Print this page
Saturday, 08 June 2019 00:00

አንቀጽ 39 - የጥቃቅን አገራት መፈልፈያ

Written by  አስረስ አያሌው
Rate this item
(2 votes)

“--ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች የደሃ ደሃ የሚባሉ ናቸው። ተበታትነው ይቅርና አንድ አገር ሆነው እንኳ ድኅነትን ማሸነፍ አልቻሉም። አንቀጽ 39 ተግባራዊ ሆኖ ከሰማንያ በላይ አገራት ቢፈለፈሉ አገራቱ በጦርነት መታመሳቸውና ሕዝባቸው በረሃብ መርገፉ ሳያንስ፣ እንደ አገር መዝለቃቸው ራሱ አጠራጣሪ ነው።--”
            
             በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ላይ የሚገኘውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መብት ያህል ፖለቲከኞቻችንን የሚያከራክር ጉዳይ ያለ አይመስለኝም። ስለ ጉዳዩ ብዙ የተባለ ቢሆንም አንቀጹን ሳነብ ያስተዋልኳቸውን ነጥቦችና የተፈጠሩብኝን ጥያቄዎች ለማካፈል ወደድኩ።
ብሔር እንጂ ክልል አይገነጠልም
በመጀመሪያ ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” ይላል። ንዑስ አንቀጽ 5 “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ” ለሚሉት ቃላት የሚሰጠው ፍቺ ፍጹም ተመሳሳይ ስለሆነ ሦስቱንም እንደ አንድ ቆጥረን ለውይይት እንዲያመቸን ብሔር በሚለው እንቀጥል። በዚህ መሠረት አንቀጽ 39 ተግባራዊ ቢደረግ፣ ኢትዮጵያ ወደ ዘጠኝ ሳይሆን ከሰማንያ ወደ ሚበልጡ ጥቃቅን አገራት ትገነጣጠላለች ማለት ነው።
አሁን ካሉት የአፍሪካ አገራት ቁጥር በላይ የሆኑ ከዞንና ከወረዳ የማይሻሉ ጥቃቅን አገራት፣ ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ተጨናንቀው ሲኖሩ ይታያችሁ። በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚሰፍነው ፍጹም ድኅነት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የሀብትና የድንበር ግጭት፣ እልቂትና ውድመት ሲያስቡት እንኳ ይዘገንናል። ዳሩ ይህ የመገንጠል መብት፤ “በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ” እንደሆነ መዘንጋት የለብንም።
ለመሆኑ በኢትዮጵያ የሚኖሩት ብሔሮች በ9 ክልሎች የተጠረዙት ለምንድነው? ትክክለኛ የብሔር ፌደራሊዝም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ ከሰማንያ በላይ ናቸው የሚባሉት ብሔሮች (ከ200 እንደሚበልጡ የሚናገሩም አሉ) በሙሉ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች መሆን ነበረባቸው። በኦሮሞ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሶማሌና ሐረሪ ብሔሮች ስም የሚጠሩ ክልሎች አሉ። ሆኖም ክልሎቹ መጠሪያቸውን ካገኙበት ብሔር ውጭ ሌሎች ብሔሮችም ስለሚኖሩባቸው፣ ብሔርና ክልል መደባለቅ የለበትም። የተቀሩት ብሔሮች ግን አንድም በስድስቱ ክልሎች ውስጥ በአናሳነት አልያም በደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ውስጥ ታጭቀው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል። በአንድ ክልል ለመካለል የጠየቁት መቼ ነው? እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው እኩልነት ተረጋግጧል የሚባለው።
