Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 09:57

ዳኛቸው ወርቁ በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ አዲስ ዘዴን የፈጠረ፣ የሞከረ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ አዲስ ዘዴን የሞከረ፣ የፈጠረ እና ተወዳጅ የስነ ጽሁፍ ሰው ነው፡፡  እንደሌሎቹ የስነ ጽሁፍ ሰዎች፣ ስነ ጽሁፍ የነፍስ ጥሪው እና የተፈጥሮ ስጦታው ብቻ አልነበረም፡፡ ስነ ጽሁፍን እስከ ሁለተኛ ዲግሪ (በማስተርስ ዲግሪ) የተማረ፣ ቴክኒኮቹንም በስራዎቹ ተግባራዊ ያደረገ ነው፡፡ በዚህም በወቅቱ ከነበሩት ደራሲዎች፡- ከሃዲስ ዓለማየሁ፣ አቤ ጉበኛ፣ በዐሉ ግርማ  እና ሌሎችም የስነ ጽሁፍ ሰዎች ይለያል፤ዳኛቸው ወርቁ፡፡ዳኛቸው የጻፈው በአማርኛ ብቻ አልነበረም፤ በእንግሊዝኛ ስራዎቹም ጭምር ታዋቂነትን አትርፏል፡፡ በ1973 የታተመው ‘The Thirteenth Sun’ የተባለው መፅሃፉ ምእራቡን ዓለም የማረከ ስራው ሲሆን በፖርቹጋልኛ፣ በጀርመንኛ እና በቻይንኛ ተተረጎሞ በሰፊው ተነቦለታል፡፡ መጽሃፉ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በ312 ዶላር ይሸጥ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው የተወለደው በ1928 ዓ.ም ነው፡፡ ለዳኛቸው ታላቅነትና የተስተካከለ ህይወት መስመር አባቱ ትልቅ ሚና አለው፡፡ አባቱ፣ አቶ ወርቁ በዛብህ ከጊዜው የቀደመ ተራማጅ ሰው ነበር፡፡

በ1914 ዓ.ም በድሬዳዋ በኩል ወደ ጅቡቲ ከዛም ፈረንሳይ በመግባት ለተወሰነ አመት ኖሯል፡፡ በአንደኛው የዓለም ጦርነትም የፈረንሳይ ወታደር በመሆን ተዋግቷል፤ በጦርነቱም ቆስሏል፡፡ በፈረንሳይ ሃገር እያለም ዘመናዊ ትምህርትን በመጠኑ ተምሯል፣ ከማዕድን ቆፋሪነት እስከ ሆቴል አስተናጋጅነት የተለያዩ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፈረንሳይ ለጉበኝት በሄዱበት ወቅት ለልዑካን ቡድናቸው ዋና አስተናጋጅ በመሆን አገልግሏቸዋል፡፡ ለዚህ ውለታውም ንጉሱ፣ ወርቁን ሊያስተምሩት ቃል ቢገቡለትም እሱ ግን በተሰጠው እድል ጓደኛው እንዲማር አደረገ፡፡ ወደ ሃገሩ እንዲመለስ ቢጠይቁትም በወቅቱ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ኋላ ላይ ግን ከአንድ አመት ቆይታ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ተመልሶ ሄደ፡፡ በ1930 ሙሉ በሙሉ ወደ ሃገሩ በመመለስ ዘመናዊነቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ በውሃ ጠገብ (ከደብረ ሲና ወጣ ያለች የገጠር ቀበሌ) አሰለፍ ሃብተወልድን አግብቶ ኑሮውን መሰረተ፡፡ ከዳኛቸው መወለድ በኋላ ግን ልጃቸውን ለማስተማር ሲሉ ወደ ደብረ ሲና ከተማ ኑሮቸውን ቀየሩ፡፡ አስገራሚው ነገር በወቅቱ ለትምህርት