Print this page
Tuesday, 02 July 2019 11:54

“አዳዲስና ወሳኝ ምዕራፎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለመፍጠር አስበናል”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)


     “ኮለኔል አወል አብዱራሂም በኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳደር ከፍተኛ ልምድ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ባለፈው አንድ አመት በኢትዮጵያ እግር ኳስ
ፌደሬሽን ውስጥ በምክትል ፕሬዝዳንትነትና በሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢነት እያገለገለ ነው፡፡ ስፖርት አድማስ ከኮለኔል አወል ጋር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ ሁለተኛው ክፍል እነሆ ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡”
 
     የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የመጀመርያ የስራ ዘመኑን እንዴት አሳለፈ?
ይህ የፌደሬሽን አስተዳደር አዲስ እንደሆነ ይታወቃል:: ከጠቅላላ ጉባዔው በተሰጠው  ኃላፊነት ሲሰራ ገና አንደኛ ዓመቱ ቢሆንም፤ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ በሌላቸው፤ ግምታዊ በሆኑ አስተያየቶች እንዲሁም ሚዛናዊ ባልሆኑ  ትችቶች ሲብጠለጠል ነው ያሳለፈው፡፡ አንዳንዴ የስፖርት ሚዲያዎችን ስትሰማ የቀድሞው ፌደሬሽን የተተቸባቸው አጀንዳዎች የአሁኑን አመራር ሲያስወቅሱ ነው፡፡ ከሶስትና አራት ዓመት በፊት የተፈጠሩ ችግሮችን  እየጠቀሱ ማጥላላትም ይስተዋላል፡፡ ህገወጥ አስተያየቶች ይበዛሉ፡፡ ገና በመጀመርያው የስራ ዘመን ላይ ፌደሬሽኑን በሆነ ባልሆነው ጥፋተኛ ማድረግ፤ በኃላፊነቱ ላይ እንደሌለ መቁጠር በፍፁም ልክ አይደለም፡፡ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው አመራር ፌደሬሽኑን ለ4 ዓመታት እንዲያገለግል ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በአጠቃላይ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የህዝብ ሃብት በመሆኑ እንደተቋም ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በሃላፊነቱ ላይ የምንገኝ አመራሮች  ከየአቅጣጫው የትችት ማዕበሎች በመብዛታቸው አልተናወጥንም፡፡ ከያዝናቸው የለውጥ ሂደቶች አንደናቀፍም፡፡ በአስተዳደራችን ላይ የሚቀርቡ ገንቢ አስተያየቶች በመለየት፤ በምንከተላቸው የለውጥ እና የእድገት አቅጣጫዎች ዙርያ የስፖርት ቤተሰቡንና ባለድርሻ አካላቱን በማሳመን፤ የተዛቡ እና ፈር የሳቱ ትችቶችን በትክክለኛ እውነታዎች በመግለፅ እየሰራን  ነው፡፡
ባለፈው 1 ዓመት ውስጥ  የተለያዩ ስራዎችን ስናከናውን ነበር፡፡ ለፌደሬሽኑ ግዜ ከማይሰጡ ተግባራት መካከል ለምሳሌ ብንናነሳ ውድድሮችን መምራት ዋንኛው ነው፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የምናካሂዳቸውን ውድድሮችን የወጣላቸውን መርሃግብር ጠብቀው እንዲሄዱ ብዙ ጥረቶች አድርገናል፡፡ በፌደሬሽኑ ስር የሚካሄዱ ሁሉንም ውድድሮች እስከ ሰኔ 30 ለመጨረስ አቅደን ነበር:: ዋናው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሊጠናቅቅ የሶስት ሳምንት ግጥሚያዎች ይቀሩታል፡፡ የሴቶች ሊግ በግዜው የተገባደደ ሲሆን፤ በከፍተኛ ሊጉ የቀሩት የ1 ሳምንት ግጥሚያዎች ናቸው፡፡ ብሄራዊ ሊጉም እያለቀ ነው፡፡ በርግጥ  ሁሉንም ውድድሮች በግዜያቸው ለመጨረስ የነበሩት ፈተናዎች ቀላል አልነበሩም፡፡ በተለይ በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች በውድድር ዘመኑ ላይ በየክልሉ  በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ያንን በመቋቋም ስንሰራ መቆየታችን የሚያስደንቅ ነው፡፡ የነበሩት ችግሮች የተለያዩ የጨዋታ መርሃ ግብሮችን አስተጓጉለዋል፡፡ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የገቡ ክለቦች የተመደበላቸውን ግዜ ጠብቀው እንዲካሄዱ ሊግ ኮሚቴው ያደረገው ጥረት ሊደነቅ ይገባል፡፡ የሊግ ኮሚቴው አባላት መደበኛቸውን ስራቸውን በመበደል ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ውጤታማዎች ሆነዋል፡፡ በውድድሮች ላይ ስፖርታዊ ጨዋነት ለማስፈን ዓመቱን በሙሉ ከተለያዩ ባለድረሻ አካላት ጋር በየጊዜው እየተገናኘን መመካከራችን አስፈላጊ ነበር፡፡ በየክልሉ በታዩ የደጋፊዎች ረብሻዎች እና የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ሊጉ እንደሚቋረጥ ወይም እንዲቋረጥ ይነገርና ግፊት ይደረግም ነበር፡፡ ይህን  ተቋቁመን የውድድር ዘመኑን ለመጨረስ ከጫፍ በመድረሳችን ደስተኞች ነን፡፡ ይህም የፌዴሬሽኑ አመራር ውድድሮችን በመምራት የተሰጠው ሃላፊነት በብቃት መወጣቱን ያረጋግጣል፡፡
የውድድር ዘመኑን አጨራረስ ከውዝግቦች የፀዳ ለማድረግ  ምን እየሰራችሁ ነው፤ የተለየ ዝግጅትስ አድርጋችኋል?
አዳዲስ ክለቦች የዋንጫ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው፤ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ግጥሚያዎች ወሳኝ መሆናቸው ለዘንድሮው ሊግ ድምቀት ፈጥሮለታል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ባለፉት 5 እና 6 የውድድር ዘመናት ለዋንጫው ከ3 እና 4 ክለቦች መፎካከራቸው በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ የሊጉ ሻምፒዮናነትም አዳዲስ ክለቦችን ማግኘቱ ይስተዋል፡፡ ዘንድሮ ይህ ሁኔታ መቀጠሉ ስኬት እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ አጨራረሱ ውበት አለው፡፡ ስለሆነም የፌደሬሽኑ አመራር በሊግ ኮሚቴው የውድድር ዘመኑን አጨራረስ ከውዝግብ የፀዳ ለማድረግ በማሰብ ልዩ ዝግጅት አድርጓል፡፡ በቀሩት የሶስት ሳምንታት ግጥሚያዎው ውድድሮችን በጥንቃቄ ለመምራት ነው፡፡ ለዋንጫ የሚፎካከሩ ሁሉም ክለቦች ቀሪ ጨዋታዎችን በተመሳሳይ ሰዓት እንዲያደርጉ እንፈልጋለን፡፡ ላለመውረድ የሚጫወቱትንም በተመሳሳይ ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ በወሳኞቹ ጨዋታዎች እስከ 3 ካሜራዎች እና ታዛቢዎችን ወደ 3 ከፍ በማድረግ በውድድሮቹ ላይ ትኩረት ለማድረግ ነው የምንፈልገው፡፡ ዓለም በሚያውቃቸው እና በሚከተላቸው ህግና ደንቡ በሚፈቅደው የጥንቃ ደረጃዎች መሰረት ነው፡፡ እግር ኳሳዊ ያልሆኑ የደንብ እና የስነምግባር ጥሰቶች ካጋጠሙ ፌደሬሽኑ ቆራጥ እርምጃዎችንም ይወስዳል፡፡
ከውድድሮች ባሻገር ፌደሬሽኑ ለዘለቄታው በማሰብ ያከናወናቸው ተግባራት አሉ?
