ ሆኗል፡፡ ከአባል ድርጅቶች መካከል የአውራነት ሚናን የተጎናጸፈው ሕወሓት፤ወደ ዳር ተገፍቶ፣ በምትኩ አዴፓ እና ኦዴፓ፣ የፊታውራሪ መንበሩኑን መቆናጠጣቸው ይታወቃል፡፡
ታዋቂው የምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ተንታኝ ፈረንሳዊው ሬኔ ሊፍሮህ፤ ያለ ሕወሓት ልእልና ሀገር ማስተዳደር የጀመረው ኢሕአዴግ፣ ከፊት ለፊቱ የቆመው የፈተና አቀበት፣ በዋዛ የሚዘለቅ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡
 “ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ፣ ዐቢይ እንደ መሪ እየገጠማቸው ያለው አጣብቂኝ በቀላሉ መልስ የሚያገኝ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ሰፊ ተቀባይነት የሙጥኝ ብለው በለውጡ ባቡር ውስጥ የያዙትን የመሪነት ሚና ያስቀጥላሉ ወይስ እንደተለመደው የጸጥታውን ክፍልና ወደ ሥልጣን ያመጧቸውን ወጣት ተቃዋሚዎችን ደጀን አድርገው፣ በተሰነካከለው የለውጥ ሐዲድ ላይ መንጎድን ይመርጣሉ?“ በማለት የሙግት ሐሳቡን፣ በኦፕን ዴሞክራሲ ድረገጽ ላይ አስፍሯል፡፡
በርግጥም ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት መሞት መጀመሩ፣ ለሀገራችን ፖለቲካ መርገምት ነው ወይስ በረከት? በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት ሃሳቦችን ላንሸራሽር::
የኢሕአዴግ ምርኩዞች
ሕወሓት/ኢሕአዴግ ራሱን ያጠናበት ቀኖናዊ ምርኩዞች ነበሩት፡፡ እነዚህ ምርኩዞች፤ ድርጅቱ ከውስጥና ከውጪ በየጊዜው የሚገጥሙትን ፈተናዎች ለመመከት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ በተለይ በአስኳል መርሁ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አማካኝነት፣ አንድን ማኅበረሰብ ጠላትና ወዳጅ ብሎ በመፈረጅ፣ ተራማጅ ሐሳብ ያላቸውን ልሂቃን ወይም ቡድኖች ሲያሸብር ኖሯል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ የልማታዊ መንግሥት ጭምብልን በማጥለቅ፣ ተጻራሪ ተብለው የተፈረጁትን ኃይሎች አደብ በማስገዛት ረገድ ለጊዜውም ቢሆን ስኬታማ ሆኖ  ነበር፡፡ በተለይ በምርጫ 97 ማግሥት፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢኮኖሚ ክንፍ የሆነውን የልማታዊ መንግሥት እሳቤን በላዩ ላይ በመደረት፣ ተፍረክርኮ የነበረውን አቋሙን ዳግም ለማጠናከር ችሏል፡፡ በብዕራቸው ሕወሓትን የሞገቱትን ጋዜጠኞች፣የሰብኣዊ መብት ተቆርቋሪዎችን እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን በልማት እንቅፋት ስም፣ ያለ አበሳቸው ከወህኒ ቤት ሲወረውሩ ከርመዋል፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ማእክልነት ቀኖና ያፈነገጡ ተሟጋች ፖለቲከኞችን በሂስና ግለ-ሂስ ስም “ኪራይ ሰብሳቢ”፣”ጸረ ልማት”፣”ትምህከተኛ”፣”ጠባብ” የሚሉ ታፔላዎችን በመለጠፍ፣ የአስተሳሰብ ነጻነትን ሲያፍን እንደነበረ የአደባባይ እውነታ ነው፡፡ ሰማኽኝ ጋሹ፣ የኢሕአዴግ ምርኮዝችን፣ በ“the last post cold war federation” በሚለው የፒኤች.ዲ መመረቂያ ጽሑፍ ላይ ግሩም በሆነ ሁኔታ አስፍሮታል፡-
The bedrock principle that TPLF/EPRDF implemented to maintain political hegemony in controlling the federal system is the principle of revolutionary democracy. The other most important ideological rhetoric regulating the political discourse in Ethiopia is the doctrine of a developmental state. The system of gimgemma is also one of the important mechanisms used by TPLF/EPRDF to control federal and regional state apparatus.
