Monday, 27 May 2019 00:00

ሃይ ባይ ያጡት አጭበርባሪ ደላሎች!!

Written by  አሸናፊ በሪሁን ከseefar
Rate this item
(0 votes)


            “--በቅርቡም ትልቅ ክፍያ የሚያስገኝ ስራ እናስቀጥራችኋለን በሚሉ አጭበርባሪ ደላሎች ተታለው ወደ ፖላንድ ያቀኑ ኢትዮጵያውያን፣ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ እነዚህ ስደተኞችም በተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ቅስቅሳ ተገፋፍተው፣ ከ8 ሺህ ዶላር
እስክ 300 ሺ ብር የከፈሉት፣ በፖላንድ ርዕሰ መዲና ዋርሶ፣ የተሻለ ስራ ታገኛላችሁ ተብለው ነበር፡፡-”
                     
              የካናዳ መንግስት በቅርቡ፣ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት፣ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን  እንደሚቀበል ይፋ ካደረገ  ወዲህ ለህገ ወጥ ደላሎች አዲስ የማጭበርበሪያ ሥራ ተከፍቶላችዋል። ቢቢሲ በአማርኛ ድረ-ገፁ ላይ በቅርቡ እንደዘገበው፤ ይህንን የሰማችው ኑአሚን መኩሪያ፣  የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር ወደ ካናዳ እንደሚወስዷት ቃል በገቡላት  ሰዎች  በኩል እንቅስቃሴ የጀመረችው፡፡ ኑአሚንም ሆነች ጓደኛዋ ወደ ካናዳ እንወስዳለን ያሉትን  ሰዎች በአካል አያውቋውም። ትውውቃቸው ከስልክ የዘለለ አልነበረም፡፡
  በ30ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኘው ኑአሚን፤ የካናዳ ጉዞ ሂደቱን የጀመረችላት ካናዳ የምትኖር የቅርብ ጓደኛዋ ናት:: ኑአሚን በተለያዩ ጊዜያት፣ ለሂደቱም ማስፈፀሚያ በሚል ወደ ካናዳ እንልክሻለን ላሉት ደላሎች፣ ከ30ሺህ ዶላር በላይ  ከፍላለች፡፡ ይሄ ገንዘብ የተከፈለው በተለያየ በአገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ባሉ የባንክ ሂሳቦች ነው። ኑአሚን፤ አራት ሺህ ዶላር ሃገር ውስጥ ባለ የባንክ ሂሳብ ስታስገባ፣ ጓደኛዋ ደግሞ ካናዳ፣ ጣልያን፣ ዱባይና ኬንያ በሚገኙ የባንክ ሂሳቦች ቀሪውን ገንዘብ ለደላሎቹ አስተላልፋለች። ይሄ ሁሉ ብር ፈሶም ግን ደላሎች አልረኩም፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ተጨማሪ ገንዘብ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አላሉም፡፡ በሁኔታው ግራ የተጋቡትና መተማመኛ ያጡት እነ ኑአሚን፣ ይኼን ጊዜ ነው ቆም ብለው ማሰብ የጀመሩት፡፡ ቢዘገዩም በደላሎች እንደተጭበረበሩ አወቁ፡፡  ተጨማሪ ገንዘብ  ሲጠየቁም  አሻፈረኝ ብለው ግንኙነታቸውን አቋረጡ፡፡
የኑአሚን ታሪክ በደላሎች እየተጭበርበሩ ያሉ የበርካታ ኢትዮጵያውያንም ታሪክ ነው፡፡ ዛሬም ወደ አውሮፓ ሀገራት  ለስራ እንልካለን በሚሉ ደላሎችና  ሰራተኛና አሰሪ አገኛኝ ድርጅቶች እየተጭበረበሩ ያሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በቅርቡም ትልቅ ክፍያ የሚያስገኝ ስራ እናስቀጥራችኋለን በሚሉ አጭበርባሪ ደላሎች ተታለው ወደ ፖላንድ ያቀኑ ኢትዮጵያውያን፣ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ እነዚሁ ስደተኞችም በተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ቅስቅሳ ተገፋፍተው፣ ከ8 ሺህ ዶላር እስክ 300 ሺ ብር የከፈሉት፣ በፖላንድ ርዕሰ መዲና ዋርሶ፣ የተሻለ ስራ ታገኛላችሁ ተብለው ነበር፡፡ ፖላንድ ከደረሱ በኋላ ግን ወፍ የለም፡፡ እናም ዛሬ ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ  ሜዳ ላይ ወድቀው  በስቃይ ላይ ናቸው፡፡  ለዜጎችዋ ስራ መፍጠር እየከበዳት ያለችው ፖላንድ፣ አዲስ ስደተኛ ልትቀበል ቀርቶ የአውሮፓ ህብረትን የስደተኞች ፖሊሲ ሳይቀር በመቃወም፣ ስደተኞችን በኮታ የመቀበልን ጥያቄ ውድቅ ያደረገች ሀገር ናት፡፡
