Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

ዜጎቿን የማታከብር አገር አትከበርም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(15 votes)

• የክብር ዜግነት መስጠት ላልተወሰነ ጊዜ መቆም አለበት • ኢህአዴግ ከ20 ዓመታት በላይ የዘራውን እያጨደ ነው
                  

             የአንጋፋው ምሁርና  ፖለቲከኛ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ድንገተኛ ህልፈት ብዙዎችን አስደንግጧል፤ አሳዝኗል፤ አስቆጭቷልም:: ህመማቸው ሳይሰማ እኮ ነው ዜና ዕረፍታቸው የተነገረው፡፡ በተለይ በክፉና በደጉ ጊዜ ከአጠገባቸው ላልተለዩት፣ ጀርመናዊቷ ውድ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው፣ ሃዘኑ ምን ያህል ዱብ ዕዳና ጥልቅ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡ ፈጣሪ፣ ብርታቱንና ጽናቱን ይስጣቸው::  
ዶ/ር ነጋሶ፤ የሚገባቸውን ክብርና ሞገስ ያላገኙ፣ የጉስቁልና ህይወት እንዲመሩ የተገደዱ፣ ነገር ግን  አኩርፈው የተሻለ ኑሮ  ፍለጋ አገራቸውን ጥለው ያልተሰደዱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ (ጀርመን እኮ እጇን ዘርግታ ነበር የምትቀበላቸው!) ከምሬ ነው ---  ዶ/ር ነጋሶ በደጉም በክፉም ጊዜ አገራቸውን እኩል ነበር የሚወዱት፡፡ ከፕሬዚዳንትነት ሥልጣን በፈቃዳቸው ለቀው፣ መኪናና ቤታቸውን መንግስት ነጥቋቸው፣ መድሃኒት መግዣ ሳንቲም ባጡም ጊዜ እንኳን አገራቸውን አልከዱም፡፡ በአገራቸው ተስፋ አልቆረጡም፡፡ የአገር ፍቅራቸው የተንጠለጠለው  በማግኘትና በማጣት ላይ አልነበረም፡፡ እንደውም እሳቸው ቤትና መኪና አጥተው ይኳትኑ በነበረ ወቅት ጭምር፣ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን  ችግር ለመቅረፍ ይታትሩ እንደነበረ ከህልፈታቸው  በኋላ እየሰማን ነው፡፡ (ሰው ካልሞተ መቼም አይመሰገንም አይደል ?!)  
በሃሳብ የተለዩትን ሁሉ ጠምዶ የሚይዘው  ኢህአዴግ ነፍሴ፣ ከ10 ዓመት በላይ ከሚኒስትርነት እስከ ርዕሰ ብሔርነት አገራቸውን ያገለገሉትን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ለመከራና ጉስቁልና ህይወት እንደዳረጋቸው ወዳጆቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ከርዕሰ ብሔርነት በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ  በግላቸው  ምርጫ ተወዳድረው ፓርላማ በገቡ  ማግስት፣ መንግስት የሰጣቸውን ቤትና መኪና  ቀምቶ፣ ጡረታና ጥቅማ ጥቅማቸውን ያለ አግባብ እንደነፈጋቸው ራሳቸውም በህይወት ሳሉ  ተናግረውታል፡፡ (ሰሚ አላገኙም እንጂ!)
