Tuesday, 02 July 2019 12:11

“የኢንቨስትመንት አዋጁን የሚፃረር ተግባር እየተፈፀመብን ነው” - ባለሀብቶች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)


  • “ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች፣ ዶላር አያመነጩም፤ የውጭዎቹ ዶላር ይዘው ነው የሚመጡት” ብሔራዊ ባንክ
  • “ዜግነትን መሰረት ያደረገ የብድር መመሪያ ለአገር ውድቀት ነው” የግል ባንክ ፕሬዚዳንት
  • የንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለስልጣን ብሔራዊ ባንክን ማብራሪያ ጠየቀ
        


      ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን አገር ውስጥ በማምረት የሚተኩ አገር በቀል ባለኢንዱስትሪዎች፤ የአገሪቱን ህግና የኢንቨስትመንት አዋጁን የሚፃረር ተግባር እየተፈፀመብን ነው ሲሉ ማማረራቸውን ተከትሎ፣ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን፣ ብሔራዊ ባንክን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡  
ባለሀብቶቹ ብሔራዊ ባንኩ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መመሪያዎች አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ከጨዋታ ውጭ እያደረገን በመሆኑ፣ ከአቅም በታች ለማምረት ብሎም ፋብሪካዎቻችንን ለመዝጋት የሚያስገድድ ሁኔታ ላይ አድርሶናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ኢትዮጵያውያን ባለ ፋብሪካዎች፤ ከአቅራቢዎች የሚገኝ የዱቤ ሽያጭ ለውጭ አገር ኢንቨስተሮች በብሔራዊ ባንክ ተፈቅዶ፣ ለእኛ ለአገር በቀሎቹ መከልከሉ፣ የአገሪቱን የኢንዱስትሪ የልማት ስትራቴጂና የኢንቨስትመንት አዋጁን የሚቃረን እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን ባይተዋርና ሁለተኛ ዜጋ የሚያደርግ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ለብሔራዊ ባንክ ብናመለክትም ምላሽ ባለማግኘታችን ለችግር ተዳርገናል፤ በአገር ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ባንኩ በጥቅምቅት 2010 ዓ.ም ባወጣው የውጭ አቅራቢዎች ሽያጭ መመሪያ፤ FXD/47/2017 የውጭ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጎ፣ የአገር ውስጦቹን ከስራ የሚያስወጣና  በአገራቸው የበይ ተመልካች የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የአገርን ኢኮኖሚ ያቀጭጫል ብለን ደጋግመን አቤት ብንልም ሰሚ በማጣታችን እጅግ ከአቅም በታች እያመረትን እንገኛለን፤ ፋብሪካዎቻችንንም ለመዝጋትና ሰራተኞቻችንን ለመበተን በሂደት ላይ ነን ብለዋል፡፡
በዚሁ መመሪያ መሰረት፤ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ  የውጭ ኢንቨስተሮች በውጭ አቅራቢዎቹ ከብሔራዊ ባንክ ለግል ንግድ ባንኮች በማጻፍ፣ ከኢትዮጵያ የዶላር ክምችት የሚከፈላቸው ልዩ የትዕዛዝ ደብዳቤ የሚያስፈልጋቸውን ጥሬ ዕቃ እያስገቡ ማምረት ሲችሉ፣ በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ግን ከገዛ አገራቸው ቋት የውጪ ምንዛሪ ዕድል በመነፈጋቸው ስራቸው መስተጓጎሉን ገልጸዋል፡፡
በአንድ የህትመት ሚዲያ ላይ በወጣ ዘገባ መሰረት፤ ከውጭ ሻጭ በብድር ደረጃ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ኢንቨስተሮች እስካሁን 5 ቢሊዮን ዶላር ሲፈቅድ, በአጠቃላይ አገር በቀል ባለፋብሪካዎች ኤልሲ የሚከፈት 300 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መፍቀዱ በአገር ውስጥ ባለኢንዱስትሪዎች ላይ ያለውን ጫና በቂ ማሳያ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
