Saturday, 22 June 2019 11:15

“ፖለቲካና እግር ኳስ ተቀላቅለዋል፡፡ የት ካልን በጨዋታ ሜዳዎች ነው”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኮለኔል አወል አብዱራሂም በኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዳደር ከፍተኛ ልምድ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ባለፈው አንድ አመት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ውስጥ በምክትል ፕሬዝዳንትነትና በሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢነት እያገለገለ ነው፡፡ ስፖርት አድማስ ከኮለኔል አወል ጋር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ የመጀመርያውን ክፍል እነሆ ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡
የደደቢት እግር ኳስ ክለብን ከምስረታው አንስተህ በመምራት  ውጤታማ ተግባራትን አከናውነሃል፡፡ ያለፈውን አንድ ዓመት ደግሞ  በእግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚው አባል ሆነህ ወደ አመራርነቱ ተመልሰሃል፡፡  ክለብን በመምራት እና ክለቦችን በሚያስተዳድር ፌደሬሽን በከፍተኛ ሃላፊነትን መስራትን እንዴት ትመለከተዋለህ? በሁለቱ  ሃላፊነቶች ያሉትን ሁኔታዎች እና ፈተናዎች ምንድናቸው?


            ክለብ መስርቼ በውጤታማነት በመምራት በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ አርዓያ ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ በመስራቴ ደስተኛ ነኝ፡፡  በስራ ያገኘሁት ስኬት ነው፡፡ ክለብን እየመራህ ውጤታማ የምትሆነው የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን በብቃት ለማከናወን ሙሉ ሃላፊነቱን ስለምትወስድ ነው፡፡ ክለብን የምትመራው አርቀህ በማለም ነው፡፡ ስኬት ሆን ብለህ አቅደህ  በብቃት በምታከናውነው ስራ የሚመጣ እንጅ በዘፈቀድ አይደለም፡፡ በምትመራው ክለብ ውጤታማ ስትሆን ደግሞ ለብሄራዊ ቡድን እድገትም አስተዋፅኦ ይኖርሃል፡፡ የክለብ ውጤታማነት በብሄራዊ ቡድን ይንፀባረቃል፡፡ይህ ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡን ክብርና አመኔታ የሚያስገኝልህ ነው፡፡
ከክለብ አመራርነት ከለቀቅኩ በኋላ ለአምስት አመታት ከስፖርቱ አስተዳደር ርቄ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሃላፊነት ራሴን ያገለልኩ ቢሆንም እግር ኳስ ህይወቴ በመሆኑ ከስፖርቱ ሙሉ ለሙሉ አልራቅኩም ነበር::
ከደደቢት ክለብ ከለቀቅኩ በኋላ ለአምስት አመታት በግል ስራዬ ላይ በማተኮር እንቀሳቀስ ነበር:: ወደ እግር ኳሱ አስተዳደር በተለይም ወደ  ፌደሬሽን  የተመለስኩት በህዝብ ግፊት ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በክለብ አመራርነት የማከብረውንና የምወደውን የስፖርት ቤተሰብ እስከመጨረሻው የመራቅ ፍላጎትም አልነበረኝም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች፤ ሁኔታዎችና ሚዲያዎች ላይ በሚነሱ ሃሳቦች እና ውይይቶች ወደ ስፖርቱ እንድመለስ የሚሰጡ አስተያየቶች