Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 09:32

“የሚያነብ የውስጥ ማንነቱን ያገኛል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

42 ዓመት በመጽሐፍ ንግድ

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ንባብን በማበረታታት አስተዋጽኦ አድርገዋል ያላቸውን ተቋማትና ግለሰቦች ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም በጣይቱ ሆቴል ባሰናዳው መድረክ ሠርተፊኬት በመስጠት አመስግኗል፡፡ መጽሐፍ በመሸጥ ሥራ ከ40 ዓመት በላይ አገልግሎት በመስጠት ተሸላሚ ከሆኑት አንዱ አቶ ይለማ በረካ ስለ ሥራ ዘርፉና ስለ ግል ሕይወታቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ከብርሃኑ ሰሙ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ሥራውን በስንት ዓመትዎ ቢጀምሩ ነው፤ በ42 ዓመት አገልግሎት ሰጪነትዎ ለመሸለም የበቁት?በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ ዳቁና ቀበሌ በ1948 ዓ.ም ነው የወለድኩት፡፡ እስከ 9 ዓመቴ ድረስ በትውልድ መንደሬ ቆይቼ በ1957 ዓ.ም አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ አጐቴን ተከትዬ ነበር የመጣሁት፡፡ መርካቶ ወስጥ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ እራሴን የማስተዳደሩን ኃላፊነት የወሰድኩት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