ግድ ካልነበረው ማህበረሰብ ልጃቸውንን ለማስተማር ወደ ከተማ መምጣታቸው ነው፡፡ ዳኛቸው ከአራት አመቱ ጀምሮ ቤተሰቡን በእረኝነት አገልግሏል፡፡ በስድስት አመቱ ግን በቀጥታ ወደ መንግስት ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርትን ጀምሯል፡፡ እንደ ወቅቱ ህፃናት የቄስ ትምህርት ቤት አልተማረም፡፡ የእናቱ ዘመድ የነበረ ሰው ግዕዝ እንዲማር ወደ ቤተክርስቲያን ቢወስደውም ዳኛቸው ግን ለትምህርቱ ፍቅር አልነበረውም፡፡ አባቱም ቢሆን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለትምህርቱ ፍቅር ስላልነበረው ወስዶት አያውቅም፡፡ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በደብረሲና ትምህርቱን የተከታተለው  ዳኛቸው፤ 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን በቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ የአባቱ ጓደኛ ለተሻለ ትምህርት ሊሴ ገ/ማርያም ቢያስገባውም ትምህርት ቤቱ  ስላልተመቸው ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ፡፡ ለከፍተኛ ትምህርት ቤተሰቦቹን እስከተለየበት ጊዜ ድረስ የቤተሰቦቹ ተጽእኖ ከፍተኛ ነበር፡፡ እናቱ ሁልግዜ ጠዋት ጠዋት ተረቶችንና ታሪኮችን ትነግረው ነበር፡፡ ይህ ገና በልጅነቱ ወደ ስነ ጽሁፉ እንደሳበው ይገመታል፡፡ ገና በልጅነቱ እናቱ የምትነግረውን ታሪኮች፣ የራሱን ፈጠራ በመጨመር ጽፎ ለማሳተም ቢሞክርም ኋላ ላይ ግን ሃሳቡን ትቶታል፡፡ ርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንደምትቀላቀል በሚወራበት ወቅት የጻፋቸው “ትርፉ ሃዘን ብቻ” እና “ያላቻ ጋብቻ” የተባሉ ቲያትሮች ለረጅም ጊዜ መድረክ ላይ ባይቆዩም በደብረሲና ከተማ ለእይታ ቀርበው ነበር፡፡ ዳኛቸው በተማሪነት ወቅቱም የከበደ ሚካኤልን ተረትና ምሳሌን፤ የመኮንን እንዳልካቸውን እና የህሩይ ወ/ስላሴን ስራዎች አንብቧል፡፡ እነዚህ ስራዎች በስነ ፅሁፍ ሕይወቱ ላይ ተፅእኖ ባይኖራቸውም የስነ ፅሁፍ ፍቅሩን ግን ከፍ አድርገውለታል፡፡  በልጅነት ጊዜው ከእኩዮቹ ጋር እንደልቡ መጫወት ቢፈልግም አባቱ ግን ጓደኞቹ ተጽእኖ እንዳያሳድሩበት በመስጋት፣ ከጓደኞቹ ጋር ብዙም እንዲጫወት አይፈቅድለትም ነበር፡፡ ከአባቱ ጋር ባለመስማማቱ የተነሳ፣ ዳኛቸው ከጓደኞቹ ጋር ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ኮበልሎ 6 ወር ተቀምጧል፡፡ ይህን ሕይወቱንም “ሰው አለ ብዬ” በሚለው ስራው አንጸባርቆታል፡፡ በትምህርት ህይወቱ የአባቱ ድርሻ ተጠቃሽ ነው፡፡ የትምህርት አያያዙን በየጊዜው እየተከታተለ በትምህርቱ በርትቶ እንዲገፋ ይመክረው ነበር፡፡ እናቱም ለእሱ የነበራት እንክብካቤ ልዩ ነበር፤ መምህሮቹም ቢሆኑ እንኳ እንዲገርፉት አትፈልግም