Monday, 13 May 2019 00:00

ቃለ ምልልስ አዲሱ የዜግነት ፓርቲ ምን ይዞ መጣ?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 • ፕሬዚዳንታዊ ሥርአት አገርን አንድ ለማድረግ ይጠቅማል የሚል እምነት አለን
            • ትልቁ ዓላማችን፣ ህዝቡ የሚተማመንበት አገር አድን ፓርቲ መፍጠር ነው
            • ቀዳሚ ትኩረታችን ምርጫ ሳይሆን የአገሪቱ ሠላምና አንድነት ነው


              ከስምንት ወራት ያህል ምክክር እና ውይይት ሲደረግበት የነበረውና ዜግነትን የፖለቲካ መሠባሰቢያው እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህን ርዕዮተ አለሙ አድርጐ የተመሠረተው አዲሱ ፓርቲ እነማን ተካተቱበት? ምን የምስረታ ሂደት አሳለፉ? አደረጃጀቱ ምን ይመስላል? ለሀገሪቱ ፖለቲካ ምን አዲስ ባህል ይዞ መጣ? የፓርቲው ራዕይና ዓላማው ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲው አደራጅ አባል የሆኑት የቀድሞው የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
ይህን ሀገር አቀፍ ውህድ ፓርቲ ለማደራጀት የታለፈበት መንገድ ምን ይመስላል?
አዲሱን ሀገራዊ ሃይል ለመፍጠር በርካታ ውጣ ውረዶች አልፈናል፡፡ በጣም ከባድ ፈተና ነው ያሳለፍነው፡፡ የለውጥ ጭላንጭሉ ከመጣ በኋላ ትግሉ የሚቀጥልበትን አዲስ መንገድ መፈለግ ነበረብን፡፡ ቀደም ሲል መግለጫ ማውጣት፣ መጋፈጥ፣ መታገል፣ መታሰርና መሞትም የሚጠይቅ የነፃነት ትግል ነበር የሚካሄደው፡፡ አሁን  በዚህ የለውጥ ጭላንጭል ውስጥ ግን፣ የጥያቄዎች ሁሉ ቁንጮ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው ይተዳደር የሚለው ነው፡፡ ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በሰው ሃይል፣ በሃሳብ፣ በፋይናንስ --- በሁሉ ነገር የተደራጀና በትክክልም የኢትዮጵያን ችግር ሊሸከም የሚችል፤ ህዝብ ተስፋ የሚጥልበትና እንደ አማራጭ የሚታይ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም፣ ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማመን ነበር የተንቀሳቀስነው፡፡ ከዚህ የደረስነው ሁላችንም የራሳችንን ህጋዊ ህልውና አፍርሰን፣ ሌሎችም ወደ ስብስቡ እንዲመጡ አግባብተን ነው፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ወደ ውህደቱ እንዲመጡ  አነጋግረናል፡፡ ጥሩ ምላሽ የተገኘውና ራስን ወደ ማክሰም የገቡት ስምንት ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎችና ንቅናቄዎች ናቸው፡፡
እስካሁን ባለፍንበት ሂደት በዋናነት፣ ማህበራዊ ፍትህን መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ስራ ሠርተናል፡፡ የትምህርት፣ የጤና፣ የኢኮኖሚ የመሳሰሉት ፖሊሲዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በፕ/ር በፍቃዱ ደግፌ የሚመራ የምሁራን ቡድን ተቋቁሞ ጥሩ ፖሊሲ አዘጋጅቶልናል፡፡
የዚህ ፓርቲ ትልቁ አካል ወረዳ ላይ ያለው አደረጃጀት ነው፡፡ ስለዚህ ውህደቱን የጀመርነው ከወረዳዎች ነው፡፡ የሁሉም ፓርቲዎች አባላትና ሌሎች በፓርቲ ያልታቀፉ ግለሰቦች በወረዳዎች ደረጃ እንዲዋሃዱ የማድረግ ስራ ሠርተናል፡፡
የወረዳ አደረጃጀቱ ምን አይነት ቅርፅ ነው ያለው?