የመርካቶ አሮጌ መጽሐፍ ተራን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በ1958 ዓ.ም ቢሆንም እኔ ወደ መጽሐፍ ንግድ የገባሁት ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ አዲስ አበባ በመጣሁ በሁለተኛው ዓመት የትምህርት ዕድል አገኘሁ፡፡ የትምህርት ታሪክዎ ምን ይመስላል?በትውልድ መንደሬ በድቁና እያለሁ የቄስ ትምህርት የመከታተል ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ጉጉት የፈጠሩብኝ ጄኔራል ወልደሥላሴ በረካና መሰል የጉራጌ መንገድ ሥራን የሚመሩ ታላላቅ ሰዎች፣ የምንማርበት ድረስ መጥተው የጐበኙን ዕለት ነበር፡፡ አጐቴን ተከትዬ አዲስ አበባ ልምጣ እንጂ ብዙም አብሬያቸው አልኖርኩም፡፡ መርካቶ ውስጥ ሸክምና ያገኙትን ሰርተው ራሳቸውን ለመርዳት ከሚሞክሩት ልጆች አንዱ ሆንኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም “የፊደል ሠራዊት” በሚል መጠሪያ የትምህርት ዕድል ያላገኙ ልጆችን ሰብስበው የሚያስተምሩ ሰዎች ዕድሉን ሰጥተውኝ በቀድሞ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት መማር ጀመርኩ፡፡ ዑመር ሰመተርን ጨምሮ በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ሲመቸኝ ቀን፣ ሳይመቸኝ በማታው ክፍለ ጊዜ እየተማርኩ ነው 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቅኩት፡፡ ዊንጌትም ገብቼ ነበር፤ ብረታ ብረት ብየዳ ስማር ዓይኔን አሞኝ ከሁለት ዓመት በኋላ አቋረጥኩ፡፡ በአሮጌ መጽሐፍ ተራ ንግድ ሲጀምሩ እነማን ነበሩ?አቶ ገበየሁ በላቸው፣ ጋሳው አግዜ መስፍን አርጋው፣ ስሜ ሻንቃ፣ ደጀኔ አበዜ፣ ክብሩ ክፍሌ…የመሳሰሉት በመጽሐፍ ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ ከእኔ በኋላም ብዙዎች መጥተዋል፡፡ መርካቶ ውስጥ የአሮጌ መጽሐፍ ንግድ እንዴትና መቼ ተጀመረ ነው የሚባለው?  መጀመሪያው አሮጌ የመጽሐፍ ተራ ከራጉኤል ቤተክርስቲያን በስተጀርባ እንደነበረ ነው የሰማሁት፡፡ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ደነግዴን የልጅ ልጅ የሚያገቡት ኮሎኔል አስፋው አንዳርጌ ናቸው መጽሐፍ ተራውን ከሚገኝበት አስነስተው አሁን ያለበት ቦታ ያመጡት፡፡ ኮሎኔሉ በአሮጌ መጽሐፍ ተራ የሚገኙትን ሁለት ብሎክ የድንጋይ ሱቆችን ሰርተዋል፡፡ አሮጌ መጽሐፍ ተራና ከቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ የመፃሕፍት መሸጫ መደብር ሥራውን መርካቶ ውስጥ በመጀመር ቀዳሚው ማነው?ስለዚህ ጉዳይ የሰማሁት ነገር የለም፡፡ አዲስ መጽሐፍ በመሸጫነት የሚታወቁ መደብሮች ግን በአራት ኪሎ፣ በፒያሳ፣ በለገሀር፣ በመርካቶና በተክለሃይማኖት አካባቢ ነበሩ፡፡ስለ መፃህፍት መሸጫዎች እርስዎ የሚያውቁትን እስቲ ይንገሩኝ…በንጉሱ ዘመን ንብረትነቱ የእንግሊዛዊያን የሆነ ኦክስፎርድ አሳታሚ ድርጅት የተባለ በአራት ኪሎ ነበር፡፡ በፒያሳ ደግሞ ባለቤቶቹ በአብዛኛው ግሪካዊያን ቢሆኑም ጃነፖሎስ፣ አፍሪካዊያን፣ ሚኑ…የሚባሉ የመፃሕፍት መሸጫ መደብሮች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወደ ዘርፉ ከመጡ በኋላ የኢትዮጵያ መፃሕፍት ድርጅትን ያቋቋሙት አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ ብርሃን መደብርን የከፈቱት አቶ ከበደ የመሳሰሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በለገሀር አካባቢ የመፃሕፍት መደብር የነበራቸው አቶ ኪሮስ ቢሆን ሌላው ናቸው፡፡ አሁን አራት ኪሎ የሜጋ መፃሕፍት ማከፋፈያ የሚኝበት ቤት “ተራማጅ” በሚል ስያሜ ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ባለቤቶቹ እነ ኃይሌ ፊዳ (መኢሶኖች) ነበሩ ይባላል፡፡ “ዋልታ” በሚል ስያሜ መጽሐፍ የማከፋፈልና የማስታወቂያ ሥራ የሚሰራም ነበር - ፒያሳመሐመድ ሙዚቃ ቤት ያለበት ሕንፃ ላይ፡፡ የኢህአፓዎችን ጽሑፍና የትርጉም ሥራ የሚያትም፣ “ጨረታ” የተባለ ተቋምም ነበር፡፡ ሶሻሊዝምን የሚሰብኩ ጽሑፍና መፃሕፍትን እነዚህ ተቋማት ነበሩ የሚያሰራጩት፡፡ ወደ በኋላ ላይ የሶሻሊዝም መፃሕፍትን ከውጭ እያስመጡ የሚሸጡም ነበሩ፡፡ሮቻቸው በተክለሃይማኖት አካባቢ ይገኝ የነበረው አቶ ሃምዛ፣ አቶ ታደሰ፣ አቶ ያሲን በዚህ ሥራ ይታወቃሉ፡፡ ቀይ ሽብር ካበቃ በኋላ አንባቢው የሶሻሊስት መፃሕፍትን እየጠላ ትኩረቱን ወደ ልቦለድ አደረገ፡፡ ደርግም ተራማጅ መፃሕፍት ቤትን ኩራዝ አሳታሚ ብሎ አቋቋመው፡፡ መርካቶ ውስጥ አቶአበጀ ጐሹ፣ አቶ ፀጋዬና አቶ ገብሬ የሚባሉ አዲስ መጽሐፍት በማከፋፈል ታዋቂ ነበሩ፡፡ የመፃሕፍትን ጠቀሜታ ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ሥራ ካከናወኑት አንዱ አቶ ከበደ እንግዳሰው ናቸው፡፡ የፓርላማ ተመራጭ የነበሩት አቶ ከበደ፤ “ፓርላማችን”፣ “የአራዳ ጩሉሌ ከነጠርጐ ቦሌ” በሚሉ ርዕሶች ያዘጋጇቸው መፃሕፍትን በየአደባባዩ በመኪና ይዘው በመዞር ንባብን ለማበረታታት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ደራሲ አቤ ጉበኛም መጽሐፍ ነጋዴዎችን ያበረታቱ ነበር፡፡ አሮጌ መጽሐፍ ተራ አዳዲስ መፃሕፍትን የማሳተም ሥራ ተጀምሮ ነበር፡፡ ማንና እንዴት ነው የተጀመረው?አቶ ተክሌ ገብሬና አቶ ጌታቸው ተስፋዬ ናቸው የሥራው ጀማሪዎች፡፡ በመጀመሪያ አጀንዳ አሳትመው አቀረቡ፡፡ በመቀጠል መጽሐፍ ወደ ማሳተም ተሸጋገሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ከደራሲያን ጋር እየተዋዋልን መጽሐፍ የምናሳትም ሰዎች ቁጥራችን እየተበራከተ ሄደ፡፡ ለምሳሌ እኔና አቶ ሳህሉ በላቸው ከ1977 እስከ 1983 ዓ.ም ብቻ በጋራ 30 መፃሕፍትን አሳትመናል፡፡ በዘመኑ በተለይ የትርጉም ሥራ ከሚሰሩት መሐል ማሞ ውድነህ፣ ፈለቀ ዓለሙ፣ ኮ/ል ጌታቸው መኮንን፣ ፋንታሁን ኃይሌ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በ1984 ዓ.ም አሮጌ መጽሐፍ ተራ ከመርካቶ እንዲነሳ ከተደረገ በኋላ ጥሩ ዕድገት እያሳየ የነበረው ሥራ ተቋረጠ፡፡ በመርካቶ አሮጌ መጽሐፍ ተራከ1976 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ብዙ አዳዲስ መፃሕፍት ታትመዋል፡፡ ንባብ እንዲበረታታ አሮጌ መጽሐፍ ተራ ምን አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ?በተስፋ ገ/ሥላሴ የሚታተመውን የፊደል ገበታ ካርቶን ተቆራርጦ እየተለጠፈ ለየክፍለ ሀገሩ ይላክ የነበረው ከመርካቶ አሮጌ መጽሐፍ ተራ ነው፡፡ በንግድ ተራው የተጐዱ መፃሕፍት የመጠረዣ አገልግሎ የሚሰጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ ማንበብ እንደ ወንጀል በታየበት በቀይ ሽብር ዘመን፣ ብዙ መፃሕፍት ከየቤቱ ወጥተው እንደ ቆሻሻ ሲጣሉ ከየወደቁበት ተነስተው ዳግመኛ መነበብ የቻሉት በመጽሐፍ ተራው ተጠብቀው በመቆየታቸው ነው፡፡ ከየትምህርት ቤቱ፣ ከየቤተመፃሕፍቱ ወጥተው እንዲቃጠሉ የወሰነባቸው ብዙ መፃሕፍትን በጨረታ እየገዛን ከተጋረጠባቸው አደጋ ማትረፍችለናል፡፡በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በመሸለምዎ ምን ተሰማዎት?ከ40 ዓመት በላይ በመጽሐፍ ንግድ ላይ የቆዩ ናቸው ተብለን የሠርተፍኬት ሽልማት የተዘጋጀልን እኔን ጨምሮ አቶ ገበየሁ በላቸው፣ አቶ ስሜ ሻንቃ፣ አቶ ተስፋዬ አደልና አቶ ደጀኔ አበዜ ነን፡፡ በዕለቱ ሦስቱ አልተገኙም፡፡ እኔና አቶ ተስፋዬ በተዘጋጀው የምሳ ግብዣ ላይ የተበረከተልንን የሠርተፊኬት ሽልማት ተቀብለናል፡፡ እኔ በዚህ መልኩ በመታሰባችን በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በሽልማቱ መካተት የነበረባቸውም ነበሩ፡፡ እንደ እነ አቶ ክብሩ ክፍሌ ያሉትን ጨምሮ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ የቤተሰብ አቋምዎ?ባለትዳርና የ4 ልጆች አባት ነኝበመጨረሻ የሚያነሱት ሀሳብ ካለ እኔ እራሴን ያገኘሁት በማንበቤ ስለሆነ ሕዝባችንም መፃሕፍት ያንብብ እላለሁ፡፡ የሚያነብ የውስጥ ማንነቱን ያገኛል፡፡

 

 

 

 

Read 3412 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 11:23