Tuesday, 21 May 2019 12:23

አልበሽር ተቃዋሚዎችን በመግደል ክስ ተመሰረተባቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ወታደራዊው መንግስት በ3 አመት ስልጣን ሊያስረክብ ተስማማ

                 በህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣናቸው የወረዱት የሱዳኑ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር፣ ተቃዋሚዎችን ገድለዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ወታደራዊው መንግስት በ3 አመታት ጊዜ ውስጥ ስልጣኑን ለማስረከብ ከተቃዋሚዎች ጋር መስማማቱም ተዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት አልበሽር በስልጣን ላይ በነበሩባቸው ጊዜያት በተቀሰቀሱባቸው ተቃውሞዎች የተሳተፉ የአገሪቱ ዜጎችን በመግደል ወንጀል ፈጽመዋል ያለው የአገሪቱ ዋና አቃቤ ህግ ባለፈው ሰኞ ክስ እንደመሰረተባቸው የዘገበው ሮይተርስ፤ ሌሎች ግብር አበሮቻቸውም መከሰሳቸውን አመልክቷል፡፡
አልበሽር ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል ያስረክብ በሚል ተቃውሞው ቀጥሎ ቢሰነብትም፣ ባለፈው ሰኞ ከአገሪቱ ተቃዋሚዎች ጥምረት ጋር በተደረገ ድርድር፣ ስልጣኑን በሶስት አመታት ውስጥ ለማስረከብ ስምምነት ላይ መደረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በስልጣን ላይ ያለው የሽግግር መታደራዊ ምክር ቤት፣ ዲክላሬሽን ኦፍ ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ ፎርስስ ከተባለው የተቃዋሚዎች ቡድን ጋር ያደረገውን ስምምነት ተከትሎ በሰጠው መግለጫ እንዳለው፣ አገሪቱ ወደ ከፋ እልቂትና ብጥብጥ እንዳትገባ ለማድረግ ሲባል ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡

Read 6362 times