Sunday, 19 May 2019 00:00

በእኔ ይብቃ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

 ተስፋ የሚለው ስያሜ በኬር ኢትዮጵያ የአንድ ፕሮጀክት ስያሜ ነው፡፡ ኬር ኢትዮጵያ በርካታ የልማት ስራዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚያካሂድ ሲሆን ተስፋ የተሰኘው ፕሮጀክት ግን በልጅነት ጋብቻ ላይ ያተኮረ በደቡብ ጎንደር በተለያዩ ወረዳና ቀበሌዎች ህጻናት ልጆች ከ12/አመት እድሜያቸው ጀምሮ  የሚዳሩበት ቦታ ላይ የሚተገበር ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ተስፋ የሚለውን ስያሜ ለምን አገኘ ? የልጅነት ጋብቻን በሚመለከት ምን እየተሰራ ነው ?የሚለውን መልስ እንዲሰጡን የጋበዝናቸው አዲስ አለም ብርሀኔ እና ሔለን ተስፋ ዮሐንስ  ናቸው፡፡  
ሄለን ተስፋዮሀንስ በህብረተሰብ ጤና የስነ-ተዋልዶ፣ የቤተሰብ ጤና እና የመስክ ኢፒድሞሎጂ ባለሙያ ስትሆን በኬር ኢትዮጵያ የስነ-ተዋልዶ ጤና ክፍል የአቅም ግንባታ እውቀት አስተዳደር አማካሪ በመሆን በክፍሉ ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ የምትሰራ ሲሆን ተስፋ ፕሮጀክትም ከክፍሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ተስፋ ፕሮጀክት በደቡብ ጎንደር ዞን በ2003ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የሚሰራውም ያገቡ አፍላ ወጣት ሴቶች ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሴቶቹን የቤተሰብ ምጣኔ እውቀትን በመጨመር፣ አመለካከታቸውን በመቀየር የቤተሰብ ምጣኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግና ከአንድ አካባቢ ወደ አንድ አካባቢ በነጻንት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ሲሆን ይሄንን ለማድረግ ማህበረሰቡን በማሳተፍ አመለካከታቸውን በመቀየር እገዛ እንዲደርጉላቸው ማድረግ ነው፡፡   
ሄለን ተስፋዮሀንስ እንዳለችው የተስፋ ልጆች ህይወትን ለመቀየር የአፍላ ሴት ወጣት ቡድንና የማህበረሰብ ቡድን ሲኖር የተስፋ ልጆች ተሰብስበው ስለ ስነ ተዋልዶና ገቢ ማስገኛና ንግድ ስልጠና ወስደው ይወያያሉ፡፡ የማህበረሰብ አባላት ደግሞ ስለ ማህበረሰቡ የያዛቸው ጎጂ ልማዶችን ደንቦች እንዴት እነደሚለዩና እንዴት እንደሚፈቱ ስልጠና ወስደው የተስፋ ልጆችን እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ በመወያየት የልጆቹ ችግርና የማህበረሰቡን ችግር ይፈታሉ፡፡ የተስፋ ፕሮጀክት የሚጠቀምበት ሞዴል የሴቶቹን የቤተሰብ ምጣኔ አጠቃቀም በ 27 ፐርሰንት የንግድ ተሳትፎ በ75 ፐርሰንት እና ቤተሰቦችና ማህበረሰቡ አንድ ላይ በመሆን 300 ያለእድሜ ጋብቻን ማስቀረት ተችሏል፡፡
ሄለን ተስፋዮሀንስ እንዳስረዳችው የተስፋ ልጆች ካሳዩዋቸው ለውጦች የተወሰኑትን ለመግለጽ ከባሎቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ብር የሚጠይቁና የሚጠብቁ የነበሩ ሴቶች የራሳቸውን ንግድ በመጀመር የቤታቸውን ወጪ በመሸፈን የራሳቸውን ቤት በመስራት ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰባቸውና ለጓደቻቸው ብር መስጠት ጀምረዋል:: ከባሎቻቸው ጋርና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተነጋግረው እራሳቸውን