Saturday, 25 May 2019 10:12

የገብረ ክርስቶስ ስለታም ግጥሞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


           ቃላትን ቀልቶ፣
አጋብቶና አግባብቶ፣ አሳምሮ ቋጭቶ፣
መብረቅ ሆነው ባርቀው፣ ነደው ተቀጣጥለው፣
ታይቶን ነበልባሉ
ሲያሳዩ ሲነግሩን፣ ሲያስቁ ሲያዝናኑን፣ ሲያረኩ
ሲያድኑ
ሲያሙ ሲያቃጥሉ
በትሁት አዕምሮ፣ በሰጠ ክሂሎት በተባ ልቦና
ተዚመው በውሉ
“አቤት ጥበብ ስራው! ተዓምረ ታምራት! አቤት
ኪነት ኃይሉ
“እሰይ ባለቅኔ እሰየው እሰየው!” ቢያሰኘንም
ቅሉ፣
ብዕሩ ዶልዱሞ፣
ሳይገነዝ ቆሞ፣
መርዶውን እንስማ፣ ቀብር እንጠራ፣ ሳናይ
ተስፋው ከስሞ፡፡
(“የካፊያ ምች”፤ ተፈሪ ዓለሙ)
ንብ ከአበባ እንደምትቀስመው፣ የገጣሚ የልቡ ከንፈር፣ የህይወትን አሮጌና ትኩስ ከንፈሮች ይስማል! … ሳቅዋን ቆርሶ፣ እንባዋን ይጠባል፡፡ እስኪሞት ድረስ፣ በልቡ እንዳትሞት ይዘምራታል፡፡ ሲያሻው ዘልዝሎም በልቡ ግድግዳ ይሰቅላታል፡፡ ተፈሪ ዓለሙ፤ የጥበበኛውን የስጋ ሞቱን የሚመኘው፣ የቁም ሞቱን ተፀይፎ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይቺን የጥበብ ሰው ግጥም፣ ተፈሪ፣ የጥበብ ማማ ላይ ቆሞ፣ በሰንደል ፅፏታል፡፡ መዐዛዋ ሩቅ፣ ፍቅሯና መልኳ ውብ ነው፡፡
ስለ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ሳነሳ፣ የተፈሪ ዓለሙን ግጥም የመረጥኩት፣ በቁም የሞተን የጥበብ ሰው ጥላ፣ የህይወት ጨለማ አድርጎ ስለቆጠረው ነው፡፡ ገብሬ ደግሞ ከፍ እንዳለ፣ እንዳጌጠና የአድናቆት ፉጨት እንደጋበዘን ተሰናብቷልና ነው!
እነዚህ ዘመን የዘለቁ እሸት ግጥሞችን የሚግጡ፣ ወርቃማ ጥርሶች ያሉት ሁሉ፣ እያጣጣማቸው፣ በስሜት ግለት አድማሳትን ይጥሳል ብዬ አምናለሁ:: ባለፈው ጽሁፌ እንዳልኩት፤ ከተራኪ ግጥሞቹ ይልቅ ቀለም የተነከሩት ሌሪኮቹ፣ የልብ ሙዚቃቸው ጣዕም አንሳፋፊ ነው፡፡ ፍቅርና ናፍቆትን ፀንሶ የሚወልደው ይህ ንዑስ ዘውግ፣ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በሚለው ግጥሙ ዘውድ ጭኗል፡፡ ዛሬም ከሌሪኩ ቁና የናፍቆት ግጥሙን ለመዝገን የዳዳኝ፣ ድንኳኖቹ የተሞሉት በዚህ ጣዕም ቅርጽ ስለሆነ ነው፡፡ ምናልባትም በብሩሽ ቀለም ነክሮ፣ በብዕር ቀለም አስምጦ ከፃፋቸው ድንቅ ግጥሞች ውስጥ ሸንጎ መቆም የምትችለውን፣ የጥበብ ፈትል ያገኘሁ መስሎኛል:: “እንደገና” የሚል ርዕስ ያላትን ይህቺን ግጥም፣ በአንድ ወቅት በኢቲቪ  ከጓደኛዬ ጋር በምናዘጋጃት “ብርሃን” በተሰኘች ፕሮግራም፣ በምስል አጅቤ  አቅርቤያት ነበር፡፡
ግጥሟ በእጅጉ መሳጭ፣ ሲበዛ ሥዕላዊ ናት፡፡ የሩቅ ሃገር ደወል፣ የልብ ውስጥ መንኮራኩር ሆና እየወሰደች ትመልሳለች፡፡ ክንፍ አብቅላ፣ አንዳንዴ በናፍቆት ጥርስ ትነቅላለች፡፡ የሰፈር ሥዕል፣ የናፍቆት ሰንሰለት፣ የትዝታ ረሀብ፣ የብቸኝነት ህመም ነገር ናት፡፡ ፈረንጆቹ Home Sickness የሚሉት ዐይነት፡፡  
የስሜታቸው ከፍታ፣ የምትሃታቸው ህመም፣ የሳቃቸው ግርጣት… የስንኞቹን ቀለም ያሳሳው ይመስላል፡፡ (ቀለም ስል የምጣኔውን አይደለም፣ ምትሃታዊ መልኩን እንጂ)
ይናፍቀኝ ነበር …
ዞሮ ዞሮ ከቤት
ይላል የኛ ተረት፡፡
አቧራው ፀሐዩ ይናፍቀኝ ነበር፣
