Monday, 13 May 2019 00:00

“ኢትዮጵያ ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም!”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

  ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን (ተዋናይ ሱራፌል ጋሻው ሙት ዓመት ላይ እንደተናገረው)

                ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ትንሽ ልጅ አንድ ታላቅ የኔታ ዘንድ “ሀሁ” ይቆጥር ነበር፡፡ ነጋ ጠባ እናት አባቱ ምሳውን በምታምር ዳንቴል ቋጥረው ይሰጡታል፡፡ ውስጡ ንፍሮ ያለበት ውሃም በጠርሙስ አዘጋጅተው ይሰጡታል፡፡ ከዚያ እጁን ይዘው መንገድ ያሻግሩታል፡፡ ከት/ቤቱም ዘበኛ ጋር ያገናኙታል፡፡ ዘበኛውም ባለበት ኃላፊነት ወደየክፍል እንደሚያደርሳቸው ተማሪዎች ሁሉ ክፍሉ ያስገባዋል፡፡
አንድ ቀን ይኸው ተማሪ እያለቀሰ ወደ ቤቱ መጥቶ፣ ቤት እንደተቀመጠ አባት ይደርስና፤
“ምነው ዛሬ ትምህርት የለም እንዴ” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ልጅ። “የኔታ መቱኝና ትምህርት ቤቱን ጥዬላቸው መጣሁ”
አባትም፤
“መቼም ሳታጠፋ ከመሬት ተነስተው አይመቱህም፡፡ በል ዕውነቷን ንገረኝ?! ከዋሸህ እኔም እገርፍሃለሁ አለቅህም ዋ!”
ልጅ፤
“መነሻውማ “ሀ” በል ሲሉኝ አልልም ስላልኳቸው ነው!”
አባት፤ ተናደደና፣
“አንት የሞትክ፣ የእኔ ልጅ ሆነህ ‹ሀ› ማለት አቅቶህ ትገረፋለህ?”
ልጅ፤
“አይ አባዬ፣ የየኔታ ጉዳቸው መች ያልቃል?”
አባት፣
“እንዴት?”
ልጅ፣
“‹ሀ› ስትል ‹ሁ› በል ይሉሃል፡፡ ‹ሁ› ብዬ ተገላገልኩ ስትል፣ ‹ሂ› በል ይሉሃል፡፡ እንዲህ እያሉ እስከ ‹ፐ› ያስለፈልፉሃል - አያድርስብህ አባዬ” አለና መለሰ፡፡
***
“ኢትዮጵያ ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም” መባሉ ዕውነትነት አለው፡፡ ደራሲ አቤ ጉበኛ፤ በእንዲህ ዓይነት አገር ውስጥ “አልወለድም” ማለቱ ነበረ፡፡ ዛሬ እነሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ዘንድ ሲደርሱ ፈተናው የመወለድ አለመወለድ ሳይሆን ተወልዶ ማደግ ያለመቻልና ያለመቻል ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ እንግዲህ መበርታት ያለብን አሁን ነው ማለት ነው! አጀንዳችን መለወጥ ነው የምንል ወገኖች፤ በአፍአዊነት እንወጣዋለን ብለን አናስብ (nothing changes in rhetoric but in action እንዲሉ፡፡ አንድም a change is as good as rest የሚለው ብሂልና everything changes except the law of change በአንደበት ፍላጎት ምንም ለውጥ አይመጣም፤ በተግባር እንጂ፡፡ ሁለትም ከለውጥ ህግ ሌላ፣ ሁሉም ነገር ይለወጣል የሚለው ዕውነት ነው የሚፀና!
ኢትዮጵያ የለውጥ ሂደቷን እሹሩሩ እያለች ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም ዕውነተኛ ለውጥ ከልብ አግኝታ አታውቅም፡፡ ከጦርነት ሌላ፣ ከግጭት ሌላ ምንም አይታ የማታውቅ አገር ምን ታድርግ? ኢኮኖሚዋ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ፣ ፖለቲካዋ ዕድሜ ልኩን የጎሽ፣ ዕድሜዋ የትየለሌ፣ ሹሞቿ እንዳየሩ ተለዋዋጭ፣ ስርዓቷ መቼም የማይጠራ አገር ናት፡፡ በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን የተሳለ አንድ የካርቱን ስዕል፤ በክብ የተቀመጡ ሹማምንትን ሁኔታ ያሳያል፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ምስሉ አንዱ ጎኑ ያለውን ሹም በሌላ ጣቱ ሲጠቁም ያሳያል፡፡ የሚቀጥለው ደግሞ ወደሚቀጥለው ሹም ጣቱን ቀስሮ ይታያል፡፡ ከሥሩ “እሱ ነው!” የሚል ተፅፎበታል፡፡ የሚቀጥለውም እንደዚያው፡፡ የሚቀጥለውም … የሚቀጥለውም … ክቡ አያልቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ህይወት እንደዚያው ነው፡፡ መቀጠሉም አይቀሬ ነው!
ዛሬ ሰላምን በወሬ ሳይሆን በተግባር እናስበው፡፡ ቅርብ ይመስለናል እንጂ መንገዱ እጅግ ረጅም ነው፡፡
“መንገዱ ረዘመ ረዘመ
ወዳንቺ ስመጣ ልቤ እየደከመ” ይባል ነበር። በጥንቱ ዘመን ዜማ!
መንገድ ሲሄዱት ብቻ ሳይሆን ሲፅፉትም ይረዝማል፡፡ የአገር መንገድ ሲሆን ደግሞ አንጀት ይስባል፡፡ ህዝብ መንገድ ካልለመደ ደግሞ ሁሉም መንገድ አሰቃቂ ይሆናል፡፡ ጥረቱና ተስፋው የሁሉም ሰው ነውና አድካሚነቱ አያጠራጥርም፡፡ ኢትዮጵያ ወልዳ ታሳድግ ዘንድ እንዲቀናት፣ የአሳዳጊነቱን ሚና ሁላችንም እንድንጫወት መመካከር አለብን፡፡ መነጋገርና መደማመጥ አለብን፡፡ የመንግስት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ህዝብ ወይም የህዝብ ቡድን፣ አገር፣ አገር … አሁንም አገር ብሎ መጮህ ይገባዋል!
ያኔ ኢትዮጵያ ዳግመኛ መውለድ ይዳዳታል!! 

Read 13465 times