የፌደሬሽኑን ዘመናዊ እና ጠንካራ አደረጃጀት በመመስረት ዘለቄታዊ ውጤቶችን ለማግኘት  የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች  ጥናቶችን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መተዳደርያ ደንቦች ላይ ያሉትን ግድፈቶች፤ ጉድለቶች እና እንቅፋቶች ለማስተካከል ልዩ ትኩረት በማድረግ ሰርተናል፡፡ በእኔ ሰብሳቢነት 12 አባላት ያሉትን ኮሚቴ በማቋቋም የተለያዩ ጥናቶች አድርገን ወሳኝና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን እያዘጋጀንም ነው::  የውድድር ዘመኑን ከጨረስን በኋላ ዓመታዊውን ጠቅላላ ጉባዔ ስናደርግ ምክረ ሃሳቦቹንና የደንብ ማሻሻያዎችን ለአባላቱ በማቅረብ እንወያያለን፡፡ በርግጠኝነት በቀጣዩ የውድድር ዘመን አዳዲስና ወሳኝ ምዕራፎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለመፍጠር አስበናል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት አስበን በቀረፅናቸው አጀንዳዎች ትልልቅ እርምጃዎች እንደሚወስን ተስፋ አድርገናል፡፡
የክለቦች የሊግ ውድድር በምን አይነት መዋቅርና ቅርጽ ይቀጥል? እንዴት  ይመራ? በሚሉት ሁኔታዎች በየዓመቱ የሚነሱት የክርክር አጀንዳዎች ለአንዴና መጨረሻ ግዜ እልባት አያገኙም ወይ?
ባሳለፍነው አንድ ዓመት ሰፊ ግዜ ሰጥተን ካደረግናቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሊጉ መዋቅርና ቅርፅን የሚመለከቱ ሁኔታዎች ይገኙበታል:: ክለቦች የሊግ ውድድራቸውን  በኩባንያ ወይም በቦርድ ያስተዳድሩ በሚሉና መሰል አጀንዳዎች ጥናቶችን በከፍተኛ ባለሙያዎች በመታገዝና ዓለም አቀፍ ልምዶችን በጥልቀት በመመርመር ሰርተናል፡፡ የጀመርነውን  የውድድር ዘመን ስንጨርስ በዚህ አቅጣጫ ያካሄድናቸውን ጥናቶች በተደራጀ መልኩ ለባለድርሻ አካላቱ ለማቅረብ ሙሉ ዝግጅት አለን፡፡
በነገራችን ላይ ስለ ሊጉ መዋቅርና ቅርፅ   በአንዳንድ ሚዲያዎች ውይይቶች ሲደረጉ በሚሰጡ አስተያየቶች በጣም እገረማለሁ፡፡ የሊጉን አካሄድ በተመለከተ  የ2011 ፕሪሚዬር ሊግን  ሳይጀመር ፌደሬሽኑ ክለቦችን ሰብስቦ ውድድሩን እንዴት እንምራው በሚል መመካከሩ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ክለቦች በሙሉ ድምፅ የተስማሙበት ሶስት አባላት ከክለብ፤ 3 አባላት ከፌደሬሽን እንዲሁም ሰብሳቢ ከስራ አስፈፃሚ  በድምፅ እንዲሁም ስምንተኛው አባል ከፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት ያለድምፅ ተወክለው ውድድር የሚመራ የሊግ ኮሚቴ ተቋቁሟል:: የውድድር ዘመኑን ስናካሂድ የቆየነውና የምንጨርሰው  በሊግ ኮሚቴው በመመራት ነው፡፡ ታድያ ይህ የውድድር ዘመን ሳያልቅ የሊጉ መዋቅርና ቅርፅ  ተገቢ እንዳልሆነ መተቸት ምን ይሉታል? አዲስ ለውጥ ለማድረግ የሚቻለው የውድድር ዘመኑ ሳይጀመር እንጅ በመካሄድ ላይ በሚገኝ ውድድር እንዴት ይሆናል፡፡ በሊጉ መዋቅርና ቅርፅ ላይ ለመወሰን የጀመርነው የ2011 ውድድር ዘመኑ ማለቅ አለበት፡፡ በ2012 የውድድር ዘመን መግቢያ ላይ የሚነሳ ጥያቄ መሆን ነበረበት፡፡ በነገራች ላይ ውድድሮችን እያካሄድንም ለሁለት ጊዜያት ክለቦችን ለስብሰባ በመጥራት በዚህ አጀንዳ ላይ ምክረ ሃሳቦችና  እቅዶችን ለውይይት በማቅረብ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ለመገናኘት ሞክረናል፡፡ ክለቦች