የአቅራቢዎቹ ብድር (Suppliers credit) መመሪያ ጉዳት አልበቃ ብሎ በቅርቡ ደግሞ አሁንም በዜግነት ላይ የተመሰረተ በዓይነት የመበደር መመሪያ ቁጥር FXD/61/2019 ጉዳይ ይበልጥ አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ፈተና ውስጥ የሚከት እንደሆነ ባለሃብቶቹ ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ባለ ፋብሪካዎች ብሔራዊ ባንኩ በተደጋጋሚ ብድር እንዲፈቅድ ሲጠየቅ፤ “ብድር እንዲፈቀድላችሁ ከፈለጋችሁ ዕቃ ኤክስፖርት አድርጋችሁ ዶላር ማምጣት አለባችሁ” የሚል ምላሽ እንደሚሰጥ፣ በሌላ በኩል ለውጭ ባለሀብቱ ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ወረፋ ከአገሪቷ ቋት ለባንኮች በሚፃፍ የትዕዛዝ ደብዳቤ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡  አሁንም የወጣው በዓይነት የመበደር (Credit in Kind) አዋጅ እኛን ያገለለና የውጭ ኢንቨስተሮችን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገ በመሆኑ፤ መንግስት እልባት ካልሰጠው፣ አገር ተረካቢ ባለ ኢንዱስትሪዎችን ማየት የሚናፈቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉ ያሳስባሉ፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ የውጭ ኢንቨስተሮች የተበደሩትንም እዳ የምትከፍለው ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ አገሪቱ ካፈራችው የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለሚከፈል ዕዳ ኢትዮጵያውያን አምራቾች ብድር መነፈጋቸው ትልቅ በደል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ያነሰ አቅም ያላቸው የውጭ ኢንቨስተሮች ሁሉ በካሽም ሆነ በዓይነት ያለምንም ወረፋ በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ብድር እየተፈቀደላቸው ሳለ ኢትዮጵያውያን የሆኑና በትልቅ አቅም የሚንቀሳቀሱ ግን እድል እንደተነፈጋቸው ነው ባለሀብቶቹ የሚገልፁት፡፡ በሌላ በኩል፤ ብሔራዊ ባንኩ  አገሪቱ ያለባትን ዕዳ ከፍላ ባልጨረሰችበት ሁኔታ ተጨማሪ አዳዲስ ባለሃብት  በማስገባት የውጭዎቹን ሲንከባከብ፣ አገር በቀሎቹ  በአገር ግንባታና ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ሚና ተዘንግቶ ከጥቅም ውጭ መደረጋቸው የሚጎዳው ድርጅቶቹን ብቻ ሳይሆን አገርና ወገንንም በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ የፋይናንስ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ባለ ኢንዱስትሪዎች፤ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ከኢንቨስትመንት አዋጅ ጋር የሚቃረን መሆኑን የአዋጅ ቁጥሩን ጠቅሰው ይሞግታሉ፡፡
በመስከረም 2005 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2005 ላይ “ባለሀብት ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገ የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት ማለት  ነው“ በማለት በአንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ አራት ላይ አመልክቷል፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ደግሞ ማንኛውም ባለሃብት ከውጭ የተበደረውን የውጭ ምንዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት እንዲያስመዘግብ ያዛል እንጂ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብት የሚል መከፋፈል ውስጥ የገባ ባለመሆኑ፣ ብሔራዊ  ባንክ በ2010 ባወጣው የውጭ አቅራቢዎች ብድርም (Suppliers credit) ሆነ በቅርቡ በወጣው በዓይነት የመበደር (Credit in Kind) መመሪያ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ላይ የተጣለው እገዳና አግላይነት በአስቸኳይ ተነስቶ እኩል ተጠቃሚ መሆን አለብን በማለት ይጠይቃሉ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢንቨስትመንት አዋጁ አንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ የውጭ ባለሀብት ስራውን ለማንቀሳቀስ የውጭ ምንዛሬ ሂሳብ መክፈት እንደሚችል ከመደንገግ ውጭ የአገር ውስጥ ባለሀብት ከውጭ እንዳይበደር አንዳችም ክልከላ እንዳልተቀመጠ ጠቁመው፤ ባጠቃላይ ብሔራዊ ባንክ በአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ላይ ይህን ሁሉ ጫናና ኩርኩም የሚያሳርፍበት ምክንያት እንዳልገባቸው ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የግል ባንክ ኃላፊዎች፣ የብሔራዊ ባንክን መመሪያና በአገር በቀል ባለሀብቶች ላይ የሚያደርሰውን ጫና አጥብቀው እንደሚቃወሙት ይገልፃሉ፡፡ የአገር በቀል ባለሀብቶችን ቅሬታና አቤቱታ እንዲሁም ምሬት ተገቢነትም ያምኑበታል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የግል