Print this page
Saturday, 27 July 2019 13:44

ከንግስት ሳባ ምድር!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(0 votes)


              ወተት የመሰለ ነጭ ልብስ የለበሱ ጥቋቁር  ህፃናት፣ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ትልቅ አዳራሽ መድረክ ላይ ቀርበዋል፡፡ ከመድረኩ ቁልቁል በትላልቅና ጥቋቁር አይኖቻቸው በፍርሃትና በኩራት ታዳሚውን ይቃኛሉ፡፡ ታዋቂው የሙዚቃ ቀማሪ ሻልሞ ግሮኒች ከፒያኖው ፊት ተሰይሟል፡፡ እነዚያ ደቃቃ ህፃናት እንደ ፏፏቴ በሚንፎለፎል ድምጽ መዝሙራቸውን ያወርዱታል፤
በጀርባዬ ምግቤን ተሸክሜ በምታባብል ጨረቃ ስር እጓዛለሁ
በስቃይና በሰቀቀንም እየተጓጓዝኩ እጠይቃለሁ
እንደ ህዋ የተነጠፈው በረሃ ለምን ይሆን ማለቂያም የሌለው!
እናም እናቴ ለታናናሾቼ እንዲህ ትላለች
‹… በርቱ፤ አሁንማ ደረስን በቃ
እግራችሁ አይዛል፣ ልባችሁ ይንቃ
ማርና ወተት የምታዘንበው ምድራችን ድንበር ለየ
የተስፋይቱ ምድር አድማስ ታየ
ደርሰናል ውጋጋኑ ታይቶናል፣ ኢየሩሳሌምን ለማግኘት ተቃርበናል! …›
ይህ ሃይም ኢዲሲ ያዘጋጀው የተጓዦቹ ማበረታቻ መዝሙር ነበር፡፡ የቤተ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚደረገውን ጉዞ ይገልፃል:: ምናልባት ታዳሚዎቹ በመዝሙሩ ውስጥ የተገለጸውን ሁናቴ አይረዱት ቢሆን እንኳ ህጻናቱ ግን ከማጨብጨብ ከቶም ዝም አላሉም፡፡
በቅርብ ጊዜያት ማንም እስራኤላዊ ያላየውን መከራ የተቀበሉ ናቸው፤ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤሎች፡፡ ታሪካቸውም እንደ ተረት ሊተረክ በቅቷል፡፡ አይሁዳውያን ቢሆኑም ቅሉ ከአፍሪካ ደረት መሃል፣ ከተራሮች አናት፣ በንግስት ሳባ አገር ከአለም ሁሉ ተገልለው የኖሩ ናቸው፡፡ ለሺህ አመታት ከእምነታቸውና ከአስተምህሮታቸው ጋር ተጣብቀው፣ የጸኑ ህዝቦች ናቸው፡፡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ከቶም ተስፋ ቆርጠው አያውቁም:: ከትውልድ ወደ ትውልድም ይህንኑ ህልም ለልጆቻቸው ሲያስተምሩ ኖረዋል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉስ በነበሩበት ወቅት የእስራኤል ወዳጅ ነበሩ፡፡ ሆኖም በዚያ ዘመን እንኳ ወደ እስራኤል የመጡ በጣም ጥቂት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ንጉሱም ከስደት ዘመናቸው ሁለቱን አመት በዚያ አሳልፈዋል፡፡ በአጋጣሚውም ፈላሻዎችን ወደ አገራቸው ይመለሱ ዘንድ በእስራኤላውያን መጠየቃቸው አልቀረም፤ ሆኖም ንጉሱ እንዲህ ሲሉ መልሰዋል ‹‹… በሃገሬ ከሰባ የበለጡ ብሔረሰቦችና የተለያዩ ሃይማኖቶች ይኖራሉ እናም ዛሬ ፈላሻዎች እንዲሔዱ ብፈቅድ፣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሶማሌዎች “ወደ ሶማሊያ እንሒድ” ቢሉ ምን እላለሁ! ለኤርትራውያንስ ምን እመልሳለሁ! እኔ የሁሉም አባት ነኝ፡፡ እናም ይህንን ትልቁን ቤተሰቤን መጠበቅ የኔ ስራ ነው፡፡…››