በሂደቱ የተሳተፍን ፓርቲዎች አባላት፣ የፓርቲው አባል መሆን የፈለጉ ግለሰቦች በሙሉ በአንድ ጉባኤ ተሰበሰብን፤ የሁለታችንም ጉባኤ ሆኖ አንድ የወረዳ አደረጃጀት ፈጠርን ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ ግንቦት 7 ብቻ አባላት ባሉት ወረዳ፣ የሁላችንም የአዲስ የተመሰረተው እንዲሆኑ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ በሙሉ አቅማችን ተንቀሳቅሰን የወረዳ ጉባኤ ያደረግነው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 312 ያህል ወረዳዎች ይሁን እንጂ በሌሎች ወረዳዎችም መደበኛ አባላትን አደራጅተናል፡፡ ቀጥሎ ያደረግነው ነገር ከእነዚህ ወረዳዎች 350 ያህል የፓርቲ ካድሬዎችን መልምለን፣ በአዲስ አበባ ሰሜን ሆቴል፣ በፓርቲው አላማና ግብ እንዲሁም ደንብና ፕሮግራም ላይ ስልጠና ሰጥተናል:: እነዚህ ምልምል ሠልጣኞች ደግሞ በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው፣ የሠለጠኑትን ለአባላት አሰልጥነዋል፡፡ በዚህ መሠረትም፣ በየወረዳዎቹ ጉባኤ ተዘርግቶ፣ ጉባኤው የመረጣቸው ናቸው፣ አሁን በዚህኛው የፓርቲው መስራች ጉባኤ፣ አባል ሆነው የተሳተፉ ግለሰቦች የተገኙት፡፡
እኔ በበኩሌ፣ እስካሁን ካለፍኩበት የፖለቲካ ሕይወት (ከቅንጅትም አንድነትም ሠማያዊም) በእጅጉ የተለየ ልምድ ያገኘሁበት ሂደት ነው፡፡ አሁን እንዳለፍንበት የመሰለ የፓርቲ አመሠራረት ተከናውኖ አያውቅም፡፡ በዚያው ልክ እንደዚህ ተስማምተን የተዋሃድንበት ጊዜም የለም፡፡ በሙሉ ቁርጠኝነትና በንፁህ ልብ፣ ከሁሉም ጋር በመግባባት ነው የሠራነው፡፡ ጥሩ አማራጭ ሆነን እንወጣለን ብለን እናስባለን፡፡
በዚህ ውህደት ውስጥ ከግለሰቦች በተጨማሪ የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው የተሳተፉት?
ግንባር ቀደም ሆኖ የመክሰም እርምጃ የወሰደው ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ እኔም ሆንኩ የፓርቲው አባላት በእጅጉ እንኮራለን:: ትልቅ ውሣኔ ነው አባላቱ የወሰኑት:: የሚገርመው ይሄን ፓርቲ አደራጅተው፣ በአመራር ውስጥ የነበሩ፣ ነገር ግን በወረዳ በተካሄደው ምርጫ ሳይመረጡ የቀሩ በርካታ የቀድሞ አመራሮቻችን፣ ሁኔታውን በደስታ ነው የተቀበሉት፡፡ ሌላው አርበኞች ግንቦት 7፣ የጋምቤላ ህዝባዊ ንቅናቄ፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ፣ አትፓ (አዲስ ትውልድ ፓርቲ)፣ የቀድሞ አንድነት አባላትና አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አንዷለም አራጌ ያሉበት ጠንካራ ስብስብም አለ:: የመኢአድ የቀድሞ አመራሮች ያሉበት ወደ 40 ወረዳ ያህል አደራጅተው፣ የዚህ ውህድ ፓርቲ አካል ሆነዋል፡፡
በጣም ግዙፍ አደረጃጀት ነው የተፈጠረው፤ በእያንዳንዱ ወረዳ በአማካይ ከ1ሺህ በላይ አባላት አሉን፡፡ ከ312 ወረዳዎች ሶስት ሶስት ሴቶች ማሳተፍ አለባቸው፡፡ ተጨማሪ አንድ እንዲሁም አምስት የጉባኤ ተወካይ ማድረግ ከፈለጉ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ፓርቲው ለሴቶችና በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እምብዛም ቦታ ሳይሰጣቸው የምናያቸውን አካል ጉዳተኞችን በእጅጉ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ከትግራይ እስከ ሶማሌ፣ ከጋምቤላ እስከ ምስራቅ የሀገሪቱ ጫፍ ተወካዮች ያሉት ፓርቲ ነው፡፡