ነበር፡፡ዳኛቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮተቤ ተምሯል፡፡ በኮተቤ ትምህርት ቤት ቆይታው ግጥሞችን ይፅፍ ነበር፡፡ 11ኛ ክፍል ሲደርስ ‘diphtheria’ በሚባል የጉሮሮ በሽታ በፅኑ በመታመሙ  በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ለ15 ቀን ተኝቶ ቢታከምም ስላልተሻለው ቤተሰቦቹ መጥተው ወስደውታል፤ ሁኔታውን ያዩት ቤተሰቦቹም ይድናል የሚል እምነት አልነበራቸውም፡፡ የዳኛቸው ከዚህ በሽታ መዳን ዳግም እንደመወለድ ነበር የተቆጠረው፡፡ ከበሽታው አገግሞ ወደ ትምህርቱ ቢመለስም በሽታው ስላገረሸበት በድጋሚ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ፡፡ ሲሻለው ወደ ኮተቤ ከመመለስ ይልቅ የመምህርነት ስልጠና ወስዶ በኮከበ ፅባሕ ትምህርት ቤት በመምህርነት ለሁለት አመት አገለገለ፡፡ ከዚያም የ12ኛ ክፍል ፈተናን እና የወቅቱን የሎንዶን ማትሪኩሌሽን ፈተናዎችን በመፈተን በሚገባ አልፏል፡፡መምህር ለመሆን ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ዳኛቸው፤ በመምህርነት ሙያ በመሰልጠን ለሁለት አመት በሐረር መድሃኒአለም ትምህርት ቤት በስኬት አስተምሯል፤ የወቅቱ ተመራቂ ተማሪዎቹም ጥሩ ውጤትን አግኝተውበታል፡፡ በዚህ ግዜ “ሰቀቀንሽ እሳት” የተሰኘውን ተውኔቱንም በመጻፍ በሐረር ቴክኒክ ትምህርት ቤት እና በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቲያትር ቤት ለእይታ አብቅቷል፡፡ ከዚህ ያገኘውን ገቢም ቀደም ብሎ ለጻፈው ለ“ሰው አለ ብዬ” ስራው ማሳተሚያ አድርጎታል፡፡ በዚሁ ግዜም ስላያቸው ፊልሞች እና ስላነበባቸው መጻህፍት፣ በአዲስ ዘመን እና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ይጽፍ ነበር፡፡ “ማን ብዙ ይከፈለው” በሚለው የወቅቱ ክርክር ላይም ደራሲ ብዙውን ሊያገኝ ይገባል የሚለውን ወግኖ በክርክሩ ላይ ተሳትፏል፡፡ዳኛቸው በወቅቱ በጥሩ የኑሮ ሁኔታ ላይ ቢገኝም በትምህርቱ ለመቀጠል ከነበረው ፍላጎት የተነሳ ትዳር አልያዘም ነበር፡፡ በ1953 ዓ.ም ወደ ወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በመግባት ለሁለት አመት ሂዩማኒቲ ቢያጠናም፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ሲከፈት ወደዛው በመዛወር፣ ለተጨማሪ ሁለት አመት ግዕዝ እና አረብኛን ጨምሮ በማጥናት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡ ዳኛቸው፣ እነዚህን ሁለት አመታት የመነሳሳቴ ዘመን በማለት ይገልጻቸዋል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታውም የወቅቱን ስርዓት የሚቃወሙ ግጥሞችን ይጽፍ ነበር፡፡ “እምቧ በሉ ሰዎች” የተሰኘውን የግጥም ስብስቡን የጻፈውም በዚሁ ግዜ ነበር፡፡   ዳኛቸው፤ በወቅቱ ስለነበሩት የስነጽሁፍ ስራዎች ሲናገር “. . .