ሁኔታዎቹ ወይ ማሽነፍ ካልሆነም አቻ መውጣት ናቸው፡፡ ሉሲዎች ለለንደን ኦሎምፒክ ለማለፍ ከጫፍ ደርሰው በደቡብ አፍሪካዎቹ ሴቶች ያጡትን እድል በአፍሪካ ዋንጫ እንደሚያካክሱ ሲጠበቅ በመልስ ጨዋታ ዳሬሰላም ላይ ከተሳካላቸው በታሪካቸው ለ3ኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ይችላሉ፡፡ የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በአዲስ አበባው ጨዋታ ኢትዮጵያውያን ለመሸነፍ ባለመፈለጋቸው ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለባቸው ተግባራት ፈፅመውብናል በሚል ለታንዛኒያ ጋዜጦች አማርረዋል፡፡ አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድናቸው አዲስ አበባ ላይ ስታድዬም ውስጥ በመልበሻ ክፍል በገጠመው ከፍተኛ የኬሚካል ሽታ መቃወሱን ሲያማርሩ ተጨዋቾች በመልበሻ ክፍልነት የስታድዬሙን ኮሪደር ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልፀው ሁኔታው በውጤታቸው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን አባላት በዳሬሰላም የሚያስተናግዱትን የመልስ ጨዋታ የተቻላቸውን መስእዋትነት ሊከፍሉበት እንደተዘጋጁ ሲናገሩ ለሁለተኛ ግዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን በሜዳቸው ለመወሰን ቁርጠኛ መሆናቸውን እየገለፁ ናቸው፡፡ በመልሱ ጨዋታ የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በቱርክ በሚገኝ ክለብ የምትጫወተውን ሙኩዋሲ የተባለች የተከላካይ መስመር ተጨዋች ለማሰለፍ መቻላቸውም የማለፍ ተስፋቸውን እንዳጠናከረ የአገሪቱ ሚዲያዎች ሰሞኑን ዘግበዋል፡፡
ከ2 ሳምንት በፊት ሉሲዎች ከታንዛኒያ እህትማማቾች ጋር በመጀመርያ ጨዋታው አዲስ አበባ ስታድዬም ላይ ሲገናኙ ጨዋታው በተጀመረ በ19ነኛው ደቂቃ ታንዛኒያዎች ግብ በማስቆጠር መሪነቱን ይዘው ነበር፡፡ በሜዳቸው በእንግዳው ቡድን 1ለ0 መመራት የጀመሩት ሉሲዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ማድረጋቸው ሲታወስ ይህ ጥረታቸው ያስገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሄለን ሰይፉ አስቆጥራ የመጀመሪያው ግማሽ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡ በሁለተኛው ግማሽ ሉሲዎች በማጥቃት ላይ በተመሰረተ አጨዋወት ከፍተኛ ብልጫ በማሳየት ለማሸነፍ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቆዩ፡፡ በመጨረሻም ተቀይራ በገባችው ቱቱ በላይ አማካኝነት ሁለተኛውን ጎል በማስቆጠር ሉሲዎች 2ለ1 የታንዛኒያ አቻቸውን ማሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