ለኛ አሁን ከምንም በላይ የምትቀድመው ኢትዮጵያ ነች፤ ምርጫ ማሸነፍ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ አረና ትግራይ በዚህ ውህደት ውስጥ እንዲካተቱ እየተነጋገርን ነው፡፡ ትልቁ አላማችን፣ ህዝቡ፣ ሀገር አድን ፓርቲ አግኝቻለሁ ብሎ የሚተማመንበትን ምህዳር መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከሌሎች አካባቢ ፓርቲዎችም ጋር እየተነጋገርን ነው:: እስከዚህ አመት ማጠናቀቂያ ድረስ ፓርቲው በ547 የምርጫ ወረዳዎች የራሱ አባላትና አደረጃጀት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ አሁንም በዚህ ፓርቲ ውስጥ ለመግባት የተዘጋ በር የለም::
የኛ ዋናው መሠረታዊ አላማ አንደኛ፤ አደረጃጀቱ ህዝባዊ መሆን አለበት፣ ሁለተኛ፤ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን አለበት የሚል ነው:: ይህን አላማ ይዘን አሁን በየወረዳዎቹ ጽ/ቤቶች ከፍተናል፡፡ 312 ተብሎ የተጠቀሰው የወረዳ ቁጥር በቀጣይ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ሙሉ ጉባኤ አለ፡፡ ሁሉም ወረዳዎች የራሳቸው 15 የስራ አስፈፃሚ፣ 5 ወይም 3 የጠቅላላ ጉባኤ ተወካይ  ምክር ቤት ያላቸው ናቸው፡፡ ጠንካራ ስራ የሠራንባቸውን ነው አሁን 312 ብለን በመግለጫ የጠቀስነው እንጂ ሌሎች ወረዳዎች ላይም ይሄው አደረጃጀት ነው የተፈጠረው፡፡
ፓርቲያችሁ በምርጫ ቢያሸንፍ፣ የፓርቲው ሊቀ መንበር፣ ጠ/ሚኒስትር የመሆን እድል አለው?
በሀገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል ውስጥ ለውጥ አድርገንበታል የምንለው አንዱ በሊቀ መንበርነት ጉዳይ ነወ፡፡ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ሁለት አደረጃጀቶች ናቸው ያሉት፡፡ አንዱ በቀጥታ ለመንግስት ስልጣን የሚዘጋጅ አካል ነው፡፡ ሌላኛው የፓርቲ ስራን የሚሠራ አካል ነው፡፡ ሥራ አስፈፃሚ፣ የጉባኤ ተወካይ ሆነው የተመረጡ በሙሉ የተለያዩ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን የወረዳ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚሠራው፣ በዋናነት የፓርቲውን የፖለቲካ ስራ ነው፡፡ ለምሣሌ ለምርጫ ተወዳዳሪ የሆነን ሰው በመምረጥ ሂደት ምናልባት የፋይናንስ፣ የተቀባይነትና የተጽእኖ ፈጣሪነት ያላቸውን፣ ነገር ግን የፓርቲው አባል ያልሆኑ ሰዎችን ሊመለምል ይችላል፡፡ ለምሣሌ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ባሉበት ወረዳ ያለው የሥራ አስፈፃሚ አካል፣ እሣቸው የዚህ ፓርቲ አባል ባይሆኑ እንኳን ለፓርላማ ተወዳዳሪ አድርጐ ሊያቀርባቸው ይችላል፤ የእርሳቸው ፍቃድ ከተገኘ፡፡ በዚህ አይነት መንገድ ነው የተደራጀው፡፡ ይሄን ስራ ከአሁኑ ነው መስራት የሚጀምረው፡፡ 547 (በፓርላማው ወንበር ቁጥር) ሰዎች ተመልምለው፣ ለቀጣዩ ምርጫ ከወዲሁ ይዘጋጃሉ ማለት ነው፡፡ የፓርቲው መሪና ምክትል መሪ በዋናነት ይሄን ስራ ነው የሚሰሩት፡፡  
ሊቀ መንበርና ም/ሊቀመንበር ሌላ ነው የሚሆነው፡፡ የፓርቲው መሪና ምክትል መሪ (የማደራጀት ስራ የሚሠሩ) እንዲሁም ሊቀ መንበርና ም/ሊቀመንበር (የዕለት ተዕለት የፓርቲውን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ) ይመረጣሉ ማለት ነው:: ስለዚህ ፓርቲው በአንድ በኩል፣ መንግስት ለመሆን የተዘጋጀ ኃይል፣ በሌላ በኩል፣ የፓርቲ ተግባር ብቻ የሚከውን ኃይል ይኖረዋል ማለት ነው:: ፓርቲው የራሱ ተሽከርካሪ፣ ንብረት ይኖረዋል:: ይህም በቀጣይ፣ መንግስት ሲሆን በራሱ ንብረት እንዲጠቀም ያግዘዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር ጠ/ሚኒስትር መሆን አይችልም ማለት ነው?