የራያን ጉዳይ እዚህ ጋ ላንሳ። ሲጀመር የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ የሚለው አነጋገር፣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው። የራያ ሕዝብ ራሱን የቻለ ብሔር ስለሆነ፣ አማራ ወይም ትግሬነትን የሚመርጥበት ምንም ምክንያት የለም። ከፈለገ ክልል፣ አልፎ ተርፎም ሉዓላዊ አገር መሆን መብቱ ነው። ይሁንና የትግራይና የአማራ ልሂቃን፣ ራያ ትግሬ ነው፣ የለም አማራ ነው በሚል ሙግት የብሔሩን ህልውና እየካዱ ናቸው።
አንቀጹ የመገንጠል መብት “በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” እንደሚል አንርሳ። ስለሆነም ጠ/ሚ አብይ ዐቢይ አሕመድ ‘ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች፤ በኢትዮጵያ አንድነት አንደራደርም፣ ለዚህ ስንል ማሠርና መግደል ቢኖርብንም እንኳ እናደርገዋለን’ ወዘተ ሲሉ ይህን መብት እየገደቡ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የመገንጠል መብትን ያረጋገጠ ሕገ መንግሥት ይዞ፣ ስለ አንድነት መስበክ ተላላነት ነው። በተጨማሪም ዐቢይና ቡድናቸው  አገሪቱ የመበታተን አደጋ በተጋረጠባት ወቅት ደረስንላት ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማል። በበኩሌ መገንጠል ሕገ መንግሥታዊ መብት ከሆነ፣ መብትን በተግባር ማዋል እንደ አደጋ የሚቆጠርበት ምክንያት አይገባኝም። ምናልባት ማለት የፈለጉት አገሪቱ ላይ አንዣብቦ የነበረውን እልቂት አስቀርተናል ከሆነ ሊያስኬድ ይችላል። ሆኖም የአገሪቱ በአንድነት መቀጠል አሁንም ዋስትና የለውም። በነገራችን ላይ የመገንጠል መብትን ያለገደብ ባረጋገጠው ሕገ መንግሥት ምሎ የሚገዘተው ኢህአዴግ፤ የመገንጠል ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ የማቅረብ መብታቸውን ገድቦባቸው፣ መሣሪያ ያነሱትን ኦነግና ኦብነግ በአሸባሪነት ፈርጆ ሲዋጋ መኖሩ የሚያስተዛዝብ ነው።
ከክልልነት ይልቅ አገር መሆን ይቀላል
‘የመገንጠል ጥያቄው በብሔሩ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በ2/3ኛ የድምፅ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ መረጋገጥ’ አለበት። ለመሆኑ ይህ የሕግ አውጪ ም/ቤት በእርግጥ አለ? እያንዳንዱ ብሔርስ የራሱ የሕግ አውጪ ም/ቤት አለው? ለምሳሌ የአማራ ብሔር ሕግ አውጪ ም/ቤት፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ም/ቤት ነው? ከሆነ የም/ቤቱ አባላት አማሮች ብቻ አይደሉም። ስለዚህ በአማራ የመገንጠል ጥያቄ ዙሪያ ም/ቤቱ ሲመክር አማራ ያልሆኑት የም/ቤቱ አባላት ከአዳራሽ ይወጣሉ ማለት ነው? አማራ ለመገንጠል ቢወስን በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት የአገው፣ አዊ፣ ኦሮሞ፣ ቅማንት፣ ወዘተ ብሔሮች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? አማራ ሉዓላዊ አገር ሆኖ፣ እነዚህ ብሔሮች ግን በኢትዮጵያዊነታቸው መቀጠል ይችላሉ ወይስ የአማራ ዜግነት በግድ ይጫንባቸዋል? ይህ በየትኛውም አካባቢ ለሚኖሩ አናሳ ብሔሮች መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ይኖሩ የነበሩት የጌድኦ ተወላጆች የተፈናቀሉት አናሳ ስለሆኑ እንደነበረ አይረሳም።
በዚህ አያበቃም፤ በአንቀጽ 39 መሠረት፣ በአማራ ክልል ውስጥ በልዩ ዞን የሚተዳደረው የኦሮሞ ብሔር ተገንጥሎ አገር መሆን ይችላል። ሁኔታውን አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሉዓላዊ አገር ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ግን በኢትዮጵያ ግዛትነቱ ሊቀጥል መቻሉ ነው። የአዲሱ አገር ስም ማን ይባል ይሆን? Little Oromia? Northern Oromia? New Oromia? ወይስ ሌላ?