ነበሩ፡፡ በተለይ ግን ከ2 ዓመት በፊት ያጋጠመውን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ደደቢት 20ኛ ዓመቱን ሲያከብር በታዋቂው የትሪቡን ስፖርት ፕሮግራም የክብር እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ነበር፡፡ በወቅቱ ስለ እግር ኳሱ ባደረገናቸው ውይይቶች የማነሳቸው ሃሳቦችን በመንተራስ ከስፖርት ቤተሰቡ የሚቀርቡ አስተያየቶች ወደ ስፖረቱ አመራርነት እንድመለስ የሚገፋፉ ነበሩ፡፡ ብዙዎች ለእኔ ያላቸውን ፍቅርና ክብር ሲያንፀባርቁ በክለብ ደረጃ የሰራኋቸውን ተግባራት በፌደሬሽኑ አስተዳደርም ላይ እንድፈፅም መሻታቸው እገነዘብ ነበር፡፡ በስፖርቱ ላይ አስተዋፅኦ እንዳበረክት በግንባር የጠየቁኝ በተለያዩ መንገዶችም ግፊት ያደረጉ ባለድርሻ አካላትም ጥቂት አይደሉም:: ከእግር ኳስ መራቅ እንደሌለብኝ የሚመክሩዕም ነበሩ:: ስለዚህም ለተሰጠኝ አክብሮት እና ፍቅር ምላሽ ለመስጠት ወደ ፌደሬሽን አመራርነት እንድመለስ አድርጎኛል፡፡ ከክለብ አመራርነት ከለቀቅኩ በኋላ ባተኮርኩበት የግል ስራ በቂ ግዜ ባይኖረኝም ወደ ፌደሬሽን ለመግባት የወሰንኩት በሙሉ አቅም ስፖርቱን ለማገልገል ነው፡፡ ለህዝቡ በተለይም ለስፖርት ቤተሰቡ ያለኝን አክብሮት ለማረጋገጥም ነው፡፡ በባህርዬ ለምሰራው ነገር በቂ ጊዜ እና ትኩረት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ፌደሬሽኑ አመራርነት ስመለስ በግል ስራዬ ላይ ተፅእኖ ሊፈጥር እንደሚችል እያወቅኩም አስተዋፅኦዌን በሙሉ አቅም ለማበርከት ነበር ሃላፊነቱን በፀጋ የተቀበልኩት፡፡
በክለብ አመራርነት አዕምሮህ ውስጥ ያለውን ግብና አቅጣጫ ለማሳካት ነፃነት ይኖርሃል፡፡ ስለዚህም ያለህን አቅም በመጠቀም ያቀድከውን ለመከወን ሙሉ ሃላፊነቱን ራስህ በመቻል መወጣት ይጠበቅብሃል፡፡ በሌላ በኩል  ግን ወደ ፌደሬሽን ሃላፊነት ስትመጣ ሃላፊነትህን በአባቡ ለማስፈፀም የምትሰራው ብቻህን አይደለም፡፡ በፌደሬሽን አመራር ውስጥ አብረህ የምትሰራው ከአንድ ፕሬዝዳንትና ከ10 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ነው፡፡ በተጨማሪ በቢሮ ደረጃ ከዋናው ማኔጅመንት አንስቶ እስከፅህፈት ቤት ደረጃ በአስተዳደሩ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ የፌደሬሽን አመራርነት ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያገናኝህም ነው:: ሚዲያው፤ የየክለቡ አመራሮች፤ ተጨዋቾች አሰልጣኞች፤ መንግስትን በሚያስተዳድር ሃላፊነት ውስጥ ነው የምትገባው፡፡ ስለዚህም በፌደሬሽን አመራርነት ያሰብከው ግብ ላይ ለመድረስ በክለብ አመራርነት እንዳለው ምቹ እና የተደላደለ አይደለም:: በፌደሬሽን ውስጥ አመራርነት ስትሰራ ትዕግስተኛ መሆን አለብህ፡፡ ለምታከናውናቸው ተግባራትም በቂ ጊዜ ያስፈልጋሃል፡፡ መታገሱ የሚያስፈልገው ከአየአቅጣጫው የሚገጥሙህን ትችቶች ለመቋቋም ነው፡፡ ያልጠሩ፤ የተደበላለቁ እና የተዛቡ ትችቶችን ተቋቁሞ ተገቢውን ስራ ለመስራት ታጋኝ መሆን አለብህ፡፡ ትችቶች መድረስ ወደ የምትፈልገው ግብ እና የምትከተለውን አቅጣጫ ሊያስቱህ አይገባም፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት በስራ አስፈፃሚው ውስጥ ስታገለግል ከታዘብካቸው ሁኔታዎች ከአየአቅጣጫው ትችቶች መብዛታቸውን ያመለክታል፡፡ ምን አሳስቦህ ነው?