አዎ! ምክንያቱም አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ከሁሉም የምርጫ ወረዳዎች ለመንግስትነት (ለምርጫ ውድድር) የተመረጡ 547 ሰዎች ተሰብስበው መሪያቸውን ይመርጣሉ፡፡ ያ መሪ ነው የሃገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሊሆን የሚችለው:: ስለዚህ የፓርቲው ሊቀ መንበር፤ ጠ/ሚኒስትር አይሆንም ማለት ነው፡፡ ሊቀ መንበሩ የፓርቲውን ስራ ነው የሚሰራው፡፡ በ547 ሰዎች በመሪነት የተመረጠውን፣ ህዝብ በምርጫ ካልመረጠው ደግሞ በሌላ ይተካል ማለት ነው፡፡
የዜግነት ፖለቲካ ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?
የዜግነት ፖለቲካ ማለት ማንም ዜጋ፣ በዜጋነቱ ብቻ የሃገሩ ጉዳይ ይመለከተዋል ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው ለምሳሌ አፋር ላይ ተሰብስበው በሌላ ቋንቋ የሚወሰነው ውሳኔ፣ በአፋር የሚኖረውን ዜጋ አይመለከተውም፤ ይሄ ዜግነትን የሚሽር ነው:: ቢያንስ ከሌላ ቦታ ሄዶ እዚያ የሚኖር ዜጋ፣ የማወቅ መብቱ (ውሳኔው ምን እንደሆነ) የለውም፤ ብሄሮች ናቸው በሱ ጉዳይ የሚወስኑት፡፡ ህውሓት የሚወስነውን፣ የሶማሌ ድርጅት የሚወስነውን ውሳኔ እኩል አውቀን እየተቸን ነው ወይ? ብለን ከጠየቅን፣ የዜግነት ፖለቲካ ማለት ምን እንደሆነ ይገባናል:: አሁን በኛ አደረጃጀት፣ ማንኛውም ሰው የኛን አላማ፣ አርማና የትግል ስልት የተቀበለ፣ የፈለገው ቦታ ሆኖ አባል ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከየትኛውም አካባቢ የዚህ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው፣ የሃገር መሪ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ማለት ነው፡፡ ዋናው መስፈርቱ ዜግነት ነውና፡፡
የጎሳ ፖለቲካ በህግ ይታገድ የሚል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
እኔ በብሄር ድርጅት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አልፈርድባቸውም፡፡ ተገደው ነው የገቡበት፡፡ እንደ ገዥ ሃሳብ ስለሆነ ነው ዛሬ “አብን”ም ሆነ  ሌላው በዚህ አደረጃጀት የተሰለፉት፡፡ ስለዚህ ህውሓት እያለ አብን፣ ኦነግ እያለ ህውሓት፣ ህውሓት እያለ ኦነግ ሊጠፋ አይችልም:: ምክንያቱም አንዱ በአንደኛው ፍርሃት ላይ የቆመ ነው፡፡
ስለዚህ እንደ ሃገር፣ የትኛው ላይ ብንቆም ነው የሚያዋጣው ብለን ከተመካከርን፣ የብሔር ፖለቲካን መስመር ማስያዝ ይቻላል:: የትኛውም የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ስለ ኢትዮጵያ አይጨነቁም ማለት ተገቢ አይደለም:: ሁላችንም እንተዋወቃለን፡፡ የኢትዮጵያ ጥላቻ የላቸውም፡፡ ስለዚህ እነዚህን አካላት ገፍተን ገደል መክተት ተገቢ አይደለም፡፡ ከሁሉም ጋር መነጋገር፣ መወያየት ነው የሚያስፈልገው፡፡