(“ሕወሓት/ኢሕአዴግ የፖለቲካ ልእልናውን ለማስጠበቅ ከሚጠቀምባቸው መሣሪዎች አንዱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ “ግምገማ”  አባላቱን ከድርጅቱ ቀኖና ማፈንገጥ አለማንፈገጣቸውን የሚቆጣጠርበት ዋንኛ ስልት ነው፡፡”)
ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ለመሞቱ ዋቢ የሚሆነው፤ አለቅጥ የተመካባቸው ምርኩዞቹ፣ ምስጥ እንደ በላው ዋርካ ተቦርቡረው የአፈር ቀለብ ለመሆን ማዘመማቸውን ስንመለከት ነው፡፡ የሬኔ ሊፍሮኽን ጽሑፍ በድጋሚ እማኝ ላድርግ፡-
“ኢሕአዴግ የሚለው መጠሪያ ስም በብዙዎች ኢትዮጵያዊያን ዘንድ አዎንታዊ ገጽታ የለውም፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ኦዲፒም ይጨምራል:: እንደውም አብዛኞች የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ ኦነግ እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ በቅንጅት ሆነው፣ ኦሮሚያ ክልል የፌዴራል መቀመጫን የማሸነፍ ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በተመለከተ ገዢው ደኢህዴን ያለው ተቀባይነት፣ ከክልሉ መከፋፈል ጋር አብሮ የሚያከትም ነው፡፡”
በርግጥም ሊፍሮህ እንዳለው፣ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ፣ በሁለት እግሩ ለመቆም እየተቸገረ ነው:: ኦዴፓ አናቱ እንጂ፣ በታችኛው ባለው የሥልጣን መዋቅር ላይ ያን ያህል የሚያስመካ ጥንካሬ የለውም:: እንደውም አንዳንድ ሂስ አቅራቢዎች፤ “ODP is a head with body” ይሉታል፡፡ አካል አልባ ጭንቅላት፣ እንደ ማለት ነው፡፡ በላይኛው የአመራር እርከን ላይ ያሉት ኃይሎች፣ ከለውጡ ጋር በአንድነት የተሰለፉ ቢሆኑም፤ በታችኛው የሥልጣን መዋቅር  ግን ይኽ አይነት ድጋፍ አይስተዋልም፡፡ ከለውጡ አመራር ጋር በአጋርነት ከመሰለፍ ይልቅ፤ ለተለያዩ ጽንፈኛ ኃይሎች ድጋፋቸውን መለገስ ይቀናቸዋል፡፡
የደኢህዴን ጉዳይም አሳሳቢ እንደሆነ በገሀድ እየተመለከትን ነው፡፡ ድርጅቱ በሐዋሳ ላይ በነጻነት ስብስባ እንኳን እንዳይቀመጥ “ኤጄቶ” በሚባለው ቡድን ሲታወክ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: ምናልባትም የክልል ጥያቄዎቹ መልስ ማግኘትን ተከትሎ፣ ሌሎች ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ከደኢህዴን በበለጠ ተሰሚነት እንደሚኖራቸው  ይጠበቃል፡፡
የአዴፓም ጉዳይ ገና በወጉ የጠራ አይደለም፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ በሰኔ 15ቱ የመንፈቅለ ክልል -መንግሥት ሙከራ ምክንያት ሰለባ መሆናቸውን ተከትሎ፣ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል፣ ፈር ለማስያዝ ደፋ ቀና በማለት ላይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከሕወሓት ጋር የገባው ይፋ የወጣ ውዝግብ፣ የኢሕአዴግን ፍጻሜ እንደሚፋጥነው እሙን ነው፡፡
የአዴፓ እና የሕወሓት ውዝግብ
ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ከመቃብር አፋፍ ላይ ቆሟል የሚሉ ወገኖች፤ የሰሞኑን የሕወሓት እና አዴፓን  ውዝግብ እንደ ተጨማሪ ማሳመኛ ነጥብ ይወስዳሉ፡፡ በርግጥም አዴፓ፣ ለሕወሓት መግለጫ የሰጠው የመልስ ምት፣ የአስክሬኑ ሳጥን የመጨረሻ ሚስማር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ሕወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ ያለውን የመረረ ጥላቻ፤ አዴፓ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስብል ደረጃ በመግለጫው እርቃኑን አውጦታል፡፡ ከዚህ በአደባባይ ከሚታይ  ቁርቋሶ በኋላ፣ ሕወሓት እና አዴፓ በኢሕአዴግ ጥላ ሥር ታቅፈው፣ በእህትማማች ድርጅትነት ይቀጥላሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ወትሮም ቢሆን፣ የሁለቱ ድርጅቶች መቃቃር እንዲህ እንዳሁኑ የከፋ ባይሆንም፣ አንዳንድ የቁርሾ ዳናዎች እየተስተዋሉ ነበር፡፡
