Monday, 03 June 2019 15:49

ህጻናት ለእግዚአብሔር የጻፉት ደብዳቤ

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(1 Vote)

“ትምህርት ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ የሚተላለፍ የህብረተሰብ ነፍስ ነው” ይለናል፤ ቸስተርቶር፡፡ ሰውን የሚያንፀው አካባቢው ነው -- ያለ ይመስለኛል፡፡ አካባቢ ደግሞ በቤተሰብና በህብረተሰብ ስርዓቶች መልክ ይይዛል፡፡ ወግ፣ ስርዓትና ባህል ይገነባል፡፡ ግለሰቡ ወጋግራ ይሆናል፤ተሸካሚ፡፡ በእርግጥ፤ ማህበረሰብ የግለሰቡ ሰብዕና እስኪዳብር ያንፀዋል፡፡ መንገዶቹ መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
[በኛ ጊዜ መደበኛ ትምህርት አሰጣጡ ጡቻና ዱላ የበዛበት ነበር፡፡ በተለይ የቤት ሥራ ሳንሰራ ከገባን ግርፋቱ፣ በአሸዋ ላይ መንበርከኩና ዛቻው ከባድ ነበር፡፡ ይኸው ትውልድ ስራም ይዞ ዛቻ፣ የደሞዝ ቅጣትና ኩርኮማ በዝቶበታል፡፡ ይኸው ጉዳይ እኔንም ተጠቂ አድርጎኛል፡፡ አጉል ልማድ፡፡ ኸረዲያ! እንደ እባብ ሰንኮፍ አውልቀን ካልጣልነው...ይበላናል፡፡]
ልጆች፤ የብሩህ ህሊና ባለቤቶች ናቸው፡፡ በቀላሉ ይደሰታሉ፤ በቀላሉ ያዝናሉ፡፡ ስሜታቸው ከህሊናቸው የራቀ ነው፡፡ ምናባቸው የፈለጉት ቦታ ይወስዳቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የምናብ ክህሎታቸውን ለማረቅና ለሚፈለገው አላማ ለማዋል እድል ይሰጣል፡፡ ህሊናቸውን ለማበልፀግም ያገለግላል:: የፈጠራ ችሎታቸውን ለመፈተሽ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ተፈጥሮ፤ የሚያፈቅራትን ልብ በጭራሽ አትከዳምና ከህፃናት ጋር ትወግናለች፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በማስተምርበት “የሳውዝ ዌስት ትምህርት ቤት” የአምስተኛና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ለእግዚአብሔር የፃፏቸውን ደብዳቤዎች  አቀርባለሁ፡፡ (የሰላምታ ደብዳቤ አፃፃፍ ክፍለ ጊዜ ላይ ለተግባር የሰሩት ነው)  እነሆ፦
***
ውድ እግዜር፤ ደህና ነህ? እኔ ደህና ነኝ፡፡ ሰዎች በጣም ይወዱሀል፤ አንዳንዶቹ ይጠሉሀል፡፡ አሁን ይሄንን ልነግርህ አይደለም የምፅፈው፤ ለሌላ  ነገር ነው፡፡ ሌላ ነገር ያልኩህ ጥያቄ ልጠይቅህ ነው:: ለዚህም ሰበብ አለኝ፡፡ ጥያቄዬ ፤ ለምንድን ነው ምኞት የማይቻለው? ምኞት በጣም ጥሩ ነዉ:: ሰዎች ደግሞ ብዙ ምኞት አላቸው፡፡ ስለዚህ ምኞታችን እንዲሳካ አድርግ፡፡ ጥያቄዬን ስለሰማህ አመሰግናለሁ፡፡
(ከሁንዴ ጌትነት፣ጀሞ፣ ክፍል 6ኛ)
ይህ ደብዳቤ ፍትህ የተጠማ ነው፡፡ ተጠያቂ ቢያደርግም፣ ምድራዊ የህብረተሰብ ስርዓቶችንም የሚሸነቁጥ ነው፡፡ በርግጥ ምኞት በራሱ ምንድን? እንዴትስ ነዉ ትክክለኛነቱ የሚታወቀው? ወይስ ምኞት የሚባል ነገር ሳይሆን መኖር ነዉ ያለው? ምኞት እንደ ግለሰብ፣ እንደ ማህበረሰብና እንደ ሀገር ይለያያል? የትኛውስ ይቀድማል? እኒህና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይርመሰመሳሉ፤ ደብዳቤውን ሳነበው፡፡
በእርግጥ መልስ መሻቴ መልሶ ወደ ልጆቹ ይወስደኛል፡፡ ምክንያቱን በግልፅ ባልረዳውም እወዳቸዋለሁ፡፡ የተምታታውን አኗኗራችንን በንፁህ ህሊና ቅርፅ ለማስያዝ ይጥራሉ፡፡ ምናባቸው ውብ ነው፡፡ እጅግ አብዝተው ደህንነትን ያሳድዳሉ፤ ሰላም ወዳዶች ናቸው፡፡ ሰላምን የመሻታቸው መነሻ የማህበረሰብ መጎሳቆል ነው፡፡ የሰላም ጥያቄያቸው ደግሞ ጥልቅ ነው፡፡ ብርታቱ አንገታችንን ያስደፋል፡፡ እነሆ ከጥልቅ ትዝብት የፈለቀ ደብዳቤ፦
