Monday, 06 May 2019 12:53

ያሬዳዊው ሥልጣኔ ክፍል - ፳ ማጠቃለያ - 2

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 “--ሰምነር ካበረከተልን አራት ሥራዎች ውስጥ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ላይ የሚያተኩሩት ሥራዎቹ፣ ሁለት ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ የተሰሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፣ ከኢትዮጵያ የተገኘውን አፍሪካዊ ፍልስፍና ለዓለም ማስተዋወቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዘርዓያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት ማስረገጥና ሐተታውም ከምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና ጋር ያለውን ዝምድና ማሳየት ነው፡፡--”
                      በማጠቃለያ ክፍል አንድ ፅሁፌ ላይ፣ እኔ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ክሽፈት፣ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ታሪክ እንዲሁም የኢትዮጵያን የምሁራንና የባህል ታሪክ የምመለከተው ከሁለት ፅንሰ ሐሳቦች - ከተአምራዊነትና ከብህትውና - አንፃር እንደሆነ ገልጫለሁ፡፡ ይሄም ምልከታ ከቅድመ ክርስትና ጥንታዊ የአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ተሸክሞ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ ያሉትን የባህል፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ልቦናና የፖለቲካ ሁኔታዎችን ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ ‹‹ተአምራዊነት›› እና ‹‹ብህትውና›› የሚባሉትን ፅንሰ ሐሳቦች ከዕለት ተዕለት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔነት አሻግረን፣ አካዳሚያዊ ተዋስዖን ማልበሳችን በኢትዮጵያ ጥናት ላይ አምስት ዋና ዋና አበርክቶዎች እንደሚኖሩት በመጥቀስ ነበረ የማጠቃለያ ክፍል አንድ ፅሁፌን የዘጋሁት፡፡ ዛሬ የማጠቃለያ ፅሁፉን የምቋጨው እነዚህን አምስት አበርክቶዎች ዘርዘር አድርገን በመመልከት ነው::
የፅንሰ ሐሳቡ የመጀመሪያው ጥቅም፣ ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ የተፀነሰውን የያሬዳዊውን ሥልጣኔ የሐሳብ ሥረ መሰረቱን (genealogy) ለመረዳት የሚጠቅመን መሆኑ ነው፡፡ የያሬዳዊው ሥልጣኔ የቆመበትን የሐሳብ ሥረ መሰረት አካዳሚያዊ በሆነ መንገድ በመረዳት ረገድ ቀዳሚው ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ሳይሆን አይቀርም፤ በመቀጠል ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› በሚለው ሥራቸው (1986):: እጓለ፣ ‹‹የያሬዳዊው ሥልጣኔ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ሃይማኖታዊ ሥልጣኔ ነው›› በማለት ነበር የሥልጣኔውን ልዩ ባህሪና የሐሳብ መሰረት የገለፀው::
ሆኖም ግን፣ እጓለ፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ማዕከል ማድረጉን በአዎንታዊነት ከመግለፅ ውጭ፣ ይህ የሥልጣኔው ባህሪ፣ የሰውን ልጅ ወደ ጠርዝ በመግፋት ያስከተላቸውን አሉታዊ ውጤቶች ሊያሳየን አልቻለም፡፡ በዚህ ረገድ የፕ/ር መስፍን አቀራረብ የተሻለ ነው፡፡ እጓለ፣ ይሄንን ማድረግ ያልቻለው ደግሞ የሥልጣኔውን ብህትውናዊ ገፅታ ለብቻው ስላላጠናው ነው፡፡ ከላይ ያነሳናቸው ሁለቱ ፅንሰ ሐሳቦች ይሄንን ክፍተት ለመሙላት ይረዳሉ፡፡
የክስተት ታሪክ እና የሐሳብ ታሪክ