በተለያየ ምክንያት በእነዚህ ሁለት መድረኮች ተሟልተው ባለማግኘታቸው ያሰብነውን ግብዓት አላገኘንም እንጅ፡፡  በፌደሬሽኑ በኩል በሊግ ካምፓኒው ምስረታ ላይ የምንሰራቸውን ተግባራት ውድድር እየመራን ነው በሚል ምክንያት ወደ ጎን አላደረግናቸውም:: አስቀድሜ እንደገለፅኩት የተለያያዩ ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመንተራስ እንዲሁም በከፍተኛ ባለሙያዎች ጥናቶችን በመስራት ተዘጋጅተንበታል::  የ2011 የውድድር ዘመን እንዳለቀ ክለቦች ለዚሁ አጀንዳቸው ምክር  እንዲያደርጉ በጠቅላላ ጉባኤው ከዚያም በፊትም ይጠራሉ፡፡ በሊጉ መዋቅር ቅርፅ እና ይዘት አማራጮቻቸውን አቅርበው ሰፊ ውይይቶች ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡  የክለቦች በመላው አገሪቱ ተዟዙሮ በመጫወት ዙርያ፤ እና ሌሎች  አስተያየቶች የየራሳቸው አቋምን ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ክለቦች ምክረ ሃሳቦቻቸውን አቅርበው ፌደሬሽኑም ባዘጋጀው የሊግ አደራጃጀት ላይ ተምክሮ ነው የውድድር ሂደቱ መወሰን ያለበት፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ መተዳደርያ ደንቡን መሰረት በማድረግም መፅደቅ ይኖርበታል፡፡ የሊጉ አደረጃጀት በዚሁ መሰረት ተወስኖ በአዲስ መዋቅርና ቅርፅ የ2012 የውድድር ዘመንን እንቀጥላለን ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡
አዲሱ የሊግ አደረጃጀት ከሚያስገኛቸው ልዩ ውጤቶች የቱን ትጠቅሳለህ? የክለቦች የፋይናንስ አቅም በማሳደግ ምን መሰራት አለበት?
የሊግ አደረጃጀቱ ለክለቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የገቢ ምንጮችን ያመጣል፤ ስፖንሰሮችን ይስባል ብለን የምንጠብቀው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ አሁን በነፃ ነው የሚካሄደው:: ስለዚህም በሊጉ የሚገኙትን የተለያዩ የገቢ ምንጮች በማስፋት ክለቦች በፋይናንስ አቅማቸው የሚጠናከሩበትን እቅድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዤ የማነሳው የስታድየም መሰረተልማቶችን ነው:: እንደሚታወቀው በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦችና አንጋፋዎቹም ስታድዬም የላቸውም፡፡ ከክልል ስታድዬሞችን ተውሰው ጨዋታዎች የሚያደርጉ ክለቦች ከአንድ ጨዋታ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ሲያስገቡ እየተመለከትን ነው፡፡ በዚህ በኩል ያለውን የገቢ አቅም ማስተዋል ነው፡፡ ተመልካቹ ወደ ስታድዬም ይገባል፡፡ የመግቢያ ዋጋውን በመጨመርና ስፖርታዊ ጨዋነት በማስተካከል ብዙዎቹ ክለቦች ትርፋማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ 20ሺ እና 30ሺ ተመልካች የሚይዙ ቀለል ያሉ ስታድዬሞችን በመስራት ክለቦች መሰረተልማታቸውን እንዲያሳድጉ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ከፋይናንስ አቅማቸው ጋር በተያያዘ የተጋረጡባቸውን አደጋዎች ማስተዋል ይገባል፡፡ የውድድር ፎርማት መቀየር ብቻ መፍትሄ ላይሆን ይችላል፡፡ ዘላቂ መፍትሄው የሚገኘው ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን በሚያሰፉበት አቅጣጫ አተኩረው ሲሰሩ ነው፡፡


Read 4539 times