Saturday, 25 May 2019 09:20

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በዝናብ እጥረት ተቸግረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ሀገራቱ ለድርቅ ተጋላጭ ሆነዋል ተብሏል

         ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመጋቢት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠበቀው ዝናብ አለመዝነቡ ከፍተኛ ሠብአዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው በተባበሩት መንግስታት የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተቋም አስታውቋል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት፡- ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ሶማሊያ፤ ከመጋቢት እስከ ሰኔ የሚፈለገው ለግብርና ስራ ተስማሚ ዝናብ፣ ከሚጠበቀው ከ50 በመቶ በታች መሆኑን የገለፀው ተቋሙ፤ በተለይ ኡጋንዳ በዚህ ወቅት ከምትፈልገው ዝናብ 20 በመቶውን ብቻ እያገኘች መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
በምዕራባዊ ኬንያና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው የዝናብ እጥረትም በአካባቢዎቹ ድርቅ እየፈጠረ መሆኑን ተቋሙ ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በኬንያ የሚጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡ በቀጣይ የበቆሎ ምርት እጥረት እንደሚፈጥር የገለፀው ተቋሙ፤ ከሚፈለገው ዝናብ 25 በመቶ ብቻ እያገኙ ያሉ የበልግ አምራች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ምርታማነታቸው በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ብሏል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያና አማራ ክልል የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ አለመገኘቱ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጐታል ያለው ተቋሙ፤ በዚህም በምግብ ዋጋ ውድነት ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ አሁንም በዋጋ ግሽበት መቸገሯ እንደማይቀር አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የግጭት ተፈናቃዮችን ጨምሮ በኢትዮጵያ 8.86 ሚሊዮን ያህል ዜጐች እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት፤ ከእነዚህ ውስጥ 4.66 ሚሊዮኑ ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችና ህፃናት ናቸው ብሏል፡፡ አሁን ስጋት በጫረው የድርቅ አደጋ ከወዲሁ በትኩረት መፍትሔ ካልተፈለገ፣ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

Read 9075 times