Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 08:27

“ግብፅ ሌላ አብዮት ይጠብቃታል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የቀድሞው አምባገነን መሪ ሁስኒ ሙባረክና ባለስልጣኖቻቸው  በህዝብ አመፅ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን ለአንድ ዓመት ገደማ በፍርድ ቤት ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ ፍ/ቤት ውሳኔ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብያኔ መሰረት፤ ሆስኒ ሙባረክ እና የቀድሞው የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሀቢብ አዲል በህዝባዊ አመፁ ወቅት ለተፈፀሙ ግድያዎች ቀጥተኛ ተጠያቂ ባይሆኑም ድርጊቱን ባለማስቆማቸው የእድሜ ልክ እስራት የተወሰነባቸው ሲሆን በሚኒስትሩ ረዳቶች ላይ ቀርቦ የነበረው ተመሳሳይ ክስ ግን ውድቅ ተደርጐአል፡፡ ከመሬት ጋር በተያያዘ ሙባረክ እና ሁለቱ ልጆቻቸው ላይ ቀርቦ የነበረው ክስም ውድቅ የተደረገ ሲሆን ስልጣንን አለአግባብ መጠቀም በሚል በሙባረክ ላይ የተመሰረተውን ክስ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቶአል፡፡

በፍርድ ሂደቱ ከስልሳ ሺህ በላይ የሰነድ ማስረጃዎች ለክሱ ማጠናከሪያ ከመቅረባቸውም  በተጨማሪ፤ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚደንት ኦማር ሱሌይማንና የወታደራዊው ምክር ቤት የበላይ ሃላፊ ሁሴን ታንታዊ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸው ታውቆአል፡፡

የፍ/ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የታህሪር አደባባይ በተቃውሞ መታመሱን የጠቆሙ መረጃዎች  በርካታ ግብፃውያን “ህግ አስፈፃሚው ነፃ ይሁን”፣ “ሙባረክና አጋሮቻቸው በሞት መቀጣት አለባቸው” የሚሉ ተቃውሞዎችን እንዳስተጋቡ አመልክተዋል፡፡

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ከውጪ ሆኖ ሲከታተል የነበረው  የሀያ ስምንት አመቱ አህመድ ካህሊል፤ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ረዳቶች በነፃ መሰናበታቸው ግርምት እንደፈጠረበት ተናግሯል፡፡ “አልካራማህ” የተባለው የአገሪቱ ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አራፋት አሚን በበኩላቸው፤ በሚኒስትሩ ረዳቶች ላይ የተሰጠው የፍርድ ውሳኔው ትክክል ነው ብለዋል- “የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ረዳቶች ትእዛዝ ተቀባዮች በመሆናቸው ተጠያቂ መሆን የለባቸውም፡፡ ትእዛዙን ያስተላለፈው ነው መጠየቅ ያለበት” በማለት፡፡ ኢማድ አል-ባኬ የተባሉ ፖለቲከኛ ደግሞ፤ ግድያውን የፈፀሙት ስድስቱ ግለሰቦች እንዴት በነፃ ይሰናበታሉ ሲሉ የፍ/ቤቱን ውሳኔ ተቃውመውታል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካል ሳይንስ ማእከል ተመራማሪ የሆኑት አክራም ሆሳም ግን  እንደውም ቅጣቱ በዝቷል ባይ ናቸው፡፡ “ሙባረክ እና አዲል በእድሜ ልክ ሳይሆን ከዛ ባነሰ ይቀጣሉ ብዬ ነበር የማስበው፡፡ ለነገሩ ሁለቱ ግለሰቦች ይግባኝ ጠይቀው የቅጣቱን ጣራ ዝቅ እንደሚያስደርጉት እገምታለሁ” ብለዋል፡፡ መሀመድ ኤልባራዲ የተባሉ ፖለቲከኛ በትዊተር ገፃቸው በሰጡት አስተያየት፤ የቀድሞው መንግስት እራሱን እየዳኘ የግብፅን አብዮት አጨናገፈው ሲሉ በውሳኔው ያለመደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በምርጫ ፉክክር ውስጥ ላሉ ግለሰቦችና ፓርቲዎች አዲስ አጀንዳ ይዞላቸው የመጣ ይመስላል፡፡ ባለፈው ምርጫ ሶስተኛ ደረጃን በማግኘት ከእጩነት የወጡት ሀመዲን ሳባሂ፤ “የአሁኑ የፍርድቤት ውሳኔ ተሽሮ የጉዳቱን ሰለባዎች አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ በአብዮታዊ ፍርድ ቤት እንደ አዲስ መታየት አለበት፤ ውሳኔው የግብፅን ህዝብ ወደ ታህሪር አደባባይ የሚመልስ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የቀረበው ማስረጃ በቂ አይደለም ያለው የሙስሊም ወንድማማችነት ፓርቲ፤ ማስረጃዎቹን የደበቁ ተቋሞች እንዲመረመሩ መደረግ አለበት” ብሎአል፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የግብፅን ገፅታ የሚያበላሽና በወደፊት የአገሪቱ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳርፍ ነው ያለው ፓርቲው፤ ግድያ የፈፀሙ የፀጥታ ሀይሎችን ነፃ በማሰናበት በሰማእታት ደም መቀለዱና የአገሪቱን የፍትህ ስርአት ሽባ ማድረጉ ግብፃውያንን በሙሉ ያስደነገጠ ነው” በማለት ውሳኔውን እንደማይቀበል አሳውቋል፡

በሚቀጥለው ሳምንት  በሚደረገው የመጨረሻ ምርጫ የሙስሊም ወንድማማቾች እጩ ከሆኑት ከሞሪስ ጋር ለፕሬዚደንትነት የሚወዳደሩት የሙባረክ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት  አህመድ ሻፊቅ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ “ሙባረክን በእድሜ ልክ እንዲቀጣ መፍረድ ማንም ከህግ በላይ እንዳልሆነ ያሳየና ለሚቀጥለው ፕሬዚደንት ትምህርት የሚሰጥ ታሪካዊ ውሳኔ ነው” ሲሉ የፍርድቤቱን ውሳኔ በማወደስ ተናግረዋል፡፡

እነ ሙባረክ ውሳኔው ከተሰጠበት እለት አንስቶ እስከ ስልሳ ቀን ድረስ ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችሉ የተናገሩት የግብፅ ፍ/ቤት ዳኞች፤ የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ትክክለኛውን ብይን እንደሰጡ ገልፀዋል፡፡ ዳኞቹ እንዲህ ይበሉ እንጂ የታህሪር አደባባይ አሁንም በተቃውሞ እየታመሰ ነው ተብሎአል፡፡

የግብፅ አብዮት በፍርድቤቱ ውሳኔ ተቀልብሶአል ያሉት ኖራን መሀመድ የተባሉ ፖለቲከኛ፤ “እኔ ወደ ታህሪር አደባባይ አመራለሁ፤ ግብፅ ሌላ አብዮት ይጠብቃታል” ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

 

 

 

Read 4308 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 09:48