Saturday, 02 June 2012 10:34

ባፋና ባፋናዎች ለዋልያዎቹ ክብደት ሰጥተዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

‹ጨዋታው 11ለ11 ነው› ስቴቨን ፒናር

ዋልያዎቹ በሚል ስሙ የሚጠራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ነገ በሩስትንበርግ ከተማ በሚገኘው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም ደቡብ አፍሪካን ሊገጥም ነው፡፡ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ዋልያዎቹ የተሰኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባፋና ባፋና ከሚባለው የደቡብ አፍሪካ  ብሄራዊ ቡድን በ71 ደረጃዎች ዝቅ ብሎ 138ኛ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን ከመሰረቱ አራት አገራት መካከል ሲሆኑ በኢንተርናሽናል ግጥሚያ ሲገናኙ የነገው ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡  የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃናት፤ ዋና አሰልጣኙ እና ታዋቂ ተጨዋቾች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከባድ ግምት እንደሰጡ ሰሞኑን በተሰራጩ ዘገባዎች ተስተውሏል፡፡ በ2014 በብራዚል ለሚስተናገደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን የሚደረገው የምድብ ማጣርያ  ትናንት ተጀምሮ ዛሬና ነገ በሚደረጉ 20 ጨዋታዎች ሲቀጥል የማጣርያው ሂደት 15 ወራት  የሚወስድ ይሆናል፡፡

በምድብ 1 ያሉት ከደቡብ አፍሪካና ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ሌሎቹ ብሄራዊ ቡድኖች መካከለኛው አፍሪካና ቦትስዋና ዛሬ በባንጉዊ ይጫወታሉ፡፡ባለፈው ማክሰኞ ምሽት የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን በአዲስ አበባ በኩል ወደ መካከለኛው አፍሪካ ከተማ ባንጉዊ ትራንዚት ሲያደርግ መጉላላት ገጥሞታል፡፡ ዜብራዎቹ የተሰኘው የቦትስዋና ልዑካን በኢትዮጵያ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ቪዛ ባለመያዙ በኢምግሬሽን ሃላፊዎች ለስድስት ሰዓት በአየር ማረፊያው እንዲቆይ መደረጉን ሜሜጊ ኦንላይን ዘግቧል፡፡

የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን አባላትን ትራንዚት ቪዛ በኢትዮጵያ የሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ የሚያስጨርስበት ጊዜ ስላልነበረው ልዑካኑ ከአየር ማረፊያው ወጥቶ በሆቴል ለመቆየት ፍላጎት ቢኖረውም ሳይፈቀድለት መቅረቱን ዘገባው አውስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ኢምግሬሽን ህግ መሰረት ከኬንያ እና ከጁቢቲ ዜጎች በቀር ለሌሎች አገራት ቪዛ የሚጠይቅ ሲሆን የቦትስዋና ልዑካን በንግድ ወይም በቱሪስት የቪዛ ፈቃድ ባለመያዛቸው ከአየር ማረፊያው መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡  በቀጣይ ሳምንት የምድብ 1 የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች በሁለተኛ ዙር ግጥሚያ ሲቀጥሉ  አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ መካከለኛው አፍሪካን ስታስተናግድ ቦትስዋና በዋና ከተማዋ ጋብሮኒ የምትጫወተው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ነው፡፡

የባፋና አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ግጥሚያውን በጥሩ ጨዋታ ባይሆን እንኳን ማሸነፍ ግድ መሆኑን ሲገልፁ ዋልያዎቹ ተስፋ በማይቆርጡበት አጨዋወታቸው፤ በደንብ በተገነባ የተከላካይ መስመራቸውና ፍጥነት ባላቸው አጥቂዎች ሊያስቸግሩን ይችላሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአማተሮች ስብስብ አይደልም ስለዚህም በቀላሉ አንመለከታቸውም ያለው ደግሞ የባፋናዎች አምበል ስቴቨን ፒናር ነው፡፡ በእንግሊዙ ቶትንሃም ሆትስፐርስ  የሚጫወተውና በፕሪሚዬር ሊጉ ለኤቨርተን በውሰት ተሰጥቶ ደንቅ ብቃት ያሳየው ስቴቨን ፒናር ግጥሚያው 11ለ11 የሚደረግ በመሆኑ ከባድ ግምት የሚሰጠው ነው ብሎ ለኪክኦፍ መፅሄት ሲናገር ማጣርያውን በድል መጀመራችን ወሳኝ ነው በማለት ለቡድን አጋሮቹ የማበረታቻ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