የማታ ማታም፣ ይገባኛል ብለው ሲከራከሩበት የቆዩትን የመብት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኙ ነው ያለፉት:: (ኢህአዴግ ቆሞ ነው ሞቶ!) ግን ነገሩ  በእጅጉ ያስቆጫል፡፡ ያሳዝናልም፡፡ የእሳቸው  መብትና ጥቅም አለመከበር፣ የሚገባቸውን ክብርና ማዕረግ አለማግኘትም፣ የእሳቸው ጉዳት ብቻ አድርገን ከቆጠርነው ተሳስተናል፡፡ አገርም ጭምር ናት ክብሯን ያጣችውና  የተጎዳችው፡፡ ዜጎቿን የማታከብር አገር፣ ራሷም አትከበርም፡፡ አገር ማለት እኮ ዜጎች ናቸው፡፡
በየትኛውም ሥርዓት የኖሩና ለአገራቸው ታላላቅ ውለታዎችና መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎችን የማያከብርና የሚገባቸውን ዕውቅና የማይሰጥ ንፉግ መንግስት፣ የዘራውን እንደሚያጭድ አትጠራጠሩ፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ፣ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት 27  ዓመታት፣ ያለፉትን መንግስታትና  ሥርዓቶች በጅምላ  ሲያወግዝና ሲረግም ነው የኖረው:: ኢትዮጵያን በማዘመን ረገድ ዋናውን መሰረት እንደጣሉና ብዙ እንደተጉ የሚነገርላቸውን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ጨምሮ፡፡ ይሄ የእርግማንና የውግዘት አባዜው ከራሱ ጋር ብቻ ቢቀር ደግሞ ደግ ነበር፡፡ ይኸው እንደሚታየው  እኛም ላይ (ህዝቡን ማለቴ ነው!) አጋብቶብናል:: ውግዘትና እርግማን ሱስ ሆኖብናል፡፡ ለዚህ እኮ ነው ያለፉትን 27 ዓመታት “የጨለማ ዘመን!” እያልን በደምሳሳው  የምንገልጸው፡፡ (ኢህአዴግ የዘራውን እያጨደ ነው!!)
በነገራችን ላይ የሾመውንና የሸለመውን መሻርና  ማዋረድ ለኢህአዴግ ብርቁ አይደለም:: ራሱ ከሰቀለበት የሥልጣንና የማዕረግ ማማ እያወረደ፣ መሬት የፈጠፈጣቸውን ኢህአዴጋውያን ብዛት ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ዛሬም በለውጥ ማግስት ኢህአዴግ ነፍሴ፣ ከዚህ ክፉ ዓመሉ ሙሉ በሙሉ አልተላቀቀም:: ከጥቂት ወራት በፊት ከሥልጣናቸው የተነሱት የቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዚዳንት፣ በሌላ የመንግስት ሃላፊነት ላይ ቢመደቡም፣ መንግስት የሰጣቸውን ቤትና መኪና ከመቅጽበት ተነጥቀው ለችግር መዳረጋቸውን በቅርቡ ተናግረዋል:: ልብ አድርጉ፤ ሰውየው በወንጀል ተጠርጥረው አልተከሰሱም፡፡ እንደውም በህንድ ዲፕሎማት ሆነው ተሹመዋል:: (ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት!) ግን ከክልል ፕሬዚዳንትነታቸው በተነሱ ማግስት፣ ቤትና መኪና ብቻ ሳይሆን ክብርና ሞገሳቸውን ጭምር ነው የተገፈፉት፡፡ (የክፋት አባዜ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?!)
መቼም ይሄ  ዜጎችን የማዋረድ  አባዜ ያልተጋባበት የመንግስት መ/ቤትና ተቋም የለም ማለት ይቻላል:: የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር፣  የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ፣ ሁለት ጎምቱ መምህራንን ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው ላይ አባርሯቸው ነበር:: (በእርግጥ የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ናቸው!) በማባረር ብቻ ግን አልበቃውም፡፡ ከሚኖሩበት  የመንግስት ቤትም  አስወጥቷቸዋል፡፡ (የመንግስት መኪና የላቸውም እንጂ  ይቀማቸው  ነበር!)
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለዓመታት ሲከምር የኖረውን  የጥፋት ተራራ በመናድ ተግባር ላይ  የተጠመደው አዲሱ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር፣ እኒህን  የተባረሩ ሁለት የዩኒቨርሲቲ መምህራን  ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ (መቼም አይመለሱም ነበር!) ኢህአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩ 44 ገደማ  መምህራንም፣ ወደ ሥራ ገበታቸው እንደሚመለሱ  ዶ/ር ዐቢይ፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ (የለውጡ አንዱ ትሩፋት ነው!)