ከ1973 በኋላ፣ ልክ ታዋቂው ራቢ /መምህር/ ኦቫዲያ፤ ፈላሻዎች እስራኤላውያን መሆናቸውን በይፋ ከተናገሩ በኋላ ነገሮች ተቀየሩ፡፡ ከሁለት አመት በኋላ የእስራኤል መንግስት እነዚህ ዜጎቹን ለመሰብሰብ ወሰነ፡፡ በ1977 መናቸም ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የሞሳድ ዳይሬክተር የነበረውን ጀነራል ሃካ አስጠርተው ትዕዛዛቸውን ሰጡ፤ ‹‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎቻችንን ሁሉ አምጣልኝ!››
በሞሳድ ውስጥ አይሁዳውያንን በሌላ ሀገር ለመጠበቅ የተዋቀረ ክንፍ አላቸው፡፡ ቢትዙር ይሉታል፡፡ እናም ይህ ክንፍ ወዲያውኑ ወደ ስራ ገባ:: የሞሳዱ ሰው፣ ዳዊት ኪምሂ፣ ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ ተላከ፡፡ የሞሳድ ምክትል ማለት ነው፤ ዳዊት፡፡ በወቅቱ ከፕሬዝዳንት መንግስቱ ጋር ተገናኘ፡፡ አገሪቱ ጦርነት ውስጥ ነበረችና ሊቀመንበሩም የእስራኤልን እርዳታ መጠየቃቸው አልቀረም፡፡ እስራኤልም ቤተ እስራኤላውያንን መውሰድ ከተፈቀዳላት መሳሪያ ለመርዳት ተስማማች፡፡ እናም እያንዳንዱ የእስራኤል ሄርኩለስ አውሮፕላን ህዝቦቹን ሊጭን ሲመጣ፣ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያመጣና አይሁዳውያንን እንዲወስድ ተስማሙ፡፡ በዚሁ ስምምነት መሰረት ግን የተዘለቀው ለ6 ወራት ብቻ ነበር፡፡ በየካቲት 1978 በውጪ ጉዳይ ሚኒስተሩ ሞሼ ዳያን የምላስ ወለምታ ነገሮቹ ተቋረጡ፡፡ ዳያን ለስዊዙ ጋዜጣ፣ እስራኤል ለመንግስቱ መሳሪያ እያገዘች መሆኑን ተናገሩና አረፉት፡፡ (አንዳንዶች ሰውየው ስምምነቱ እንዳይቀጥል አውቀው ያደረጉት ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡) በወቅቱ ኢትዮጵያ ከሶቭየት ጋር ሃይለኛ ፍቅር ወድቃ ነበር፡፡ መንግስቱ በድርጊቱ እጅግ በጣም ተናደዋል፤ ቢሆንም በግልጽ ሆኔታዎቹን አምነው ባይናገሩም ሁሉም ነገር እንዲረቋጥ አደረጉ፡፡ በሞሳድ ቤት ግን ሁሉም ነገር እንደቀጠለ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ መምህሩና ወደ ሱዳን የተሻገረው ኢትዮጵያዊው ፈረደ፤ የጻፈው ደብዳቤ በሞሳድ ጠረጴዛ ላይ ደረሰ፡፡  በጥቂቱ እንዲህ ይላል ‹‹…ሱዳን ገብቻለሁ፡፡ እባካችሁ የአውሮፕላን ትኬት ላኩልኝ፡፡›› ሞሳድ ወደ ሱዳን ትኬት ሳይሆን ዳኒ ሎርን ላከና ፈረደን አገኘው፡፡ እንደተገናኙ ፈረደ ሌሎች ዜጎችን በየስደተኛ ጣቢያው እንዲያፈላልግ ስራ ተሰጠውና በወራት ውስጥ ሰላሳ ያህሉን ማግኘት ቻለ፡፡ ሞሳድ ሁሉንም ወደ እስራኤል በስደተኛ መልክ ወደ ተለያዩ አገሮች እየላከ፣ ቀጥሎ ወደ እስራኤል እንዲገቡ አደረገ፡፡ ፍለጋው ቢቀጥልና ፈረደም በካርቱምና በአካባቢው ቢንከራተትም ተጨማሪ  ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ በመጨረሻ ራሱ ወደ እስራኤል እንዲገባ ተነገረው፡፡ ፈረደ ግን አሁንም ፍለጋውን እንደሚቀጥል በመወሰን አልሔደም፡፡ እዚያ የነበሩ ሁሉም የሞሳድ ሰዎች ወደ አገራቸው ቢመለሱም እርሱ ግን ቀረ፡፡ እሱ ከሄደ ሌሎች ወንድሞቹ ከዚያ በኋላ ፈላጊ እንደማይኖራቸው ተገንዝቧል፡፡