የቀድሞው የባፋናዎቹ አምበል ሉካስ ሬዴቤ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ውጤታማነቱ መመለሱን የሚያሳይበት መሆን  እንዳለበት አሳስቧል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ከ2 ዓመት በፊት የአለም ዋንጫን ከተሳተፈ በኋላ እምብዛም ስኬት እንዳልነበረው ያስታወሰው ራዴቤ ሁለት አፍሪካ ዋንጫ አምልጠውት ለ2013 የአፍሪካ  ዋንጫ በአዘጋጅነት ማለፍ ችሏል ብሎ ለስምንት ወር ድል የራቀው ቡድኑ ለ2014 የዓለም ዋንጫ በምድብ ማጣርያ በኢትዮጵያ ለሚጀምረው ጉዞ ከባድ ጥረት እንደሚጠበቅበት ተናግሯል፡፡ጎል ዶት ኮም በጨዋታው  ውጤት ላይ ከአንባባቢዎቹ ባሰባሰበው ድምፅ በነገው የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ጨዋታ ማን ያሸንፋል በሚል የተተነበዩ 3 ግምቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ ከትንበያዎቹ 26.09 በመቶ ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጭ ደቡብ አፍሪካን 2ለ0 ማሸነፏ መገመቱ ቀዳሚ ሲሆን 8.7 በመቶ አሁንም ኢትዮጵያ 1ለ0 ታሸንፋለች የሚል ድምፅ ተሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ 8.7 በመቶ  ድምፅ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ 3ለ0 እንደምታሸንፍ ተገምቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በደቡብ አፍሪካ ክለቦች ሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ፓይሬትስ የተጫወተው ፍቅሩ ተፈራን በወሳኝ ተጨዋችነቱ ያነሳው አንድ ዘገባ ፍቅሩ ምንም እንኳን አሪፍ አጥቂ ባይሆንም ባለው ከፍተኛ የታጋይነት ሞራል ሊያስቸግር ስለሚችል እሱን ለማቆም የባፋና ተጨዋቾች ማቀዳቸውን አትቷል፡፡ ለግብፁ ክለብ ዋዲ ዴልጋላ የሚጫወተው ሳላሃዲን ሰኢድ በናይጄርያ ላይ ባገባቸው ሁለት ጎሎቹ መፈራቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ የባፋናዎቹ አሰልጣኝ በበኩላቸው ጌታነህ ከበደ ስለተባለው የኢትዮጵያ ምርጥ አጥቂ መስጋታቸውን ለስዌታን ጋዜጣ ሲናገሩ የኢትዮጵያ ቡድን በፅናቱ ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ በማለት ቡድናቸው የመጨረሻ ዝግጅቱን በ15 ደቂቃ ልምምድ እና በጂም እንቅስቃሴዎች በማጠናከር ለእሁዱ ጨዋታ በትኩረት ዝግጅቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው 26 ተጨዋቾችን የያዘ ሲሆን በእንግሊዝ፤ሆላንድ፤ቤልጅዬምና ስዊድን የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎችን ስብስቡ አካትቷል፡፡ ባፋና ባፋና ምርጥ የተባሉ አጥቂዎችን ከአገሪቱ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ማሰባሰቡን የገለፀው ስዌታን ጋዜጣ  እነ ሻባላላ፤ ኑምቬቴና ቤኒ ማካርቲ ያሉበት የአጥቂ መስመር በውድድር ዘመኑ በደቡብ አፍሪካ ሊግ በድምሩ 60 ግቦች ያስቆጠሩ ተጨዋቾች መያዙ በብዙ ግብ ኢትዮጵያን ለማሸነፍ  ተስፋ እንደሚሰጥ አውስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅት በኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታ አለመታጀቡ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ አጀማመሩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡  ብሄራዊ ቡድኑ አንድ ወር እና ከዛ በላይ እንዲዘጋጅ በፌደሬሽኑ መታሰብ ቢኖርበትም ይህን ማድረግ አልተቻለም፡፡  የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች እጅግ በጣም የሚያምር ጨዋታ መጫወት ብቻ ሳይሆን ያለባቸውን የአጨራረስ ችግር  በመቅረፍ የምድብ ማጣርያውን በከፍተኛ ትኩረት ማድረግ አለባቸው፡፡ በዓለም ዋንጫው ማጣርያ ዋልያዎቹ  በተለይ  ከሜዳ ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣትን መተግበራቸው የማለፍ ተስፋቸውን ያጠናክረዋል፡፡

 

 

Read 3107 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 10:36