Sunday, 23 June 2019 00:00

በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

 • በታሪክ ለመጀመርያ ግዜ በ24 ብሄራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ
              • ማዳጋስካር፤ ብሩንዲና ሞሪታኒያ በታሪክ የመጀመርያቸው ነው
              • ለሽልማት የተዘጋጀው 16.4 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ እያንዳንዱ ቡድን በተሳትፎ ብቻ 475ሺ ዶላር ያገኛል፡፡ ሻምፒዮኑ የሚሸለመው
                ደግሞ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ነው
              • የሚሰለፉት 552 ተጨዋቾች የዋጋ ግምታቸው 2.5 ቢሊዮን ፓውንድ ነው


             32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ ዋና ከተማ የተጀመረ ሲሆን ታዋቂው የግብፅ ጋዜጣ አልሃራም በድረገፁ እንደዘገበው የአፍሪካ ዋንጫው በስፖንሰርሺፕ፤ በሚዲያ መብት እና በተያያዥ ንግዶች እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን ለግብፅ ኢኮኖሚ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ እንደሚያመጣ ተገምቷል፡፡ለሰባት ጊዜያት የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን የውድድሩን ከፍተኛ የውጤት ክብረወሰን የያዘችው ግብፅ የ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅነት ከካሜሮን በመረከብ በስድስት ወራት ውስጥ መስተንግዶዋን አድርጋለች፡፡ ግብፅ የአፍሪካ ዋንጫውን የምታስተናግደው ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን ከዘንድሮ በፊት በ1959፤ በ1974፤ በ1986 እና በ2006 እኤአ 4 የአፍሪካ ዋንጫዎችን አስተናግዳለች፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ 24 ብሄራዊ ቡድኖችን ማሳተፉና  የሚካሄድበት ወቅት ከፈረንጆች አዲስ አመት መግቢያ በ6 ወር መሸጋሸጉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው የሚካሄድበት መደበኛ ወቅትን ለመቀየር ካፍ የተገደደው በአውሮፓ ክለቦች ሲሆን አስቀድሞ ውድድሩ ሲካሄድ የነበረበት ወቅት ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች አማካይ የውድድር ዘመን ጋር መገጣጠሙ በተደጋጋሚ ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ የብሄራዊ ቡድኖቹ ብዛት ከ16 ወደ 24 ያደገው ደሞ ባለፈው አመት ከተጀመረው የአውሮፓ አገራት ሻምፒዮንሺፕ በተቀሰመ ልምድ እና የተሳታፊ አገራትን እድል ለማስፋት መሆኑ ተገልጿል፡፡ የብሄራዊ ቡድኖች ብዛት መጨመር አዘጋጅ አገር በስፖርት መሰረተልማት ሊኖራት የሚገባውን አቅም ያሳድጋልም ተብሏል፡፡
አልሃራም ጋዜጣ እንዳወሳው በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ከሚሰለፉ 552 ተጨዋቾች መካከል 315 በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ 201 ከአፍሪካ ፤ 32 ከቻይና እንዲሁም 4 ከአሜሪካ ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው ለመሰለፍ ወደ ግብፅ መግባታቸውንም አመልክቷል፡፡ በሊግ ደረጃ 95 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ለአፍሪካ ዋንጫው በማቅረብ የፈረንሳይ ሊግ 1 ቀዳሚ ሲሆን  የደቡብ አፍሪካ አብሳ ሊግ 