በመቀጠል ለብቻው በየስደተኛ ጣቢያው ሰዎቹን ያገኛቸው እያስመሰለ፣ አገር ቤት የሚያውቃቸውን ስሞች ሁሉ እየጻፈ ለሞሳድ ሪፖርት መላክ ጀመረ፡፡ ወደ ኢትዮጵያም በመመለስ በየመንደሮቹ እየተዛወወረ ሰዎቹን ማሳመን ቀጠለ:: ወሬው እንደ ሰደድ በመዛመቱ እንደ አዲስ ስደቱ ተቀጣጠለ፡፡ ማርና ወተት ወደ ምታዘንበው የተስፋ አገራቸው ለመግባት ኢትዮጵያውያን ፈላሾች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚስጥር ወደ ሱዳን ፈለሱ፡፡ ጥቂት ስንቅ ሰንቀው፤ አደገኛውን በርሃ ተናነቁት፡፡ ለሊት ይጓጓሉ፣ ቀን ባገኙት ቦታና በዋሻዎች ይደበቃሉ፡፡ በዚህ ጉዞ ብዙዎች ታመው፤ ህጻናት በውሃ ጥም፣ በእባብና በጊንጥ በመነደፍ አልቀዋል፡፡ በቂ ስንቅም ስላልነበራቸው በርሃብ ረግፈዋል፡፡ በመንገድ ላይ በሽፍቶችና በቀማኞች ተዘርፈዋል፤ ሴቶች ተደፍረዋል፤ ብዙዎች ተገድለዋል፡፡
በ1981 በጋ፣ ዳኒ ሊሞር ከጓዶቹ ጋር በመሆን ወደ ሱዳን ተመለሰ፡፡ በድብቅ ስደተኞቹን መገናኘት ነበር አላማው፡፡ እናም በፎርጅድ ፓስፖርት በመጠቀም፣ በንግድ አውሮፕላኖች ሰዎቹን ማጓጓዝ ያዘ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው የተመቸ ስላልነበረ ጉዞው በባህር እንዲሆን ተወሰነ፡፡
ሞሳድ አንድ የአውሮፓ የቱሪስት ኩባንያ አቋቋመ፡፡ ኩባንያው ሱዳን አቅራቢያ የተዘጋ ሪዞርት ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ተከራየ፡፡ በሪዞርቱ ውስጥም የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው አሰልጣኞችና ሰራተኞች ተቀጠሩ፡፡ በርግጥ ከአገሬው ሰዎች ውጪ ያሉት በሙሉ የሞሳድ ኤጀንቶች ናቸው፡፡ የሪዞርቱ ፖስተርና ማስታወቂያ በአውሮፓ አገሮች በሚሰሩ የጉዞ ወኪሎች ሁሉ ተበተነና ስራ ጀመረ፡፡
ቀን ቀን ብዙ ደንበኞችን የሚያስተናግድ ቢሆንም ለሊት የሞሳድ ሰዎች ከመንደሮቹና ከካምፖቹ ዜጎቻቸውን ለቃቅመው፣ በአራት ትራኮች ጭነው ያመጣሉ፡፡ መጀመሪያ ከባድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ነጭ አይተው ስለማያውቁ ይደነግጡ ነበር፡፡  ዳኒ ሊሞር አንድ ጊዜ አብሯቸው በመፀለዩ ነበር፤ እነዚህ ነጭ ሰዎች የእነርሱ መሆናቸውን መቀበል የጀመሩት፡፡ ለጥንቃቄ ሲባል ሁሌም ዝግጁ እንዲሆኑ አስቀድሞ ይነገራቸዋል እንጂ መቼ እንደሚመጡና እንደሚወስዷቸው አያውቁም ነበር፡፡ በድንገት ማታ ይመጡና በኮሚቴዎቻቸው በኩል ያሰባስቧቸዋል:: ከዚያ በየፍተሻ ጣቢያው ለሚገኙ ወታደሮች ጠቀም ያለ ገንዘብ እየሰጡ ወደ መጨረሻ ነጥባቸው ይወስዷቸዋል፡፡ የእስራኤል ባህር ሃይል ወደ ዳርቻው ተጠግቶ ይጠብቅና ሰዎቹን በኮማንዶች እየመራ ከመርከብ ያሳፍራል፡፡ (እጅግ አስቸጋሪና አስጨናቂ ግዳጅ ነበር፡፡)
የባህር ሃይሉ አዛዥ ጋዲ ስለ ፈላሻዎቹ ሲናገር እንዲህ ይላል … ‹‹በፀጥታ ይመጣሉ፣ ይቀመጣሉ … ትንፍሽ ሳይሉ ይጓዛሉ… ›
በመጋቢት 1982 አንድ ድቅድቅ ጨለማ ለሊት፤ ቤተ እስራኤሎችን ወደ መርከቡ እየጫኑ እያለ አራት ኤኬ 47 የታጠቁ የሱዳን ወታደሮች ይደርሳሉ፡፡ በጨለማው መሳሪያዎቻቸውን ደግነው ‹እጅ ወደ ላይ!› እያሉ መጮህ ይጀምራሉ፡፡ ዳኒ ሊሞር ያለ የሌለ ድፍረቱን ሰብስቦ እንዲህ ሲል በእንግሊዝኛ ይጮሃል .. ‹‹እናንተ ሰዎች አብዳችኋል እንዴ፡፡  በቱሪስቶቻችን ላይ ልትተኩሱ ነው…›› ሰዎቹ በአዲሱ ሪዞርት (አሩስ - Arous’s) ለዋና የመጡ ቱሪስቶች መሆናቸውን በማስረዳት ድርጊታቸው ሪዞርቱን እንደሚጎዳውና በማግስቱ ክስ እንደሚያቀርብባቸው በማውራት መንበልበሉን ሲቀጥል፣ ወታደሮቹ ይቅርታ ጠይቀው ተመለሱ፡፡ እናም በመርከብ የመውሰዱ ነገር ከዚህ በኋላ አደጋ ላይ እንደሆነ ስለታመነበት ቆመ፡፡ አዲስ መንገድ መፈለግ እንዳለበት ስለታመነበት፣ በሪዞርቱ የሚገኙ የሞሳድ ሰራተኞች ሁሉ በአንድ ለሊት አገሪቱን ለቀው ወጡ፡፡ አንድ ማለዳ በሪዞርቱ የሚሰሩ የአገሬው ሰዎች ጠዋት ሲነቁ፣ በበጀት ምክንያት ባለቤቶቹ ስራውን መተዋቸውንና ሰራተኞች ወደ የአገራቸው መሄዳቸውን የሚገልጽ ማስታወሻ ብቻ ነበር የተገኘው፡፡ ለቀሩት የውጭ እንግዶች ደግሞ ሁሉም ወደ የአገራቸው ሲመለሱ ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸውም ደብዳቤው ይገልጻል፡፡
በሞሳድ ቤት የሚቀጥለው ኦፕሬሽን የአየር ሃይሉን ራይኖ ሄርኩለስ ሲ -130 አውሮፕላኖች በመጠቀም እንዲካሔድ ተወሰነ፡፡ ሱዳን ለእስራኤል የጠላት አገር መሆኗ ልብ ሲባል፣ እጅግ አደገኛ ቁማር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በግንቦት 1982 የሞሳድ ባልደረቦች ወደ ሱዳን ተመለሱ፡፡ አውሮፕላኑን አንድ የቀድሞ የእንግሊዞች አውሮፕላን ማረፊያን በመጠገንና በድብቅ በማሳረፍ 213 ሰዎችን መውሰድ ቻሉ፡፡ በመቀጠል ሱዳኖች ያልታወቀ እንቅስቃሴ በዚያ ቦታ መታየቱን ስለጠረጠሩ፣ ሞሳዶች ከፖርት ሱዳን 46 ኪሜ ርቀት ላይ ሌላ ቦታ አዘጋጁ፡፡ እናም ከዚህ ቦታ በሰባት የተለያዩ በረራዎች፣ በእያንዳንዱ 200 ያህል ሰዎችን አሻገሩ፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ደግሞ ከ1500 ሰዎች በላይ ተጓጉዘዋል፡፡
የሱዳን ደህንነቶች አዲስ ሰለሞን የተባለውን ቤተ-እስራኤላዊ ይዘው ለ42 ቀናት ያህል ሲያሰቃዩት፣ ድርጊታቸው ሁሉ የተጋለጠባቸው መስሏቸው እስራኤሎች እጅግ ተደናግጠው ነበር፡፡ ሆኖም አዲስ ሰለሞን ምንም አይነት ሚስጥር ሊነግራቸው አልቻለም፡፡ በቀጣይ አመት በአካባቢው ድርቅ እጅግ የከፋ ስለነበር፣ በአሜሪካ አደራዳሪነት፣ እስራኤል ምግብና ነዳጅ እየረዳች፣ በረራ እንዲፈቀድላት ጠየቀች፡፡ ሱዳኖች ቀጥታ ወደ እስራኤል በሚደረግ በረራ ሳይሆን