አፈሩ ጠጠሩ ይናፍቀኝ ነበር፣
የመንደር ጭስ ማታ …
ይናፍቀኝ ነበር የሳር ቤት ጥቀርሻው
መደቡ ምሰሶው፣
ማገሩ ግድግዳው፣ አጥሩና ጥሻው
የፈራረሰ ካብ
ግን አቧራው ለምን ናፈቀው ይሆን? በሚኖርበት የሰለጠነው ዓለም፣ በቅቤ የታጠበ የሚመስል አስፋልት እያለለት፣ አቧራን ምን አመጣው? አፈሩና ጠጠሩ ለምን ልቡን ጎሰመው? ይህ መቼም አስገራሚ ስሜት ነው፡፡ የስነ ልቦና ምሁራኑ እንደሚሉት፤ በልጅነት ዕድሜው፣ በኢ-ንቁ አዕምሮው ውስጥ ያጎራቸው ትዝታዎቹ እየተናዱበት ወይም እንደ በቆሎ ተፈልፍሎ ብቅ እያለበት ነው፡፡ ከአፈሩና ጠጠሩ ይልቅ፣ አረንጓዴ ካባ የመሰሉ፣ በአበባ ቀለማት ያጌጡ አደባባዮች ነፍስን ያስደንሱ ነበር፡፡ ግና ናፍቆት እንዲያ አይደለም፤ ንፋስ እንደሚያውለበልባት ሻማ፣ ራስን እያነደደ፣ ገላ ያቀልጣል፡፡ ለካስ ገጣሚ ገብሬ፣ ትዝታ ፈረሱ፣ ልጅነት ደግሞ - ነፍሱ ናት:: እንዴት ቀድዶ፣ ይጥላታል፡፡ ለእርሱ ያገሩ ነገር፣ የህዝቡ ፍቅር… አንዳች ማንፀሪያ የለውም፡፡ “ሀገሬ” በተሰኘው ግጥሙ ላይ ያነፃፀራቸው ነገሮች ለዚህ አብነት ናቸው፡፡
በሀገር መመካት፣
በተወላጅነት፣
በባለቤትነት፣
እዚያ አለ ነፃነት፡፡
አገሬ ሀብት ነው፡፡
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎው ክትፎ ስጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው ቃሪያው ሙክት ሰንጋ፡፡
ጠጁ ነው ወለላ
ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ፡፡
ፍቅር እንዲህ ነው!! “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” አይነት፡፡ በአንድ በኩል ተወላጅነቱ ባለቤትነቱና ክብሩ ናፍቆታል፡፡ ሀገር ውስጥ “ከየት መጣህ?” ወይም አስቴር እንደምትለው “ከየት ነሽ ጥያቄ ሆዴን ያስብሰኛል!” ዓይነት ድምፀት አለው… ቁስል ቆስቋሾች፣ የእንባ ከረጢት ቆፋሪዎች ናቸው፡፡ የባዕድነት ስሜት፣ የብቸኝነት ብርድ! “ባይተዋርነትና ርቀት!”…  አባብተውታል፡፡
ደ‘ሞ ይመጣና ሚዛኑን በዚህና በዚያ ደፍቶ፣ “ጎመኑ ጮማ ነው፤ ቆሎው ክትፎ ስጋ፣ ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ፡፡” ይላል፡፡ ይህን የተጋነነ ማንፀሪያ የተጠቀመው ወዶ አይደለም፡፡ ይሄን የሚፈጥረው የሀገር ስሜት ነው፡፡ ወገን ከጎን ሲኖር፣ የተወለዱበት አፈር ጠረን ውስጥ ሲኮን፣ እንዲህ ነው፡፡ ሁሉም ይጣፍጣል! ናፍቆት ስጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስንም ያከሳል፡፡ ለዚያውም በእነሱ ዘመን ደግሞ ሀገር ዘውድ ናት። ሀገር ኩራት ናት! መሰደድ ሽሽት ነው፡፡ መሰደድ ፍርሃት ነው፡፡ በዚያም የተነሳ በውጭ ሃገር ቋንቋ የሚናገር ሰው ብርቅ ነበር:: ያ -ነው ገብሬን ያማሰለው፡፡ ያ - ነው ያቆሰለው:: በላቡና በእንባው የፃፈ ያስመሰለው፡፡ ጊዜውና ሁኔታው ተጣምረው የፈጠሩት ስዕል ነው፡፡
የገብሬ ገፀ-ሰብ፤ የሳር ቤት ጥቀርሻ ይናፍቀው ነበር፡፡ መደቡ ምሰሶው፣ ማገሩ፣  ግድግዳው ሁሉ… የፈራረሰው ካብ ሳይቀር፡፡ ግጥም ብሎ የታጠረ የግንብ አጥር ባለበት ሀገር እየኖሩ፣ የፈራረሰ ካብ መናፈቅ ህመም ነው፡፡ ናፍቆት ህመም አይደል! ባማሩ ህንፃዎች ውስጥ እየኖሩ ጥቀርሻ መናፈቅ!
