Saturday, 25 May 2019 09:16

በምዕራብ ወለጋ በመከላከያና በታጠቁ ቡድኖች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ለተፈናቃዮች እርዳታ እንዳይደርስ እያደረገ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል እየካሄደ ባለ ጦርነት ምክንያት ለግጭቱ ተፈናቃዮች አስፈላጊ እርዳታ ለማድረስ የረድኤት ድርጅቶች መቸገራቸውን የተባበሩት መንግስታት አስታወቀ፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት በመከላከያ ሠራዊት እና “ባልታወቁ” የታጠቁ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ግጭት እየተካሄደ ነው ያለው በቢጊ፣ ቦጊድርመጂ፣ ቂሊጡካራ፣ ላሎአሳቢ፣ ለታሲቡ፣ ማናሲቡ እና በተለያዩ የነጆ ወረዳዎች ነው፡፡
በዚህም ተፈናቃዮች በብዛት ወደሚገኙበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን የሚወስደው የነጆ መንገድ መዘጋቱን የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቆ በዚህም ምክንያት የረድኤት ተቋማት እርዳታ ለማድረስ መቸገራቸውን ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡  አካባቢው መረጋጋትና ሠላም መጥፋቱን ተከትሎም ላለፉት 8 ወራት የከማሺ ዞን ተጐጂዎችን የተባበሩት መንግስታት ለማግኘት መቸገሩም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የረድኤት ተቋማት ለተፈናቃዮች እርዳታ ለማቅረብ ረጅም የመንገድ አማራጭ ማለትም የምስራቅ ወለጋን አቅጣጫ ለመጠቀም መገደዳቸውን በዚህም ለተጐጂዎች ተገቢው እርዳታ በሰአቱ እየደረሰ አለመሆኑን አስታውቋል የመንግስታቱ ድርጅት፡፡
በአካባቢው የሚገኙ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ መንግስት በቅርቡ ባቀረበው መረጃው 72ሺህ 593 ያህሉ ተፈናቃዮች ወደ ተፈናቀሉበት ካማሺ ዞን መመለሳቸውን እንዲሁም 109ሺህ 374 ያህሉ በኦሮሚያ ድንበር አካባቢ መስፈራቸው መገለፁን የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቋል፡፡  

Read 1478 times