Saturday, 20 July 2019 11:39

የጅማ ዩኒቨርሲቲ 4ኛው ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ተካሄደ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

- 31 የጥናትና ምርምር ጽሑፎች በዓለም አቀፍ ምሁራን ቀርበዋል
     - ጉባኤው በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል
       
     በጅማ ዩኒቨርስቲ የኦሮሞ ጥናት ተቋምና እንግሊዝ አገር በሚገኘው የኦሮሞ ጥናት ኔትወርክ ድርጅት ትብብር፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው አራተኛው ዓለምአቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ትላንት ማምሻውን ተጠናቀቀ፡፡ “Oromia State Formation and Socio Economic and Political order In Ethiopia and Horn” (የመንግስት አመሰራረት ሂደትና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታው፣ በኦሮሚያ፣ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ”) በሚል ርዕስ ከትላንት በስቲያ ሐምሌ 11 በጅማ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የስብሰባ ማዕከል የተጀመረው አለምአቀፍ ጉባኤው በዘርፉ ጥልቅ ምርምር ባካሄዱ ዓለም አቀፍ ምሁራን 31 የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው፣ እስከ ትላንት ምሽት ሰፊ ውይይትና ምክክር የተደረገባቸው ሲሆን፤ ጥናትና ምርምሮቹ የአገራችንን ወቅታዊ ጉዳዮች የሚዳስሱ እንደሆኑና የተለያዩ የፖሊሲ ግብአቶችና ምክረ ሃሳቦች እንደተገኙባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጀማል አባ ፊጣ የጉባኤውን አላማ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የእስከዛሬው የመንግስት አመሰራረት ሂደት በቀጠናው (በምስራቅ አፍሪካ)፣ በኢትዮጵያና በኦሮሚያ ያለውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ በመመርመር የፖሊሲ ግብአቶችን ማመንጨት አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉዳይ የእስከዛሬው የመንግስት አመሰራረት ሂደት ማህበረሰባዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን በጥልቀት በመዳሰስ፣ ምክክር ማድረግና አለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታዎች እኛ ላለንበት ቀጠና (የቀንዱ አካባቢ) የፀጥታና መረጋጋት ጉዳይ ያለውን አንደምታ በጥልቀት መፈተሽ እንዲሁም የቋንቋ ፖለቲካ ገጽታ በኢትዮጵያ ትላንት፣ ዛሬና ነገ ያለውንና የሚኖረውን ሁኔታ መመርመር… ዋና ዋና አላማዎቹ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
ለጉባኤው ከውጭና ከአገር ውስጥ 81 የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን፤ ጥናታዊ ጽሑፎቹን በመመዘን ለጉባኤው ይመጥናሉ የተባሉ 31 ጥናቶች ለጉባኤው መቅረባቸውን የገለፁት ዶ/ር ጀማል እነዚህ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች በማቅረብ ከአገር ውስጥ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ከአሜሪካ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከአውሮፓ ከአፍሪካ (ሱዳን) የመጡ ምሁራን እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡  በጉባኤው ላይ የኦሮሞ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ኤገሬ፣ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣና የኦሮሞ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሲፈን ቆርቼን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የክልል ባለስልጣናት፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶችና ተመራማሪ መምህራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲ ስቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች መታደማቸው ታውቋል፡፡  በጉባኤው ላይ ፖለቲከኛው ጀዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባና ሌሎችም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ምሁራን ተሳታፊ እንደነበሩ ታውቋል፡፡  


Read 951 times