ልጅነታችን በውስጣችን ውስጥ የራሱን ዓለምና ከተማ እያፈረሰ፣ የሚኖር ሌላ ሕይወት ነው፡፡ አንዳች የህይወት ገጠመኝ በኮረኮረው ቁጥር ወይ በሳቅ አሊያም በእንባ በህይወታችን ጉንጭ ላይ ሊንቆረቆር ይችላል፡፡ እንደ እሳተ ጎመራ ከልብ ስር የተደበቀው ፈንድቶ፣ እሳት ቀለሙ ሲረጋ የሚይዘው መልክ ዓይነት፡፡
ዛሬ የምንኖረው ህይወት፣ ያንን ጠንካራ ህንፃ የሸፈነ የጨርቅ ድንኳን ስለሆነ ንፋስ በገለበው ቁጥር የጎመራ ጽጌረዳ አበባ ስዕል እናያለን፡፡ የቱንም ያህል ዝቅ ያለ ህይወት ቢኖረን እንኳ ሳቅ የተርከፈከፈበትና ተስፋ የለመለመበት በመሆኑ፣ ከዛሬው በጌጣጌጥና በአሸንክታብ ከደመቀው የዕድሜ ዘመን ይልቅ ይጣፍጣል፡፡ ዕድሜ ወደፊት ሲሄድ ናፍቆት ግን ወደ ኋላ ነው፡፡ ለዚያ ነው ገብረክርስቶስ ወደፊት ሄዶ ወደ ኋላ የሚያንጎራጉረው፡፡
ቀጭን ጠባብ መንገድ በመንደር የሚሮጥ
ቅጠል የሸፈነው፣
    ሣር ያለባበሰው፣
እነዚህ፣ እነዚያ ይናፍቁኝ ነበር፡፡
የተቆላ ቡና፣
    የሚወቀጥ ቡና፣
የጎረቤት አቦል ሁለተኛ፣
የተረጨ ቆሎ የሚያርቅ መጋኛ፣
የሚጨሰው እጣን …
    እንጀራ በመሶብ ወጥ የፈሰሰበት
    ያገልግል እንጀራ የሚቧጠጥ ፍትፍት፣
የክክ ወጥ የሽሮ፣
የሥጋ የዶሮ፣
በመጀመሪያ አደባባዩ፣ ሰፈሩ፣ ቀዬው ናፈቀው:: ቀጠለና የቡናው ሽታ፣ ከዚያ የሙቀጫው ድምፅ፣ የተፈላው ቡና፣ አቦልና ሁለተኛው፣ የቡና ቁርስም አልቀረው! ይህንን የቡና ስርዓት የሚያጅበው ደግሞ ዕጣን ነው፡፡ የዕጣኑን ጉም አመጣው፡፡ ይህ ሁሉ ቁፋሮ፣ በናፍቆት ጥፍሮች ነው፡፡ የልብ መንተክተክ፣ የረሀብ ስሜት ነው፡፡ የተቆላ ቡና የትም ሀገር አለ፡፡ በማሽን ወላፈን ተገርፎ፣ ውስኪ መስሎ ይቀርባል:: ግን በገበቴ አሊያም በሳህን ላይ አድርጎ ጢሱን ማሽተት የኛ ነው፡፡ ጎረቤት ተጠራርቶ፣ አንዷ እመቤት እየፈተለች፣ ወይ ነጠላ እየቋጨች፣ ጨዋታ መጫወት፣ ወግ ማውጋት እዚያ የለም፡፡
ቆሎ መበተን ኋላ ቀር ባህል ነው፡፡ ጥቅምና ፋይዳ የለውም፡፡ ግን እሱም ቢሆን ሲርቁት ይናፍቃል፡፡ ከአድማስ ባሻገር በትካዜ፣ በልብ ጆሮ ላይ ያፏጫል፡፡ እንጀራ በወጥ! እንጀራ በክክ ሽሮ! ፈሰስ አድርጎ መብላት ብርቅ እደለም፡፡ ሲርቅ ግን፣ ያም ቦታ አለው፡፡ ያም ብዙ ስዕል አለው፡፡ መሶብ ከብቦ መብላት ይናፍቃል፡፡ መጎራረስም እንዲሁ:: አገልግል የኛ ነው፤ ፈረንጅ አገር የለም፡፡ ፍትፍት በጣት መቧጠጥም የናፍቆት መግለጫ ኃይል ነው:: እዚህ ግጥም ላይ ተነፃፃሪ ዘይቤ፣ የግጥሙ አጥንት የበረታ ስዕል እንዲፈጥር አድርጎታል፡፡ መግቢያው ላይ ንቡር ጠቃሽ ዘይቤን ተጠቅሟል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ምሰላው ኃያል ነው፡፡ የፎቶግራፍን ያህል ፈዛዛ አይደለም፡፡ በቀራፂ የተሰራ፣ በዐይን የሚታይ ትረካ ይመስላል፡፡
“የሚቧጠጥ ፍትፍት” የሚዳሰስ ምሰላ ነው፡፡ የሚታየው፣ የሚደመጠው ምኑ ቅጡ! ዕ-ብ-ድ ያለ ግጥም ነው!!
