Sunday, 16 June 2019 00:00

ኢትዮጵያውያን ሙስሲሞች እንደማንኛውም ዜጋ ሲወለዱ ኢትዮጵያዊ ናቸው

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

ባለፈው ሰሞን የማህበራዊ ሚዲያውን አጨናንቆት ከሰነበተው ጉዳዮች አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሚሊንየም አዳራሽ፣ በረመዳን የአፍጥር ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር ውስጥ “‘በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች’ የሚል ቃል ተናገሩ” የሚል ሃሳብ ነው፡፡ ሳምንታዊው ኢትዮጲስ ጋዜጣ እና ድሬ ትዩብ ባወጡት ዜና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቃል እንደተናገሩት አድርገው ዘግበዋል፡፡ አንዳንድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ጭምር በተመሳሳይ ርእስ መዘገባቸውንም ታዝበናል፡፡
ሙስሊሞችን ያስቆጣው ዘገባው ሳይሆን ለዘገባው ርእስነት የተመረጠው “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች” የሚለው ሐረግ ነው፡፡ በበኩሌ እንደ ሙስሊም ያለኝን ስሜት በወቅቱ በፌስቡክ ገጼ ላይ ገልጫለሁ፡፡ በዚህ ጽሁፍ ግን ከስሜት ወጣ ብዬ፣. ጉዳዩን ለማየት እሞክራለሁ፡፡ ይህንንም በማሰብ ነው የማህበራዊ ሚዲያው ጩኸት እስኪያባራና ወደ ሰማይ የጓነው አቧራ ወደ መሬት እስኪመለስ ትንሽ ዘግየት ያልኩት፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከዐረብ ሀገር ተሰደው መጥተው፣ በኢትዮጵያ ጥገኝነት ተሰጥቷቸው የሚኖሩ የሚመስላቸው ሰዎች “ጥቂት” እንዳልሆኑ አስባለሁ፡፡ ይሄ ትልቅ ስህተት ነው! በመሰረቱ “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች” የሚለው አገላለጽ፤ እንደ እስክንድር ነጋ ባሉ “አንጋፋ” ጋዜጠኞች እንዲሁ በዘፈቀደ የተነገረ አይመስለኝም:: እነ እስክንድር የጽንሰ ሃሳቡን ምንነትና ታሪካዊ መነሻውን ያውቁታል፤ ችግሩን ይገነዘቡታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በቅን ልቡና የተፈጸመ ስህተት አድርጌ ለመውሰድ የሚቸግረኝም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
እኔ ባደረግኩት ማጣራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ባደረጉት ንግግር ውስጥ፤ “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች” የሚል ቃል አለመናገራቸውን አረጋግጫለሁ፡፡ ካስፈለገ በመገናኛ ብዙሃን የተላለፈውን ድምፅ መለስ ብሎ ማዳመጥ ይቻላል:: እናም ድሬ ትዩብና ኢትዮጲስ ጋዜጣ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተናገሩትን ሃሳብ ከየት እንዳመጡት አይታወቅም፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ስህተት መፈጠሩን አምኖ በሳምንቱ እትም ላይ ማረሚያ በማውጣት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ድሬ ትዩብም እንዲሁ ማረሚያ አድርጓል፣ ይቅርታም ጠይቋል፡፡
“በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች” የሚለው አገላለጽ ላይ ላዩን ስናየው “ተራ ቃል” ሊመስለን ይችል ይሆናል፡፡ ሀሳቡ ተራ ቢመስልም ምን ያህል ሰዎችን እንዳስቆጣና እንዳስከፋ በማህበራዊ ሚዲያ ከተላለፉት መልእክቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ብዙ ነገር ልንማር ይገባናል፡፡ ያ ቃል የሚፈጥረውን ህመም ሊያውቀው የሚችለው የጉዳዩ ሰለባ ሆኖ ለዘመናት የኖረው ሙስሊም ማህበረሰብ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሌሎቻችንም ስህተቱን ልንረዳና ህመሙ ሊሰማን ይገባል፡፡
ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአፄዎቹ የአገዛዝ ዘመን፣ ይህንን ህመም ብቻውን ሲታመም ኖሯል፡፡ ከ1968 ዓ.ል ወዲህ ይህ ቃል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበረ የመሰላቸው ሰዎች በርካታ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ፤ አፄዎቹ በማህበረሰቡ ላይ የጫኑት የእኩይ አስተሳሰቡ ውርዴ፣ ዛሬም ጊዜ ጠብቆ፣ እያገረሸ ዜጎችን ማቁሰሉ አስደንጋጭ ነው፡፡ አስተሳሰቡ እስከነ ሰንኮፉ ካልተነቀለ ወደፊትም ጊዜ እየጠበቀ መፈንዳቱና በየዘመኑ የሚመጡ ሙስሊሞችን ማቁሰሉ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ስላደረብኝ፣ የጉዳዩን አስከፊ ገጽታ ለአንባብያን ለማስታወስ ስል ነው ይህቺን መጣጥፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁት፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በኢትዮጵያ የበቀለ አንድም ሃይማኖት የለም፡፡ በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ሃይማኖቶች “መጤዎች” ናቸው፡፡ አይሁድም፣ ክርስትናም፣ እስልምናም ከባህር ማዶ የመጡ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡ እዚች ሀገር የበቀለ ሃይማኖት አለ ከተባለ ምናልባት “ዋቄፈታ” ብቻ ይመስለኛል:: ኢትዮጵያውያን ግን የመጣውን እየተቀበሉ ለዘመነ ዘመናት፣ እዚችው ምድር የነበሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ስናየው፤ መጤዎቹ ሃይማኖቱን የተቀበሉት ሰዎች (ኢትዮጵያውያን) ሳይሆኑ ወደ ሀበሻ ምድር የመጡት ሃይማኖቶች ናቸው፡፡
የሌሎቹን ሃይማኖቶች አመጣጥ ለጊዜው እንለፈውና የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን የእስልምናን አመጣጥ በአጭሩ እንይ፡፡ እስልምና በነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) አማካይነት መሰበክ ጀመረ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ሀበሻ ምድር ገባ፡፡ እስልምናን ይዘው ወደ ሀበሻ ያመጡት የነብዩ ልዑካን ብዛት መጀመሪያ 16 (ወንድ 12 እና ሴት 4) ነበሩ፡፡ በኋላ ደግሞ 50 ሰዎች ተጨመሩ፡፡ ከዚያ በኋላም በተከታታይ የመጡ ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሰሃባዎች (ልቡካን) ብዛት፣ ወደ 180 ገደማ መሆናቸውን የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ:: ከእነዚህ ሰሃባዎች ውስጥ ጥቂቶች ሞተው በሀበሻ ምድር ተቀብረዋል፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊት ክርስቲያን አግብቶ፣ ክርስትናን ተቀብሎ እዚሁ ቀርቷል:: ሌሎቹ ግን የመጡበትን አምላካዊ መልእክት አድርሰው፣ አስተምረው ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡ ከዚያ በኋላ እስልምናውን ይዘው የቀጠሉት፣ እምነቱን የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው እንጂ ከባህር ማዶ የመጡ ዐረቦች አልነበሩም፣ አይደሉም፡፡
የታሪክ ሰነዶች እንደሚነግሩን ከሆነ ልክ እንደ ሌሎቹ እምነቶች ሁሉ በዚያ ወቅት በሀበሻ ምርድ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፤ እስልምናን ተቀብለው አሁን እስካለነው ትውልዶች ድረስ ሃይማኖቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሯል፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከዚያ ዘመን ጀምሮ ያሉት አፄዎች፤ የእስልምና ሃይማኖትን የተቀበሉ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሀገር ክህደት በመቁጠር በርካታ ግፍና መከራ አውርደውባቸዋል፡፡ ዜግነታቸውን እስከ መካድ ደርሰዋል፡፡
አንድ ሰው የአንድ ሀገር ዜግነት እንዳለው ዋነኛው ማረጋገጫ የመሬት ባለቤት መሆን መቻሉ ነው፡፡ ይህንን በደንብ የሚገነዘቡት አፄዎች፤ ሃይማኖታቸውን ወደ እስልምና የቀየሩ ዜጎች ከመሬታቸው እንዲነቀሉና መሬት አልባ እንዲሆኑ አደረጓቸው፡፡ (ለምሣሌ፡- የእኔ ቅድመ አያት፣ ቅድመ አያት፣ ምንጅላት… ወይ ክርስቲያን ወይ አይሁድ ወይ ፓጋን ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ የነብዩ (ሰዐወ) ልዑካን ያመጡትን እስልምናን ተቀብለው ሙስሊም ስለሆኑ ሀገሬ እንዳይሉና ሀብት እንዳያፈሩ፣ መሬት እንዳይኖራቸው ተደረጉ እንደማለት ነው)
