Sunday, 16 June 2019 00:00

ከዲባባ ፈርቀዳጆች ታላቅየዋ አትሌት - እጅጋየሁ ዲባባ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

እጅጋየሁ ትውልዷ  የኦሎምፒያኖች ከተማ በሆነችው የአርሲዋ በቆጂ ነው፡፡ ስድስት ልጆች በነበሩበት የዲባባ ቤተሰብ ሶስተኛዋ ነበረች፡፡ ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ በ1992 እኤአ በባርሴሎና  ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያ በመጎናፀፍ የመጀመሪያውን ጥቁር አፍሪካዊት ኦሎምፒያን ስትሆን እጅጋየሁ ገና የ10 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ የደራርቱን አንፀባራቂ ድል  በቴሌቪዥን ተመለከተች፡፡ ወደ ሩጫው ስፖርት ለመግባት ከፍተኛ መነሳሳት ውስጥ የገባችበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በበቆጂ  ትምህርት ቤቷ የነበሩ ስፖርት መምህሯ ለአትሌቲክስ ስፖርት ያላትን ችሎታ አስተውለዋል፡፡ ስለዚህም በት/ቤቶች መካከል በሚደረገው ውድድር እንድትሳተፍ ምክር ሰጧት፡፡እድሉን የተቀበለችው ሳታመነታ ነበር፡፡ የመጀመርያ ውድድሯን ያደረገችው ምን አይነት የሩጫ ልምድ ሳይኖራትና በቂ የሚባል ሥልጠና ሳታደርግ ቢሆንም በቀላሉ ነበር ያሸነፈችው፡፡ ይህ ውጤቷም በ1998 በተካሄደው የኦሮሚያ ሻምፒዩና ላይ የአርሲን ዞንን ወክላ እንድትወዳደር አስመረጣት፡፡ በ8 ኪ.ሜ የወጣት ሴቶች ውድድር በማሸነፏ በኦሮሚያ ማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ ዓይን ውስጥ ገባች፡፡ በተመሳሳይ የውድድር ዘመንም ይህን የመጀመርያ ክለቧን በመቀላቀል የሩጫ ዘመኗን  ጀምራለች፡፡ የኦሮሚያ ማረሚያ ቤት ክለብ አትሌት ሆናም  ከ10 ዓመታት በላይ የተወዳደረች ሲሆን ከብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ዶክተር ወልደ መስቀል፤ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ እና ሌሎች ጋር  አብራ ለመስራት በቅታለች፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን በሁለት ኦሎምፒኮች፤ በ3 የዓለም ሻምፒዮና እና የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች በከፍተኛ ልምድ፤ ዲስፕሊንና የቡድን ብቃት አገልግላለች:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የግሎባል አትሌቲክስ አባል የነበረች ሲሆን ለረጅም ጊዜያት አብሯት የሰራው ማናጀሯ ማርክ ዌትሞር ይባላል፡፡  
የሁለቱ የኢትዮጵያ ታላላቅ ኦሎምፒያኖች ጥሩነሽና ገንዘቤ ዲባባ ታላቅየዋ አትሌት የሆነችው እጅጋየሁ ፕሮፌሽናል አትሌት ሆና ባሳለፈችው የሩጫ ዘመን በተለያዩ የርቀት ምድቦች ተወዳድራለች፡፡  በረጅም ርቀት 10ሺ እና 5ሺ ሜትር፤ በአገር አቋራጭ፤  በጎዳና ላይ ሩጫ ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሰፊ ልምድ ያገኘች ናት:: ከኮሌኔል ደራርቱ በኋላ ከዲባባ ቤተሰብ ለወጡት የኢትዮጵያና የዓለማችን ምርጥ አትሌቶች የነበራት ከፍተኛ ልምድና   ስኬት  ፈሩን እንደቀደደላቸው በተደጋጋሚ ብዙዎች መስክረዋል፡፡
አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ ባሳለፈችው የሩጫ ዘመን በኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር 1 የብር ሜዳልያ ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር 2 የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች 1 የወርቅ ሜዳልያ፤ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 1 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በዓለም የአትሌቲክስ ፍፃሜ 1 የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም 1 የጎልደን ሊግ ውድድር ያሸነፈች ነበረች፡፡