በፌደሬሽኑ አስተዳደር ላይ የሚቀርቡ ትችቶች በአመዛኙ በእውቀት ላይ የተመሰረቱ አለመሆናቸውን ከሚያሳስቡኝ ሁኔታዎች አስቀድሜ የማነሳው ነው፡፡ ብዙ ትችቶች እና ነቀፋዎች እውቀትን መሰረት ያላደረጉ ናቸው፡፡  ግምታዊነት ያመዘንባቸዋል፡፡ አንዳንዴ ረጅም ዓመታት ያለፋቸው ሁኔታዎች መልሶ በማራገብ ሲተች ታስተውላለህ፡፡ በተለይ በሚዲያ በኩል በሚቀርቡ ትችቶች ላይ ብዙ ቅሬታዎች እንዳሉኝ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃናት ላይ ፌደሬሽኑን አስመልክቶ በሚቀርቡ ትችቶች ላይ የእውቀት ማነስ፤ የመረጃ እጥረት እና የጥራት መጓደል መኖሩን ነው የምታዘበው፡፡ ለእግር ኳሱ የሚጠቅመው በእውቀት እና በመረጃ ላይ ተመስርተው የሚቀርቡ ትችቶች ናቸው፡፡ የትችት ዓለማው ለቢዝነስ፤ ለግል እርከታ መሆን አልነበረበትም፡፡ ዋናው ትኩረት የስፖርቱ እድገት ቢሆን ነበር የሚመረጠው፡፡
ፌዴሬሽኑ የጋራ ነው፡፡ ስለዚህም በቀና መንፈስ መተቻቸት ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ትችት ለዕድገት አስፈላጊ ነገር ስለሆነ ነው፡፡ በቀና መንፈስ ከትክክለኛ  ዕይታ ተነስቶ ትችት ማቅረብ ጥሩ ነው፡፡ ትችትን የምንጠቀመው ለማናናቅ መሆን የለበትም፡፡ ስለሚተቸው ጉዳይ በአግባቡ የማያውቅ የፈለገውን ማብራርያ በማቅረብ የሚተቸውን አካል ቢያናንቅ ትክክል ሆኖ አይደለም፡፡ በፌደሬሽኑ ላይ ትችቶችን የሚያቀርቡ ባለድርሻ አካልነት ስለሚሰማቸው መሆኑን እናምናለን፡፡ በጋራ ተባብሮ  መሄድና መስራት ለእግር ኳስ ዕድገት ጠቃሚ ነው፡፡
እግር ኳስና ፖለቲካው ተቀላቅለዋል በሚል ብዙዎቹ ይበሳጫሉ፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራሮች የፖለቲካ አጀንዳዎችን ያራምዳሉ፡፡ ይህን የመሳሳሉ  ትችቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተደጋጋሚ እና በብዛት እየተንፀባረቁ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ፖለቲካው እግር ኳሱን እያመሰ ነው ወይስ እግር ኳሱ ነው ፖለቲካውን የሚያምሰው?
ይህ አይነቱ አባባል ለይቶ የሚያየው ነገር የለም:: በማንኛውም አገር የተለያዩ ነገሮችን ማደበላለቅ ጥሩ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተደበላለቀ ነገርን ለማጥራት ይከብዳል፡፡ ስለዚህም ፖለቲካውንና እግር ኳሱን አደበላልቆ መመልከት ልክ አይደለም፡፡
ፖለቲካውና እግር ኳሱ ተቀላቅለዋል በማለት ሚዲያው እና ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በደፈናው የሚናገሩ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የስታድዬሞችን ድባብ እየቀየሩ መምጣታቸውን በማመልከት ደጋፊዎች ቢመሰክሩ ግን ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም  ደጋፊው ችግሩን በቅርበት ያውቃል፡፡ ፖለቲካ ወደ ስፖርቱ እየገባ ከሆነ የቱ ጋር ነው ብሎ የመለየት ግዴታ ደጋፊዎች ላይ የለባቸውም፡፡ ሚዲያ ግን አጥርቶ ማየት እና መለየት አለበት፡፡
ወይም ሌላ ባለሙያ መለየት ካልቻለ በቀር ፖለቲካው ኳሱን እያመሰው ነው ብሎ ለመተቸት ይከብዳል፡፡ ለምን ቢባል የቱ ጋር ችግሩ እንዳለ ስለማያሳይ ነው፡፡  ፖለቲካና እግር ኳስ ስለመቀላቀላቸው ከጠየቅከኝ የእኔ ምላሽ አዎ ነው፡፡ ችግሩ የቱ ጋር እንዳለ ስለማውቅ ነው፡፡ አዎ በተለያዩ ስታድየሞች ደጋፊው በፖለቲካዊ አጀንዳዎች ራሱን እየጠመደ ያለበት ሁኔታ ይንፀባረቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ እነዚህን ችግሮች የሚያስወግድበትን ርምጃዎችና አቅጣጫዎች አስቀምጦ የበኩሉን እየሰራ ነው:: በፌደሬሽኑ በኩል በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ አተኩረን ስንሰራ እግር ኳስ እግር ኳስ ብቻ ሆኖ መሄድ እንዳለበት እያስገነዘብን ነው፡፡ ይህን የምንሰራው ደግሞ ከየክለቦቹ አመራር ጋር እንጅ ከደጋፊዎች ጋር አይደለም፡፡ ፌዴሬሽኑ ስፖርታዊ ጨዋነትን ወደ ክለቦቹ ያወርዳል፡። ክለቦቹ ደግሞ ይህንኑ ወደ ደጋፊዎቻቸው ያደርሱታል፡፡  ፌዴሬሽን ግንኙነቱ በቀጥታ ከክለብ ጋር እንጅ ከደጋፊው ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ደጋፊን በቀጥታ የሚገናኘው ክለቡ ስለሆነ ነው፡።