የጎሳ፣ የብሔር ወይም የዘር ፖለቲካን ይቁም የሚለው እንግዲህ የማህበረሰቡ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ የትኛውም ሃገር በዚህ የፖለቲካ መስመር ያለፈለት የለም፡፡ የተባላ የተጫረሰ ተሞክሮ ነው የምናገኘው እንጂ መልካም ነገር የለውም:: ስለዚህ ይሄን ማህበረሰቡ የሚወስነው ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ግን ብዙ ሰው ወደዚህ ነገር ባይገባ ብለን ነው የምንመክረው፡፡ ጉድጓድ ውስጥ ያለን አካል ለማውጣት እንዴት ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፡፡ ጫፍ ላይ ቸክለህ ቆመህ ነው በገመድ መሳብ ያለብህ እንጂ አንተም ከገባህ ማን ያወጣሃል፡፡ ነገርየው ዛፍ ከሆነ በኋላ በቀላሉ መስበር ማለት ሀገር ማፍረስ ነው፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ በሂደት ነው መውጫ መንገዶች መፈጠር ያለበት፡፡ ለምሳሌ የሶማሌ ክልል ገዥ ፓርቲ በቅርቡ ያሳለፈው፣ ማንኛውም ሶማሊኛ የሚችል ኢትዮጵያዊ ሊቀላቀለኝ ይችላል ያለው አንድ እርምጃ ነው፡፡ ሌሎችም በዚህ መልኩ አንድ እርምጃ ከተራመዱ፣ ወደ ሌላኛው እርምጃ በሂደት መሻገር ይቻላል፡፡ በአንድ ጊዜ ይቁም ይታገድ  ማለት ግን ግዙፍ ዛፍን መስበር ማለት ነው፡፡ ዘረኝነት በኔ እምነት ጥልቅ ጉድጓድ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጥልቅ ጉድጓድ መውጣት የሚቻለው በጥበብ እንጂ በኃይል አይደለም፡፡ መውጫው መንገድ ልክ እንደ መወጣጫ ደረጃ ነው መሆን ያለበት፡፡  
አዲስ የመሰረታችሁት ፓርቲ በፌደራሊዝም ጉዳይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
በፌደራል ስርአቱ ላይ ግልፅ አቋም ነው ያለን፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ያልተማከለ አስተዳደር ነው፡፡ ፌደራላዊ ስርአት ነው የሚያስፈልጋት:: በዚህን ያህል ብዝኃነትና የህዝብ ብዛት ውስጥ አሃዳዊነት በፍፁም አያዋጣም የሚል ድምዳሜ ነው ያለን፡፡ ግን ፌደራላዊ አወቃቀሩ በመጀመሪያ የሚመልሰው አስተዳደራዊ አመቺነትን መሆን አለበት:: በቁጥር አንድ ያስቀመጥነው አስተዳደራዊ አመቺነትን ነው፤ ቀጥሎ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ነው፤ ከዚያም ባህል፣ ቋንቋ፣ የህዝብ አሰፋፈር፣ የህዝብ ስነ ልቦና የመሳሰሉ መስፈርቶችን አካትቶ መዋቀር አለበት የሚል ነው ፕሮግራማችን፡፡ ይሄን ስናስብ፣ በዋናነት ምሁራን ብዙ የደከሙበትን ጥናት መነሻ አድርገናል:: የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን ውስጥ አለሁበትና በዚያ አጋጣሚ የተጠኑ ጥናቶችን ለመመልከት እድሉ ገጥሞኛል፡፡ በብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት እነ ዶ/ር አስፋው፣ እነ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ የመሳሰሉ ምሁራን ለሃገራችን ምን ይበጃል ብለው በንፁህ ልቦና የለፉበትን ጥናት ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ የእያንዳንዱን ማህበረሰብ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት የሚያከብር አወቃቀር መከተል የሚለው ፕሮግራማችን ነው፤ ካሸነፍንም ይሄን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡
ህገ መንግስቱን በተመለከተ ሃሳባችሁ ምንድነው? ምን ዓይነት መንግስታዊ ሥርዓት ነው የምትከተሉት?
