Saturday, 27 July 2019 12:32

ከጋላቢ ፈረስ ይልቅ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች

Written by 
Rate this item
(16 votes)


        ከዕለታት አንድ ቀን አባትና ልጅ፣ ቁጭ ብለው ወጥመዳቸው አልገባ ብሎ ስላስቸገራቸው ጅብ ይመካከራሉ፡፡ አባት መላ ያሉትን ለልጃቸው ይነግሩታል፡፡ (አንዳንድ ተረቶች ተመላላሽ ታካሚ በመሆናቸው ብዙ ዘመን ተሻግረውም ድንገት ዳግሞ ይከሰታሉ፡፡ የሚከተለው ተረት ይሄ ዕድል ከገጠማቸው መካከል አንዱ መሆኑ ነው፡፡
አባት - “ቆይ ልጄ መላ መላውን ልንገርህ?”
ልጅ - “አባዬ እሺ መላው ምንድን ነው?”
አባት - “ልነግርህ አይደል አትቸኩላ!”
ልጅ - “እሺ ዘዴውን ብቻ ንገረኝ”
አባት - “እንካ ይሄን ጠመንጃ”
ልጅ - “ምን ላረግበት?”
አባት - “አትቸኩላ ልጄ!”
እጠመንጃው አፈሙዝ ላይ ሙዳ ሥጋ ታሥርና የገመዱን ጫፍ ቃታው ላይ ታስረዋለህ፡፡ ጅቡ ሙዳውን ሲጐትተው ቃታውን በራሱ ላይ ይስበዋል፡፡ አለቀለት ማለት ነው፡፡”
ልጅ - “አባዬ ከባድ ብልሃት ነው ያስተማርከኝ፡፡ አሁኑኑ ሄጄ ገመዱንና ሙዳ ሥጋውን አዘጋጀዋለሁ” ብሎ ልጅየው ይሄዳል፡፡ እንደተባለው ጠመንጃው አፈሙዝ ላይ ሙዳውን አስሮ ውጤቱን መጠበቁን ቀጠለ፡፡ ከጥቂት ስዓታት በኋላ ልጅየው ወደ አባቱ ሲሮጥ መጣና፤
አባት - “ልጄ ምን ተፈጥሮ ነው ይሄ ሁሉ ሩጫ?”
ልጅ - “አባዬ ጉድ ሆነናል?”
አባት - “እንዴት? “ለምን?”
ልጁም - “ጅቡ፣ ጠመንጃውን በአፈሙዙ በኩል ሳይሆን ሰደፉን ነክሶ ይዞት ሮጦ!”
አባት - “አዬ ልጄ ጉድ ሆነናላ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው! ዕዳ ከሜዳ ነው የገጠመን!”
***
ከቶውንም እንደ አተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) የሚመላለስብንን የአገራችን ችግር፣ “የተማረ ይግደለኝ” የተባለለት ምሁር፤ ደግ ምላሽ ቢሰጥበት ደግ ነው!
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን” የመጨረሻውን ቃል ለጀግናው ተውለት ይበሉን እንጂ ጀግናው ማን እንደሆነ ገና ለይተን አላወቅንም፡፡ አለማወቃችንን ደግሞ እንደ በረከት ልንወስደው አንችልም፡፡ ራሳችንን ቅዱስ ለማስመሰል እየሞከርን ካልሆነ በስተቀር፡፡
የዱሮ መምህራችን ፖለቲከኛው ሌኒን (One Step forward two steps back) - አንድ ደረጃ ወደፊት ሁለት ደረጃ ወደ ኋላ ብሎናል፡፡ የገባን ገብቶናል፡፡ ያልገባን ገና ይገባናል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ አገራችን ከእንደዚያ ያለ ማጥ ውስጥ የተዘፈቀችበት ሁኔታ ያለ ይመስላል፡፡ እየቆየ ግን የምትድንበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሐምሌት ….
“…በምናውቀው ስንሰቃይ
የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችን ማቅማማት
ወኔያችንንም ተሰልበን
ከዕለት ወደዕለት ስንሳብ ካባቶች በወረስነው ጋድ
የአዘወተርነውን ፍርጃ
እያስታመምን መለማመድ
መርጠን መሆኑ አይካድም
ያልታየ አገር አይናፍቅም
ቢያሰኝም አይታወቅም
የመንቀሳቀሳችን አቅሙ
እያደር ከህሊናችን ይደመሰሳል ትርጉሙ”
ኢትዮጵያ ለማደግ የሚያስፈልጋትን ኮታ ትሻለች እንጂ መፈናፈኛ እስኪጠፋት ድረስ የተጫነችን አገር አይደለችም፡፡ መንገዷን ታውቅ ዘንድ መንገድ የምናውቅ ሰዎች ቀና ቀናውን እናሳያት፡፡ ተማርን የምንባል እናስተምራት፡፡ የልጆቿን አዕምሮ እናበልጽግላት፡፡ ለተስፋ መቁረጥ ዕድል አንስጥ፡፡ መግቢያ መውጪያው ያምርልን ዘንድ ከገብረክርስቶስ ደስታ ጋር፤
“ደሞም ማወቅ ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
በተለይ ወጣቱ ውስጥ የበራ ብርሃን ካለ፣ በብርሃን ፍጥነት መንገድ እንስጠው፡፡ ብርታታችን የሚለካው በዚህ ነው፡፡ ሀገራችን መላ ትፈልጋለች፡፡ ብዙ መዘዘኛ ችግሮች አሉባት፡፡ እንዴት እንፍታለት ማለት ያባት ነው፡፡ ልጆቿን ማስተማር ምርጡ መላ ነው፡፡ ልጆቿ ስለሌሎች መጨነቃቸው አይቀሬ ነውና፡፡
ይለወጣል ቀኑ
ይሻራል ዘመኑ
እናንተ ራቁና ወደኛ ብቻ ኑ!!

Read 10431 times