ወደተነሳንበት ዋና ጉዳይ ስንመለስ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ በህይወት ሳሉ የሚገባቸውን መብትና ጥቅም እንዲሁም ክብር ባያገኙም ቅሉ፣ ቢያንስ ከህልፈታቸው በኋላ ተገቢውን የሽኝትና የቀብር ሥነሥርዓት ማግኘታቸውም ተመስገን ነው፡፡ (የሃዘን ቀን መታወጁ፣ ለክብራቸው 21 ጊዜ መድፍ መተኮሱ፣ ቀብሩ በወታደራዊ  ሥነሥርዓት መከናወኑ ወዘተ--) የቀድሞው ኢህአዴግ  በሥልጣን ላይ ቢሆን ኖሮ  እኮ እቺንም “ክብር” መንፈጉ አይቀርም  ነበር:: (ፈጣሪ አገራችንን ከውርደት አድኖልናል!) ይታያችሁ--- ከተማሪነት እስከ ምሁርነት በፖለቲካ ትግል ውስጥ ያሳለፉ፣ ከኦነግ እስከ ኦህዴድ እንዲሁም አንድነት ፓርቲ ድረስ ያደራጁና የመሩ፣ ከሚኒስትርነት እስከ ርዕሰ ብሄርነት አገራቸውን ያገለገሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ --- በክብር ባይቀበሩ  ኖሮ፣ ዓለም እንዴት ይታዘበን እንደነበር፡፡ (ከውርደት ተርፈናል!!)
በነገራችን ላይ  የኦህዴድ መሪዎች እነ አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ በ11ኛው ሰዓት ላይ ደርሰው፣ ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ለትራንስፖርት የሚጠቀሙበት መኪና መስጠታቸውና የህክምና ወጪያቸውን መሸፈናቸው እንዲሁም በአማካሪነት እየሰሩ ወርሃዊ ደሞዝ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸታቸው (በትክክል መተግበሩን ባላውቅም) የሚደነቅ ነው፡፡ በምቾት ባይንደላቀቁም ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል  በእፎይታ ህይወታቸውን እንደመሩ  እገምታለሁ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም:: ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ  በትላልቅ መንግስታዊ ሥነሥርዓቶችና ዝግጅቶች ላይ እየተጋበዙ መገኘታቸውም  (ለምሳሌ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አዲስ አበባ በመጡ ጊዜ) ቀላል ነገር አይደለም፡፡ (የቀድሞ ርዕሰ ብሔር  እንደነበሩ የተዘነጉ ሰው እኮ ናቸው!) ሌላው የሚያጽናናው ነገር፣ ዶ/ር ነጋሶ በአገሪቱ ላይ የለውጥ ተስፋ መፈንጠቁን አይተው ማለፋቸው ነው፡፡ በዚህም ነፍሳቸው በሃሴት ጮቤ ትረግጣለች ብዬ አምናለሁ:: አብዛኛውን  ህይወታቸውን ያሳለፉት ለውጥ ለማምጣት ሲታገሉ ነውና፡፡
አንድ ነገር አሰብኩ፡፡ በቀድሞው የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዶ ላይ የተፈጸመውን በደልና ኢ-ፍትሃዊነት እያዩ፣ አብረዋቸው ለዓመታት የኖሩት ጀርመናዊቷ ውድ ባለቤታቸው፣ (ወደ አገራቸው መመለስ እየቻሉ!) ኢትዮጵያንና መንግስታችንን ምን ያህል እንደታዘቡ መገመት አያዳግትም፡፡ ይሄን ለማካካስና የአገራችንን ገጽታ ለመቀየር ለእኒህ ጀርመናዊት ወይዘሮ፣ የክብር ዜግነት ቢሰጣቸው የሚል ሃሳብ ብልጭ ብሎልኝ ነበር:: ግን ጥቂት