Saturday, 22 June 2019 11:24

ከመጠን ያለፈ ውፍረትና እርግዝና ሲጣመሩ የሚያስከትሏቸው ችግሮች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የአንዲት ሴት የሰውነት ክብድት ከመጠን ያለፈ የውፍረት ልኬት ውስጥ በገባባት ወቅት ብትጸንስ፣ እርሷም ላይ ሆነ ጽንሱ ላይ የጤና እክል ሊደርስ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎችና የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ያመላክታሉ፡፡
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ሲኖር አንዲት ሴት ሊኖራት የሚችለውን ለጽንስ ዝግጁ የሆነን እንቁላል የማኳረት ሂደቷንም ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ ይህ ተጽእኖ የሚፈጠረው ጽንስን ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከሩ ሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ቀደም አለምንም ችግር እንቁላል የማኳረት ሂደታቸውን ተከትሎ ጸንሰው የወለዱ ሴቶች ላይም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች ዳግም ለመጸነስ ባቀዱበት ጊዜ ሰውነታቸው ላይ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ካለ ውፍረቱ የሴቶቹ ማህጸን የተለመደውን እንቁላል የማኳረት ሂደቱን በማስተጓገል ጽንሱ እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡
ይሁንና የሴቷ ማህጸን ችግሩን ተቋቁሞ ለጽንስ የሚያስፈልገውን እንቁላል በተገቢው መልክ ማኳረት ከቻለና ጽንሰ ቢፈጠር የሴቷ የእርግዝና ጊዜ በተለያዩ ውስብስብ በሆኑ የጤና እክሎች የተሞላ ይሆናል:: ከመጠን ያለፈ ውፍረት እርግዝናን ሊያስተጓጉልና ውስብስብ የጤና እክል ሊፈጥር የሚችልባቸው ውስብስብ የጤና እክሎች አሉ፡፡ ከነዚያም ውስጥ አንዱ የጽንስ መጨናገፍ ሲሆን ሌላው ደግሞ የጽንሱ በማህጸን ውስጥ እያለ ህይወቱ አልፎ መወለድ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዘው በዋነኝነት የሚነሱ ሌሎች የጤና ችግሮች ደግሞ የስኳር ህመም፣ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊትና የኩላሊት አሊያም የሌሎች የውስጥ አካሎች ሥራ መበላሸት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእነዚህ የጤና ችግሮች ብቻ የማይገታው ውስብስብ የእርግዝናና የውፍረት ጥምረት የሚያስከትለው የጤና እክል፣ እርግዝናው በቀጠለባቸው ጊዜያቶች ከልብ ጋር ተያያዥ የሆኑ የጤና ችግሮችም ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪም ጽንሱን የተሸከመችው እናት በተኛችበት ትንፋሽ የመቋረጥ አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል:: እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁማ እናትየዋ የመውለጃዋ ጊዜ ከደረሰ በማህጸን የሚደረገውን ተፈጥሮአዊውን የመውለድ ሂደት ማከናወን ይሳናታል፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች እናትየዋን በቀዶ ጥገና ማዋለድ የሚገደዱ ሲሆን፣ በቀዶ ጥገናው አማካኝነት የሚኖረው ቁስልም ኢንፌክሽን ሊፈጥር ይችላል፡፡ በዚያም ብቻ አይቋጭም ቀዶ ጥገና ሲኖር ሊፈጠሩ የሚችሉ ሌሎች ውስብስብ ችግሮችም  ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
