Saturday, 02 June 2012 10:22

14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አጓጉቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለትንበያ  ዝሆን፤ አሳማና ሽኮኮ ተዘጋጅተዋል

በሚቀጥለው ሳምንት የሚጀመረው 14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖች የተቀራረበ አቋም፤ በምርጥ ተጨዋቾች መብዛትና በአውሮፓ ታላቅ ሊጎች የፉክክር ደረጃ  መጠናከር ከፍተኛ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ በጉጉት ተጠበቀ፡፡ በሌላ በኩል የአውሮፓ ዋንጫውን ውጤቶች ከምድብ ጨዋታዎች እስከ ዋንጫው አሸናፊ ድረስ ለመተንበይ በፖላንድ ዝሆን ፤ በዩክሬን ደግሞ አሳማና ሽኮኮ እየተዘጋጁ ናቸው ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ተደርጎ በነበረው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ፖል የተባለው ኦክቶፓስ በተመሳሳይ የትንበያ ድራማ ከነበረው አስደናቂ ተሞክሮ በኋላ በአውሮፓ ዋንጫ ሊተገበር የታቀደው ይህ የእንስሳት ትንበያ ውድድሩን አጓጊ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ የ14ኛውን የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች ውጤትና ሻምፒዮናውን ቡድን ለመተንበይ በፖላንድ በሚገኝ ዙ በዝግጅት ላይ የምትገኘው  ሲታ የተባለች የ33 ዓመት እድሜ ያላት ዝሆን ናት፡፡ ሲታ የተባለችው ዝሆን የአውሮፓ ዋንጫው ከመካሄዱ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በሚደረግ ስነስርዓት በኩምቢዋ እየጠቆመች የጨዋታዎቹን  አሸናፊ በመለየት እንደምትሰራ  ተነግሯል፡፡

ሲታ በቅርብ ግዜ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ቼልሲ  ባየርሙኒክን እንደሚያሸንፍ በመገመት ተሳክቶላታል፡፡ ሌላዋ የውድድሩ አዘጋጅ ዩክሬን  ለትንበያ ያዘጋጀችው አሳማ ነው፡፡  ካራዬክ በሚል ስሙ የሚጠራው ይህ የ2 አመት እድሜ ያለው አሳማ የቢራ ወዳጅ እና ኳስ በቴሌቭዥ የማየት ሱስ ያለበት እንስሳ መሆኑ እየተገለፀ ነው፡፡ አንድ የዩክሬን ነዋሪ ደግሞ በደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ ተንባይ የነበረውን ኦክቶፓሱን ፖል የተካች ፍሬድ የተባለች ሽኮኮ ለትንበያ ድራማ ማዘጋጀቱን ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ላይ ተሳትፈው ያልተሳካላቸው ሌሎች የጨዋታ ውጤት ትንበያ የሰሩ እንስሳት ደግሞ በአውሮፓ ዋንጫው የትንበያ ትኩረት ማግኘት ያልቻሉት ጃኮ የተባለ ፓሮትና ካተሪን የተባለች አህያ ነበሩ፡፡

ኢኤ ስፖርት የተባለና የዩሮ 2012 ኦፊሴላዊ ጌም የሰራ  ኩባንያ በበኩሉ ላይ ማን እንደሚያሸንፍ በሰራው ዝርዝር ትንበያ በዋንጫ ጨዋታው ጀርመን 2ለ1 በሆነ ውጤት ሆላንድን በመርታት ሻምፒዮን ትሆናለች ብሏል፡፡ ይሄው የኢኤ ስፖርትስ ትንበያ እንግሊዝ ከሩብ ፍፃሜ እንደምትወጣ፤ ስፔን በግማሽ ፍፃሜው በሆላንድ ተሸንፋ ከዋንጫው ጨዋታ በፊት እንደምትሰናበትና ጣሊያን ደግሞ በግማሽ ፍፃሜው በጀርመን እንደምትባረር ዘርዝሯል፡፡