በረጅም ርቀት በ2004 እ.ኤ.አ ግሪክ፤ አቴንስና በ2008 እ.ኤ.አ ቻይና ቤጂንግ ከተሞች ላይ ሁለት ኦሎምፒኮችን  ለመሳተፍ የበቃች ኦሎምፒያንም ናት፡፡  በ2004 እኤአ የግሪኳ ከተማ አቴንስ ያስተናገደችው 28ኛው ኦሎምፒያድ ላይ እጅጋየሁ የመጀመርያ የኦሎምፒክ ተሳትፏዋን ያገኘችው በውድድር ዘመኑ  ላይ ባስመዘገበቻቸው ሚኒማዎች ነበር:: በመጀመርያ በ5ሺ ሜትር ቋሚ ተሰላፊ ሆና ስትመረጥ በ10ሺ ሜትር ደግሞ  በተጠባባቂነት ነበር የተያዘችው፡፡ ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ግን አትሌት ብርሃኔ አደሬ ከኢትዮጵያ ቡድን አባልነት በአወዛጋቢ ሁኔታ ተሰረዘች፡፡ ይህ ሁኔታም እጅጋየሁ የምትሮጥበት ምድብ ቀያይሯል፡፡ ስለሆነም በአቴንስ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን ቻለች፡፡   በ5ሺ ሜትር ደግሞ አትሌት መሰረት ደፋርን በመተካት ኦሎምፒኩን ተሳትፋለች፡፡ በሁለቱም የረጅም ርቀት ውድድሮች አገሯን በኦሎምፒክ መድረክ ለመወከልም በቅታለች፡፡
አቴንስ ኦሎምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር  ውድድሩ ላይ ለኢትዮጵያ የተሰለፉት ከአክስቷ  የቀድሞ አትሌትና አሁን የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ እና ከወርቅነሽ  ኪዳኔ ጋር ነበር፡፡ በሚያስደንቅ የቡድን ስራ ተጋግዘው ነበር የሮጡት፡፡
እጅጋየሁ የወርቅ ሜዳልያውን ኢትዮጵያ እንድትወስድ ከፍተኛ ጥረት አድርጋ ነበር፡፡ የወርቅ ሜዳልያውን ስትወስድ እጅጋየሁ ደግሞ በሩጫ ዘመኗ ብቸኛውን የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ለማሳካት ችላለች፡፡ በ2008 እኤአ  ቻይና፤ ቤጂንግ  ላይ ሁለተኛውን የኦሎምፒክ ተሳትፎ በ29ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ስታገኝ ደግሞ በ10ሺ ሜትር ተወዳድራ በ14ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰችው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፍተኛውን ስኬት ለማስመዝገብ የበቃችው በ2005 እኤአ በፊንላንድ ሄለንስኪ ላይ በረጅም ርቀት ሁለቱም ውድድሮች ኢትዮጵያን ለመወከል በቅታለች:: በ5ሺ ሜትር እና  በ10ሺ ሜትር ሁለት ነሐስ ሜዳልያዎቭን ለመጎናፀፍ የበቃችበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነበር፡፡
በ2010 እኤአ ላይ በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የተሳተፈችው በሜሞርያል ፔፔ ግሬኮ የ7 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ሲሆን በኬንያዋ ሲልቪያ ኪቤት ተቀድማ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችበት ነው፡፡ የመጀመርያ የማራቶን ውድድሯን ደግሞ  በ2011 እኤአ ላይ በቺካጎ ማራቶን ያደረገች ሲሆን በራሽያዋ ሊሊያ ሾብኩቮ ተቀድማ ነበር፡፡ በወቅቱ የቺካጎ ማራቶኑን ሊሊያ ያሸነፈችው በማራቶን ታሪክ በመጀመርያ ውድድር የተመዘገበ የምንግዜም ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከግዜ በኋላ ይህ ውጤቷ በዶፒንግ በመሰረዙ አሸናፊቱን አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ እንድትወስድ ተደርጓል:: የሆነው የማራቶን ሰዓቷም በመጀመርያ የማራቶን ውድድር የተመዘገበ 2:22:09  ሶስተኛው ፈጣን ሰዓት ነው፡፡

እጅጋየሁና ምርጥ ሰዓቶቿ
3000 ሜትር - 8:35.94 min (2006)
5000 ሜትር - 14:32.74 min (2004)
10,000 ሜትር - 30:18.39 min (2005)
በግማሽ ማራቶን  - 1:16:40 hrs (2001)
በማራቶን  - 2:22:09 hrs (2011)

Read 6077 times