Saturday, 20 July 2019 11:47

ኢሠመጉ፤ የሰብአዊ መብት አያያዝ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)


    በሀገሪቱ ተስፋ ሰጪ በሆነ ሁኔታ ተጀምሮ የነበረው የሰብአዊ መብት አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ፣ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ማጣራት ሳይደረግ እስራት መፈፀሙም ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
ኢሠመጉ ወቅታዊ የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ገምግሞ ባወጣው ሰፊ መግለጫ፤ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ የዜጐች መረጃ የማግኘት መብት፣ የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ የዜጐች በፈለጉት ቦታ በነፃነት ተዘዋውሮ የመኖርና የመስራት እንዲሁም የእስረኞች አያያዝ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታውቋል፡፡
በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በሰብአዊ መብት መከበር፣ ሃሳብን በነፃነት በመግለጽና በሌሎች የዲሞክራሲ ሁኔታዎች በእጅጉ ስኬታማና ተስፋ ፈንጣቂ ነበር ያለው ኢሠመጉ፤  የዲሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት ረገድም የተሄደበት ርቀት እጅግ የሚያበረታታ መሆኑን  በመግለጫው አስቀምጧል፡፡
በቅርቡ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ በብቃታቸው እጅግ የተመሠከረላቸው ናቸው ያለው ኢሠመጉ፤ ሹመታቸው ተገቢ ነው ብሏል፡፡ የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝም በቀጣይ ሊያሻሽሉ ይችላል የሚል ተስፋ መፈንጠቁን ኢሠመጉ ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ “በተለይ ከሰብአዊ መብት አያያዝ አንፃር ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲሸረሸር ቆይቶ ሁኔታው አሁን አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል” ያለው ኢሠመጉ፤ መንግስት አፋጣኝ ማሻሻያዎችን ማድረግ አለበት ብሏል፡፡
በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በባለስልጣናትና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ መንግስት አግባብ ያልሆነ የእስራት ዘመቻ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ በጋዜጠኞችና በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት በሚያቀርቡ ሰዎች ላይ መክፈቱን የጠቆመው መግለጫው፤ ይህ የመንግስት ድርጊትም ከለውጡ በፊት የነበረውን የጭቆናና  አፈና ስርአት የሚያስታውስ ነው ብሏል፡፡
በዚህ እርምጃ 66 የአብን፣ 30 የኦፌኮ፣ 6 የኢዜማ እንዲሁም የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት አባላትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ግለሰቦች መታሰራቸው፣ በሀገሪቱ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቶ በነበረው ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና ሌሎች መሠረታዊ መብቶች በዘላቂነት መረጋገጥ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ፣ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብሏል - መግለጫው፡፡
ከታሣሪዎቹ መካከል 6 ያህሉ በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን በቤተሰብ የመጐብኘት መብት መነፈጋቸውን፣ ኢሠመጉ ታሣሪዎቹን ለመጐብኘት በደብዳቤ ለፖሊስ ያቀረበው ጥያቄም ምላሽ ማጣቱን በመጠቆም፣ ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶች አሳሳቢ በሆነ መልኩ በድጋሚ እያንሠራሩ መሆናቸውን ጠቁሟል::
የፀረ ሽብር ህጉ፣ መንግስት ራሱ፣ የዜጐችን መብት እንደሚጥስና ተቃውሞን ለማፈን ይጠቀምበት የነበረ ህግ መሆኑን በገለፀበትና የጠቅላይ አቃቤ ህግም አዋጁን በማሻሻል ሂደት ላይ ባለበት ወቅት በዚህ በተወገዘ ህግ፣ በታሣሪዎች ላይ ምርመራ መጀመሩ ለውጡ ወዴት እያመራ ነው የሚል ጥያቄ ስጋት አስነስቷል ብሏል - ኢሠመጉ፡፡
ኢሠመጉ በዚህ መግለጫው ካነሳቸው ጉዳዮች አንዱ የኢንተርኔት መዘጋት ጉዳይ ሲሆን መንግስት በዘፈቀደ የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚዘጋበት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፤ በባህርዳር እና አዲስ አበባ በባለስልጣናት ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ ለበርካታ ቀኖች አገልግሎቱ መቋረጡም ያልተመጣጠነ እርምጃ ነው ብሏል፡፡ መንግስት ከእንዲህ አይነቱ በጅምላ ኢንተርኔትን የመዝጋት እርምጃ እንዲቆጠብ እንዲሁም ከዚህ አንፃር መንግስትን የሚቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ እንዲወጣ ጠይቋል፡፡
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው የቃላት ጦርነት አስጊ መሆኑን ያመለከተው የኢሠመጉ መግለጫ፤ ፓርቲዎቹ ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡
“አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ የሠላም እጦት ስጋት ውስጥ እንደምትገኝ ይታወቃል” ያለው ኢሠመጉ፤ ከዚህ ስጋት ለመላቀቅ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በእርጋታና በኃላፊነት ስሜት ህዝብንና የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ መፍትሔ እንዲፈልግ አሳስቧል፡፡
ሰላምን ያመጣሉ በሚል የተቋቋሙት የሠላምና እርቅ እንዲሁም የማንነትና ድንበር ኮሚሽኖች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡም ኢሠመጉ በዚህ ሰፊ ጉዳዮችን በዳሰሰበት ወቅታዊ መግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡    

Read 6875 times