የአውሮፓ ብሄራዊ ቡድኖች ወቅታዊ የብቃት ደረጃን ለመለካት የፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ዋና ማስረጃ ነው፡፡ ውድድሩ አንድ ወር ሲቀረው በወጣ ደረጃ ጀርመን፤ ስፔን ፤ሆላንድ፤ ጣሊያን፤ ፖርቱጋልና እንግሊዝ ተከታታይ ደረጃ የያዙ የአውሮፓ ምርጥ ቡድኖች ናቸው፡፡ በፊፋ ያለፈው 4 ዓመት የእግር ኳስ ደረጃ ስሌት ግን ያለፈው 13ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆና የምትቀርበው ስፔን ትመራለች፤ ጀርመን ፤ሆላንድ ፤እንግሊዝ ፤ ፖርቱጋል ክሮሽያ ፤ጣሊያን፤ ስዊድን ፈረንሳይ ፤በደረጃው ተከታታይ ሆነው ሰፍረዋል፡፡ በእግር ኳስ ደረጃቸው ደካማዎቹ ብሄራዊ ቡድኖች ሁለቱ አዘጋጅ አገራት ፖላንድና ዩክሬን  ናቸው፡፡

በአውሮፓ ዋንጫው ትኩረት ይስባሉ ተብለው ከተጠበቁ ክስተቶች የመጀመርያው የጣልያኑ ባልቶሊ ከዘረኛ ደጋፊዎች ጋር  እሰጥ አገባ ሊገባ ይችላል መባሉ ሲሆን ተጨዋቹ ምንም አይነት የዘረኝነት ስድብ በጨዋታ ከሰማ ሜዳውን ለቆ እንደሚወጣ ማሳሰቡ እያነጋገረ ነው፡፡  በፖላንድ እና በዩክሬን ያሉ ነውጠኛ ደጋፊዎች በዘረኛ ተግባራት የአውሮፓ ዋንጫውን ሊያደፈርስ የሚችል ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብሎም እየተሰጋ ነው፡፡ በውድድሩ በጥሎ ማለፍ ወቅት በመለያ ምቶች በሚሰናበቱ ብሄራዊ ቡድኖች የትኞቹ ተጨዋቾች ኢሊጎሬ ይስታሉ የሚለው ፍራቻም እያከራከረ ሰንብቷል፡፡ ሌላው በጉጉት የሚጠበቀው የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ማን ይጨርሳል የሚለው ክርክር ሲሆን የጀርመኑ ጎሜዝ፤የሆላንዱ ቫንፕርሲ እና የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ ቅድምያ ግምት እየወሰዱ ናቸው፡፡

ስፖርት ኢንተለጀንስ በዩሮ 2012 ላይ በሚሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች በሚሰለፉ 368 ተጨዋቾች ዙርያ በሰራው አሃዛዊ ትንተና የአውሮፓ ዋንጫው በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የተሟሸ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በዩሮ 2012 79 ያህል ተጨዋቾች ወይንም 21.4 በመቶ ያህሉ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ባሉ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ከዩክሬንና ከግሪክ በስተቀር በሌሎቹ 14 ብሄራዊ ቡድኖች ያሉ ተጨዋቾች በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾች በቡድን ስብስባቸው ይዘዋል፡፡ 7 የፈርንሳይና የሆላንድ ፤ 4 የስፔንና የዴንማርክ፤ 3 የስዊድና የክሮሽያ፤ 2 የፖርቱጋልና የቼክ  እንዲሁም 1 የጣሊያን፣ የፖላንድና የሩስያ ብሄራዊ ቡድን ተሰላፊዎች በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ሌሎች ተጨዋቾች 48 በጀርመን፤ 33 በስፔን፤ 31 በጣሊያን፤ 29 በሩስያ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ በክለብ ደረጃ ለዩሮ 2012 በብዛት ጨዋታ በማቅረብ የሚመራው ለ5 ብሄራዊ ቡድኖች 13 ተጨዋቾችን ያቀረበው ባየር ሙኒክ ሲሆን ሪያል ማድሪድ 11 ተጨዋቾችን ለ4 ቡድኖች፤ዲያናሞ ኪዬቭ 10 ተጨዋቾችን ለ2 ቡድኖች፤ ቼልሲ 9 ተጨዋቾችን ለ5 ቡድኖች፤ አርሰናል 8 ተጨዋቾችን ለ7 ቡድኖች፤ ማንሲቲ 8 ተጨዋቾችን ለ5 ቡድኖች በማቅረብ ተጠቅሰዋል፡፡