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚደንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር፣ ሐምሌ 2010 ዓ.ም. አስፈላጊውን ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታ ሳያሟሉ ተገንጥለናል ማለታቸውና ይህን ተከትሎ የቀሰቀሱት ዐመፅ ለውድቀት ዳረጋቸው እንጂ ለመገንጠል ማሰባቸው ፍጹም ሕጋዊ ነበር። በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ የክልሉን ም/ቤት ሰብስበው በ2/3ኛ ድምፅ የመገንጠል ጥያቄውን አፀድቀው፣ ለፌደራል መንግሥት በመላክ ሕዝበ ውሳኔ እስከሚካሄድ በትዕግስት ቢጠብቁ ኖሮ፣ በወንጀላቸው ሳይጠየቁ የሉዓላዊ አገር መሪ በሆኑ ነበር።
በነገራችን ላይ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፤ አንድ ብሔር ክልል ከመሆን ይልቅ ሉዓላዊ አገር መሆን ይቀለዋል። በአንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት፤ የብሔሩ ም/ቤት ቤት የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርበው ለፌደራል መንግሥት ሳይሆን ለክልሉ ም/ቤት ነው። ለምሳሌ የኩናማ ብሔር ክልል መሆን ቢፈልግ ጥያቄውን ለትግራይ ክልል ም/ቤት ያቀርባል። ም/ቤቱ ውስጥ ደግሞ ትግራዋዮች አብላጫ ቁጥር እንደመያዛቸው መጠን ጥያቄውን ለማፈንና ሕዝበ ውሳኔ እንዳይካሄድ ለማደናቀፍ መሞከራቸው የማይቀር ነው። ከአማራና ቅማንት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ያው ነው። በአንጻሩ አንቀጽ 39ን ካነሳን አንድ ብሔር የመገንጠል ጥያቄ የሚያቀርበው በቀጥታ ለፌደራሉ መንግሥት ስለሆነ ጥያቄው ከእሱ በቁጥር በሚልቅ ሌላ ብሔር ከመዋጥ ይድናል። በእርግጥም ኩናማና ቅማንት ከክልልነት ይልቅ አገር መሆን ይቀላቸዋል።
አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው” ይላል። እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት በደቡብ ክልል 10 ገደማ የሚሆኑ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ለክልሉ ም/ቤት አቅርበዋል። ሆኖም ም/ቤቱ የሲዳማ ዞንን ጥያቄ ብቻ ተቀብሎ፣ የሌሎቹን ጥናት ይደረግበት በሚል በይደር አቆይቶታል። አንቀጹ በማንኛውም ጊዜ ክልል መሆን እንደሚችሉ እየደነገገ፣ የአንዱን ጥያቄ ተቀብሎ የሌሎቹን ግን ይታሰብበት ማለት ፍጹም አድሏዊና ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ነው። ለነገሩ የሲዳማ ዞን ጥያቄ ራሱ ከቀረበ 1 ዓመት ቢጠጋውም፣ የክልሉ ም/ቤት እስካሁን ሕዝበ ውሳኔ አላደራጀም። እዚህ ላይ ሕዝበ ውሳኔ የማደራጀት ኃላፊነት፣ የምርጫ ቦርድ የሚመስላቸው አንዳንድ ወገኖች ተቋሙን አላግባብ ሲተቹ ታዝቤያለሁ።
ሕዝበ ውሳኔ
ወደ አንቀጽ 39 አተገባበር ስንመለስ የመገንጠል ጥያቄው፣ በ2/3ኛ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ የፌደራል መንግሥት በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት ይጠበቅበታል። ሦስት ዓመት የመጨረሻው የጊዜ ወሰን ነው እንጂ ከዚህም ሊያንስ ይችላል። ይሁንና የ3 ዓመቱ ጊዜ ለምን አስፈለገ? ብሔሩ እስከ መገንጠል ያለው መብቱ ያለ ገደብ የተጠበቀ ከሆነ የጊዜ ገደብም ሳያስፈልግ፣ በቀጥታ ወደ ሕዝበ ውሳኔው ለምን አይገባም? ሕዝብ እንዲወያይበት ነው እንዳይባል የሕዝብ ሚና መወያየት ሳይሆን በሕዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጠት ብቻ ነው። በዚህ ላይ የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ ሌሎቹ ብሔሮች መገንጠል የፈለገው ብሔር ምን እንደጎደለበትና ምን ቢደረግ ውሳኔውን ሊቀይር እንደሚችል የመደራደር መብት የላቸውም። የሚያሳዝነው ብሔሩ ከተገነጠለ በኋላ ዳግም የሪፐብሊኩ አባል የሚሆንበት አንዳችም መንገድ አለመኖሩ ነው።