ህገ መንግስቱን እያፈረሱ ከዜሮ መጀመር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሰብአዊ መብትን የሚመለከቱና ሌሎች ጠቃሚ ያልናቸውን እንዳሉ እንወስዳቸዋለን፤ ነገር ግን ለዚህች ሃገር የማያስፈልጉ በክፋት የተሰነቀሩ አንቀፆች የምንላቸው አሉ፣ እነሱ እንዲቀየሩ እንታገላለን:: ሥርአቱን ፕሬዚዳንታዊ ማድረግ ሌላው አላማችን ነው፡፡ ፕሬዚዳንታዊ ሥርአት ሃገርን አንድ ለማድረግ ይጠቅማል የሚል እምነት አለን:: አንድ ሰው ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር ቢያንስ ሦስትና አራት ክልል ማሸነፍ አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ያሳተፈ መንግስት ለማቆም ፕሬዚዳንታዊ ሥርአት በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እነ ዶ/ር ዐቢይ፣ ለማ፣ ገዱ፣ ደመቀ ሲመጡ፤ አንድም ሰው ሃይማኖታቸውንና ብሔራቸውን ለማየት አልፈለገም፡፡ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ምን ሃሳብ አላቸው? የሚለውን ነው ያየው፡፡ ይሄ ሥርአቱ ፕሬዚዳንታዊ ቢሆን ጠቃሚ እንደሆነ ያሳየናል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ግን የፓርቲ መስመርን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ይሄ በቂ ውክልናና ቅቡልነት አለው ለማለት ማረጋገጫ አናገኝም፡፡
የዚህ ፓርቲ ዋነኛ  ፈተናዎች የሚሆኑት ምንድን ናቸው? የለያችኋቸው ጉዳዮች አሉ?
አዎ! ዋነኛ ፈተናዎቹ ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ብሔረሰብን፣ ዘርን ወይም ጐሣን ማዕከል አድርጐ የተዋቀረውና ታርጋ ላይ የተለጠፈው፣ ባንክ ላይ፣ የቀበሌ መታወቂያ ላይ፣ ሚዲያ ላይ የተለጠፈው የብሔር ታርጋ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራ አጥነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ሃብታም ናት ስንል፣ ጥሩ የሚሠራ የሰው ሃይል አላት፣ በቂ መሬት፣ ጥሩ አየርና ውሃ አላት:: እነዚህን አገናኝቶ የተትረፈረፈ ምርት ማግኘት ሲቻል፣ አሁን ግን ሰው ሁሉ የሚበላውና የሚያስበው ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ይሄን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሀገር፣ በንጉሡም በደርግም በወያኔም በተሠራው ፖለቲካ  የተነሳ  ህዝቡ ተጠራጣሪ፣ ፈሪና ዘረኛ እንዲሆን ተደርጓል:: ይሄ እንደ ሀገር እየሠበርን ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ከራሱ ጋር እንዲታረቅ፣ ማንንም እንዳይፈራና እንዳይጠራጠር መደረግ  አለበት፡፡ የብሔር ድርጅት መነሻው ፍርሃት ነው፡፡ እየመጡብህ ነው ከሚል ሥነልቦና ነው የሚነሳው:: ካልተደራጀን እናልቃለን የሚል ፍርሃት በህዝቡ ላይ ይለቀቃል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ መደራጀት ብቻውን ምን ይሠራል፣ ተነስ እንታጠቅ ይላል፣ ከታጠቀ በኋላ  ምሽግ ቆፍረን እንጠብቃቸው ይባላል፡፡ ግን ጠላቱ ጭንቅላት ውስጥ ስለሆነ የተባለው ቢጠበቅ ቢጠበቅ አይመጣም፡፡ ሲጠበቅ ካልመጣ ደግሞ እኛ ለምን አንሄድም ይባላል፡፡ የትም ሀገር ብንሄድ፣ የብሔር ፅንፍ አካሄዱ ይሄው አይነት ነው፡፡ ከዚያ መጠፋፋቱ ይከተላል ማለት ነው፡፡
በርዕዮተ አለማችሁ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄው ምንድን ነው?    