ይህ ማለት ግን አንድም ሙስሊም መሬት አልነበረውም ለማለት ሳይሆን ብዙሃኑ ሙስሊም የመሬት ባለቤት አልነበረም ለማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ አሁን ድረስ እንደሚታየው ሙስሊሞች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸው ሚናና ተሳትፎ አንድም በንግድ አሊያም በእደ ጥበብ ዘርፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ረገድ ታዋቂዎቹ የታሪክ ምሁራን እነ ማርካኪስ እና ሪቻርድ ፓንክረስት (#Markakis and #Pankrust) የጻፉትን ማንበቡ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡
የሩቁን ዘመን ትተን የዛሬ መቶና መቶ ሃምሳ ዓመት የነበረውን ታሪክ መለስ ብለን ብናስተውል፤ በማዕከላዊ መንግስት በሀገር አስተዳደር ዙሪያ የሙስሊሞች ተሳትፎ ካላቸው ቁጥር አኳያ በጣም አናሳ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሙስሊሞች እንደ ባዕድ፣ አልፎ ተርፎም እንደ ጠላት በጥርጣሬ ይታዩ ነበር፡፡ ሙስሊሞች ወታደር እንዳይሆኑ ግልጽ ድንጋጌ ነበር፡፡ ሙስሊሞች ወታደር መሆን ከፈለጉ ሃይማኖታቸውን ብቻ ሳይሆን ስማቸውን ጭምር መቀየር ግድ ነበር:: ይህ የሚደረገው ደግሞ ሙስሊሞች ጠመንጃ ከያዙ መንግስት ይገለብጣሉ ተብሎ ስለሚፈራ ነው፡፡ ሙስሊሞች ምስጢር ለጠላት አሳልፈው ይሰጣሉ ተብለው ስለሚጠረጠሩ በመዝገብ ቤትና በመሳሰሉት ሰነዶች ባሉበት አካባቢ እንዲሰሩ አይደረጉም ነበር፡፡ ይሄ ትናንት የነበረ የታሪካችን አካል ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ሙስሊሞች በሀገሪቱ ጠረፍ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ በመሆኑ እንኳን ምስጢር አውጥተው ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ፤ የሀገርን ሉዓላዊነት ቀድመው የሚያስከብሩት እነርሱ እንደነበሩ ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡
በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት በግልጽ፣ በአደባባይ፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በጋዜጦችና በሬዲዮ ጭምር “በኢትዮጵያ የሚኖሩ እስላሞች” እየተባለ ይነገር ነበር፡፡ ጋዜጠኞችም በዘገባዎቻቸው እንደ ደህና ነገር ይህንኑ ያስተጋቡ ነበር፡፡ አንድም የእስልምና ሃይማኖታዊ በዓል እውቅና አግኝቶ አይከበርም ነበር፡፡ “የቁራ አገሩ ዋርካ የእስላም አገሩ መካ” እየተባለ በተረትና ምሳሌ በይፋ፣ በአደባባይ ይገለጽ ነበር፡፡ በሀገሪቱ አንድም ሙስሊም እንደሌለና (ቢኖርም የሀገሪቱ ባለቤት እንዳልሆነ ተደርጎ ተወስዶ) ሀገሪቱ የክርስቲያኖች ብቻ መሆኗን በሚያረጋግጥ መልኩ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” ይባልም ነበር፡፡ “አንድ ሀገር፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ባንዲራ፣…” የሚለውና እስከ አሁን ድረስ በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር የሚቀነቀነው ሃሳብ፣ በሀገሪቱ አንድ ሃይማኖት ብቻ ያለ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
በእኔ በራሴ ላይ የደረሰውን ልንገራችሁ፡፡ በ1980 ዓ.ል በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ 7ኛ ፎቅ አንድ ጽሁፍ ይዤላቸው የሄድኩት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የዓምድ አዘጋጅ፣ ስሜን አነበቡና “አብዱራህማን፤ እስላም እኮ ጋዜጠኛ መሆን አይችልም” አሉኝ፡፡ ደስ የሚለው ነገር በተለያዩ ጊዜያት የወሰድኩላቸውን ጽሁፎቼን ከአድናቆት ጋር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ “ከአስተዋልነው” በሚለው ዓምድ ላይ አትመውልኛል፡፡ ከእርሳቸው ቢሮ አለፍ ብሎ በዐረብኛ ቋንቋ የሚታተመውን “አል-ዓለም” የተሰኘ ጋዜጣ የሚያዘጋጁ ጋዜጠኛ የሥራ ባልደረቦቻቸው እዚያው አጠገባቸው እያሉ “እስላም ጋዜጠኛ መሆን አይችልም” ማለታቸው እስከ አሁን ድረስ ይገርመኛል፡፡ ምናልባት ሰውየው ጋዜጠኛ ማለት በአማርኛ የሚጽፍ ብቻ ሳይመስላቸው አይቀርም!
