Saturday, 08 June 2019 00:00

“ነብይ ባገሩ እንዲህ ይከበራል” የምስጋናና የኪነ-ጥበብ ምሽት ተካሄደ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ደራሲ ገጣሚ ተርጓሚና ፀሐፌ ተውኔት ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን ለማህበረሰቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ፣ ለመራው መንገድና ላጋራው እውቀት፤ ምስጋናና አክብሮት ለመስጠት የተዘጋጀው “ነብይ ባገሩ እንዲህ ይከበራል” የምስጋናና የኪነጥበብ ምሽት ትላንት በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ በድምቀት ተካሄደ፡፡ ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱና የመሶብ ባህላዊ ባንድ መስራችና ዋሽንት ተጫዋች ጣሰው ወንድም ሃሳብ አፍላቂነት በተዘጋጀው በዚህ የምስጋና ምሽት፤ ገጣሚያን ሰዓሊያንና ሙዚቀኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ ገጣሚና ጋዜጠኛ ተፈሪ አለሙ፣ አርቲስት አበባ ባልቻና አዋቂው በሃይሉ ገ/መድህን ስለታላቁ የጥበብ ሰው ነቢይ መኮንን የሚያውቁትን ለታዳሚ ገልፀዋል፡፡
ሰዓሊያን በበኩላቸው ነቢይን እንደ ገጣሚ፣ እንደ ተርጓሚ፣ እንደ ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ምን ሊመስል ይችላል በሚል በገባቸው መጠን በመድረኩ ላይ በስዕል ገልፀውታል፡፡ በተጨማሪም ገጣሚያኑ ጌትነት እንየው፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ተስፋሁን ፀጋዬ፣ አበባው መላኩ ደምሰው መርሻ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ምስራቅ ተረፈና ረድኤት ተረፈ የግጥም ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ተፈሪ አለሙና በሃይሉ ገ/መድህን ወግ አቅርበዋል፡፡
“አንድ ሰው በርካታ ስራዎችን ሰርቶ ምንም እንዳልሰራ ሊቆጠር ይችላል፤ ነገር ግን የሰራውን ያበረከተውን መስዋዕትነቱንና አስተማሪነቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ለራሱ ለመንገርና ከፍታውን ለማሳየት፣ ከዛም ራሱን መቃኘት እንዲችል እንዲህ አይነት መድረኮች ወሳኝ ናቸው” ያለው ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ፣ ነቢይ መኮንንም በዚህ መድረክ ሲመሰገንና አክብሮት ሲቸረው ራሱንም ይቃኝበታል በሚል የምስጋና መድረኩ መዘጋጀቱን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፤ የአዲስ አድማስ መስራችና ዋና አዘጋጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 967 times