አሰብኩና ተውኩት፡፡ ምክንያቱም ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል:: እንኳን ለውጭ አገር ዜጋ ለኛም ለራሳችን የሚያጓጓና የሚያስቀና አልሆነም፡፡ አንድም ባዕድ የውጭ ሃይል ሳይደርስብን፣ እርስ በርሳችን  የምንገፋፋና ከቀዬ የምናፈናቅል፣ ወገናችንን ከጎጆው አውጥተን  ሜዳ ላይ የምንበትን (በክፋት- በጠባብነት- በድንቁርና- በስግብግብነት-) ህዝቦች ሆነናል:: (በ2 ዓመት ውስጥ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አፈናቅለናል!) እናም ወደድንም ጠላንም---- ኢትዮጵያዊነት ለጊዜው መገለጫው ይሄ ነው፡፡ እንደ ጥንቱ የሚያጓጓና የሚያስቀና አይደለም፡፡ የሚያስፈራና በርቀት በትዝብት የሚመለከቱት እንጂ! በዚያ ላይ እኛ ራሳችን መቼ  በ”ኢትዮጵያዊነት” ላይ ተስማማንና ነው ለሰው አገር ሰው ዜግነት የምንሰጠው!? ኢትዮጵያዊነትን እኛ ባለቤቶቹ  መቼ አከበርነውና ነው ለሌላው በክብር ለመሸለም የምንነሳው?! ሌላም ፍራቻ አለኝ፡፡ ዜግነት የምንሰጣቸው የውጭ  ሰዎች ሁኔታችንን አይተው “No Thank you” ብለው ኩም ቢያደርጉንስ?! ይሄን ይሄን አሰብኩና የክብር ዜግነት መስጠት የሚለውን ነገር ከጭንቅላቴ አወጣሁት:: እንደውም  ላልተወሰነ ጊዜ፣ የክብር ዜግነት መስጠት ቢቆም ጥሩ ሳይሆን አይቀርም እላለሁ፡፡ (በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ መጀመሪያ እኛ እንስማማ!)
በነገራችን ላይ በአገር ውስጥ  ስደት ከዓለም ቀዳሚ ያደረገንን ክፉ የማፈናቀል አባዜ የጀመረው እኮ ራሱ ኢህአዴግ  ነው፡፡ እንዴት መሰላችሁ ---- ስንቶቹን ራሱ የሾማቸውን የመንግስት ባለሥልጣናት ከሥልጣናቸው ሲያወርዳቸው ከሃላፊነታቸው  ብቻ አልነበረም የሚያፈናቅላቸው፡፡ ከመኖርያ ቤታቸውና ከመሰረታዊ የኑሮ ፍላጎታቸው ጭምር ነው፡፡ በዚህ መሰረት በአንድ ወቅት ከፍተኛ ሹመትና  ክብር  የነበራቸው በርካታ ግለሰቦች  ያለ አግባብ ከኑሯቸውም ከክብራቸውም ተፈናቅለዋል:: (በፈጸሙት ወንጀል ዘብጥያ የወረዱትን አይመለከትም!) ሌላ ልጨምርላችሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት፣ “ህገ ወጥ ግንባታ” በሚል ሰበብ፣ በራሱ በኢህአዴግ መራሹ - መንግስት ከመኖርያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ በቅርቡ እንኳን (በለውጡ ማግስት ማለቴ ነው!) የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ህገወጥ ግንባታ በሚል ስንት ዜጎች ናቸው ተፈናቅለው  ሜዳ ላይ የተበተኑት፡፡ (መንግስታዊ ማፈናቀል በሉት!) እነዚህ ዜጎች ህገወጥ ቢሆኑም እንኳን ህገወጥ እንዲሆኑ የፈቀደላቸው ማንም ሳይሆን እራሱ ኢህአዴግ  ነው፡፡ እናላችሁ -- ዛሬ በየቦታው የተስፋፋውን የማፈናቀል አባዜ ያስተማረው ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ አሁን ታዲያ የዘራውን እያጨደ ነው፡፡ (እኛንም ጭምር እያሳጨደን ነው!) ፈጣሪ በቃችሁ ይበለን!!

Read 5218 times