የፅንሰ ሐሳቦቹ ሁለተኛው አበርክቶት ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከሌላ መዓዘንና መነፅር ለማየት አዲስ ዕድል የሚሰጠን መሆኑ ነው:: በኢትዮጵያ፣ ታሪክን መፃፍ በጣም ጥንታዊ ሙያ ነው፡፡ የታሪክ አንፃረ ትርክቱ ግን የታሪኩ ፀሐፊ እንደ ወጣበት ሙያና የህብረተሰብ ክፍል የሚወሰን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ በሀገራችን ለረጅም ጊዜ ታሪክ ሲፃፍ የነበረው ከነገስታቱና ነገስታቱ ከሚከተሉት ሃይማኖት አንፃር ነበር:: በኋላ ላይ ግን (19ኛው ክ/ዘ መጨረሻ ላይ) እነ አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ ይመጡና የታሪክ አፃፃፋችን እንዴት ከወገንተኛነት በፀዳ መልኩ እንደሚፃፍ ማሳየት ጀመሩ፡፡
እነዚህ ሁለቱም የታሪክ አፃፃፎች በቦታና ጊዜ የተቀነበቡ ክስተቶችን ተከትለው የሚፃፉ ናቸው - ‹‹የክስተት ታሪክ›› ናቸው:: ‹‹ተአምራዊነት›› እና ‹‹ብህትውና›› የሚባሉት ፅንሰ ሐሳቦች ግን ታሪክን ለመዘገብ ሌላ ሦስተኛ መንገድ - ‹‹የሐሳብ ታሪክን›› - ይከተላሉ፡፡ ይሄም መንገድ ከክስተት፣ ከጊዜና ከቦታ በላይ ለአንድ ፅንሰ ሐሳብ ትኩረት በመስጠት፣ ፅንሰ ሐሳቡ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ዕድገቱ ድረስ ያለውን ሂደት የሚዘግቡ ናቸው፡፡ ሂደቱ ‹‹ፍልስፍናዊ የታሪክ አፃፃፍ›› ይባላል፤ ታሪክን ከአንድ ትልቅ ፅንሰ ሐሳብ የታሪክ ጉዞ አንፃር ብቻ መመልከት ነው፡፡ የአዘጋገቡ አድማስ ጠባብ ቢሆንም፣ በይዘት ረገድ ግን ጥልቅ ነው:: እጓለ ‹‹በከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› መፅሐፉ ላይ ይሄንን ፍልስፍናዊ የታሪክ የአፃፃፍ መንገድ ያሳየን ቢሆንም፤ በዚህ መንገድ ፅፎ ያሳየን በዋነኛነት የአውሮፓውያኑን የሐሳብ ታሪክ ነው::
ሦስተኛ፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና በይዘት፣ በቀጣይነት፣ በተያያዥነትና በዕድሜ ያበለፅገዋል፡፡ እስከ አሁን ዘመን ድረስ ያሉት የሀገራችን ምሁራን ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› ሲባል ወዲያው ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ፕ/ር ክላውድ ሰምነር፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ያዋቀረበት መንገድ ነው፡፡ ሰምነር ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› በሚል ርዕስ አራት ጥራዞችን አሳትሟል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ ሁለቱ (ቅፅ 2 እና 3) ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ያልተፃፉ፣ ሆኖም ግን በየገዳማቱ ለረጅም ጊዜ ስንጠቀምባቸው የነበሩ የትርጉም ሥራዎች ናቸው፡፡
ሰምነር ካበረከተልን አራት ሥራዎች ውስጥ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ላይ የሚያተኩሩት ሥራዎቹ፣ ሁለት ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ የተሰሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፣ ከኢትዮጵያ የተገኘውን አፍሪካዊ ፍልስፍና ለዓለም ማሳየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዘርዓያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት ማስረገጥና ሐተታውም ከምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና ጋር ያለውን ዝምድና ማሳየት ነው፡፡ ባጠቃላይ፣ ሰምነር ‹‹የኢትዮጵያን ፍልስፍና›› ያደራጀበት መንገድ የውጭውን ዓለም ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ፣ ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ህይወትን ከ17ኛው ክ/ዘ በፊትና በኋላ ካለው የኢትዮጵያ ባህልና ምሁራን ጋር ሊያስተሳስራቸው አልቻለም፤ በሀገሪቱ የሐሳብ ታሪክ ውስጥም ትክክለኛ ሥፍራቸውን ሊያገኝላቸው አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ሰምነር ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ህይወትን በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ውስጥ የ17ኛው ክ/ዘ ድንገተኛ ክስተት አድርጓቸዋል፡፡