የነበረውን የፍትህ መዛባት፤ማህበራዊ ሁኔታ፤ ተመጣጣኝ የስራ ክፍያና የስራ ሁኔታ እንዲሁም የስራ ቅጥር ለዜጎች ሁሉ በእኩል ሁኔታ ይፈፀሙ የሚሉ የተቃውሞ ጽሁፎች ነበሩ” ለ”ብላክ ላየን” መጽሃፍ አዘጋጅ፤ ለሞልቬር፤ እንደገለጸለት፡፡ በወቅቱ የነበሩት ስራዎች በዳኛቸው እይታ ከአብዮተኝነት ይልቅ የተራማጅነት ይዘት ነበራቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም አብዛኛዎቹ የስነ ጽሁፍ ስራዎቹ ግጥሞች ነበሩ፡፡ ዳኛቸው ለመመረቂያ ጽሁፉ በግዕዝ ስነ ግጥሞች ላይ ጥናት አድርጓል፡፡ ከተመረቀ ከሶስት አመት በኋላም “ትበልጭ” ቲያትርን ለእይታ አብቅቷል፡፡ ከምረቃው በኋላም ዳኛቸው በዩኒቨርስቲ ውስጥ ከረዳት ምሩቅነት እስከ ሌክቸረርነት ድረስ አስተምሯል፡፡ በ1962 ባገኘው ነጻ የትምህርት እድል የፈጠራ ጽሁፍ (Creative Writing) በአሜሪካ አዮዋ ዩኒቨርስቲ ለሶስት ዓመት ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውንም በስነጥበብ (Fine Art) ተመርቋል፡፡ ከትምህርት መልስም “ማሚቴ እና ሌሎች” በሚል ርዕስ ሁለት ታሪኮችን ለህትመት አብቅቷል፡፡ አሜሪካ ትምህርት ላይ እያለም  ስምንት ታሪኮችን በእንግሊዝኛ ቢጽፍም ተጨማሪ ለመጻፍ ሃሳብ ስለነበረው አላሳተማቸውም ፡፡በአዲስ አበባ የኒቨርስቲም በአስተማሪነቱ ወቅት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች የተነሳ ከዩኒቨርሰቲው አስተዳደር ጋር ስምምነት አልነበረውም፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ የማይከታተል የባላባት ልጅ ውጤት እንዲያስተካክል ሲጠየቅ ፈቃደኛ አልነበረም፤በዚህ ምክንያትም ከጉዳዩ ጀርባ በነበረው የወቅቱ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አክሊሉ ሃብቴ ጋር በመጋጨቱ፤ ከስራ እሰከ መታገድ ደርሶ ነበር፡፡ ከነዚህ ሁሉ ነገሮች በኋላም ዳኛቸው “አደፍርስ”ን ፅፏል፡፡ ዳኛቸው የሚናገረው አንድ ስራ ብቻ እንዳለው ነው እሱም፤ “አደፍርስ”፡፡ ዳኛቸው “አደፍርስ”ን እንደ ብቸኛ ስራው የሚናገረው ቀደምት ስራዎቹን በሙሉ ለ”አደፍርስ” እንደመዘጋጃ ስለሚቆጥራቸው ነው ይላል ሞልቬር፡፡የ”አደፍርስ”ን ውስብስብነት እና ከባድነት ዳኛቸው አይቀበለውም፡፡ “የተጠቀምኩት ተወልጄ ያደኩበትን አካባቢ አማርኛ ነው”“አደፍርስ”ን አስመልክቶ በወቅቱ የተለያዩ ደራሲዎች የሚከተለውን ብለው ነበር ፣አድፍርስ በኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ ፈርቀዳጅ ነው፡፡ ከተለመደው የተረት ተረት አቀራረብ ከ ሀ-ፐ የሚሄድ አይደለም፡፡ የተለየ ሲኒማዊ አቀራረብ ነበረው፡፡ ከመሃል ጀምሮ ያደጉ ገፀባህርያት ይዞ በአጭር ልብ ወለድ ዘመን መቋጨት ከተለመደው የተረት ተረት አተራረክ በጣም