ባንክ ፕሬዚዳንት በሰጡት አስተያየት፤ “የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያላቸውን ጥሪት አሟጠውና ተበድረው ነው ፋብሪካ ያቋቋሙት፤ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀጥሉ ከተፈለገ መደረግ አለበት ብለን እኛም የጠየቅናቸው የአቅራቢዎቹን ብድር (Suppliers credit) መፍቀድ ያለበት የውጭ ምንዛሪውን የሚከፍለው ባንኩ ነው እንጂ ብሔራዊ ባንክ ፈቃጅና ከልካይ መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡ እኝሁ ኃላፊ ጨምረውም፤ “እርግጥ አንዳንዴ ብሔራዊ ባንኩ ለውጭዎቹ ዶላር እንዲፈቀድ ደብዳቤ ቢፅፍላቸውም የለንም ብለን የምንከለክልበት ወቅት አለ፤ ከሌለን እንዴት  መክፈል እንችላለን” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
የአገር ውስጥ ባለ ኢንዱስትሪዎች ጥሪታቸውን አሟጠው ተበድረውና ንብረታቸውን አስይዘው እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ እናንተ ባገኛችሁ ጊዜ ዶላር አግኙ በማለት አገር በቀል ባለ ኢንዱስትሪዎችን ማግለል በጣም ጎጂ ነው ይላሉ - የግል ባንኩ ፕሬዚዳንት:: በአንፃሩ ገና ያኔ ከውጭ ለኢንቨስትመንት ስራ የሚሆን ካፒታል ለማስመዝገብ 500 ሺህም ሆነ አንድ ሚሊዮን ዶላር ይዞ ለመጣ የውጭ ኢንቨስተር  ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና መጉላላት በተደጋጋሚ የውጭ አቅራቢዎች ብድር (Suppliers credit) እንደልብ መፍቀድ ፍትሐዊነቱ አይታየኝም፤ እኛም መመሪያው ሲወጣ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጮኸንላቸዋል የሚሉት የባንኩ ሬዚዳንት፤ ይህንንም የምናደርገው በዜግነት ላይ ብቻ በመመስረት ኢትዮጵያውያንን ለመጥቀም ሳይሆን ጉዳዩ ፍትሐዊ ውድድርን ስለሚጎዳ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ባለ ኢንዱስትሪዎች ደንበኞቻችን ስለሆኑና የባንኩም ዋና ተበዳሪ በመሆናቸው ጭምር ነው ይላሉ፡፡
የውጭ ኢንቨስተሮች ከውጭ የሚበደሩትን የውጭ ምንዛሬ ብድር የሚከፍለው ማነው የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው እኚሁ የባንክ ፕሬዚዳንት ሲመልሱ፤ ይህንን ጉዳይ አንስተን የብሔራዊ ባንክ ገዢዎች ባሉበት ነግረናቸዋል ይላሉ፤ እዳውን የምትከፍለው ኢትዮጵያ ነች ሲሉም ያክላሉ፡፡
“የኛ አገር ባለሀብቶች እዳውን አገራቸው እየከፈለች መብቱን ተከልክለው እንዳይበረቱና እንዳይሰሩ እድሉን ተነፍገዋል” የሚሉት እኚሁ የባንክ ፕሬዚዳንት፤ “የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚሰሩት ከባንኮች ተበድረው በመሆኑ የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት  ሰርተውና አምርተው ብድራቸውን ካልከፈሉ የእኛም አበዳሪ የባንኮች ብድር ይበላሽብናል፤ በዚህም ጊዜ ባንኮች የባለኢንዱስትሪዎችን ንብረት ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ ሁሉም ሻጭ ከሆነ የሚገዛውስ ማን ሊሆን ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ “ልዩ ተጠቃሚ የሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያጋብሱትን ትርፍ የሚልኩት ወደ ውጭ ወይም ወደ አገራቸው አይደለም ወይ” በማለትም ይጠይቃሉ፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊ፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ከባለኢንዱስትሪዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመው፤ አገሪቱ ላይ ባለው አጠቃላይ የዶላር እጥረት ምክንያት ችግሩ መከሰቱን ይገልፃሉ፡፡ “በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ አጠቃላይ የወጭ ንግድ ወድቋል፣ከውጭ የሚጠበቀውም ረሚታንስ እየመጣ አይደለም፤ ስለዚህ ለውጭ ኢንቨስተሮች ቅድሚያ የሚያሰጠው ጉዳይ ኢንቨስትመንታቸውን በውጭ ምንዛሬ ይዘው ስለሚመጡ ነው” ሲሉ የባንኩ ኃላፊ ያስረዳሉ፡፡ በአንፃሩ፤ የአገር ውስጥ ባለፋብሪካዎች ግን ኤክስፖርት አያደርጉም፤ የውጭ ምንዛሬም አያመነጩም፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታና አገሪቱ ውስጥ ባለው የዶላር እጥረት ሳቢያ ምን ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዶላር አመንጪ ባለመሆኑ የሚገኘውን ዶላር እንዴት አብቃቅቶ ማከፋፈል እንዳለበት ነው የሚጨነቀው ብለዋል - የብሔራዊ ባንክ ኃላፊው፡፡