በሌላ በሶስተኛ አገር ተደርጎ እንዲሆን ፈቀዱ፡፡ እናም በኦፕሬሽን ሞሰስ በ48 ቀናት፣ 7800 ሰዎችን በቤልጅየም በኩል አሻገሩ፡፡ ይህም ሚስጥራዊ ግዳጅ በሎስ አንጀለስ ታይምስ ላይ ወጣና ጠቅላይ ሚኒስትር ሽሞን ፔሬዝ ‹‹ ሁሉንም ዜጎቻችንን እንመልሳለን … ›› የሚል ይዘት ያለው መግለጫ በመስጠታቸው ሱዳን ውሉን አቋረጠች፡፡ እስራኤሎቹ ለጥቂት ሳምንታት አፋቸውን ቢዘጉ፣ ሁሉንም  ቤተ እስራኤላውያን መውሰድ በተቻላቸው ነበር፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የሚስጥር ግዳጆቹን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደንቀው እስራኤሎቹን ለመርዳት ተስማሙና በኦፕሬሽን ‹ንግስት ሳባ!› ሲአይኤ፣ 500 ቤተ እስራኤላውያን፣ ከሱዳን ወደ አገራቸው አሻገረ፡፡ በ1991 በኢትዮጵያ የደርግ መንግስት፣ በጦርነት በተዳከመበት ወቅት ኦፕሬሽን ሰለሞን ታቀደ፡፡ እስራኤል 35ሚሊየን ዶላር ለመክፈል፣ አሜሪካ ደግሞ በደርጉ ውስጥ ለሚገኙ ዋና ዋና ሰዎች መሸሸጊያ ለመስጠት ተስማሙ:: በዚህን ወቅት ደግሞ የአማጽያኑ (ወያኔዎቹ) መሪዎች ለተወሰነ ጊዜ የተኩስ አቁም ሊያደርጉም ተስማምተው ነበር፡፡ ለዚህ ግዳጅ 36 ሰዓት ብቻ ነበር የተፈለገው፡፡
አየር መንገዳቸው 30 እንዲሁም ብዙ የአየር ሃይሉ አውሮፕላኖች ወደ ኢትዮጵያ ዘመቱ፡፡ በ34 ሰዓታትም 14400 ሰዎች ተወሰዱ፡፡ ሪከርድ በተመዘገበበት አንድ ቦይንግ 747 በረራ ውስጥ 1087 ሰዎች ተጭነው የነበሩ ቢሆንም አውሮፕላኑ ሲያርፍ 1088 ሆነው ነበር፡፡ አንድ ህጻን በበረራ ላይ ተወልዷል፡፡
ምንም እንኳ ከዚያች የገጠር ክፍል ወደ ከተማ የተወሰዱት ህዝቦች፣ የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ በተወሰነው ህዝብ መገለል፣ እንዲሁም እንደ እውነተኛ ዜጋ ያለመቆጠር ያጋጠማቸው ቢሆንም ህዝቦቹ አሁንም አገራችን በሚሏት ምድር ይኖራሉ፡፡ የመጨረሻ የመዝሙራቸው አንጓም እንዲህ ይላል ፤
የውዷ እናቴን ምስል ከጨረቃዋ ፊት ላይ አያለሁ
ሳዝንም ሆነ ስተክዝ እያየሁት እጽናናለሁ፤
ብታደልና እዚህ ከጎኔ በህይወት ብትኖር
እውነተኛ አይሁዳዊ መሆኔን ታስረዳቸው ነበር፡፡
***
( MOSSAD, The greatest mission of  the Israeli secret service, by Michael Bar-Zohar & Nissam Mishal ከሚለው የሞሳድ ጀብዱ ትረካዎች ውስጥ አጥሮ የቀረበ፡፡ አመቶች ሁሉም በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር ፡፡ በተጨማሪ ኔት ፍሊክስ THE RED SEA DIVING RESORT በሚል ርዕስ በእውነተኛ ታሪኩ ጭብጥ ላይ ተመርኩዞ የሰራው ፊልም የፊታችን ጁላይ 31 ይወጣል፡፡ በፊልሙ ላይ ታዋቂ  ተዋናዮች የተወኑበት ሲሆን ቅድመ ፊልም ቅንጨባውን (trailer) በዩቲዩብ ከ2ሚሊየን በላይ ሰዎች አይተውታል፡፡ ፊልሙ የተቀረጸው በደቡብ አፍሪካና በናሚቢያ ነው፡፡)

Read 1556 times