ይለያል፡፡ አደፍርስ የሚለየው በቋንቋው ነው፡፡ ቅኔያዊ አቀራረብ አለው፡፡ የአረፍተ ነገር አገነባቡ የንግግር አይነት ነው፣ ይህም በወቅቱ ከተለመዱት የልብ ወለድ አይነቶች ይለየዋል፡፡ከምዕራፍ ወደ ምዕራፍ ሲሻገር በምልሰት እና በገለጻ እንደ አዲስ ይጀምራል፡፡ “አለ” ወይም “አለች” በሚሉት ቃላት ዓረፍተ ነገሩን ይበጣጥሰዋል፡፡ በአካባቢያዊ ገለጻ ይጀምራል፤ ምልልሱም የገፀባህርያቱን የትምህርት ደረጃ አካባቢና መደብ ያሳያል፡፡ ደራሲው ቃላትን ይፈጥራል፣ እነዚህ ቃላት ግን ከማህበረሰቡ እሩቅ አይደሉም፡፡ መፅኃፉ በብዙ መልኩ ተጠቃሽ ነገሮቹ ተራማጅነት ሲሆን በወቅቱ ግን ተቀባይነትን ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ለዚህም እንደምክንያት አንባቢ እስከሚርቀው ድረስ ከባድ ነው የሚለው ወሬ በሰፊው በመዛመቱ፣ መጽሃፉ በበቂ ቅጂዎች ታትሞ አለመሰራጨቱ፣ ወዲያውኑ ተነቦ የሚዋጥ ሴራ ስለሌለው፣ ለብዙሃኑ የተጻፈ ስላልነበር፤ ብዙሃኑ የተማረ ስላልነበር እና ደራሲው በወቅቱ የተማረውን የስነ ፅሁፍ ስልት ስለተገበረው ለሁሉም አንባቢ ምቹ እንዲሆን አላስቻለውም ነበር፡፡ ምንም እንኳ ዳኛቸው “የተጠቀምኩት ተወልጄ ያደኩበትን አካባቢ አማርኛ ነው” ቢልም፣ የተጠቀመባቸው ቃላት መክበድ እና በመዝገበ ቃላት ላይ አለመገኘታቸው፣ የአፃጻፍ ቴክኒኩ አለመለመድ እና የወቅቱ ተደራሲም የኪነጥበብ ንቃት ማነስ ለመፅኃፉ አለመነበብ ይጠቀሳሉ፡፡     ጋሼ ስብሃት ዘነበ ወላ በጻፈው “ማስታወሻ” ላይ እንደተናገረው፡-  “. . . “አደፍርስ” ላይ በተሰጠው የተንዛዛና አሰልቺ ትችት ምክንያት ይህ ሰው ከጥበብ ራሱን ለየ፡፡ ከዚያምበኋላየአማርኛ ልብወለዶችን መጻፍ ተወ፤ ይልቁንም ወደ ቴክኒካዊ እና ማስተማሪያ ጽሁፎች በማዘንበሉ ታላቅ ሰው አጥተናል” ሲል ቁጭቱን ተናግሯል፡፡

 

ዳኛቸው፣ “በባህላዊ ቅኔ ግጥሞች” እና “የልብ ወለድ አጻጻፍ ስልት” ላይ መጽሃፍ በመጻፍአሳትሟል፡፡ በቀድሞው ኢኮል ኖረሜ ሱፔርየር፣ በአሁኑ ጥቁር አንበሳ ትምህረት ቤትም ስነ ግጥም አስተምሯል፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ የደረጃዎች ተቋም ውስጥ መስራት እንደጀመረ አብዮቱ ፈነዳ፡፡ በዚሁ ወቅትም የጻፈው የህጻናት መጻኅፍት በ1971 በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ታትመዋል፡፡ ከ”አደፍርስ” በኋላ ወደ ቴክኒካዊ ስራዎቹ ያዘነበለው ዳኛቸው፣ በ1977 “የጽሁፍ ጥበብ መመሪያ”ን እንዲሁም ከዶ/ር አክሊሉ አምሳሉ ጋር በመሆንም የአማርኛ ፈሊጥ እና ዘይቤ ላይ መጽሃፍ አዘጋጅተዋል፡፡ በተመሳሳይ ወቅትም ለኢትዮጵያ ደረጃዎች ተቋም የሳይንሳዊ እና ቴክኒካዊ ቃላቶች መፍቻ መዝገበ ቃላት አዘጋጅቷል፡፡ በአብዮቱ ወቅት የማይታተሙ ስራዎችን እየጻፈ እንደነበር የተናገረው ዳኛቸው፤ ላለመታተማቸውም ምክንያትም “አብዮቱ በራሱ ከእሱ ጽሁፍ በበለጠ ኪናዊ እና ፈጣን ነበር” ይላል፡፡ ሌላው እንደ ምክንያት የጠቀሰው ነገር ደግሞ የወቅቱን ምቹ አለመሆን ነው፡፡ የሚፅፈው ነገር በአፍታ ወደ እውነታ ይቀየር ስለነበር ጽሁፎቹ ከአብዮቱ በኋላ ታሪካዊ ዶክመንቶች ሊሆኑ እንደሚችሉም ይናገር ነበር፡፡ ዳኛቸው፣ ስለ ራሱ ስራ “አደፍርስ” ሲናገር “. . .