የአገር ውስጥ ባለ ኢንዱስትሪዎች ልክ እንደ ውጪዎቹ አምራቾች ሁሉ ገቢ ምርት በአገር ውስጥ ምርት እየተካንና ለብዙ ሰው የስራ ዕድልን እየፈጠርን እንዴት ቅድሚያ አይሰጠንም ማለታቸው ትክክለኛ መከራከሪያ ነው፤ ሆኖም ባለው የዶላር እጥረት ምክንያት ለውጪዎቹ ብቻ ኢትዮጵያ ከምትከፍለው የአቅራቢዎች ብደር ፈቅደናል፤ ይላሉ ኃላፊው፡፡
ይሁን እንጂ የግል ባንኩ ፕሬዚዳንት የብሔራዊ ባንክ ኃላፊውን አስተያየት አይቀበሉም፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ከውጭ ዶላር ይዘው መጡ ከተባለ ስንት ዶላር ይዘው መጡ? መቼ ይዘው መጡ? አሁን የሚፈቀድላቸውስ የውጭ ምንዛሬ ስንት ነው? በየስንት ጊዜውስ እየተፈቀደላቸው ነው? ማዘዝ ያለበትስ ማነው? አላማውስ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው ይላሉ - ፕሬዚዳንቱ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዶላር ያመጣሉ ብሎ የሚሞግተው እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች ድርጅታቸውን ሲያቋቁሙ ለካፒታል ማሟያ ያመጧትን የውጭ ምንዛሬ በመጥቀስ ይመስለኛል ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት፤ “ይህ ደግሞ አንድ ጊዜ የመጣ፣ በጣም አነስተኛና ወጥ ባለመሆኑ ጥሬ ዕቃ ማስመጫ የውጭ ምንዛሬ ብድር ለነሱ ብቻ በተደጋጋሚ መፍቀዱ ፍትሐዊነት የሚጎድለው ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ አመክንዮም የሌለው ነው” በማለት ይከራከራሉ፡፡ እንደው ለመሆኑ ጥቁር ገበያ ይህን ያህል ያደገው ለምንድነው? የሚለውም መጠናት አለበት ይላሉ - የግል ባንኩ ፕሬዚዳንት፡፡
“መመሪያ ለማውጣት ከመቸኮል በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ቢመካከሩ፤ቢወያዩና የሃሳብ ግብአት ቢሰበስቡ ይሄ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ነበር የሚሉት እኚሁ ፕሬዚዳንት፤ እንደውም የብድሩ ጉዳይ ለባንኮቹ ቢተው ኖሮ ካለኝ እፈቅድለታለሁ ከሌለኝ የለኝም እላለሁ፤ የውጭ ወይም የአገር ውስጥ ባለሀብት የሚለው አድሎም አይፈጠርም ነበር” ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በአዋጅ ቁጥር 813/2006  የተቋቋመውና ማንኛውንም ሀቀኛ ያልሆነ አሳሳች ወይም የንግድ ጥቅምን የሚጎዳ ተግባር እንዳይፈጠር ወይም እንዳይፈፀም፤ሲፈፀምም በተጠረጠረው ድርጅት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ስልጣን የተሰጠው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ባለስልጣን በበኩሉ፤ ከአገር ውስጥ ባለ ኢንዱስትሪዎች በተደጋጋሚ የቀረበለትን አቤቱታ ምክንያት በማድረግ  በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ብሔራዊ ባንክን ግንቦት 29 ቀን 2011 በደብዳቤ መጠየቁን ይገልፃል፡፡
በባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልቃድር ኢብራሂም በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፤ በእርግጥም በባለ ኢንዱስትሪዎች ተደጋጋሚ አቤቱታ የንግድ ውድድርን የሚጎዳ በመሆኑ በዚሁ መሰረት ማብራሪያ እንዲሰጥ ለብሔራዊ ባንክ  መስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ መፃፉን አስታውሰው፤ ሆኖም ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱንና  ምላሽ እየጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን ብሔራዊ ባንክን የማዘዝ ስልጣን መስሪያ ቤታችን ባይኖረውም ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ በህጉ ላይ ለሚመለከተው አካል አቅርበን ውይይት እንዲደረግበትና መሻሻል ያለበትም ከሆነ እንዲሻሻል እንጠይቃለን ብለዋል -  አቶ አልቃድር፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትንት ኮሚሽንና የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባለመሳካቱ ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ በማንኛውም ጊዜ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን ግን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡

Read 2739 times