45 ፤ የእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ እና ሻምፒዮንሺፕ 43 ተጨዋቾችን በማሳተፍ በተከታታይ ይጠቀሳሉ፡፡ ሴኔጋል እና ካሜሮን ሙሉ ለሙሉ ከአገር ውጭ የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎችን በስብስባቸው የያዙ ሲሆን አልጄርያ ጋና ሞሮኮ ከአገር ውስጥ ሊግ ከመረጣቸው 1 ተጨዋቾች በስተቀር ቡድኖቻቸውን በፕሮፌሽናሎች አደራጅተዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በአብሳ ሊግ ከሚጫወቱት 17  ተጨዋቾችን በመያዝ  ቀዳሚ ስትሆን ታንዛኒያ 14 እንዲሁም አንጎላ 13 ተጨዋቾቻቸውን ከአገር ውስጥ ሊግ መልምለዋል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከቦች መሃመድ ሳላህ፤ ሳዲዮ ኦማኔ፤ ሪያድ ማህሬዝ አሌክስ ኢዮቢ በአፍሪካ ዋንጫው ይሳካላቸው ተብለው ከሚጠበቁት ተጨዋቾች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ
ባግዳድ ቡኔን ጃ ከአልጄርያ፤ ሃኪም ዚዬክ ከሞሮኮ፤ ምብዋና ሳማታ ከታንዛኒያ፤ ሳሊፍ ሳኔ ከሴኔጋል፤ ሙውሳ ማሬጋ ከማሊ፤ አንድሬ ኦናና ከካሜሮን ኖውሌጅ ሙውሶና ከዚምባቡዌ፤ እንዲሁም ኒኮላስ ፔፔ ከአይቬሪኮስት ትኩረት የሚስቡ አዳዲስ ተጨዋቾች እንደሚሆኑም ተዘግቧል፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ ከትልልቅ ክለቦች የሚሰሩ የተጨዋች መልማዮች፤ የዝውውር ደላሎች እና ኤጀንቶች በአፍሪካ ዋንጫው በብዛት እንደሚገኙም እየተገለፀ ነው፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ፤አርሰናል፤ ፓሪስ ሴንትዠርመን እና ኢንተርሚላን በጋና፣ ናይጄርያ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች ላይ የሚጫወተቱትን ወጣት ተጨዋቾች ለመውሰድ ይሰማራሉ፡፡
በአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፉት ብሄራዊ ቡድኖች በአማካይ ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያወጡ መረጃዎች ሲያመለክቱ ፤ የጋና ብሄራዊ ቡድን ለሚያሰልፋቸው ተጨዋቾች 80ሺ ዶላር ለቡድኑ አባላት 10ሺ ዶላር በነፍስ ወከፍ እንደሚሰጥ፤ በሌላ በኩል ከ100 በላይ ለሚሆኑ ለጥቋቁሮቹ ክዋክብት ደጋፊዎች 3.7 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ ወደ ስፍራው መጓጓዙን ከ55 በላይ የሚዲያ አባላትን ወደ ውድድሩ ለመላክ የ2.5 ሚሊዮን ዶላር  ድጋፍ የጋና መንግስት ወጭ ማድረጉን የጋና ሶከር ኔት ዘገባ አውስቷል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ለሚሳተፉ 24 ብሄራዊ ቡድኖች ለዝግጅት ብቻ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በነፍስ ወከፍ 260ሺ ዶላር ተበረክቶላቸዋል:: በአፍሪካ ዋንጫው ለሻምፒዮን 4 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሁለተኛ 2.5፤ ለሩብ ፍፃሜ ተፋላሚዎች 800ሺ ዶላር ከሽልማት ገንዘብ እንደሚታሰብም ታውቋል፡፡
ከ56 የካፍ አባል አገራት መካከከል አዳዲስ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን እነሱም ማዳጋስካር፤ ብሩንዲ እና ሞሪታኒያ ናቸው፡፡ 12 አገራት የአፍሪካ ዋንጫን ተሳትፈው የማያውቁ ሲሆን እነሱም  መካከለኛው አፍሪካ፤ ቻድ ኮሞሮስ ኤርትራ ኢስዋቲኒ ጋምቢያ ሌሶቶ ስዋቶሜ ኤንድ ፕሪንስፔ ሲሸልስ ናሚቢያ እና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡

Read 11143 times