እስካሁን የተዘረዘሩት ውስብስብ የጤና እክሎች ባመዛኙ ጽንሱን የተሸከመችው እናት ላይ ያተኮሩ ናቸው:: ነገር ግን በውፍረት ላይ የሚደረብ ጽንስ እንደምንም ተሳክቶ መወለድ ከቻለ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈ ህጻን አማካይ ከሆነ የእድሜ አቻዎቹ ህጻናት የሰውነት ይዘት የበለጠና የወፈረ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የህጻኑ ሰውነት ውስጥ ገና ጽንስ እየነበር ከእናቱ የወረሰው የተከማቸ ስብ አለ ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ህጻኑ በለጋ እድሜው ከመጠን ባለፈ ውፍረት እንዲሰቃይ ይዳረጋል፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ አንዳንድ ህጻናት ሲፀነሱ ተፈጥሯዊ የሆነ አካላዊ ግድፈት ካላቸው እዚያው ማሕጸን ውስጥ እያሉ በአልትራሳውንድ ማሽን ታግዞ በቀላሉ አይቶ ችግሩን መለየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በማህጸን ውስጥ ያለ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለው ጽንስ ተፈጥሯዊ እክል ቢኖረው እንኳን በአልትራሳውንድ ማሽንም ቢታገዝም በቀላሉ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመከላከል አንዲት ሴት እርግዝናን ስታስብ ሰውነቷ ላይ ያለውን የስብ ክምችት ምን ያህል እንደሆነ ማጤን ይሮርባታል፡፡ በዚያም መሰረት መቀነስ የሚገባት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ካላት የተላያዩ መንገዶችን በመጠቀም መቀነስ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ሊዘነጋ የማይገባው አንድ ነጥብ ጽንስ ተፈጥሮ እስከሚወለድ ድረስ የሚመጣ የክብደት መጨመር ስላለ ነው፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች እንደሚሰጡት አጠቃላይ መመሪያ ግን፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላት ሴት ከጸነሰችና ጽንሱ አንድ ብቻ ከሆነ፣ እርግዝናዋ ተጀምሮ ወልዳ እስከምትገላገል ድረስ ልትጨምር የሚገባት የክብደት መጠን፣ ከአምስት ኪሎ ግራም እስከ ዘጠኝ ኪሎ ግራም ድረስ ብቻ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም የተጸነሰው ጽንስ መንታና ከዚያ በላይ እንደሆነ የሚያሳይ ከሆነ ደግሞ እናትየዋ መጨመር ያለባት ክብደት ከ11 ኪሎግራም እስከ 19 ኪሎ ግራም ድረስ ብቻ ሊሆን እንደሚገባው ሐኪሞች አበክረው የመክራሉ፡፡   
እጅግ የበዛ የሰውነት ውፍረት ያላቸው ሴቶች ቢያረግዙ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ውፍረት የመጨመር መመሪያዎች ባነሰ ውፍረት ቢጨምሩ፣ በማህጸናቸው የያዙት ጽንስ ተገቢ ከሆነው የጽንስ መጠን በላይ እንዳይሆን ይረዳዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመከረው ደግሞ በተቻለ መጠን ለከፍተኛ ውፍረት የተጋለጡ ሴቶች ካረገዙ፣ በህክምና ባለሙያ በመታገዝ እርግዝናው እንዳለ ውፍረታቸውን እንዲቀንሱ ማድረግ ነው፡፡ ቢሆንም ግን የተለያዩ የምርምር ውጤቶች እንደሚያመላክቱት በእርግዝና ጊዜ ውፍረት መቀነስ አሊያም እርግዝናው ከተፈጠረ በኋላ የሚኖረው የክብደት መጠን ያነሰ መሆን የተረገዘውን ህጻን ያለጊዜው እንዲወለድ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተወለደው ህጻን የሰውነት መጠን የጫጨም ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን በእርግዝና ጊዜ ከሚመከረው የክብደት መጠን በታች ከመጨመር ይልቅ፣ በዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች በመታገዝ ተገቢው የክብደት መጠን ብቻ እንዲጨመርና፣ ከዚያ ያለፈ አላስፈላጊ አሊያም ትርፍ የክብደት መጠን እንዳይጨመር ቁጥጥር ማድረግን ይመከራል፡፡