አንድሬ አርሻቪን ከራሽያ፤ ቶማስ ሮዚስኪ ከቼክ፤ ሩኒ ከእንግሊዝ፤ ሮናልዶ ከፖርቱጋል፤ ባላቶሊ ከጣሊያን፤ ቫንፒርሲ ከሆላንድ ፤ቤንዜማ ከፈረንሳይ ፤ፋብሪጋዝ ከስፔን፤ ፖዶልስኪ ከጀርመን፤ ሼፍቼንኮ ከዮክሬንና ዝላታን ኢብራሞቪች ከስዊድን የሚጠበቁ ምርጥ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በያዘው የወጣት ስብስብና በማይዋዥቅ አቋሙ ለዋንጫው አሸናፊነት ቅድሚያ ግምት አግኝቷል፡፡ በአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች በሚወዳደሩ ክለቦች የሚጫወቱ  ኮከብ ግብ አግቢዎችና ምርጥ አማካዮች ያሰበሳበው ብርቱካናማው የሆላንድ ቡድንም ካለፈው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ወዲህ በዋና የዋንጫ ተቀናቃኝነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡

ከፍተኛ ጫና ያለበትና የዓለም ምርጥ አማካዮችን ያሰባሰበው የዓለም ዋንጫና የአውሮፓ ዋንጫ ድርብ ሻምፒዮን የሆነው የስፔን ብሄራዊ ቡድንም ቀላል ተፎካካሪ ይሆናል አልተባለም፡፡ ባንድ የውድድር ዘመን ከ50 በላይ ጎል የሚያገባው ሮናልዶ ለአውሮፓ ዋንጫው ኮከብ ግብ አግቢነት ተቀዳሚ ምርጫ መሆኑም ለፖርቱጋል ተፎካካሪነት እድል አሰጥቷል፡፡ እንግሊዛዊውን አሰልጣኝ  ሮይ ሁጅሰንን ከውድድሩ መጀመር 1 ወር በፊት ያገኘው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው ብሄራዊ ቡድን ሆኖ ለተቀናቃኝነት አድፍጧል፡፡ በተሟማቀ ሊግ በተደራጀው የፈረንሳይ ቡድን አቋም ግምት ለመስጠት ቢያዳግትም አዲስ ትውልድ በሆነው የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ከባላቶሊ ጋር አዳዲስ ክዋክብት ይዞ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ተጠብቋል፡፡ 16 ብሄራዊ ቡድኖችን በማሳተፍ በፖላንድና ዩክሬን 8 ከተሞች በሚገኙ 8 ስታድዬሞች የሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ በ4 ምድብ የተከፈለ ሲሆን ተመጣጣኝ አገራትን በያዙ ምድቦች ተደልድሏል፡፡ በምድብ 1 ላይ ሩስያ፤ ቼክ ሪፖብሊክ፤ ግሪክና ከአዘጋጆቹ አንዷ ፖላንድ ሲገኙ ምድቡ ቀላሉ ድልድል የተደረገበት ተብሏል፡፡ የሞት ምድብ ሊባሉ የበቁ ሁለቱ  ምድቦች ናቸው፡፡  ጀርመን፤ ሆላንድ፤ፖርቱጋልና ዴንማርክን የያዘው ምድብ 2 እና ስፔን፤ ክሮሽያ፤ ጣሊያንና አየርላን ሪፖብሊክን ያፋጠጠው ምድብ 3 ናቸው፡፡ እንግሊዝ፤ስዊድን፤ ፈረንሳይና ሌላዋ አዘጋጅ ዩክሬን የሚገኙበት ምድብ 4 ተመጣጣኝ ምድብ ተብሏል፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ያቀረበው የሽልማት ገንዘብ 196 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ 16 ብሄራዊ ቡድኖች በነፍስ ወከፍ 8 ሚሊዮን ዩሮ የሚሰጣቸው ሲሆን በየምድብ ጨዋታው ለሚያሸንፍ ብሄራዊ ቡድን 1 ሚሊዮን ዩሮ ይታሰባል፡፡ ብሄራዊ ቡድኖች ለሩብ ፍፃሜ ሲደርሱ 2 ሚሊዮን፤ ለግማሽ ፍፃሜ 3 ሚሊዮን ዩሮ ሲሰጣቸው በዋንጫ ጨዋታው ለሁለተኛ ደረጃ 4.5 ሚሊዮን እንዲሁም ለሻምፒዮኑ አገር 7.5 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚበረከትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተያያዘ በአውሮፓ ዋንጫው በሚሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች ተጨዋቾቻቸውን ላቀረቡ ክለቦች የሚከፈል 100 ሚሊዮን ዩሮ ተዘጋጅቷል፡፡

 

 

 

Read 2703 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 10:30