Saturday, 18 May 2019 00:00

ለመዲናዋ ፅዳት የባህሪ ለውጥ ያስፈልጋል!

Written by  ሂሮዬ ሺማቡኩሮ
Rate this item
(4 votes)

  በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ስትጓዙ የማይገጥማችሁ የቆሻሻ ዓይነት የለም - ፌስታል፣ የውሃ ፕላስቲኮች፣ የቢራ ቆርቆሮ፣ የሻገተ እንጀራ በፌስታል፣ የበግ ጭንቅላት፣ ጥቅም ላይ የዋለ ኮንዶም፣ የግንባታ ፍርስራሾች፣ አደገኛ የጠርሙስ ስባሪዎች ወዘተ…፡፡ የመዲናዋ ውበት መሆን የነበረባቸው ወንዞች ቆሽሸውና ተበክለው አፍንጫ የሚያሲዙ ሲሆኑ በቆሻሻና በፌስታል ክምሮች የተሞሉ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡   
ሀብታም ሆኑ ድሃ፣ የተማሩ ሆኑ ያልተማሩ፣ ህፃናት ሆኑ አዋቂ --- በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ቆሻሻ የማይጥል ማግኘት ይቸግራል፡፡ ለምሳሌ፡- ውድ የሚባሉ  አውቶሞቢሎችን የሚያሽከረክሩ፣ የተደላደለ ኑሮ የሚመሩ ሰዎች መስታወታቸውን ወረድ አድርገው፣ ሶፍት መንገድ ላይ ሲወረውሩ እመለከታለሁ፡፡ በጃፓን ጎዳናዎች ላይ ከሞላ ጐደል ቆሻሻ የለም ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ሰዎች በአብዛኛው መንገድ ላይ ቆሻሻ አይጥሉም፡፡ አንድ የ6 ዓመት ህፃን ልጅ እንኳን በመንገድ ላይ እየሄደ ሶፍት ወይም መስቲካ መጣል ቢፈልግ፣ የቆሻሻ ማጠራቀምያ (ቅርጫት) ፈልጎ ነው የሚጥለው፡፡ ምናልባት ካላገኘ ግን ቤቱ ሲደርስ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ይጥላል እንጂ በየመንገዱ ዝም ብሎ አይጥልም፡፡  እዚህ ግን የኮሌጅ ተማሪዎች ሳይቀሩ በመማሪያ ክፍላቸው ውስጥ ቆሻሻ ሲጥሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡   
ሰዎች በየመንገዱ ቆሻሻ መጣል ጎጂ መሆኑን ይገነዘባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቆሻሻ በተገቢው ቦታ ሲጣል ሊቃጠል ወይም ዳግም ጥቅም ላይ ሊውል (ሪሳይክል ሊደረግ) ይችላል፡፡ በተለይ በየመንገዱ የምንጥለው ስስ ፌስታል ለዘመናት ሳይበሰብስ የሚቀመጥ ነው፡፡ እስከ ልጅ ልጆቻችን … ዘመን ምንም ሳይሆን ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ከዚህም የሚከፋው ግን እንስሳትና ዓሶች እነዚህን ላስቲኮች እየበሉ ለሞት መዳረጋቸው ነው፡፡  በሰሜን ውቅያኖስ 94 በመቶ ያህሉ የአዕዋፋት ሆድ ዕቃ ውስጥ የተለያዩ  ላስቲኮች እንደሚገኙ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ዓሶች በወንዞች ውስጥ የሚለቀቁ መርዘኛ ኬሚካሎች እየተመገቡ እንደሚሞቱ ተረጋግጧል፡፡ አስቡት! እነዚያን ዓሶች እኛ ብንመገባቸው ምን ሊገጥመን እንደሚችል፡፡ ራሳችን በግዴለሽነት በምንጥለው ቆሻሻ የሚበከሉ ወንዞች፣ ለወባና ለአተት ወረርሽኝ ያጋልጡናል:: በየመንገዱ የምንጥላቸው ቆሻሻዎች በተለይ በክረምት ወቅት የፍሳሽ ቱቦዎችን በመዝጋት፣ የበለጠ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚያስከትሉም መዘንጋት የለብንም::
ምርጫው እንግዲህ የራሳችን ነው፡፡ ለነዋሪዎች በቆሻሻ መንገድ ላይ መጓዝ ይሻላል ወይስ በንፁህ መንገድ ላይ? ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ ከባቢ የትኛው ነው? ቆሻሻ ክፍል ወይስ ንፁህ ክፍል? ሰራተኞች የበለጠ ምርታማ የሚሆኑት በንፁህ ፋብሪካ ውስጥ ሲሰሩ ነው ወይስ በቆሻሻ ፋብሪካ ውስጥ? እንደሚታወቀው፤ ቆሻሻ አካባቢ በጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ፤ በሥነ ልቦናችንም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ዘወትር እሁድ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 1 ሰዓት ድረስ አካባቢያችንን እንድናፀዳ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ጥሩ ጅምር ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን በየመንገዱ ቆሻሻ የመጣል ልማዳችንን ካልቀየርን ከተማዋን በቀላሉ ማጽዳት የምንችል አይመስለኝም፡፡ ለመዲናዋ ፅዳት የባህሪ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ጥቂት የመፍትሔ ሃሳቦችን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡
ከሁሉም በፊት ሰዎች ለምን ቆሻሻ በየመንገዱ መጣል መጥፎ እንደሆነ ማወቅና መገንዘብ አለባቸው፡፡ ዝም ብለን “ቆሻሻ በየመንገዱ አትጣሉ!” ማለት ዋጋ የለውም፡፡  ቆሻሻ መጣል የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤት ለህብረተሰቡ በቅጡ ማስረዳት ያሻል፡፡ በዚህ ዙሪያ አስፈላጊ መረጃዎችን በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች ማሰራጨት ይኖርብናል፡፡ በት/ቤቶች ውስጥ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች  ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ መንገዶች፣ ት/ቤቶች፣ ወንዞች ወዘተ … “ከመፅዳታቸውና ከፀዱ በኋላ” ያለውን ለውጥ የሚያሳዩ አነቃቂ ፕሮግራሞችን እያዘጋጁ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በመላው ዓለም ቀልብን የሳበው “KoMari” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በዩቲዩብ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡
በት/ቤት ውስጥ የፅዳት ውድድር ማዘጋጀት፡- ተማሪዎች ት/ቤታቸውንና አካባቢያቸውን የማፅዳት ውድድር ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ፣ የላቀ ክንውን ላሳዩ ዕውቅናና ሽልማት መስጠት፡፡ ውድድሩ ከዝነኛ አርቲስቶች ጋር በመተባበርና በንግድ ተቋማት ድጋፍ ሊዘጋጅ  ይችላል፡፡
በየት/ቤቱ የጽዳት ጊዜ መጀመር፡- እኔ በጃፓን የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ፣ በየቀኑ ከትምህርት በኋላ ክፍላችንን እናፀዳ ነበር:: የክፍላችንን ወለል እንጠርጋለን። ዴስኮችና ጠረጴዛዎችን እንወለውላለን፡፡ አንድ ተማሪ ቆሻሻ መሬት ላይ ወድቆ (ተጥሎ) ከተመለከተ ዝም ብሎ አያልፍም፤ አንስቶ የቆሻሻ ማጠራቀምያ ውስጥ ይከታል እንጂ፡፡ በነገራችን ላይ የፅዳት ጊዜ የተለመደው በጃፓን ብቻ አይደለም፤ 30 በመቶ የሚሆኑት የዓለማችን ት/ቤቶች ይሄን አሰራር ይተገብሩታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም በሲንጋፖር የሚገኙ ት/ቤቶች የፅዳት ጊዜን መተግበር ጀምረዋል::
በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች፣ የንፅህና ሞዴል መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እንደ ላሊበላ ያሉ የዓለም ቅርሶችና የሰሜን ተራራን የመሰሉ ውብ ተፈጥሮአዊ ስፍራዎች ንፁህ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የእነዚህ አካባቢዎች ንፁህ መሆን የሚጠቅመው ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ አይደለም፤ ለቱሪስቶችና ለአገሪቱ የገፅታ ግንባታም ጠቃሚ ነው፡፡  
የእቃ መያዣ ፌስታሎች፡- እንደ ሌሎች አገራት ሁሉ በኢትዮጵያም በእቃ መያዣ ስስ ፌስታሎች  ላይ ገደብ ሊጣል ይገባል፡፡ ለምሳሌ ቻይና ከ0.025 ሚሊ ሜትር በታች የሆኑ ስስ ፌስታሎችን ማምረትና መጠቀምን አግዳለች፡፡ ፈረንሳይ በመደብሮች ውስጥ ስስ ፌስታሎችን ማከፋፈል ከልክላለች፡፡ አይስላንድ ደግሞ በፌስታሎች ላይ  ግብር ጥላለች፡፡
የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፡- በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች ዳግም አገልግሎት ላይ መዋል (ሪሳይክል መደረግ) እንደሚችሉ መረዳት ጀምረዋል፡፡ ይህ መረዳት (ግንዛቤ) የበለጠ ትኩረት ማግኘት ያለበት በፕላስቲክ ማምረቻ ኩባንያዎች ነው፡፡ ባዶ የውሃ ፕላስቲኮችንም በንቃት መሰብሰብ አለባቸው፡፡
የለስላሳና የቢራ ቆርቆሮዎች፡- ባዶ የለስላሳና የቢራ ቆርቆሮዎችን እንዲሁም ቆርኪዎችን በየቦታው መጣል የለብንም። የተጣሉትንም መሰብሰብ ተገቢ ነው፡፡ በተለይም የቢራ ፋብሪካዎች በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል፡፡  
 የግንባታ ፍርስራሾችን በየመንገዱ መጣል ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበትና ቅጣት ሊጣልበትም ይገባል፡፡ በሌላ በኩል፤ በየቦታው በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፍረው ሳይደፈኑ የሚቀሩ ጉድጓዶች በሰው ህይወት ላይ ሞትን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ከመሆናቸው አንጻር የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በትኩረት መቆጣጠርና መከታተል ይኖርበታል፡፡   
ቀደም ሲል የጃፓን ጎዳናዎች ከሞላ ጐደል ንፁህ መሆናቸውን ጠቅሼ ነበር፤ ነገር ግን 100 ፐርሰንት ወይም ሙሉ በሙሉ ንፁህ ናቸው ማለት አልችልም:: ከስንት አንድ በግዴለሽነት በየመንገዱ ቆሻሻ የሚጥል አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ቆሻሻ በየመንገዱ የመጣል መጥፎ ልማድን ለማስቆም ቀጣይ ጥረቶችና የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች ሳያሰልሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻም፤ ከዚህች ቅፅበት ጀምሮ የቤተሰብ አባላቶቻችን በመንገድ ላይ ማንኛውንም ቆሻሻ እንዳይጥሉ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ፡፡ ከቆረጥን እናደርገዋለን፡፡ ዋናው ነገር የባህሪ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ነው፡፡   

Read 1242 times