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ባለ ጊዜ ጽንስ የቋጠሩ ሴቶች በመጀመሪያው የእርግዝና ክትትላቸው ላይ የስኳር በሽታ መከሰት ወይም አለመከሰቱን የህክምና ባለሙያዎች ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈው የማዮ ክሊኒክ ሪፖርት ያመላክታል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ምርመራ የእናትየዋ የስኳር በሽታ ምርመራ ውጤት የስኳር በሽታን አመላካች ነገር የሌለው ከሆነ ምርመራው ዳግም ከ24 እስከ 28 ባሉት የእርግዝና ሳምንታት እንዲደገም ይመከራል፡፡ ይሁንና ገና በመጀመሪያው የምርመራ ውጤት ላይ እናትየዋ የስኳር በሽታን እንዳዳበረች የሚያመላክቱ ውጤቶች ካሉ፣ እርግዝናዋን የሚከታተሉ ሐኪሞች በእናትየዋ ደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠንን መከታተልና መቆጣጠር ይገባቸዋል፡፡
አንዲት እናት ከጸነሰች በኋላ የመጀመሪያውን የአልትራሳውንድ ምርመራ በደንቡ መሰረት የምታደርገው ከ18 እስከ 20 ባሉት የእርግዝና ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው:: ይህ የምርመራ አይነት በዋናነት የሚደረገው የጽንሱን አካላዊ ቅርጽን ለመከታተል ነው፡፡ የአልትራሳውንዱ ምርመራ በዚህ ጊዜ የሚደረገው በማሽኑ ታግዞ ማህጸን ውስጥ ያለውን የጽንስ ሁኔታ ለመከታተል እናትየዋ ሆድ ላይ የሚገኘው የስብ ከምችት በቀላሉ እይታን ሊጋርድ ስለሚችል በመሆኑ የማዮ ክሊኒክ ሪፖርት ያሳያል:: በመሆኑም ከመጠን ያለፈ ውፍረት በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ ይህ ችግር የባሰ ሁኔታ ውስጥ ስለሚከተው ማሸኑን በመጠቀም ዙሪያ እጅግ የላቀ ልምድ ያካባተ ባለሙያ ከማስፈለጉም በላይ የማሽኑ ይዘት የላቀ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተም መሆን አለበት፡፡ ሂደቱ በዚህም ብቻ የሚገታ ባለመሆኑ በምርመራው ውጤታማና የተረጋገጠ መረጃን ለማገኘት ምርመራው መደጋገም እንዳለበት ይነገራል፡፡           
ከውፍረትና እርግዘና ጋር ተያዞ የሚነሳው ሌላው ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ደግሞ፣ ጽንሱን የተሸከመችው እናት በተኛችበት ትንፋሽ የመቋረጥ ሁኔታ ሊያጋጥማት የሚችልበት አደጋ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ትንፋሽ የመቆራረጥ ክስተት ደጋግሞ የሚያጋጥማቸው ነፍሰጡሮች ለፕሪኢክላምፕሲያ (preeclampsia) እና ለሌሎች ውስብስብ የጤና እክሎች ይዳረጋሉ፡፡ አንዲት ነፍሰጡር በእርግዝናዋ ወቅት ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የሰውነት ውሃ ማዘል፣ እጅግ በበዛ መልኩ ውፍረት መጨመርና በሽንት ውስጥ ፕሮቲን ከታዩባት ለፕሪኢክላምፕሲያ ለመዳረጓ ምልክቶች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
አንዲት ሴት ጤናማ በሆነ መልኩ ለመውለድ እርግዝናዋን ጤናማ ሊያደርጉላት የሚችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማከናወን አለባት፡፡ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላት ሴት ለመውለድ ካቀደች፣ ጽንሱን ከመቋጠሯ በፊት ከጽንስና ማህጸን ሀኪም ጋር መማከር አለባት፡፡ ይህንን ተከትሎም የህክምና ባለሙያዋ/ባለሙያው እረግዝናው ከመፈጠሩ በፊት የሥነ-ምግብ ባለሙያ ጋር ሄዳ ውፍረቱን ጤናማ በሆነ መልኩ እንደትቀንስ ያደርጋሉ፡፡ እርግዝናውን የፈለገችው ሴትም ሂደቱን በደምብ ተከታትላ ለማርገዝ ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት ላይ መድረስ ትችላለች፡፡

Read 12382 times