ስለዚህ ሚዲያውም ሆነ ሌላው ባለድርሻ አካል ደጋፊዎቻቸውን እግር ኳስን  ከሚያምሱ ሁኔታዎች ማውጣት ያለባቸው ክለቦች እንደሆኑ ማመን ይገባዋል፡፡ በየክለቦቹ ደጋፊዎችን ከፖለቲካ አጀንዳዎች ከማራቅ፤ ከብጥብጥ እንዲርቁ በማድረግ እና ስፖርታዊ ጨዋነትን በማስፈን በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ነው መሰራት ያለበት፡፡ የፌዴሬሽኑን ጥረት ማገዝና  የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡  ሁሉንም ጉዳይ በፌደሬሽኑ አስተዳደር ላይ መደፍደፍ ልክ አይደለም፡፡ ሁሉንም ችግሮች ፌዴሬሽኑ ላይ በጭፍን የሚጫንባቸው ሁኔታዎች በዝተዋል፡፡ ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም፤ ለምን መፍትሄውን የሚያስቀምጥ አይደለም፡፡ ፖለቲካና እግር ኳስ ተቀላቅለዋል፡፡ የት ካልን በጨዋታ ሜዳዎች ነው፡፡ በየስታድዮሞቹ አካባቢያዊነት፤ ብሔርና ዘር እየተንሸራሸረ ነው፡፡ መወገድ አለበት፡፡ ችግሮቹ በቃላት፤ በፅሁፍ፤ በዝማሬ ሲገልፁ እየተመለከትን ነው፡፡ አንዳንድ ስታድየሞች ላይ ደጋፊዎች የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ለእግር ኳሱ አሳሳቢ አደጋዎች ናቸው፡፡
የእግር ኳስ ሜዳው፤ ማዕዱ የሁለቱ ተጋጣሚ ክለቦች ነው፡፡ ስለዚህም ሁለት ክለቦች በጨዋታ ሜዳ ላይ ሲገናኙ ደጋፊዎችን በስፖርት ጨዋነት  በመቅረፅ ማቅረብ አለባቸው፡፡   የፌዴሬሽኑ ሚና ለሚፈጥሩት ስራ ለሚያስተላልፉት ትምህርት ልዩ ልዩ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ የትምህርትና የስልጠና ማቴርያሎች ማገዝና ሙያተኞችን ማቅረብ ነው የፌደሬሽኑ ሃላፊነት፡፡ ደጋፊዎቻቸውን መምከር ያለባቸው ክለቦች ናቸው፡፡ እኔ የአገራችን ሜዳ ብዙ ብቁ ሙያተኞቹ እንዳሉበት አምናለሁ፡፡ እግር ኳስን ለማስተካከል መቼ ነው የጋራ ዓላማ ይዘን የምንሰራው?
ፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች በፖለቲካዊ መስፈርት ተቀመጡ ናቸው የሚል ትችትን እሰማለሁ፡፡ በግሌ ግን የማውቀው ነገር የለም:: እስቲ በፌዴሬሽኑ ካለን 11 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ማነው በፖለቲካ የመጣው ፡፡ የስራ አስፈፃሚው አባላት በግል ሙያቸው የሚተዳደሩ፣ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ስራዎች የተሰማሩ ፤ ከፍተኛ የስፖርት ባለሙያዎች በመሆን የሚያገልግሉ … ናቸው፡፡
ፖለቲካ ውስጥ አለ ተብሎ የሚጠቀስ የስራ አስፈፃሚ አባል ቢሆን አንድ የፓርላማ ተመራጭ  ብቻ ናት፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽኑን አመራር ከፖለቲካ ተፅዕኖ ጋር ማያያዝ ነውር ነው፡፡ ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ማንም ሰው ስልጣን ፈልጎ ወይም ለመጠቀም አስቦ የመጣ የለም፡፡ ሁላችንም ለፌዴሬሽኑ ግዚያችንና ገንዘባችን እያጠፋን ነው የምናገለግለው፡፡ እኔ በበኩሌ በፌደሬሽኑ የያዝኩትን ሃላፊነት እንደ አገራዊ ግዴታዬ እቆጥረዋለሁ፡፡
ገንዘባቸውንና ግዚያቸውን ሰውተው የሚያገለግሉ አገር ወዳድ ግለሰቦችን የፖለቲካ አጀንዳዎችን ያራምዳሉ ብሎ መፈረጅ ያሳፍራል::   ከህብረተሰባችን ከምናውቀው ባህላችን የወጣም ነው፡፡  በአጠቃላይ ያለሁበት ስራ አስፈፃሚ  ፖለቲካዊ ሹመት ያለው ፖለቲካ የሚያራምድ ነው ብዬ በፍፁም አላምንም፡፡ ስለዚህም እውነተኛ ነገር ይዞ መነቃቀፍ መወቃቀስ ያስፈልጋል፡፡
ይቀጥላል

Read 1842 times