ይህ ሁሉ ትርክት ሙስሊሞችን የሚያገል፣ መጤና ሀገር አልባ የሚያደርግ፣ ሀገሪቱ የእነሱ እንዳልሆነች የሚሰብክ ነበር፡፡ ይህ ትርክት ከሰዎች አእምሮ በአጭር ጊዜ ሊፋቅ እንደማይችል ይገመታል:: በመሆኑም፤ እነዚህ የተንሻፈፉ እውነታዎች መጥፎ ጠባሳቸውን አትመው ያለፉ የታሪካችን መጥፎ አሻራዎች መሆናቸውን አዲሱ ትውልድ ሊገነዘብ ይገባል፡፡
ይህ እኩይ አስተሳሰብና የተንሸዋረረ አመለካከት መንግስት የማይቀበለው እንደሆነ በግልጽ የተነገረው በደርግ ዘመን ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ከ1968 ዓ.ል ጀምሮ የሙስሊሞች ሦስት ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች” የሚለው ቀርቶ “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች” መባልም ተጀመረ፡፡ ሙስሊሞች እንደ ዜጋ ተቆጠሩ፡፡ ውትድርናን ጨምሮ በየትኛውም የሥራ መስክ የመሰማራት መብታቸው ተረጋገጠ:: የመሬት ባለቤት እንዲሆኑም ተደረገ፡፡ በ1987 ዓ.ል በወጣው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ደግሞ የሙስሊሞች ዜግነታዊና ሃይማኖታዊ መብቶች እውቅና ተሰጣቸው፡፡
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች (ጥንትም ሆነ ዛሬ ያሉት) እዚቺው ምድር የተፈጠሩ ኢትዮጵያውን መሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ጥገኝነት የተሰጠው “ለእስልምና” ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥገኝነት የተሰጠው ሃይማኖት ደግሞ እስልምና ብቻ አይደለም፡፡ ክርስትናም፣ አይሁድም በኢትዮጵያ በየዘመኑ ጥገኝነትን ያገኙ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡ ልዩነታቸው የአመጣጥ ቅደም ተከተል ብቻ ነው:: የአመጣጣቸውም ቅደም ተከተል ደግሞ አንዱን በሌላው ላይ “መጤ ነህ” ሊያስብል የሚችል ምክንያት የለውም፡፡
በዚህ ወቅት አንዳንድ ጋዜጠኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተናገሩትን እንደተናገሩ አድርገው ማቅረባቸው አሳፋሪ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ድንቁርና የወለደው አካሄድ ሀገሬን እወዳለሁ፣ ለሰዎች መብት እታገላለሁ ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ “የእስላም አገሩ መካ የቁራ አገሩ ዋርካ” የሚለውን ድንቁርና የወለደው ፈሊጥ ከተቀበረበት አፈሩን አራግፎ በማንሳት፣ የፊውዳል ሌጋሲ (ውርስ) ለማስቀጠል ከመንቀሳቀስ በላይ ለአንድ ጋዜጠኛ ሞት የለም! እንዲህ ያለው ነገር እንዲቀጥል ልንፈቅድለት አይገባም፡፡ እናም እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡
ዛሬ እንደ አዲስ ይህንን “በኢትዮጵያ የሚኖሩ እስላሞች” የሚለውን አግላይ፣ ኢ-ህገ መንግስታዊ አባባል ማቀንቀን ለምን እንዳስፈለገ ባይገባኝም፣ ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ዜጋ ሁሉ ይህንን አብሮነታችንን የሚንድ ነቀርሳ የሆነ አስተሳሰብና አመለካከት አጥብቆ ሊያወግዘው ይገባል፡፡ ከሙስሊም ወገኖቹ ጎን ቆሞ ተቃውሞውን ሊያሰማ ይገባል፡፡ ይህንን ባልቴት አስተሳሰብ፤ በጋራ ጠራርገን ወደ ዘላለማዊ መኖሪያው ወስደን፣ አርቀን ቀብረን፣ ከአፄ ምኒልክ ሀውልት አጠገብ የመታሰቢያ ሐውልት ልናቆምለት ይገባል፡፡ የእኩይ አመለካከቱ ግብዓተ-መሬት እስኪፈጸም ድረስ እየተቀባበልን ልናወግዘው ይገባል፡፡
በመጨረሻም፤ እንደ አንድ ሙስሊም፣ ስሜታዊ ሆኜ፣ አንዲት ሃሳብ እንዳቀርብ የአንባብያንን ፈቃድ እጠይቃለሁ፡፡ … አዎ! … እኛ ኢትዮጵያዊ ሆነን የተወለድን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ነን! የዘር ሀረጋችን ወደ ኋላ ቢቆጠር መነሻው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አንድ ግንድ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እናም … ዜግነታችንን ማንም ምድራዊ ኃይል ሊያረጋግጥልን አይችልም - አረጋጋጮቹ እኛው ራሳችን ብንሆን እንጂ!!!
ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1229 times