Saturday, 13 July 2019 11:38

የምርጫ “ይራዘም አይራዘም” አስገራሚ ውዝግብ!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 በመጪው ዓመት ግንቦት ላይ የሚደረገው አገራዊ ምርጫ “ይራዘም አይራዘም” የሚለው ጉዳይ አስገራሚ ውዝግብ ፈጥሯል፡፡ “ምርጫው ይራዘም” እንዲሁም “ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ መካሄድ አለበት” የሚሉትን ሁለት ሃሳቦች የሚያንፀባርቁት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለአፍታም እንኳን አንድ ላይ ቁጭ ብለው በጉዳዩ ላይ ሊነገሩ፤ ሊወያዩ አልሞከሩም፡፡
ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው በመገናኛ ብዙሃን ነው ይሄን ሃሳብ የሚያስተላልፉት፡፡ ምርጫው  በዚህ ውዝግብ ላይ ምሁራን ምን ሃሳብ አላቸው ይህ ጉዳይ ከሀገር ሠላም አንድነት ፀጥታ አንፃር እንዴት ይታያል የምርጫውን መራዘም አለመራዘም ጉዳይ የሚወሰነውስ ምንድን ነው ለሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ላይ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና የፖለቲካ አቀንቃኙ አቶ ኦባንግ ሜቶን ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ አውግተዋል፡፡


          ፖለቲከኞች በአንድ በኩል ቀጣዩ ምርጫ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መካሄዱ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ይላሉ በሌላ በኩል፤ ምርጫው ፍፁም ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ መሆን እንዳለበት አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ዲሞክራሲያዊና ከውዝግብ የፀዳ ምርጫ ለማድረግ፣ የተረጋጋ አገርና በቂ የዝግጅት ጊዜ ስለሚያስፈልግ የምርጫው ጊዜ መራዘም እንዳለበትና ተጣድፈን ወደ ምርጫ መግባት እንደማይገባን የሚከራከሩ  የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው
ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ይካሄድ ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ አሁን ያለው ጊዜ ከአንድ አመት በታች ነው፡፡ በአንድ አመት ውስጥ በሚካሄድ ምርጫ፣ እንዴት ህዝብ ትክክለኛ መሪውን አጥንቶ፣ መምረጥ ይችላል? ተጨማሪ 10 ወር ያህል ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ ሠርግ እንኳ ለመደገስ፣ ሰው በትንሹ ሶስት ወር ይፈጅበታል፤ እንኳን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ፡፡ ምርጫ ዝም ብሎ ሂደት መሆን የለበትም፡፡ አላማ ሊኖረው ይገባል፡፡ ሰዎች ትክክለኛ መሪያቸውን የሚመርጡበት ነው መሆን ያለበት፡፡ በኔ አመለካከት፤ ምርጫ በቀረው አንድ አመት ውስጥ ቢካሄድ ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ አላምንም:: በተለይ በአሁኑ ሰዓት ፀጥታ ባልተከበረበት፣ በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች በመሣሪያ በሚገደሉበት ሁኔታ… ወደ ምርጫ መግባት የበለጠ አደጋን መጋበዝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ፣ የክልል ጥያቄ ውዝግብ የመሳሰሉ ውስብስብ  ችግሮች አሉ፡ እነዚህን የት አስቀምጠን ነው ምርጫ በጥድፊያ የምናደርገው? የምንሠራው ስራ ውጤታማ  እንጂ የይስሙላ መሆን፣ የለበትም ምርጫ ለህዝብ ከሆነ ህዝብ ነው ባለቤቱ፡፡ ስለዚህ የህዝብ ፍላጐትም ሊጠና ይገባል፡፡
ወደ ምርጫ የሚገቡ የፖለቲከ መሪዎች፣ ዝግጅታቸው ምንድን ነው? ሀገር የመምራት ስነ ልቦና አላቸው ወይ? ይሄ ሁሉ ከምርጫው በፊት መመለስ አለበት፡፡ ሁሉም ከምንም በፊት ማሰብ ያለበት ስለ ሀገር ቀጣይነት ነው፡፡ ስለ ሀገር የሚጨነቁ ሰዎች ተሰባስበው፣ በዚህ የምርጫ ጉዳይ ላይ በመወሰን፣ ጊዜውን ቢያራዝሙት የተሻለ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ለህዝብ ሳይሆን ለፖለቲከኞች ብቻ ነው የሚጠቅመው፡፡ ሀገርንም አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡
በአሁኑ ወቅት ፖለቲከኞች ትኩረት መስጠት ያለባቸው እንደ ምንም ምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን ለመያዝ ነው ወይስ በአገሪቱ ላይ ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ነው? የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል? ምርጫው በተቀመጠበት የጊዜ ገደብ ካልተካሄደ “ህገ መንግስት መጣስ ነው” በሚል አጥብቀው የሚቃወሙ ወገኖችም አሉ?