***
ለእግዜር ሰማይ ቤት
ውድ እግዝሄር! ለጤናህ እንዴት ነህ?
እኔ የምፈልገው የኔቢጤዎች ጤናቸውና መኖሪያቸው እንዲስተካከልላቸው ብቻ ነው፡፡
እስካይህ ቸኩያለሁ!!
(ከሜሪ ክብሮም፣ ጀሞ፣ ክፍል 5ኛF)
***
ደብዳቤው የማህበረሰቡን ህፀፅ አጉልቶ ያሳያል:: በተለይም ይህ ዘመን እንደ ህብረተሰብ አሳፋሪ ስራ የተሰራበት ወቅት ነው፡፡ ልጆቻችንም የችግሮቻችን ሰለባ ሆነዋል፡፡ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ በርግጥ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር በአቤቱታ መልክ ቢያቀርቡትም፣ ችግሩን የሰው ልጅ የፈጠረው መሆኑን ጠንቅቀው ያውቁታል፤ ጥያቄዎቹ ማንን እንደሚመለከቱም ጭምር ይለያሉ:: (እነሆ ከምጡቅ ምናብ ባለቤት ከሆነው ንቁ ተማሪ ኢዮስያስ ማዕረጉ  የተሰነዘረ ትዝብት፡፡)
***
የሰላምታ ደብዳቤ
ከኢዮስያስ ማዕረጉ
ምድር/ኢትዮጵያ/ጀሞ
ቀን፦20/06/2011ዓ.ም
ለእግዜር
አድራሻ፦ ሰማይ ቤት
ውድ እግዜር ሆይ! ለጤናህ እንደምን አለህ:: ስምህ የተመሰገነ ይሁንና እኔ ደህና ነኝ፡፡
እንደምታውቀው በተለያየ ነገር  ወይም በዜና ላይ የምንሰማው፤ ጦርነት አልያም ይሄ በሽታ ይሄን ያህል ሰው አጠፋ የሚል ነው፡፡ ታድያ እኔ የምጠይቅህ ነገር ቢኖር አንድ ነው፡፡ እሱም ሰላምና ጤናን ነው:: በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍንና ጤነኛ እንድንሆን ነው፡፡ ሌሎቹን ነገሮች ሰው ስለፈጠራቸው ራሱ ይፈታቸዋል፡፡ እነዛን ግን አንተ እርዳን፡፡
                          ኢዮሲያስ ማዕረጉ
                            ፊርማ
       ያልኩህን እስተምትፈፅም ድረስ ደስተኛ ሁን!!
(ከኢዮሲያስ ማዕረጉ፣ ጀሞ፣ ክፍል 5ኛF፣ 2011ዓ.ም)
***
“ህፃናትን ወደ እኔ ይምጡ አትከልክሏቸው”  የተባለው ለዚህ ይሆን? አጃኢብ ነው፡፡
የግለሰብ፣ የማህበረሰብ፣ የሀገርና የአለም ደህንነት እንዳይናጋ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ይተቻሉ:: ከፍ ሲልም ፈጣሪን ይጠይቃሉ፡፡ ይሞግታሉ:: የኖሩበት ህብረተሰብ ያወረሳቸውን ግንዛቤ መነሻ በማድረግ ሞራላዊ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ እንደኔ  እንደኔ፤  ህብረተሰብ የማይጠብቀውንና የማይኖረውን ሞራላዊ እሴት ለምን  ገነባ? እያሉ የሚሳለቁ ይመስለኛል፡፡ ድህነትን አጠፋለሁ እያለ  ድህነትን የሚያስፋፋ ከሆነ፣ ሰላም አሰፍናለሁ እያለ የሚያፈናቅል ከሆነ፣  የእሴት ዋጋው ምኑ ላይ ነው? ያሉ ይመስለኛል፡፡ ለዛሬ አንድ ልጨምርና ላብቃ፡፡ ለሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ እነሆ፦
***
ውድ እግዚአብሔር! እኔ ስሜ ሮቤል ነው፡፡ እንዴት ነህ ግን፡፡ አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ:: ሰዎችን የሰራኸው በጭቃ ነው እንዴ? ያው ሰው ይሰራል የሚባለው ከጭቃ  ነው፡፡ ወደ ምድር እስክትመጣ ጓጉቻለሁ፡፡ የዓለም መጨረሻ መቼ ነው? አሁን ነው?
(ከሮቤል ፀጋዬ፣ ጀሞ፣ ክፍል 5ኛG)
***
የሚከነክኑና እረፍት የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው:: እንደ ሀገር ትውልዱን የሚመጥንና ለቀጣይ ህልውናው ሀይል የሚያስታጥቅ ስራ እንስራ፤ መልዕክቴ ነዉ፡፡ ኸረ ወዲያ !! (ከልጆቼ ደብዳቤዎች  የስሜት ማማ ላይ ብንሸራሸር ይሻለኛል::) የጥበብ ዋጋዋ ምንድን ነው! መኖር እንጂ፡፡
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1411 times