Saturday, 25 May 2019 09:21

ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠ/ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች አንድነታቸውንና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የሃይማኖት አባቶች ለሠላም፣ ለፍቅርና ለእርቅ ተግተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባልተለመደ መልኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (አርክበ ካህናት) የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ሳይጠበቁ ድንገት መከሰታቸው ለፓትሪያሪኩና የሲኖዶሱ አባላት መደነቅን ፈጥሯል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤው ከሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር ችግር የፀዳች ጠንካራ ቤተክህነት እንድትፈጠር መትጋት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ፍትህ ለማግኘት የመንግስት ተቋማትን ደጅ የሚጠኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ካህናትም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ እንዲያገኙ ጠይቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችንና የአካል ጉዳተኞች መርጃ ማዕከላትን እንድታቋቁም ሃሳብ ያቀረቡት ዶ/ር ዐቢይ፤ የተፈጥሮ ሃብትን በመንከባከብና በመጠበቅ የምትታወቀው ቤተ ክርስቲያን በመጪው ክረምት በመላ ሀገሪቱ በሚደረገው የችግኝ ተከላ ላይ በንቃት እንድትሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን፤ አድባራትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለመሳለም ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የህዝቦችን ፍቅርና አንድነት ለማጠናከር እንዲተጉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በመጪው የረመዳን ፆም ፍቺ ወቅትም ክርስቲያኖች ለሙስሊም ወገኖቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት በአሉ የሚከበሩባቸውን አካባቢዎች ቢያፀዱ መልካም መሆኑን የመከሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በእለቱ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአንድነት የአፍጥር ስነሥርዓት ላይ ክርስቲያኖች የበአሉን መከበሪያ ቦታዎች ለማጽዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል - ለሙስሊም ምዕመን::
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ጉብኝት መደነቃቸውን የገለፁት ፓትሪያሪክ ብፁዐ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነትና ተጠቃሚነት ቀናነታቸውን እያረጋገጡልን ነው ብለዋል:: የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ እምነት አባቶች ጉባኤ መምጣትም ታሪክን የቀየረ ነው ያሉት ፓትሪያሪኩ፤ “ቀድሞ እኛ ነበርን ወደ መንግስት ባለስልጣናት የምንሄደው፤ አሁን የመንግስት ባለስልጣናት ወደኛ መጥተዋል” ሲሉ መደነቃቸውን ገልፀዋል፡፡
በደርግ ዘመን ተወርሰው በኢህአዴግም ሳይመለሱ የቀሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ህንፃዎች ጠ/ሚኒስትሩ እንዲመለሱ ማድረጋቸው ባለውለታ ያደርጋቸዋል ያሉት ፓትሪያሪኩ፤  ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ንብረት መመለስ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡
በዚያው እለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአንድነት አፍጥር ስነሥርዓት ላይ በቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ የተገኙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የእስልምና እምነት አባቶችም ለሀገር ሠላም፣ ፍቅርና እርቅ በትጋት እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
በረመዳን መራራቅንና መከፋፈልን በማስወገድ፣ ሙስሊሙ በአንድነት መቆሙ እንዳስደሰታቸው በመግለጽም፤ የረመዳን ወርን በፆም ስናሳልፍ በፍቅር፣ በአንድነትና በቅንነት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ “የሙስሊሙ አንድነትና ሠላም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠቅማል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ሙስሊሙ ለወደፊትም አንድነቱን እንዲያጠናክር መክረዋል፡፡ መንግስታቸው የሙስሊሙን ጥያቄዎች ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢስላማዊ ባንክ እንዲቋቋም መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ፤ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጋራ የሚሰግድበት እንዲሁም የመላው አለም ሙስሊሞችን ትኩረት የሚስብ መስጊድ ለመገንባት መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መስጊድ ግንባታ ላይም ክርስቲያኖች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠ/ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍጥር ስነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ብዙዎቹ ሙስሊሞች  በደስታ ብዛት ማንባታቸውንና ደስታቸው ወደር የለሽ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ በሥነስርዓቱ ላይ የተገኙ ሙስሊም ታዳሚዎች፤ መንግስት በዚህ መልኩ ለእስልምና ሃይማኖት ክብርና እውቅና መስጠቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ የአፍጥር ስነስርዓት ላይ ለሙስሊሙ አንድነት ተግተዋል የተባሉት የሠላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ከመጅሊሱ ከፍተኛ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡  

Read 8894 times