እንደዚህ የሚያስቡ ሰዎች ናቸው ችግር የሚፈጥሩት፡፡ እነዚህ ሰዎች ህዝቡንና የሀገር መረጋጋትን አያስቡም ማለት ነው፡፡ በኔ አመለካከት፤ ዋናው መቅደም ያለበት በምርጫ ተወዳድሮ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ አይደለም፤ ሀገርን በአንድነት ማቆየት ነው፡፡ እኛ አሁን የምንፈልገው፤ ሀገር የሚያረጋጋ መሪ እንጂ ሀገር የሚመራ መሪ አይደለም፡፡ ሠላም ሲኖር ነው፣ ፖሊሲ አውጥቶ ሀገር የሚመራው፡፡ አሁን ሀገር የማዳን ጉዳይ ነው፡፡  የስልጣን ፍላጐት የበለጠ ሀገርን ያፈርሳል፡፡ ለሁሉም ግን መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ስልጣን የሚያዘው ሀገር ሲኖር ነው:: ሀገር ባልተረጋጋበት በምርጫ የሚያዝ ስልጣን ምንድን ነው ትርጉሙ? ህገ መንግስት ደግሞ በሰዎች ለሰዎች ተሠራ እንጂ ከሀገር ህልውና በላይ አይደለም:: ስለዚህ ተነጋግሮና ተወያይቶ ምርጫውን ማራዘም ይቻላል፡፡
“ምርጫው መራዘም የለበትም” የሚሉ ወገኖች፤ በምርጫው ማግስት ሊፈጠሩ የሚችሉ ውዝግቦችና ቀውሶችን አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የዘነጉት ይመስላል፡፡ ይሄ ሁኔታ አደጋውን የበለጠ የከፋ አያደርገውም? ከዚህ አንፃር ከምሁራን ምን ይጠበቃል?
አሁን ያለው የብሔር እንጂ የሀገር ፍቅር አይደለም፡፡ ሁሉም የሚያስበው ስለ ክልሉ እንጂ ስለ ሀገር አይደለም፡፡ ሰዎች ትኩረታቸው አብሮነት ላይ ሳይሆን ሰለ ግለኝነት ነው፡፡ ይሄ ነው ችግራችን:: ልሂቃኑ ችግሩን ደጋግመው ማስገንዘብ አለባቸው:: እሣት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ለምን ያስፈልጋል? አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው ከሀገር ባንዲራ ይልቅ ለብሔር ባንዲራ ነው፡፡  በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚደረገው? መጀመሪያ ውስጣችን ያለው በሽታ መዳን አለበት:: ቁስሉ መፈወስ አለበት፡፡ በእርቅና በመግባባት መፈወስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በፊት እንዴት ነው ምርጫ የሚደረገው? ፓርቲዎች እኮ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እየሠሩ አይደለም፡፡ በጠመንጃ የተባረሩ ፓርቲዎች አሉ እኮ፡፡ በሌላ በኩል፤ ምርጫ ቦርድ ምን ያህል ነው የተለወጠው? እስከ ታች ድረስ ምን ያህል መሻሻል ተደርጓል? እነዚህ ሁሉ ሳይረጋገጡ ወደ ምርጫው ብንገባ አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው፡፡  ከምርጫው በኋላ የሚፈጠሩ ችግሮችን መቆጣጠር የሚችል አስተማማኝ ሃይል አለን ወይ? አሁን መከላከያ የፖሊስ ሥራ እየሰራ ነው፡፡ ፖሊስ ደግሞ ራሱ ብሔር ሆኗል፤ በብሔር ነው እየሠራ ያለው፡፡ ይሄ ሁሉ ባልተስተካከለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አደጋ አለው፡፡ ከሶሪያ አንማርም? ሀገር ሲኖር እኮ ነው ሥልጣን የሚኖረው፤ ስለ ሥልጣንም የሚታሰበው፡፡ እኔ አደራ የምለው፤ የምናደርገው ነገር ሁሉ በስሜታዊነት እንዳይሆን ነው፡፡
የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት በተደጋጋሚ ቃል እንደገባው፤ መጪውን ምርጫ ነፃ፡ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ የማድረግ አቅም አለው ብለው ያስባሉ? (ቅን ፍላጐት ቢኖረውም ማለቴ ነው) ምናልባት ቢሸነፍስ በሠላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር ያደርጋል ብለው ይገምታሉ?
እኔን አሁን የሚያሳስበኝ እሱ አይደለም፡፡ ለቃላቸው ታማኝ ይሆናሉ አይሆኑም የሚለው አይደለም፡፡ ዋናው ነፃ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ወይ? የሚለው ነው፡፡ እሱ ከተፈጠረ ጠ/ሚኒስትሩ ፈለጉም አልፈለጉም በምርጫ ከተሸነፉ ስልጣናቸውን ያስረክባሉ፡፡ ዋናው ነገር፤ ሀገር ይረጋጋ፣ የህግ የበላይነት ይስፈን፣ ተቋማት ይፈጠሩ፤ ምርጫ ከተካሄደ እና ከተሸነፉ ለምን ስልጣን አይለቁም? ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ህግ ነው የሚያስተዳድራቸው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ተቃዋሚዎች በምርጫው ቢሸነፉ፤ ሽንፈታቸውን በፀጋ እንደሚቀበሉት ምን ማስተማመኛ አለ? “ምርጫው ተጭበርብሯል” በሚል ውዝግብና ግጭት እንዳይፈጠር ምን ማድረግ ይገባል?
ህዝቡ መጀመሪያ እኮ የእነሱን አላማ ማወቅ አለበት፡፡ አሁን መቼ አወቀ? መቼ ነገሩት? ለመንገርስ ምን ምቹ ሁኔታ አለ?  የት ነው የፖለቲካ ፓርቲ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መራጭ ያዘጋጀው? አፋር ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል… የት ሄደው ምን ሠሩ? ታዲያ እንዴት ነው የፖለቲካ ስራ ሳይሠራ፣ አዲስ አበባ ተቀምጦ “ምርጫው ተጭበርብሯል፤ አሸንፈናል” ሊባል የሚችለው? ይሄ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ህግን ማጠናከር፣ በህግ መስራትና በሃቅ መሄድ ያስፈልጋል፡፡Read 4229 times