አደፍርስ ተራማጅ፣ምክንያታዊ እና በችግር የተከበበ ሰው ነበር፡፡ ከማህበረሰቡ የተለየ እና አብሮ ለመሄድ ያልቻለ፤ ከተግባር ይልቅ ምክንያትን የሚደረድር የዘመኑ ሰው ነበር” ይላል፡፡ ኛቸው፣በአደፍርስ የጥንቷን እና ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ግጭቶች አሳይቷል፡፡ ጥንታውያኑ የመኖር ሃይላቸው የሆኑትን እሴቶቻቸውን በማጥበቅ ህይወታቸውን ይመራሉ፤ዘመናውያኑ ግን ወይ እነዚህ እሴቶች የሏቸው ወይ ከህይወታቸው አያዋህዷቸው በእውቀት ብቻ የተሞሉ ነበሩ፣ ይላል፡፡ቸው ስራዎቹ ምንም እንኳን በችግር የተከበቡ ቢሆኑም በኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ እድገት ተጠቃሽ ሚና እና ጉልህ ስፍራ አላቸው፡፡ዳኛቸው፣ ከስነ ጽሁፍ ስራው ባሻገርም የበአሉ ግርማ “ኦሮማይ” እስከታተመበት ጊዜ ድረስም የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የቦርድ ስብሳቢ በመሆን ሰርቷል፤ ከኦሮማይ መታተም በኋላ ግን እሱም ሆነ የቦርድ አባላቱ በሙሉ ከስራ ተባረዋል፡፡ ዳኛቸው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ቢሆንም ብዙውን ግዜ ግን ብቻውን ማሳለፍን ይመርጥ ነበር፡፡ ሰዎች ላይ እምነት ስላልነበረው ብዙ ጓደኞችም አልነበሩትም፡፡ መንግስቱ ለማ ግን የቅርቡ ሰው ነበሩ፡፡ በ1983 ዓ.ም ከመደበኛ ስራው በጡረታ ከተገለለ በኋላ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አማካሪ በመሆን አገልግሏል፡፡ ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው በምግብ መመረዝ ምክንያት በ1987 ዓ.ም ህዳር 22 ቀን በሞት ተለይቶናል፡፡ ህዳር 23 ቀን 1987 ዓ.ም በደብረ ሲና መድሀኒአለም ቤተ ክርስቲያን ከ17 ዓመት በፊት የቀብር ስርዓቱ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ታላቅ ሰው በሞት ቢለየንም ያልታተሙ ስራዎቹን ግን ትቶልን አልፏል፡፡ “Shot From the Mountain Top” በሚል የፃፈውን ልዩ እና ተወዳጅ ስራ በማለት ሲገልጸው፤ ለመጠናቀቅ ጥቂት የቀረው ሌላም ፅሁፍ ነበረው፡፡ዳኛቸው ወርቁ በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ አዲስ የአፃፃፍ ዘዴን የፈጠረ የሞከረ፤ ለስነ ጽሁፉም ዕድገት እንደ ማዕዘን ድንጋይ ሊጠቀስ የሚገባው ታላቅ ሰው ነበረ፡፡

 

 

 

Read 8591 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:22