መግለጽ የማይችሉ የነበሩ አሁን ከባሎቻቸው ጋር መወያየትና ቤት ውስጥ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ መሆን ጀምረዋል፡፡ ስለ ቤተሰብ ምጣኔ የማያውቁ አውቀው ከባሎቻቸው ጋር በመወያየት ተግባብተው ባሎቻቸው የቤተሰብ ምጣኔ እንዲጠቀሙ የቀጠሮ ቀናቸውን እንኳን ባሎቻቸው ያስታውሷቸዋል፡፡ ጓደኞቻቸውና እህቶቻቸው ያለእድሜ እንዳይዳሩ ቤተሰቦቻቸውን በማነጋገርና ለማህበረሰብ ቡድን ሪፖርት በማድረግ ያለእድሜ ጋብቻን ለመቀነስ የራሳቸውን ሚና በመጫወት ላይ ናቸው፡፡ የተስፋ ልጆች ባሎቻቸው ከቤት እንዳይወጡ ይከለክሉዋቸው የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከባሎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቀይሮ በነጻነት ወደ ገበያ፣ ጓደኞቻቸውንና ቤተሰባቸውን ለመጠየቅ ከቦታ ለመንቀሳቀስ ችለዋል፡፡
ሄለን ተስፋዮሀንስ በማጠቃለል እነዚህ የመጡት ውጤቶችን ለማስፋፋትና የመጡትን ለውጦች ዘለቄታዊነታቸውን ለማረጋገጥ አሁን በያዝነው አመት የተስፋ ፕሮጀክት ሞዴልን ለደቡብ ጎንደር የመንግስት አካላት በማስረከብ መንግስት በራሱ ደቡብ ጎንደር ላይ እንዲስፋፋው የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይህ ድሮ ተስፋ ከሚሰራበት ቦታ በማስፋፋትና ሌሎች ተሞክሮውን በመውሰድ አሁን ካለው የተስፋ ሞደል በበለጠ ተጽእኖ ያለው ሞዴል በመፍጠር ለሌሎች አከባቢዎች ተደራሽነትን ማገጋገጥ ይሆናል፡፡
አዲሰ አለም ብርሀነ በኬር ኢትዮጵያ ውስጥ የማህበራዊ ለውጥ እና ስርአተ ጾታ አማካሪ  (Social transformation and  Gender advisor) ነች፡፡ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ በሚተገበሩ የተለያዩ ስራዎች ላይ የምትሳተፍ ሲሆን በደቡብ ጎንደር የተተገበረው የልጅነት ጋብቻን የመከላከል ስራ አካል ሆና ቆይታለች፡፡  አዲስ አለም እንደገለጸችው ዋናው ስራ ሴት ሕጻናቱ በልጅነታቸው ቢዳሩም በልጅነታ ቸው እርግዝና እንዳይገጥማቸው (ለማዘግየት) እና ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እንዲሁም ቤተሰ ባቸውን ለመምራት የሚያስችላቸውን አቅም እስኪያገኙ ድረስ ህብረተሰቡ፤ የትዳር አጋራቸውን ባሎቻ ቸውን ጨምሮ በሚችሉት አቅም እንዲተባበሩ ሲሰራ ቆይቶአል:: በዋነኛነትም እርግዝናን በማዘግየት ትምህርታቸውን እንዳያ ቋርጡ ለማድረግ አስችሎአል፡፡  ይህንን ፕሮግራም እውን ለማድረግ የሚጠቀሙበትም መንገድ የህብረተሰብ ውይይት የተሰኘው አሰራር ነው፡፡ ያ ውይይት ማህበረሰቡን የሚያሳትፍ ሲሆን በየትኛው ጉዳይ ላይ መነጋገር ይሻላል የሚለውን የሚመርጡትም ተወያዮቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በማንኛውም አሰራር ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለማህረሰቡ ሲሆን ለውጥ ሊመጣ ያስችላል በሚባሉ ጉዳዮች ላይ በስምምነት ውይይቱ ሲደረግ ቆይቶአል፡፡  አዲስ አለም እንዳለችው ውይይቱን የሚሳተፉት በልጅነታቸው ያገቡ ልጆች፤ቤተሰቦ ቻቸው፤ ባሎቻቸው፤ እንዲሁም በማንኛውም ጉዳይ ላይ በምትሰጠው ውሳኔ የምትደመጠው የባል እናት ጭምር ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአካባበው ያሉ የሀይማኖት አባቶች፤የቀበሌ አመራሮች ያካተተ ውይይት ነው፡፡ የህብረተሰቡ አባላት ውይይቱ እንዲደረግ የሚፈልጉት ከሚ ደርሱ ከችግሮች በመነሳት ነው፡፡ የደረሰውን ችግር ወደመድረክ በማውጣት የችግሩ መጥፎ ጎን ምን እንደሆነ በግልጽ በመወያየት እራሳቸው ችግሩ የሚፈታበትንም መንገድ በጥልቀት ተወያይተው መልስ ሰጥተው የሚለያዩበት መድረክ ነው፡፡  ተስፋ የተሰኘው ፕሮግራም አንዱ ያበረከተው አስተ ዋጽኦ ሴት ልጆች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግ ሎትን እንዴት እና ለምን ተጠቃሚ መሆን እንዳለ ባቸውን ጥቅሙ ምን እንደሆነ እንዲረዱት ማድረግ ነው፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አቅር ቦቱ ቢኖርም እንኩዋን በመጠቀም ረገድ የነበረው አስተሳሰብ የተዛባ በመሆኑ ይህንን ወደትክክ ለኛው ገጽታ መመለስ ሌላው ፕሮግራሙ የሚሰራው ስራ ነበር፡፡  
ሴት ልጆች ትዳር ሲመሰርቱ ዋናው እና የሚጠበቀው ነገር ልጅ እንዲወልዱ መሆኑ፤
ሴቶች ልጆች ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ሲሉ መድሀኒት ወይንም የመከላከያ
መንገዶችን ተግባራዊ ቢያደርጉ እንደልባቸው ከትዳር ውጪ ሊማግጡ ይችላሉ የሚለው አስተሳሰብ ዛሬም በብዙዎች ዘንድ ይስተዋላል፡፡  ህብረተሰቡ ከላይ የተጠቀሱትን አስተሳሰ ቦች አስወግዶ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጣ ለማድረግ የሚሰራው ስራ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ሴት ልጅ ከተዳረች በሁዋላ ልጅ መውለድ አንዱ ግዴታዋ ነው ብለው የሚያምኑ ወይንም ደግሞ መድሀኒቱ ላለመተማመን መንገድ ይከፍታል የሚለውን አስተሳሰብ ለማስቀረት የተኬደበት መንገድ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን ሴት ልጅ እንዳገባች ወደ እርግዝናው ባትሄድ፤የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ባልና ሚስቱ ተመካክረውና ተማምነው ቢጠቀሙ ፤ልጅቱ ወደ ትምህርትቤት ብትመለስ የሚኖረውን ጥቅም በማስረዳት ህብረተሰቡ እንዲቀበለው ለማድረግ የተሰራው ስራ ውጤታማ በመሆኑ ተስፋ ሞዴል በስራ ላይ በነበረበት ጊዜ በአካባቢው ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ መድሀኒቶች ጠቀሜታ ወደ 27% አድጎ ተመ ዝግ ቦአል ፡፡ አዲስ አለም እንደገለጸችው ሴት ልጆቹ ከስነተዋልዶ ጤና ባሻገርም በእጃቸው ያሉ ሳንቲሞችን እየቆጠቡ ሲቸግራቸው በመበዳደር እንዲሁም ዶሮ ማርባት የመሳሰሉትን ስራዎች በመስራት ገንዘባቸውን እንዲያሳድጉ እና እራሳቸውን እንዴት ከጥገኝነት ማውጣት እንዳለባቸው እንዲያውቁ ማድረግ እንዲሁም በሰው ፊት ቆመው መናገር እንዲችሉ ማድረግ ጎን ለጎን የተሰራ ስራ ነው፡፡     
ተስፋ ፕሮጀክት በስራ ላይ በቆየባቸው ደቡብ ጎንደር አካባቢ፤ ሴቶች ልጆች ሀሳባቸውን በግልጽ ለቤተሰቦቻቸው ማቅረብ፤ ወንዶች (ባሎች) ከሚስቶቻቸው ጎን በመሆን የስነተዋልዶ ጤናን እና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ እገዛ ማድረግ እና ሴት ልጆች በእኔ ይብቃ በሚል ስሜት ለትዳር በመታጨት ላይ ያሉ ሴት ሕጻናትን በመከላከል ከ300/ሶስት መቶ በላይ ሊፈጸሙ የነበሩ የልጅ ነት ጋብቻዎች እንዲቋረጡ ማድረግ ተችሎአል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለስራው መሳካት የተባበሩ አካ ላትን በሙሉ ኬር ኢትዮጵያ እንደሚያመሰግን አዲስ አለም ብርሃነና ሔለን ተስፋ ዮሐንስ ገል ጸዋል፡፡

Read 8200 times