ይህ ክፍተት ሊፈጠር የቻለው ደግሞ፣ ሰምነር ፈላስፋዎቹን ከሀገራቸው የባህልና የምሁራን ታሪክ ጋር የሚያስተሳስራቸውን ሐሳብ፣ ከሐተታቸው ውስጥ ለይቶ ማውጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ግን፣ ‹‹ፈላስፎቹ ይበልጥ የሚብከነከኑበት የሀገራቸው ባህል የትኛው ነው?›› የሚለውን ጥያቄ በመጠየቅ መልሱን ማግኘት ይቻላል፡፡ የዚህ ጥያቄ መልሱ ‹‹ብህትውናና ተአምራዊነት›› ነው:: ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ‹‹ብህትውናንና ተአምራዊነትን›› ሲተቹ፣ በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ እስከ ስድብ ድረስ ይሄዳሉ፡፡
ለጥያቄያችን መልሱን በዚህ መንገድ ካገኘን በኋላ ቀጣዩ ሥራ የብህትውናንና የተአምራዊነትን ሥሩን፣ ቅርንጫፎቹንና ፍሬዎቹን ለማግኘት፣ በታሪክ ሰንሰለት ወደ ኋላና ወደ ፊት መጓዝ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ሂደት ነው ‹‹ብህትውናና ተአምራዊነት›› የሚባሉትን ፅንሰ ሐሳቦች የኢትዮጵያን ፍልስፍና በይዘት፣ በቀጣይነት፣ በተያያዥነትና በዕድሜ የሚያበለፅጉት፡፡ የሥልጣኔውን ኪነ ጥበባዊ ሥረ መሰረት፣ በቅዱስ ያሬድ በኩል፣ ከሠሙነ ሕማማት ጋር ስናስተሳስረው ደግሞ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ስነ ውበታዊ (Aesthetic) ቅርንጫፍ ያወጣል፡፡
አራተኛ፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች በተደጋጋሚ ያጋጠማቸውን ክሽፈቶች መንስኤውን በተመለከተ እስከ ዛሬ ድረስ ከነበሩት ምልከታዎች የተለየ አዲስ ምልከታ ያቀብለናል፡፡ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች ክሽፈታቸውን በተመለከተ ምሁራኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶችን እንደ መንስኤ ያቀርባሉ፡፡ ጉዳዩን በተለይ ከኢትዮጵያዊና ምዕራባዊ የባህልና ትምህርት ግጭት ጋር አያይዘው የሚመለከቱ ምሁራን፣ በዚህ የባህል ግጭት ውስጥ ከዘመናዊነት ጋር በተፃራሪነት የሚቆሙት ብህትውናና ተአምራዊነት ያላቸውን ሚና በተመለከት ትኩረት ሲሰጡት አይታዩም፡፡ ከዚህ አንፃር ይሄ ምልከታ ተጨማሪ ግብአት መሆን ይችላል፡፡
አምስተኛ፣ ፅንሰ ሐሳቡ፣ ለኪነ ጥበባዊ ሒስ ያለው አበርክቶትም ትልቅ ነው፡፡ የሀገራችን የኪነ ጥበብ ሐያሲያን፣ በአሁኑ ወቅት፣ የአርት ሥራዎችን የሚሄሱበት አንዱና ዋነኛው መንገድ ከእውናዊነት (Realism) አንፃር ነው፡፡ የእውናዊነት አስተምህሮ የሚገመግመው ደግሞ ማንኛውም የአርት ሥራ ምን ያህል ማህበራዊ እውነታዎችን አስመስሏል? የሚለውን ነው:: በብህትውናና በተአምራዊነት ባህል የተቀረፀ ማህበረሰብ እውናዊነትን የአርት መዳኛ አድርጎ የሚጠቀም ከሆነ፣ የአርት ሥራዎች ተመልሰው የብህትውናውን ባህል እንዲያንፀባርቁ የሚያስገድድ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄም ዘመናዊነትን ለሚያልም ማህበረሰብ በአርቱ በኩል የተደቀነ አደጋ ይሆናል፡፡ ‹‹ብህትውና›› እና ‹‹ተአምራዊነት›› የሚሉት ፅንሰ ሐሳቦች ግን የአርት የመሄሻ መንገዳችን እውናዊነትን እንዲሻገር (ብህትውናና ተአምራዊነት ያልተጫነው እንዲሆን) እና ‹‹ዘመናዊነት›› (Modernism) የሚባለውን የአርት የመሄሻ ስልት እንዲጠቀም ያበረታታል፡፡ ይሄም ኪነ ጥበባችን የድሮው አስተሳሰብ ላይ ከሚቀረቀር ይልቅ ከህዝቡና ከሀገሪቱ ርዕይ ጋር ወደፊት ተመልካች እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡
‹‹ብህትውናና ዘመናዊነት›› እና ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› በሚሉ ትልልቅ ርዕሶች ሥር ሳቀርባቸው የነበሩትን 27 መጣጥፎች በዚሁ ጨርሻለሁ፡፡ እስከ መጨረሻው ፅሁፍ ድረስ አብራችሁኝ ለነበራችሁ አንባቢዎች ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን በኢሜይል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1267 times