መቼም ሕዝበ ውሳኔው እስከሚካሄድ ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ የብሔሩ ም/ቤት የመገንጠል ጥያቄው ተቀባይነት እንዲያገኝ በስፋት መቀስቀሱ ስለማይቀር፣ 51 በመቶ ድጋፍ ማግኘት አዳጋች አይሆንም። እንግዲህ 49 በመቶው የብሔሩ ተወላጅ አንድነትን ቢመርጥም እንኳ ውጤቱን ማስቀየር አይችልም። ምናልባት በኢትዮጵያዊነቱ ሊቀጥል ይችል ይሆናል። ሆኖም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሁለት አገር ዜግነት ይኖራል ማለት ነው። ይህን ተከትሎ የሚመጣውን መፈናቀልና የቤተሰብ መለያየትም ማሰብ ይኖርብናል።
በንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት፣ የአንድ ብሔር ሉዓላዊ መሬት፣ ብሔሩ የሰፈረበት መልክዓ ምድር ነው። ለምሳሌ የጉራጌ ብሔር ሉዓላዊ መሬት የቱ ነው? የጉራጌ ዞን ነው? በእኔ ግምት በዞኑ ውስጥ ከሚኖረው የብሔሩ ተወላጅ ብዛት የማይተናነስ ቁጥር ያላቸው ጉራጌዎች፤ በመላ አገሪቱ ተሰራጭተው ይኖራሉ። ታዲያ እነዚያ ሁሉ አካባቢዎች የጉራጌ መሬቶች ናቸው ማለት ነው? ጉራጌ ቢገነጠል ይዟቸው መሄድ ይችላል? ጥያቄው ለወላይታው፣ ለጋሞው፣ ለስልጤው፣ ለሀድያውና ለሌላውም ተመሳሳይ ነው።
እናም ብሔሩ በሰፈረበት መልክዓ ምድር የሚኖሩ ተወላጆች፤ ሙሉ በሙሉ መገንጠልን ቢደግፉ እንኳ ቁጥሩ ከእነሱ የማይተናነሰው በሌላ አካባቢ የሚኖር ጉራጌ አንድነትን መምረጡ የሚቀር አይመስለኝም። ምክንያቱም የጉራጌ ብሔር መሬትን የሙጥኝ ብሎ በግብርና ከመተዳደር ይልቅ በሁሉም አቅጣጫ ተበትኖ በንግድ ሥራ ላይ እንደመሰማራቱ መጠን፣ ለዚህ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ የሚበጀው አንዲት ዞን ይዞ መገንጠል ሳይሆን ከሌሎች ብሔሮች ጋር በአንድነት መኖር ነው። እንግዲህ ይህ ባተሌ ሕዝብ ነው፤ በአንድ ሕዝበ ውሳኔ አማካኝነት በአንድ ሌሊት የውጭ ዜጋ ሆኖ የሚያድረው።
 የጥቃቅኑ አገራት የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች የደሃ ደሃ የሚባሉ ናቸው። ተበታትነው ይቅርና አንድ አገር ሆነው እንኳ ድኅነትን ማሸነፍ አልቻሉም። አንቀጽ 39 ተግባራዊ ሆኖ ከሰማንያ በላይ አገራት ቢፈለፈሉ አገራቱ በጦርነት መታመሳቸውና ሕዝባቸው በረሃብ መርገፉ ሳያንስ፣ እንደ አገር መዝለቃቸው ራሱ አጠራጣሪ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያን የከበቧት አገራት ተበታትና ሲያገኟት መሬቷን መቀራመታቸውም አይቀርም። ያኔ ጂቡቲ እንኳ ሳትቀር የኢትዮጵያ ቁራሽ ይደርሳታል። አገር እሆናለሁ ያለ ብሔር ሁሉ፣ ህልውናው እስከ ወዲያኛው ያከትማል።
ዳሩ አንቀጽ 39 የማይሸራረፍ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። እንደ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፤ ነጋ ጠባ ስለ አንድነት እየሰበኩ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ማስከበር አይቻልም። ወይ አንደኛችንን ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል ዛሬውኑ መነጋገር እንጀምር። ሕገ መንግሥቱም ለዚህ በሩ ዝግ አይደለም። አንቀጽ 39 የሚገኘው መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በሚለው ምዕራፍ 3 ሥር ነው። ይህን ምዕራፍ ለማሻሻል ሁሉም የክልል ም/ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቅ አለባቸው። (ማሻሻያውን ማን እንደሚያቀርበው ባይታወቅም) ይህ እንደምንም ከተሳካ ማሻሻያው በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ም/ቤቶች 2/3ኛ ድምፅ ማግኘት የሚከብደው አይመስለኝም። ምናልባት ያን ጊዜ ለየትኛውም ብሔር ዋስትና የማይሰጠው አንቀጽ 39፣ ከነአገር የማፈራረስ ተልዕኮው ተወግዶ፣ ስለ አንድነት ማውራት ትርጉም ይኖረው ይሆናል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 571 times