ግጥሙ ከዶሮ ወጥ - ወደ መጠጡ ሰፈር ይዘልቃል፡፡  
ይናፍቀኝ ነበር ቅራሪ ጉሽ ጠላ
ይናፍቀኝ ነበር ፊልተር ዞማ ኮላ፡፡
ያገራችን ድግስ …
        ከበሮ ጭፈራው
ዝላዬ እስክስታው፣ ስካሩ ሁካታው፣
ትርክምክሙ ነበር ግፊያው ትንቅንቁ
ኳኳታው እርግጫው ዘፈን ድብልቅልቁ፡፡
“አሸወይና ወይና”
“እስቲ እንደ ጎጃሞች”
“አሲዮ ቤሌማ … ኦሆሆ! ኦሀሀ!”
የቄስ ትምህርት ቤት
    የሕፃናት ድምፅ፣
“ሁ…ሁ..ሂ..ሃ” ዜማ ነበር የናፈቀኝ
የድጌ ጭፈራ ነበር የናፈቀኝ፡፡
        ከበሮ ጽናጽል፡፡
ሆሣዕና ጥምቀት፣
ፋሲካ ሁዳዴና ስግደት
    ቡሄ ሆያ ሆዬ፣
ጠላው ብቻ ሳይሆን ቅራሬም ውል ብሎታል:: ከዚያ በኋላ ወደ ድባቡን ፈጥኗል፡፡ ከበሮ የታጀበ ጭፈራ! … እስክስታው ባይኑ ዞሯል፡፡ ግፊያው ትርክምክሙ ይታየዋል፡፡ እኛ ደግሞ በዚያ ግፊያና ሁካታ ውስጥ ላባቸው ጠብ ጠብ የሚሉ ሰዎች ይታዩናል፡፡ “አሸወይና ወይና” የሚለው ዜማ ወደ ጆሮዋችን ይመጣል፡፡ አሲዮ ቤሌማ .. የቄስ ትምህርት ቤት… የህፃናት ድምፅ!... ይህ አካባቢ ለእኛ ነጠላውን አይታየንም፡፡ የኔታ ጭራቸውን እየነሰነሱ ፊታችን ብቅ ይላሉ፡፡ ኩርኩምም ሊከተል ይችላል፡፡
በዐላቱ… ሆሳዕና ጥምቀት፣ ፋሲካ፣ ቡሄ …በናፋቂው ገፀ ሰብ ልቡና ውስጥ እንደ ችቦ ይነድዳሉ:: ቄጤማ መነስነስ… ዘንባባ ማሰር… ሙልሙል መግመጥ… የግጥሙ ጉዞ አጃቢዎች መሆናቸውን፣ የዳበረውንና የነበረውን የህይወታችንን ሸበጥ እየነቀለ ያቀብለናል፡፡ ነፍሳችን በሳቅ ሻሻቴ ትታጠባለች፡፡
የገብረ ክርስቶስ ግጥሞች ስሜታቸው ኃያል፣ ሳቃቸው ሸራፋ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ሙሉ ሳቅ ስንፈልግ ግማሹን በሀሳባቸው ማጥ ውስጥ ይቀብሩታል፡፡ ሰዓሊው ገጣሚ፣ ገጣሚው ሰዓሊ ነው፡፡ አንዷን ግጥም ሙሉዋን ለማየት ቦታ ይገድበናል፤ በሌላ ቀን ህልም እንለፈው!

Read 2286 times