በሌላ በኩል፤ ወደ አረብ ሃገራት ሰራተኞች እንዲልኩ ህጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው  ሰራተኛና አሰሪ አገናኝ ድርጅቶች፤ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጭ ወደ አውሮፓ፣ እስያና ሌሎችም  ሀገራት እንልካለን የሚሉ አማላይ  ማስታወቂያዎችን በድረ ገፆቻቸው ላይ በመለጠፍ፣ ማጭበርበራቸውን ቀጥለውበታል:: ለዚህ ደግሞ ሰዎችን ወደተለያዩ የአውሮፓና እስያ ሀገራት ለመላክ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፈቃድ እንዳገኘ ሲያስተዋውቅ  የነበረውና በቅርቡ መግለጫ የተሰጠበት “ኢትዮጵያ ሰራተኛና አሰሪ  አገናኝ” የተባለው ድርጅት  አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ወደተለያዩ አገራት ለስራና ለጉብኝት  ለመላክ ህጋዊ ዕውቅና እንደተሰጠው  በመግለጽና ለዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የድጋፍ ደብደቤ የጻፈለት በማስመሰል ድረ ገፁ ላይ በመለጠፍ፣ ብዙዎችን ሲያጭበረብር ቆይቷል፡፡ ዕውቅና ተሰጥቶናል ባለው ደብዳቤ ላይም ደርጅቱ ወደ ካናዳ፣  እንግሊዝ፣ ጀርመን ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ሰፔን እንዲሁም ከእስያ ሀገራት መካከል ደግሞ ወደ ቻይና፣ ጃፓን፣ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ወደ ሌሎችም ውጭ  ሀገራት በህጋዊነት እንደሚልክ ይገልፃል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ ለድርጅቱ ምንም አይነት ደብዳቤ እንዳልፃፈና ዜጎችም በዚህ የሃሰት ደብዳቤ ተታለው ችግር ላይ እንዳይወድቁ ማስጠንቀቂያ  ሰጥቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ይህን ድርጅትም ሆነ  መሰል ወንጀል የሚፈጽሙ ሌሎች ድርጅቶችን ተከታትሎ ለህግ እንደሚያቀርብም አስታውቋል፡፡
ካናዳ፣ አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ለመሄድ በማሰብ፣ የተጭበረበረ  ቪዛና የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ሲባል ሐሰተኛ ማስረጃዎችን መጠቀም  እንደ ከፍተኛ ወንጀል ይቆጠራል። አገራቱ ሐሰተኛ ማስረጃ መጠቀማቸውን ያረጋገጡባቸውን ስደተኞች፤  በወንጀል ከመክሰስ ባለፈ፣ ዕድሜ ልካቸውን ወደ አገራቸው  እንዳይገቡ እገዳ ሊጥሉባቸው ይችላሉ፡፡
ማንኛውም ሰው ኑሮውን የማሻሻል ፍላጎት ቢኖረውም፣ ይህን ፍላጎቱን ለማሳካት ግን ትክክለኛውንና ህጋዊውን  መንገድ  መከተል ይኖርበታል፡፡ ዜጎች የሥራ ዕድል ተገኝቷል ወይም ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጣችኋል ስለተባለ ብቻ  ገንዘባቸውን በከንቱ ማፍሰስ የለባቸውም:: ከሁሉም  በፊት የመረጃውን ትክክለኛነት ከሚመለከታቸው ተቋማት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄ ለአጭበርባሪ ደላሎች የሚከፈለው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ፤ በአገር ውስጥ የራስን ሥራ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ማሰብ ይገባል፡፡ የግድ ስደትን ከመረጥን ደግሞ እንደነ አሚን አጭበርባሪ ደላሎች እጅ ላይ እንዳንወድቅ  ህጋዊ መንገዶችን ብቻ መጠቀም ይበጃል፡፡
 ሰዎችን ወደተለያዩ የውጭ አገራት እንልካለን በሚል የሚያጭበረብሩ ደላሎችና ድርጅቶች፣ አንድ የሚላቸው ያጡ ይመስላሉ፡፡ ዛሬም ስምና አድራሻቸውን እየቀያየሩ፣ ብዙዎችን ለከፋ ችግርና መከራ እየዳረጉ ነው፡፡  መንግስት  ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ በመላክ፣ ለእንግልትና  ለስቃይ ብሎም ለሞት እየዳረጉ በሚገኙ  ደላሎችና  ድርጅቶች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ሊታደግ ይገባል፡፡ 

Read 2821 times