ሕወሓት ልእልናውን ተነጥቆ ወደ ዳር ከተገፋበት ዕለት እንስቶ፣ የለውጡን አስተዳደር በማብጠልጠል ብሎም ከማእከላዊው መንግሥት ለሚወጡት ሕጎች ተገዢ ላለመሆን ሲያንገራግር እንደከረመ ይታወቃል፡፡ አዴፓ በአንጻሩ  የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ዋና ሞተር እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
ሕወሓቶች፤ አዴፓ ለሚለው መጠሪያ እውቅና መስጠት የፈለጉ አይመስሉም፡፡ የድርጅቱ ቱባ ሹማምንቶችም ሆኑ አክቲቪስቶች፤ ብአዴን በሚለው የድሮ ስም ነው ለመጥራት የሚመርጡት:: ምናልባትም ብአዴን፤ የድሮ ገዢነታቸውን ስለሚያስታወሳቸው ይሆናል፤ ከስያሜው ጋር የሙጥኝ ያሉት፡፡
ሕወሓት በ1983 ዓም በፖለቲካ ውሳኔ ከአማራ ክልል በግድ የወሰዳቸውን ግዛቶች በማስመለሱ ረገድ የአዴፓ አቋም በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ብሔርተኞች ጋር የተለየ አይደለም፡፡ በዚህም በአማራ ብሔርተኞች የሚቀነቀነውን አጀንዳ ጠቅልሎ በመወስድ፣ በክልሉ ያለውን ተቀባይነት በእጅጉ እያሳደገ መጥቷል፡፡
የአማራን ሕዝብ አንገት ለመስበር የተቋቋመው ብአዴን፣ በዝገመተ ለውጥ የሕዝብ አጋር ሆኖ ራሱን ከሕወሓት ተጽእኖ ነጻ ማውጣቱ፣ ለሀገራችን ፖለቲካ በረከት እንጂ መርገም አይደለም፡፡ አዴፓ እንደ ድርጅት መጠናከሩ፣ ከኦዴፓ ጋር ያለውን የኃይል ሚዛን (ፓውር ባላንስ) ጤናማ በማድረግ የሚጫወተው ሚና አሌ የሚባል አይደለም፡፡
ሕዳግ  
ሕወሓት፤ በኢሕአዴግ ስም ያነገሰው የሽብር አገዛዝ፣ የፖለቲካ ባህላችንን በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ በፖለቲካ ድርጅቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሀገሩንና ወገኑን የሚታደግ ሩቅ ሐሳብ ልሂቅ ደሀ አድርጎናል፡፡ ያሉትም ቢሆኑ በአድርባይነት ካባ ለገዢው መንግሥት የሚያሸረግዱ፣ በጠባብና ግላዊ ዓላማ ዙሪያ ተቀንብበው፣ ፀረ-ምሁራዊ በሆነ ሐዲድ ላይ የሚነጉዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሰዓት፣ በፖለቲካ ልሂቃን የታነጸና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው፤ በሁለት እግሩ የቆመ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት በምህዳሩ ላይ አለ ብሎ በድፍረት መናገር ያስቸግራል፡፡ እንደውም ብዙዎች ኢሕአዴግ በስም፣ በቅርጽና በይዘት ተቀይሮ ቢመጣ ይመርጣሉ፡፡  
በርግጥ በሕወሓት/ኢሕአዴግ በደል ያልደረሰበት የኅብረተሰብ ክፍልን ማግኘት ፈፅሞ የሚሞከር አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የድርጅቱ ግብአተ ቀብር መፈጸምን በጉጉት የሚጠብቅ ኃይል ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ትልቁ ነጥብ ግን፣ ኢሕአዴግ የተወውን የስልጣን ክፍተት ማን ይሞላው? የሚለው ነው፡፡ የጽንፈኛ ብሔርተኞች ተጽእኖ በሚያስበረግግ ደረጃ እየጎላ በሄደበት በዚህ ወቅት ሀገሪቷን ወደ ተረጋጋ መደላድል ላይ ማን ያስቀምጣት? በሚለው ነጥብ ዙሪያ ሀሳቦችን ማንሸራሸር አስፈላጊ ነው:: ስለዚህ ኢሕአዴግን ያገለለ የመፍትሄ ውሳኔ የምንወስድበት ቅንጦት ላይ አይደለንም፡፡ እንደውም የኢሕአዴግ ዝግመተ ለውጥ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል፣ የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ርብርብ ወሳኝ ነው፡፡
አዴፓ በተራማጁ ፖለቲከኛ ሙስጣፋ የሚመራውን ሶዴፓ እና ሌሎች መሰል ድርጅቶችን በማቀፍ አዲስ ሀገራዊ ፓርቲ ቢመሠርት፤ኦዴፓም በተመሳሳይ አጋሮችን በማሰበሳብ፣ ሌላ ሀገራዊ ፓርቲ ቢያቋቁም፤ ከዚያም ሁለቱ ትልልቅ ሀገራዊ ፓርቲዎች ጤናማ ፉክክር ውስጥ ቢገቡ የተሻለ ይሆናል፡፡ በኢሕአዴግ መቃብር ላይ የሚቀለሱት የለዘብተኛ የብሔር ፓርቲዎች፣ በጊዜ ሂደት  በዜግነት ፖለቲካ ላይ ምህዋሩን ወደተከለ፣ የፖለቲካ ድርጅት የሚቀይሩበትን ፍኖተ-ካርታ በመንደፍ፣ ሀገራችንን ከገባችበት ቅርቃር ያወጧት ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡


Read 1501 times