እዚህ አገር በአንድ በኩል፤ ሁሉ የሞላላቸው፣ ቁርሣቸውን ቻይና፣ ምሣቸውን አውሮፓ የሚበሉ የናጠጡ ሃብታሞች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእለት ጉርስ አጥተው በየመንገዱ የወደቁ አሉ፡፡ የኛ ሀገር እውነታ ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ በምንም የገበያ ሁኔታ መንግስት ከግለሰብ ጋር ገበያ ውስጥ ገብቶ ውድድር አያደርግም፤ ከገበያ ጨዋታ ይወጣል፡፡ ነገር ግን የሚደግፋቸው፣ የሚረዳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ መንገድ መሠረተ ልማት ይሠራል:: ዶ/ር መረራ “የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪውን ይበላል” ይላል:: ጋሽ አንዳርጋቸው ፅጌ ደግሞ “ነገሩ እንደዚያ ብቻ አይደለም፤ የሚበላው ያጣ ህዝብ ያለውን ይበላል” ይላል፡፡ ስለዚህ ሀብት ያለው ሃብቱን፣ እውቀት ያለው እውቀቱን የማካፈል ኃላፊነት አለበት፡፡ ይሄን እናስተምራለን፤ በፖሊሲም እንሠራበታለን፡፡ የብሔረሰብ ፖለቲካን በተመለከተ ቀስ በቀስ ጉዳቱን እያስረዱ እያስተማሩ፣ ወደ ሃሳብ ፖለቲካ የሚወርድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይሄን ፓርቲ በምናደራጅበት ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ስንሄድ፣ ሰው የብሔር መካረሩ ስጋትና መሠላቸት እንደፈጠረበት ተረድተናል፡፡ ትክክለኛ የህዝቡ ስሜት ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ አንድ አሰባሳቢ ነገር መሳቡ አይቀርም፡፡
አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔርተኛ ድርጅቶችን “ምን ይዘህልን መጣህ” ብሎ መጠየቅ ጀምሯል፡፡ ትክክለኛ አካሄዱ ይሄ ነው:: እንደው ነፃ በወጣ ሀገር፣ ነፃ አውጪ ነኝ ማለት ህዝቡ ሠልችቶታል፡፡ እኔ የምመኘው፤ እኛ በሃሳብ ስንፋጅና ስንጣላ፣ ህዝቡ እንዲስቅ እንጂ እኛ ህዝቡን እያጋጨን እንድንስቅ አይደለም:: አሁን እየሆነ ያለው ግን እኛ የእነ እንትናና የእነ እንትና ተወካዮች ተጣልተን ስናበቃ፣ በአካል ተገናኝተን ስንሳሳቅ፣ ህዝቡ ይፋጃል፡፡ ይሄ ፍፁም መለወጥ አለበት፡፡ ሂላሪና ትራምፕ ሲወራረፉ የአሜሪካ ህዝብ እንደሚዝናና ሁሉ፣ እኔና ሌላው ስንወራረፍ ህዝብ እንዲባላብን ሳይሆን እንዲስቅብን ነው የምፈልገው፡፡
ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?
እኛ ቀዳሚ ትኩረታችን  ምርጫው ሳይሆን የአገሪቱ ሠላምና አንድነት ነው፡፡ ሽግግሩ ላይ ነው ዋነኛ ትኩረታችን፡፡ ሽግግሩ በጥሩ ሁኔታ ከተከናወነ፤ ምርጫ ሁላችንም የምንዝናናበት ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ተቋማት መጠናከራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: የህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ አለበት፡፡ በአንድ በኩል ህዝብና ቤት ቆጠራ መካሄድ የለበትም የሚሉ ፓርቲዎች፣ በሌላ በኩል ምርጫ መደረግ አለበት ሲሉ ግራ አጋቢ ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች እኮ በራሣቸው ተመርጠው ጨርሰዋል፡፡ እንግዲህ ችግሩ የሚመጣው ፌስቡክ ላይ ያገኙት ላይክና ትክክለኛው መራጭ የሚሰጣቸው ድምጽ ሲለያይ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ተቋማት በቅድምያ ይጠናከሩ፣ በአገሪቱ ላይ አስተማማኝ ሠላም ይስፈን፣ ከተቻለ ህዝብና ቤት ቆጠራ ይካሄድ፡፡ ይህ ሁሉ ተሟልቶ ምርጫ የሚደረግ ከሆነ፣ አንድ ወንበር እንኳን ብናገኝ፣ ኢትዮጵያ ሠላም ከሆነች፣ ተጨባብጠንና ተመራርቀን ለመለያየት ዝግጁ ነን፡፡  

Read 10936 times