Sunday, 07 July 2019 00:00

የስደተኞች መከራ በእስር ቤቶች

Written by  አሸናፊ በሪሁን ከSeefar
Rate this item
(1 Vote)

ብዙዎቹ ስደተኞች ከአፍሪካ እየተነሱ ወደ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ የሚያደርሰውን ጎዳና ሲያያዙ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ቀጠና የሆኑትን የመንንና የሊቢያን ምድር ማቋረጥ ይኖርባቸዋል:: ከፊታቸው ባሕር፣ ከጀርባቸው ደግሞ በረሀንም አቆራርጠው፣ ብዙ ስደተኞችን የበላውን ክፉ ማዕበል ተጋፍጠው፣ በለስ ቀንቷቸው በሕይወት ለሚደርሱት አጋጣሚው መልካም ነው፡፡ ላልተሳካላቸውና  ለማምለጥ ሲሞክሩ ለሚያዙትና በህገ-ወጥ አስተላላፊዎች እጅ ለሚወድቁት ግን  የመንና ሊቢያ፣ የገሃነም ደጆች ይሆኑባቸዋል፡፡
በሰብአዊ ቀውስና ጦርነት ሳቢያ ወደ ደቀቀችው የመን የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር አያሌ ነው፡፡ እንደ  የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት  ግምት፤ በ2018 ዓ.ም መጨረሻ፣ ወደ 150 ሺ የሚደርሱ ስደተኞች የመን ገብተዋል ፡፡ በ2018 ዓ.ም ወደ የመን ከተሰደዱት መካከል 92 በመቶ የሚሆኑት የተሰደዱት ደግሞ ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ብዙዎቹም በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው  የመን እንደደረሱ፣ የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
በጦርነት አውድማ ውስጥ በሆነችው የመን  የድንበር ቁጥጥሩ የላላ  ነው፡፡  ስደተኞችም በደላሎች ድጋፍ በቀላሉ የየመንን ምድር አቋርጠው ይገባሉ፡፡ በዚህ ሂደትም፣ ስደተኞች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ የፈንጅ ወረዳዎችን ማለፍ የግድ ነው፡፡  የተኩስ ልውውጥ ሰለባ ሊሆኑም ይችላሉ::  ይህን ሁሉ መከራ አልፈውም ታዲያ  በህገ-ወጥ አስተላላፊዎች እጅ ላይ ይወድቃሉ፡፡
የሜዲቴራኒያን ሶማሊያ እየሆነች ነው የምትባለው ሊቢያም፤ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚሹ ሕገ ወጥ ስደተኞች፣ እንደ ዋና መሸጋገርያቸው የሚጠቀሙባት እምብርት ናት፡፡ ከዓመታት በፊት ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን፤ የሥራ ዕድል የሚያገኙባት ማዕከል የነበረችው ሊቢያ፣ ዛሬ የዘግናኝ ድርጊቶች  መናኸርያ ሆናለች።
ሜዲስንስ ሳንስ ፍሮንቴሪስ (MSF) የተባለ የህክምና እርዳታ የሚሰጥ ተቋም፣ በመጋቢት 2019 በትሪፖሊ፣ ሳቢያ በተባለ የማቆያ ማእከል ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች፣ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ችግር እንደተጋረጠባቸው  ጠቁሟል፡፡ ይህ ከ3ሺ በላይ ስደተኞች የታጨቁበት ማዕከል፤ ከያዛቸው ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ህፃናት ናቸው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከስድስት ወር በላይ እዚሁ ታጭቀው የቆዩ ናቸው፡፡ የሊቢያ መንግስት፤ በአሁኑ ሰዓት ከ5,700 በላይ ስደተኞችን፣ እንደ ሳቢ በመሳሰሉ መንግስት በሚቆጣጠራቸው የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራል።
በሊቢያም ሆነ የመን ውስጥ የሚገኙት እነዚህ  ስደተኞች ታዲያ ለህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪ መረቦች እጅግ የተጋለጡ ከመሆናቸውም በላይ በወንበዴዎች የከፋ ስቃይ ይደርስባቸዋል፡፡ ሃይ ባይ የሌላቸው እነዚህ ሰው አዘዋዋሪዎችም ታዲያ ጭካኔ እንጂ ርህራሄ የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም፡፡  ስደተኞችን ሲፈልጉ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ይደበድቧቸዋል፤ ሲያሻቸው ይደፍሯቸዋል፤አንዳንዴም እንደ ዕቃ አጫርተው ለባርነት ይሸጧቸዋል፡፡ ተደጋጋሚ የሆነ ጥቃት ያደርሱባቸዋል፡፡ ዛሬም በርካታ ስደተኞች በእስር ቤቶች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ይማቅቃሉ:: በእስር ቤቶች፣ የግዳጅ ሥራ መደበኛ ከመሆኑም በላይ ለእስረኞቹ የሚሰጠው ምግብና ሕክምና እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
 በቅርቡ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት፤ ሊቢያ ውስጥ እዚህም እዚያም ሕግ እናስከብራለን የሚሉ የታጠቁ ቡድኖች፣ ህገ ወጥ የሰዎች አስተላላፊዎችና በአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር የሚገኙ እጅግ ሰፋፊ እሥር ቤቶችን የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት፣ ስለሚፈፅሙት የስቃይና የባርነት አያያዝ፣ ፆታዊ ጥቃትና የዝርፊያ ተግባር በዝርዝር አስፍሯል።
“ሊቢያዊያን ድንበር ላይ በጎማ ቧምቧ ይደበድቡናል፤ አሸዋ ይዟቸው መንቀሳቀስ ያልቻሉትን ተሽከርካሪዎች ገፍተን እንድናወጣ ያስገድዱናል። ፊታችን ሆነው እየበሉና እየጠጡ፣ በሚጠብሰው ፀሃይ አሰልፈው ያቆሙናል።” ሲል አንድ ሊቢያ ውስጥ ታስሮ በስቃይ ላይ የነበረ እስረኛ ለተመድ ተናግሯል፡፡ ስደተኞች፤ በየመንም ተመሳሳይ ስቃይና በደል ይደርስባቸዋል ፡፡ ስቃይ የበዛባቸው ስደተኞችም ከእስር ቤቶች ይፈቱ ዘንድ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ  ጩኸታቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትም፣ በደቡባዊ የመን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የታሰሩ 3 ሺህ ስደተኞች እንዲለቀቁ በቅርቡ ጠይቋል። አብዛኛዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት ስደተኞችም ኢትዮጵያውን ናቸው። ስደተኞቹ የታሰሩት በኤደንና ላህጅ በተባሉ ከተሞች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ  2500 የሚሆኑት ስደተኞች ኤደን በሚገኝ አንድ ስታዲየም ውስጥ ታጉረው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ ኮሌራና ሌሎች መሰል ተላላፊ በሽታዎች ከተከሰቱ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ብዙዎቹ ስደተኞች ለእስር የተዳረጉት በደላሎች ተታለው መደበኛ ባልሆነና  በህገ ወጥ መንገድ ከአገራቸው በመውጣታቸው ነው፡፡ መደበኛ ወይም ህጋዊ ያልሆነ የስደት መንገድን መምረጥ የሚያስከትለውን መከራ ለአመታት ለእስር ተዳርገው፣ ከተሰቃዩት ከእነዚህ እስረኞች ታሪክ ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡ እኛም፤ የእነዚህ ስደተኞችን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለውን መደበኛ ያልሆነውን የስደት መንገድ በመከላከሉ ረገድ፣ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል እላለሁ፡፡

Read 2461 times